የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በተመለከተ ታሪክ፣ ሁኔታና ወቅታዊ ጥያቄዎች በፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ የራዕይ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ፬ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የቀረበ መግቢያና አጠቃላይ ሁኔታ
በመጀመሪያ ዲያስፖራ የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ተቀባይነትን አግኝቶ ሥራ ላይ ከዋለ ቢያንስ ወደ
ሠላሳ ዓመታትን አስቆጥሯል። የቃሉ ሥረ መሠረት የጥንት የግሪክ ቋንቋ ሲሆን የተበተኑ፣ ከአካባቢያቸው ርቀው
የወጡ ማለት ነው። እነኝህ ሰዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ፈልሰው ባህላቸውንና ማንነታቸውን ለሌላው
እያስተዋወቁና እየተወራረሱ የሚኖሩ ናቸው።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ በታሪክ ጥንት የተበተኑ ህዝቦች እስራኤላውያን ሲሆኑ በባቢሎናዊያን ሲወረሩ
(538 BC) አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የሚያመለክት ነው። ያም ስደት ከወራሪና ከግፍ ግዛት
ለመማለጥ ነበር። በዚህ ሁኔታ እንዲሁ ግሪኮች፣ አርመኖች፣ አውሮፓውያንና እስያውያን ተሰደዋል።
አፍሪካውያኖችም በባርነት ቀንበር ስር ወድቀው ተሸጠውና ተሰደው መሥፈራቸው በታሪክ የሚጠቀስ ነው።
ይህን ቃል ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ተቀባይነት አግኝቶ አገልግሎት ላይ የዋለው ባለፉት ከ፴ እስከ ፵
(ከ30 እስከ 40) ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ነው። በታሪክ
ከተጠቀሱት የዲያስፖራ (የመበተን) ሁኔታ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት የውጪ ወራሪ ሕዝቧን አፈናቅሎ፣
ወይም ረሃብና የተፈጥሮ አደጋ ሕዝቧን አስገድዶ ከሀገር የወጡ ሳይሆን ሀገር ውስጥ በተከሰተው ምክንያት፣
ሰብዓዊ መብቶችን የጨፈለቀ፣ ህዝብን የሚያስተዳድር ሳይሆን የሚገዛና የሚነዳ ሥርዓት በመንገሡ ነው። ይህም
ሁኔታ ያለፈውን የደርግና የአሁኑን በህዝባዊ ወያኔ የሚመራውን ኢዴሞክራሲያዊና ኢፍትሐዊ ሥርዓትን
ይመለከታል።
እነዚህ ሁለቱ ሥርዓቶች በመጀመሪያ ከፈጣሪ የተሰጡትን ሰብዓዊ መብቶችን ከመንፈግ ጀምሮ፣
የሀገሪቷን ዜጎች በጎሣ በመከፋፈል፣ ከፋፍለህ ግዛ የሚለውን የቅኝ ገዢዎችን ሥርዓት በመዘርጋት፣
የኢኮኖሚውንና ሌሎችም ህዝባዊ ተቋማትንና የፖለቲካ መብቶችን ጨምድዶ በመያዝ ነፃነትን በማሣጣት ነው
።የኢኮኖሚና የአገዛዝ ስልቱ አንዱን ወገን ከሌላኛው በማበላለጥና የተዛባ ዕድገትን ለማስፈጸም ሲሆን በፖለቲካ
2
ሳይንሱ ትምህርት Antonio Gramsci እና Leo Marquard የውስጥ ቅኝ አገዛዝ  (Internal Colonialism)
በማለት የደቡብ ጣሊያን ግዛትና የዘረኛውን የደቡብ አፍሪካን ሁኔታ እያንዳንዳቸው የመዘገቡትን ይመስላል።1
ስለዚህ ዜጎች የትውልድ ሀገራቸው ባዕድ ስትሆንባቸው ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ለመፈለግ እራስን ለማዳንና ለማሻሻል
ከነአካቴው የእውን ባዕድ ሀገሮች ወደሚባሉት ፊታቸውን ለማቅናት ተገደዋል።
በ1991 ዓም በተደረገው የተማረው የሰው ኃይል ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚጎርፍበትን ግፊትና
ምክንያት በተመለከተ ጌታቸው መታፈሪያና ማይገነት ሽፈራው*(1) እንዳስረዱት ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የነፃነትና
