ቴዎድሮሥ ኃይለማርያም (ዶ/ር)

1. ኢትዮጵያዊነት ማለት ምንድነው?

ይህ ጥያቄ የራሷን የኢትዮጵያን ያህል አንጋፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቱ ሲጨነቁና ሲጠበቡበት ቢኖሩም ፣ በተለይ ባለፉት ሃምሣ ዓመታት የሀገራችን ህልውና የተንጠለጠለበት ጉዳይ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ነገር ግን የጥያቄውን ዕድሜ ጠገብነትና ግዝፈት ያህል ፣ ቀጥተኛና አጥጋቢ ምላሽ ፈልገን ለማግኘት እንቸገራለን፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ምንድነው?›› ብለን የቅርብ ባልጀሮቻችንን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ረዥም ዝምታ ነው፡፡ በቃ ኢትዮጵያዊነትማ ኢትዮጵያዊነት ነው! ለብዙዎቻችን ኢትዮጵያ የህይወታችን አካል እንጂ የምንመራመርባት ርዕስ አይደለችም፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት ነው?

 

 

ኢትዮጵያዊነት በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መሆን ማለት ነው፡፡ የአንዲት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ፣ ህዝብና መንግሥት ማንነት ነው፡፡   በርካታ ማህበረሰቦች በረዥም ታሪካዊ መስተጋብር ያዳበሩት ቤተሰባዊ ሥነ-ልቡናና ራሳቸውን ከሌሎች የሚለዩበት ማህበራዊና ህሊናዊ ድንበር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነገዳዊ ፣ አውራጃዊ ፣ እምነታዊ ፣ መደባዊ የመሳሰሉ ዝንቅና ውስብስብ  ድሮችን አካትቶ በዘመናት የተሸመነ ባለ ህብረ ቀለም ካባ ነው፡፡

ሁለተኛ ኢትዮጵያዊነት ማለት በኢትዮጵያ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ብሄርተኝነት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቅርፅ ፣ ይዘትና አቅጣጫ የሚነድፍና የሚመራ ፍልስፍና ነው፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያዊነት  የህዝቧን አንድነት ፣ የመንግሥቷን ቀጣይነት ፣ የግዛቷን ሉአላዊነት ፣ የዜጎቿን እኩልነት የሚያቀነቅን የአብሮነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በርዕዮታዊ ፣ ባህላዊና ታሪካዊ አንድነት ላይ የቆመ ብሄርተኝነት ነው፡፡

በአጭሩ ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሀገራዊ ብሄር ማንነትና ፍልስፍና ነው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ብሄርነት የስሜትም የፖለቲካም ማህበረሰብነት ድምር ነው፡፡ በአንድ ወገን መተሳሰሪያው የጋራ ባህል የሆነ ፣ ያለፈውን እድልና ፈተና ተንተርሶ ወደፊት የሚመጣውን እጣ ፈንታ ተስፋ የሚያደርግ የጋራ ስብዕና መንፈስ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ ማህበራዊ ሥነ-ልቡና የሀገር ፍቅር ፣ አርበኝነት ፣ ህዝባዊነት ፣ ብሄራዊ ስሜት በሚሉት ሊገለፅ ይችላል፡፡

በሌላ ወገን ኢትዮጵያዊነት በግዛተ መንግሥቱ የሚገኙ ዜጎች ሁሉ በብሄራዊ ማህበሩ አባልነት በቀጥታ በትውልድ የሚቀዳጁት ህጋዊ ሰውነት ነው፡፡ ለመላው ኢትዮጵያውያን አስገዳጅነት ያለው ማንነት ነው፡፡ ሰዎች በኢትዮጵያዊ ዜግነት ይወለዳሉ  እንጂ ፣ ኢትዮጵያዊ ልሁን ብለው አይጠይቁም፡፡  ሁን ተብለውም አይጠየቁም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ማለት ብቻ ኢትዮጵያዊነታቸውን አይሰርዘውም፡፡ አንድ ንዑስ ማህበረሰብ ወይም የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች በስሜት ከኢትዮጵያዊነት ቢነጠልም ፣  በሌላ ብሄራዊ መንግሥት ሥር ካልገባ በስተቀር  ፖለቲካዊ  ዜግነቱ አብሮት ይኖራል፡፡