የመብት እጦት ከሀገራቸው እንዳስወጣቸው፣ እንደገፋቸው (Push  factor) በጥናታቸው መዝግበዋል።
በተቃራኒው እነኝህ የግፊት መንሥዔዎች ቢያከትሙ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ
ኢትዮጵያውያን ምኞታቸውን ገልፀው ነበር። ከዚህ ጥናት በመነሳት በዚያን ጊዜ የደርግ መውደቅ ሁኔታዎችን
በበጎ ሁኔታ ይቀይረዋል፣ ሰላምና የሰብዓዊ መብቶች ይነግሣሉ ብለው ሁለቱም አጥኝዎች ቢመኙም ያ የውሃ ሽታ
ሆኖ ቀረ። እነሆ ደርግን የተካው ኢህአደግ ከደርግ የባሰ በመሆኑ ሳይፈልግ ሁኔታው አስገድዶት ከሀገር
የሚኮበልለውንና የዲያስፖራውን ቁጥር የእጥፍ እጥፍ ያደረገው ኢህአድግ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምድር ገሐነም ስለሆነችባቸውና ተስፋም እየጨለመ ስለሄደባቸው በተገኘው
አጋጣሚ፣ በተከፈተው መንገድ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ ወገኖቻችን በባህር እየሰመጡ፣ በአራዊት እየተበሉ፣
የተረፉት የዘመኑ ባርነት ሰለባ በመሆን እየተሰቃዩና እየተደፈሩ ኑሮን በባዕድ ሀገር እየገፉት ነው።
ለወላጆቻችን የመከራና የድህነት ቀን እናወጣለን በማለት በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንገላቱትን
ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ታሪክ በሚገባ ያስቀምጠዋል። ግፍ ፈፃሚዎችም ለጊዜው ከህግ ያመለጡ ቢመስላቸውም
ከታሪክ ተጠያቂነት ግን አያመልጡም።በአጠቃላይ ሁኔታው ይህን ይመስላል።

*(1) Getachew Metaferia and Maigenet Shferraw, The Ethiopian Revolution of 1974 and Exodus Ethiopian Trained Human Resources,  African Studies Volume 24, The Edwin Mellen Press, Lewiston, N.Y. 1991 መጽሐፍ ይመልከቱ።

3
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሁኔታ
በአፄ ኃለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ አያሌ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ግንባታ እንዲሰማሩ ተብሎ ለከፍተኛ
ትምህርትና ለልዩ ልዩ ሥልጠና ወደ ውጪ ሀገር ይላኩ ነበር። የፋሽስት ወረራ አብላጫውን የተማሩትን
ቢጨፈጭፍም የጠላት ወረራ ካበቃ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በብዛት ለትምህርትና ለሥልጠና ኢትዮጵያውያንን ወደ
ባህር ማዶ መላክን ቀጠሉበት። ትምህርታቸውንና ልዩ ሥልጠናቸውን ካከናወኑ በኋላ ሁሉም ለማለት ይቻላል
እሽቅድምድሙ ቶሎ ወደ ሀገር መመለስ ነበር።
ይህ ሁኔታ በደርግ ዘመን ተለወጠ። በተለይም ከ1977 ዓም ከቀይሽብር እልቂት በኋላ በተለይ ወጣቶች
ከሞት የተረፉት ከሀገራቸው ነብሴ አውጭኝ በማለት መሸሽ ጀመሩ። ብዙዎቹም በየበረሃውና በየዱሩ የአራዊት
ቀለብ ሆኑ። የቀይ ሽብር ግድያ በተፋፋመበት ወቅት በየቀኑ ወደ አንድ መቶ ለጋ ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ
ብቻ ተገለው እሬሳቸው በጎዳና ይጣል ነበር። በዚያ ሰዓት የተማረና ወጣት መሆን ባብዛኛው ወንጀል ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የስደት ፣ የስቃይና የእንግልት ዘመን ተጀመረ። ኢትዮጵያውያን ወደ አጎራባች ሀገሮች ተሠደው
ለጊዜው መጠለያ አገኙ። ብዙዎቹም በዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ባልሆኑ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶች እንደ UN
Higher Commission for Refugee , (UNHCR) እና የካቶሊክ የስደተኞች መልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎት
ሰጪ ድርጅቶች አመቻችነት ወደ ሦስተኛ አገሮች እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣አውሮፓና አውስትሬሊያ ድረስ
እንዲሰፍሩ ተደረገ። ብዙ ኢትዮጵያውያንም የነዚህ ድርጅቶች ተጠቃሚ ሆኑ። የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ
የተበተነ ህዝብ የሚለውም በዚህ ሁኔታ ተጀመረ።
በዚህ ሂደትና ሁኔታ ባለፉት ሁለት መንግሥታት በደርግና በህወሃት በሚመራው ሥርዓት ሥር ከመኖር
ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሚሸሿት እንጂ የሚሸሹባት አልሆን ብላለች። የዚህ የኢትዮጵያ
ሁኔታ በጥንት በታሪክም ሆነ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ከተከሠተው የህዝብ ፍልሰትና መበታተን ተለይቶ
ብቸኛ ሁኔታ (Unique) ሆኖ መታየት የለበትም። ሆኖም ግን በ1948 ዓም እስራኤል በተመሠረተችበት ጊዜ
የፍልስጤማውያን ፍልሰትና ቀደም ብሎም የአርመኖች በ1915 ዓም በቱርኮች የግፍ ግድያና እንዲሁም በናዚ
4
ጀርመን ከአይሁዶች የ6ሚሊዮን የዘር ማጥፋት (holocaust) እንዲሁም በቅርቡ በ2011 ዓም በኢራክ ጦርነት
ምክንያት የ1.6 ሚሊዮን ህዝብ ስደት ጋር አይስተካከልም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያውያኖች የስደት ሁኔታ በሀገሪቱ
የረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን ጥቁር ነጥብ ወይም ጥላሸት የጣለ፣ ልዩ ምዕራፍ የከፈተና ሰፊ
እንድምታም ያለው ታሪክ ያስመዘገበ ነው።
የኢትዮጵያዊያን ስደትና የዲያስፖራው ሚና ምን መሆን አለበት?
በየዓለማቱ የተበተኑትና የተዘሩት የኢትዮጵያ ፍሬዎች ቁጥራቸው በደንብ አይታወቅም። ባጠቃላይ ግን
ዘረ ኢትዮጵያዊያን ወደ 3 ሚሊዮን ይጠጋሉ ይባላል። አብዛኛዎቹ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ይገኛሉ። በቅርብ
ዓመታት ውስጥ አሜሪካ ውስጥ የሰፈሩት የጥቁር ህዝቦች ከጠቅላላው የአገሩ ህዝብ ቁጥር 5% ይሆናሉ። ከነዚህ
ውስጥም በቁጥር የሚበልጡት የጀማይካ፣ሄይቲ፣ናጀሪያ፣ ትሪኒዳድና ቶቤጎ ዜጎች ሲሆኑ ኢትዮጵያውያኖች
አምስተኛ ናቸው። በአሜሪካ ውስጥ ያሉት *(2) ቁጥራቸውም ወደ አንድ ሚሊዮን ይጠጋል ይባላል።
በዓለም ዳርቻ የተበተነው ይህ ዜጋ ከኢትዮጵያ ወጣ እንጂ ኢትዮጵያ ከውስጡ አልወጣችም። ስለ ውድ
ሀገሩ የግልና የወል ትውስታ ይዞ ይኖራል (private and collectiv memory)። አንድ ቀን ወደ ሀገሬ
እመለሳለሁ በማለት እንደሌሎቹ የመጀመሪያ ትውልድ ዲያስፖራ ማለሙም አልቀረም። በውጪው አገርም
ኢትዮጵያን መሥርቷል። የሃይማኖት ተቋማትን መሥርቶ፣ በየሶሻል ሚዲያው፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በመጽሔት፣
በቴሌቪዥን፣በየማህበሩ፣ በየተቋማቱ ስለሀገሩ ይወተውታል። ድምፅ ላጣውና ለታፈነው ወገኑ ድምጽ በመሆን
እሮሮውን ያሰማል፣ ለሀገሩና ስለሀገሩ ባለበት አገር ባለሥልጣናትን ይማፀናል፣ የበረዶ ቁርና የፀሐዩን ሀሩር
ሳይበግረው ሰልፍ ይወጣል፣ ህዝቡን ለመታደግ ገንዘብ ያወጣል፣ ብሎም ለወገኑ ፈጠኖ ይደርሳል።*(4)
ይህ ኢትዮጵያዊ በአብዛኛው ከፍተኛ ትምህርት፣ ሥልጠናና ተመክሮ ያካበተ ነው። እንደሌሎቹ ሁሉ
ይህ ዲያስፖራ አንድ ወጥያልሆነ፣ ልዩልዩ ዕይታ ያለው፣ በፍላጎቱም የተለያየ ነው።ከመተባበር በቀላሉመከፋፈል

*(2) Monica Anderson, “Arising share of the U.S. Black population is Foreign born” Pew Research center, social and demographic Trends, April 9, 2015.