አነዚህ ሁለት የስሜትና የፖለቲካ ገፅታዎች መሳ ለመሳ የሆኑበትና ፍጹም ብሄራዊ አንድነት ያለው ሀገር የሚገኘው በተምኔታዊው ዓለም ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ስለሀገራቸው ፣ መንግሥታቸውና ብሄራዊ ማንነታቸው የሚኖራቸው ስሜትና ቅንዐት ፣ በማንኛውም ወቅትና በመላ ሀገሪቱ ወርድና ቁመት ወጥና ያልተዛነፈ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ በርካታ  ምክንያቶች ቢኖሩም ፣ በዋነኝነት የመንግሥቱ ፖለቲካዊ ቁመና በተለዋወጠበት ታሪካዊ ፍጥነትና ስፋት ልክ ፣ በማዕከሉና ዳርቻው ወይም በነባሩና አዲሱ መካከል ባህላዊና ትዕምርታዊ ትስስር አለመደርጀቱ ነው፡፡ ይህ ልዩነት ዋነኛው የባዳነትና የባይተዋርነት መንስኤ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ‹‹ማነው ኢትዮጵያዊ?›› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ፣ በስሜታዊውና ፖለቲካዊው ድንበር መካከል ያለውን ርቀት ይወስናል፡፡ ጉዳዩ የአንድ ሀገር ብሄራዊ ህብርና ጥንካሬ መለኪያ በመሆኑ ፣ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ዋነኛ ተግባርም ልዩነቱ እንዲጠብብ መጣር ነው፡፡ መድረሻ ግቡ ደግሞ ብሄራዊ ቀጣይነትና ህልውናን ማረጋገጥ ነው፡፡

  1. የኢትዮጵያዊነት ህልውና አዕማዶች

ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ ማንነትና ፍልስፍና ነው ብለናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ህልውና ደግሞ እጅግ ተፃራሪና ፅንፈኛ የብሄርተኝነት አመለካከቶች የሚንጸባርቁበት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ በአንዱ ጥግ ኢትዮጵያ ጥንትም የነበረች ወደፊትም የምትኖር ዘላለማዊ ናት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!››፡፡ በሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ከተወሰኑ ቡድኖች ምኞት ውጭ ህልውና የሌላት ምናባዊ ፍጡር ናት፡፡  ሆኖም እነዚህ የእምነት እንጂ የታሪክ ድምዳሜዎች አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያ ታሪካዊ ህልውና ያላት ሀገር እንጂ ዘላለማዊም ምናባዊም አይደለችም፡፡  ኢትዮጵያዊነትም ይህን ሀገራዊ ህልውና የሚያንፀባርቁ የበርካታ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ረቂቅም ግዙፍም ፣ ህሊናዊም ነባራዊም ፣ ታሪካዊም ባህላዊም ፣ ፖለቲካዊም ማህበራዊም መልኮችና ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ የአንድ ብሄርተኝነት መንፈስና ባህሪ የሚወሰነው እነዚህ በተለያየ ደረጃ በሚቀየጡበት ውስብስብ ሚዛን ቢሆንም ፣ ዘመን የማይሽራቸው የኢትዮጵያዊነት ህልውና አዕማዶች ህዝብ ፣ ሀገርና  መንግሥት ናቸው፡፡ ሥርወ ቃሉ ግዕዝ የሆነው ‹‹ብሄር›› የነዚህ ሶስት አካላት ድምር ነው፡፡

ሀ. ህዝበ ኢትዮጵያ ፡- የኢትዮጵያዊነት አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ ህዝብ የሌለው ማንነትና ብሄርተኝነት ሊኖር አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ብሄራዊ አቋም ያለው ማህበረሰብ  የሚያስፈልጉትን አበይት መስፈርቶች ያሟላል፡፡ የጋራ ስም ፣ የጋራ ሀገር ፣ የጋራ መንግሥት ፤ አነሰም በዛም የጋራ ታሪክ ፣ የጋራ ህግና ባህል ፣ የጋራ መንፈስና ስብዕና አለው፡፡ ከሁሉም በላይ በጋራ ተስፋ የተሳሰረ ቤተሰብ እንጂ ፣ በልዩነት የተዳበሉ ህዝቦች ጥርቅም አይደለም፡፡

ኢትዮጵያዊነት በህዝብ ህሊናና የእለት ተእለት ህይወት ሰፊና ጥልቅ መሰረት በመያዙ ምክንያት ፣ አገዛዞች ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ጥቃት ቢከፍቱበት ፣ ብሄራዊ መንግሥቱ ቢዳከምና ቢፈራርስ እንኳን በተደጋጋሚ  የሚያንሰራራበት አቅምና ዋስትና አግኝቷል፡፡

ለ. ሀገረ ኢትዮጵያ ፡- ማለት ከዚህ ጫፍ እሰከወዲያኛው ወይም ከዚህ ዲግሪ እስከዚያኛው ተብላ የምታበቃ ደረቅ ግንዛቤ አይደለችም፡፡ በድርቡ ግዛታዊና መልክዐ ምድራዊ ቁመናን ፣ የታሪክና የባህል ማህደርነትን  እንዲሁም የወላጅነትንና ፈጣሪነትን ባህሪ አሰተሳስራ ትይዛለች፡፡