*(3) በቅርቡ ታትሞ የሚወጣው የዶር ማይገነት ሽፈራውን “ Struggle from Afar” መጽሐፍ ይመልከቱ።
5
የሚቀናው መሆኑን ብዙዎች ይታዘባሉ። ሆኖም ግን ከሌሎች አገሮች ዲያስፖራ ተመክሮ በመማር የቀኑ ለገዢዎች
ቀና ደፋ ሳይል አገሩን በበለጠ ለመርዳትና ለመገንባት ይችላል።
እርግጥ ለምሣሌ ኢህአድግ የዲያስፖራ ቀን በዓል በማዘጋጀትና፣ ዲያስፖራውን የሚያገለግል መስሪያ
ቤት በውጭ ጉዳይ ሚኒሲቴር ሥር በ2002 ዓም በመክፈትና በየኤምባሲው የዲያስፖራው ተጠሪ ተሠየመ
ቢባልም አብዛኛው ዲያስፖራ ጥቅሙንም ያየውና ግልጋሎቱን ያገኘ አይመስልም። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ
ረገድ ፍላጎቱ ካለ ከብዙ አገሮች መንግሥታት ገንቢ ትምህርት ሊያገኝ ይችላል። ለምሳሌ ከአንዳንድ የአፍሪካ
አገሮች ደቡብ አፍሪካን ማሊ ከመሳሰሉት ሊማር ይችላል። በዚህ ዓይነት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአገሩ
ዴሞክራሲና ቀና መንግሥት ቢኖር የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም ተቋማት ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦና እርዳታ
ሊያደርግ ይችል ነበር።ዲያስፖራው እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ አገር ዕድገት ገንቢና አጋር ሆኖ መታየት አለበት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አገር ቤት ያሉትንም ሆነ በውጪ አገር የተበተኑትን ዜጎች በተለይ ለየት ያለ አመለካከት
ያላቸውን በጠላትነት ይፈርጃቸዋል።እንደ ሁለታኛ ዜጋ ይመለከታቸዋል። በቋንቋ በመከፋፈልና መግሥት
የጠነሰሰውን ፖለቲካ በግድ ተጋቱልኝ ይላል። ይህ ደግሞ ለአገር አይበጅም። የመንግሥት ዓይነተኛ ተግባር
የተለያዩ ሀሳቦችንና እይታዎችን ማጣጣምና ማግባባት ሲሆን ለብዙኃኑ ሃሳብ ተገዢ መሆን አለበት። የብዙኃን
ፍልስፍና (Pluralist Philosophy) ይህንን አበክሮ ያስተምራል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አስተዋጽኦ
በተዘራበት አገር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከመንግሥት ጥላ ውጪ የሚከተሉትን እያበረከተ ነው።
፩ኛ) ባህላዊ ቅርሶችን ማስተዋወቅና የባህል አምባሳደር መሆን
በባህር ማዶ ፈሰው የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ባህል፣ ቋንቋ ፣ሃይማኖት፣ ምግብ፣ ዘፈንና ቁሳቁስ
ለአካባቢው ህዝብ በማስተዋወቅ በመንግሥት ያልተሾሙ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን እያስተዋወቁ ነው። በዚህ
ረገድ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ በአሜሪካን ዋና ከተማ የባህል አምባሳደር (Cultural Ambassador)
ሆነው በሰፊው እንዲያገለግሉ ታሪክና ሁኔታ አስገድዷቸዋል። የኢትዮጵያውያን ጋዜጣዎች፣ የምግብ ዓይነቶች
በየመደበሩ ሲገኙ ፤ የሬዲዮ አገልግሎቶች፣ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ በአየር ሞገዱ እየናኙ ነው።
6
የአማርኛ ቋንቋም የዋሽንግተን ዲሲ መንግሥት እንደ አንድ የመግባቢያና የአገልግሎት መስጫ ቋንቋ በማድረግ
እውቅና ሰጥቶታል። የባህልና የማህበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (Community  center)
ከኢትዮጵያውያን አልፈው ለሌሎችም ህብረተሰብ አገልግሎት እየሰጡ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህዝባችን
ይህንን ሲያይ መንፈሣዊ ቅናት ያሳድርበታል።
፪ኛ)የዳበረው የኢትዮጵያ የሰው ኃይል ፍልሰት ለዓለም በሞላ በረከት በመሆን አገልግሎት ይሰጣል።
ኢትዮጵያዊያን በየምክንያቱ በአመዛኙ በፖለቲካ ምክንያት ከአገር ፈልሰው ወጥተው ውይም
ለየሙያቸው ማደግና መሻሻል በፖለቲካው ምክንያት ሰፊ ዕድል ባለመኖሩ በእውቀት፣ በትምህርት፣ በሞያ፣
በስልጠና የዳበረው የሰው ኅይል ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ለምሳሌ እንደህክምና ያለ ሙያ በቁጥር አብላጫው
በዓለም ሁሉ ፈሶ ይገኛል። በእውቀትና በልምድ የዳበረ የሰው ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቀቱና ተሞክሮው
ለአገር ግንባታ ቢያስፈልግም በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ በፖለቲካው ወይም በመንግሥት አፋኝነትና አድሎዎች
ምክንያት ከአገር ተሰዶ ዘፋኟ እንዳለችው የአባይን ልጅ ውሃ እየጠማው ለሌሎች ግን በረከትና ሲሳይ ሆኗል።
፫ኛ) ዲያስፖራው ለኢትዮጵያ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።
ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ (remittance) ከፍ ያለ ነው። አገሪቷ ወደ
ውጪ ከምትልካቸው ቡና፣ሌጦ፣ ቆዳ፣ ወርቅና የቅባት ጥራጥሬዎች ተጠቃለው ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ
ገቢ የማይተናነስ ጥሬ ገንዘብ ወደ አገራቸው ይልካሉ። ባለፈው ዓመት ወይም በ2015 $3 7 ቢሊዮን ዶላር
ሲላክ አብዛኛው ወይም 44 በመቶ የተላከው ከሰሜን አሜሪካ ነበር። ከዚህ ከተሠጠው የገቢ (remittance)
አኃዝ የበለጠ ገንዘብም ወደ አገር እንደገባ ይታመናል። በባንክ ከሚዘዋወረው ሌላ የበለጠው በግለሰቦችና
በደላሎች የሚላከው በርካታ ገንዘብ እንደሆነም ይታመናል።
ይህ ሬሚታንስ ሌሎች ዜጎች ወደ ትውልድ አገራቸው ከሚልኩት ጋር ሲመጣጠን ትንሽ ነው።
ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስ ይላል፣ ፍልሠቱም የቅርብ ጊዜ ነው። በጠቅላላው አፍሪካ አገሮች ወደ
$40 ቢሊዮን ዶላር  remittance ያገኛሉ። ይህም ገንዘብ ድህነትን ለመቀነስ ዓይነተኛ መድኃኒት ሆኗል።
7
እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ከጥሬ ገንዘብ በተረፈ በንግድ፣ በተቋማት ግንባታና ቴክኖሎጂ በማዘዋወር
የመንግሥት ቦንድ በመግዛት በጥቂቱም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ዲያስፖራው መንግሥት ላይ አመኔታ
ቢኖረውና ሁሉን አቃፊ ሥርዓት ቢኖር ኖሮ ውጪ አገር ያለው ዜጋ ለውድ ሀገሩ ተዓምር ሊሠራ ይችል ነበር።
የቻይና፣ የህንድ፣ የእስራኤል፣ የደቡብ ኮሪያና የታይዋን ኤኮኖሚ ነብስ የዘራው በዲያስፖራ ነው። በአፍሪካም
ቢሆን እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ማሊ፣ኬንያና ናይጀሪያ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። አንዳንዶቹም ለዜጎቻቸው ጥምር ዜግነትን
ይፈቅዳሉ። ለምሳሌ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ጋምቢያ፣ ቡርኪናፋሶና ቡሩንዲ ጥምር ዜግነት ይፈቅዳሉ። ዴንማርክ  በ2015
ለዜጎቿ ጥምር ዜግነት ፈቅዳለች። ምክንያቱም ጥቅሙ እያታወቀ ሄዷል። ይህ ሁኔታ በተለይ ጠባብ እይታ
ባላቸው በኢትዮጵያ፣በኤርትሪያ፣ ማላዊ በሁለቱ ኮንጎዎች (Democratic Republic of Congo  እና
Republic of Congo) ጥምር ዜግነት የሚባል አይታሠብም። ምክንያቱም የዲያስፖራው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ
ያስፈራቸዋል። ከዲያስፖራው የሚፈልጉት ገንዘባቸውንና የፖለቲካ ሎሌነታቸውን ብቻ ነው። ስለዚህ
ኢትዮጵያውያን የማትነጥፍ የገንዘብ ጥገት ሆነው የሚታለቡበትን ሁኔታ መፈተሽ ይኖርባቸዋል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ገንዘባችሁን ብቻ ላኩ የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ አይታለምም
የሚለውን ዲያስፖራው ልዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ኢትዮጵያ ውስጥም የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ ህዝቡ
ከአፈና እንዲላቀቅ በበለጠ መታገል አለበት። ዲያስፖራው በነፃነት በትውልድ አገሩ ውስጥ ብቁ ተሳትፎ
ለማድረግ ሲባል በልዩ ልዩ መልኩ በቀጥታ የምርጫ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል። ሌሎች አገሮች
እንደሚያደርጉት ዲያስፖራው በፖስታ፣ በኤሌትሮኒክ መሥመርና በኤምባሲ በኩል ድምፅ እንዲሰጡ በማድረግ
መብታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ የተወሰነ መቀመጫ ቢመደብላቸውና ብቁ ተሳትፎ ቢያደርጉ
ለሚወዷት ትውልድ አገራቸው ተጨባጭና ገንቢ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በየውጪው አገር ጆሮአቸው አውቆ
የደነቆረውን የፖለቲካ ተቋማት እንደ እስቴት ዲፓርትሜንት ያሉትን ከመማጠንና ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ
መንግሥት ጀምሮ በምዕራብ አገሮች የሚደረገው ሠላማዊ ሠልፍ ጨርሶ ባይቀየርም ሊቀንስ ይችላል። የኢትዮጵያ
ገዢዎንችም በዴሞክራሲ ሥርዓትና በኢትዮጵያዊያን የህሊና ሸንጎ (Public  Opinion) ልንሟገታቸው
8
እንችላለን። ይህ የአሁኑ ኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካበቃ በኋላ የዲያስፖራው የቤት ሥራ ይሆናል። በዚያን ጊዜ
የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉን አቃፊና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ብለን እናስባለን።
ምኞታችንና ተስፋችን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የሚል ማበላለጥ አይኖርም። ሁሉም ከዳር እስከ ዳር
የኢትዮጵያ ዕንቁና የሚያንፀባርቁ ፈርጦች ይሆናሉ። ይህም ሁኔታ እንዲ ፈጠር ሁሉም ኢትዮጵያዊ መትጋት
አለበት።ኢህአድግ የደቀነውን እንቅፋት መወጣጫ መሰላል አድርገን የተሻለች አገር መፍጠርና እውን ማድረግ
አለብን።
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በቀላል የሚታይ መሆን የለበትም። በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ የህግ
የበላይነትና አርቆ አስተዋይ መሪ ካለ በአግባቡ በአገር ዕድገት ላይ ብሎም በድህነት ቅነሳ ላይ ዲያስፖራው በበለጠ
በማሳተፍ መጠነ ሰፊ ዕርዳታ ማሰባሰብ ይቻላል። ይህንን የነቃ ህዝብ በቀላሉ መደለልም አይቻልም። ይህን የሰው
ሃይል ሚና በመገንዘብ ነው የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ዲያስፖራ ስደስተኛ የአፍሪካ ቀጠና(ሪጅን) ያለው።
ከሌላው የአፍሪካ መልከዓ ምድርና ስነልቦና ተለይቶ መታየት የለበትም በማለት ነው። እንዲሁም ዲያስፖራው
በአገር ግንባታ ላይ የሚያደርገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ ነው የዓለም ባንክ በመስከረም 2007 ዓም
የአፍሪካ ዲያስፖራ ፕሮግራም ያቋቋመው።
እንግዲህ የዲያስፖራው በአገር ግንባታ ላይ ያለው ሚና እየታወቀና እየታየ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን
በዲያስፖራ ዜጎች ላይ አራት ታላላቅ ወንጀሎችና በደሎችን እየፈፀመ ነው።
 አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነት በመንፈግ፣ ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ህዝብ
ለህዝብ ሲያጋጭ፣ የጎሣ ምንጠራ ሲያካሂድ (ethnic cleansing)፣ ሲገልና ሲያስገድል ኢትዮጵያዊያን
ህይወታቸውን ለማትረፍ መሰደድን መርጣዋል። በዚህም ሂደት ላይ ብዙዎች በአሰቃቂና በጣም
በሚያሳዝን ሁኔታ ተሰውተዋል። በስደተኛው ላይ ችግር መከሰት፣ የዲያስፖራው ቁጥር መብዛትና
መንገላታት ላይ ኢህአደግ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።
9

 ሁለተኛ መንግሥት ከዲያስፖራው ጋር በፖለቲካ ምክንያት ሆድና ጀርባ በመሆኑ ለአገር ዕድገት
የሚጠቅመውን የሰው ሃይል በማግለል እንደሌሎቹ አገሮች በሚገባ ሊጠቀም አልቻለም:: ይህም በአገሪቷ
ዕድገት ላይ ሌላ አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል።
 ሦስተኛ ጉዳት ተልካሻ ለሆነ የፖለቲካ ቁማር ዲያስፖራውን ከአገሩ ህዝብ ጋር ለማጣላት አሸባሪ
በማለትና ልዩልዩ ቅጽል በማውጣት ጤናማ ያልሆነ መንፈስ ሊያመጣ ይሞክራል።
በመጨረሻም በውጪ አገር አንዳንድ በገንዘብ የተገዙትን በማሠማራት እኩይ ተግባሮችን እንዲፈጽሙ፣
ጥርጣሬን በህዝቡ መሐከል እየነዙ፣ የሀሰት ወሬ እያናፈሱ ስብዕናን እያጎደፉ፣ በንግድ ቤቶች፣ በቤተ እምነቶችና
በሌሎችም ተቋማት እየተሠገሠጉ ዲያስፖራውን እያመሡት ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ
አምባገነኖች በስደት በሚኖሩ ዜጎች ላይ እስከ መግደል ድረስ የተፈጸመውን ያስታውሰናል። እነኝህ መንግስታትም
ሲወገዱ በአንፃሩ ዲያስፖራው ሰላም ሲያገኝ በአገሩ ዕድገት ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገና ትውልድ አገሩን እየታደገ
ይገኛል። የአሁኑ የቻይና ዕድገት ዓይነተኛ ምሣሌ ሲሆን በአውሮፓም በአየርላንድ በገዢው ክፍል ጋባዥነት
የአገሪቷን ምጣኔ ሀብትና ዕድገት የአይርሾች ዲያስፖራ መልካም ውጤት አስመዝግቧል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የምትቀስመው ብዙ ትምህርት አለ። ነገር ግን ይህ መንግሥት በራሱ
ዓለም ውስጥ የሚኖር ሲሆን አገሪቷን ወደ ባሰ አስፈሪ ጎዳና እየወሰዳት ነው ። ስለዚህ በአገር ቤትና በዲያስፖራ
ያለው ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን ለማዳን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አሁን ተባብሮ መሥራት ይጠበቅበታል።
ዲያስፖራ የሚለው ቃል ስደትና ስቃይን አመላካች ቢሆንም ለጆሮ ቢከብድም ከቅርብ ዓመታት በኋላ በአገር
እድገት፣ በኤኮኖሚ መንሠራራትና በፖለቲካ አስተዋጽኦ በየአገሩ ተአምር እየሠራ ነው። የኢትዮጵያውያንም ሁኔታ
ከዚህ ተለይቶ መታየት የለበትም

መስከረም ፲፪ ቀን ፳፻፲ / September 23, 2017