ሀገረ ኢትዮጵያ ከህዝብና ከመንግሥት የሚዋረስ ስብዕና ያላት ብሄራዊ ምድር ናት፡፡ እናት ሀገር እምዬ ትሰኛለች፡፡ አፈሯ ፣ አየሯ ፣ ወንዞቿ ፣ ጋራዋና ሸንተረሯ ፣ ሌሎችም መደበኛ የተፈጥሮ ገፅታዎቿ ግኡዛን ሳይሆኑ ፣  በህይወትም በሞትም ከማንነት የተቆራኙ የኢትዮጵያዊነት አካላት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያውያን መንፈስ ጥልቅ ስሜትን የሚጭሩና በህዝባዊ ትውፊቶች ፣ ግጥሞችና ዜማዎች ፣ በስም አወጣጥ ልማዶች የሚቀነቀኑ ናቸው፡፡ ሀገረ ኢትዮጵያ ለክብሯና ልዕልናዋ ይቀኝላታል ፣ ይዜምላታል ፣ ይፀለይላታል ፣ ይሞትላታል፡፡

ሐ. መንግሥተ ኢትዮጵያ ፡- በዋነኝነት አስተዳደራዊ ተቋሙን  ፤ አልፎም ወጉን ፣ ሥርዓቱን ፣ ህጉንና ታሪኩን የሚገልፅ ግንዛቤ ነው፡፡ ልዕለ ዘውጋዊ ተቋምና የብሄራዊ አንድነቷ ማሰሪያ የሆነው መንግሥት ፣ የኢትዮጵያዊነት ጠንሳሽ ፣ የህልውናዋ ዘብ ፣ የሥልጣኔዋ የክብርና ኩራቷ መለዮ ነው፡፡

በአንፃራዊነት መንግሥተ ኢትዮጵያ ዘላቂነት ሲኖረው ፣ አገዛዙ ወይም ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ተለዋዋጭ ነው፡፡  ስለዚህም መንግሥታዊ ወይም ይፋዊ ኢትዮጵያዊነት በየዘመኑ የሚነሱ አገዛዞች ባህሪ ፣ ርዕዮታዊ ውዥቀቶችና የሃይል አሰላለፎች ነፀብራቅ ነው፡፡ ከአንዱ ሥርዓተ መንግሥት ወደሌላው ከህዝባዊ ኢትዮጵያዊነት ጋር ሊመሳሰልም ሆነ ሊለያይ ይችላል፡፡  ዞሮ ዞሮ  ግን መንግሥታዊ ብሄርተኝነት የሥልጣን ማስከበሪያ ፖለቲካዊ መሣሪያነት ዝንባሌ አያጣም፡፡

የብሄርተኝነት አንዱ ባህሪው የማይከለስና የማይበረዝ ሆኖ መታየት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብሄራዊ ማንነት የተሸመነበት ባህል ፣ ታሪክ ፣ እሴቶች ፣ ተቋማትና ርዕዮት እንደ ማህበረሰቡ ነባራዊ እጣ ፈንታ መለዋወጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በአንድ የሆነ ዘመንና የታሪክ አጋጣሚ እንደተወለደ ሁሉ በሂደት ሲያድግና ሲያብብ ፣ ሲቀጭጭና ሲጠወልግ ፣ መልሶ ሲያንሰራራና ሲለመልም እዚህ ደርሷል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከስሟ በስተቀር በነበረበት የዘለቀ ነገር የላትም ለማለት ያስደፍራል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ማህበራዊና ህሊናዊ ድንበር ብቻ ሳይሆን ፣  የፍፁም ሉዐላዊነቷ ማህደር ሀገረ ኢትዮጵያ ቁመና ጭምር በየዘመናቱ ሃይል አሰላለፍ ሲሰፋና ሲጠብብ ኖሯል፡፡ መንግሥተ ኢትዮጵያ ሲበረታና ሲፍረከረክ ፣ መንበሩ ሲፀናና ሲነቀነቅ ፣ ሰንደቁ ሲወድቅና ሲነሳ በታሪክ ጎዳና አዝግሟል፡፡ የኢትዮጵያዊነት አድማስም የመንግሥቱን እጣ ፋንታ እየተከተለ ሲንሰራፋና ሲኮማተር ፣ መንፈሱ  ተግ እልም ሲል ፣ ማዕከሉ ካንዱ ጫፍ ወደሌላው  ሲንሸራተት ታይቷል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ መደቦችና ንዑስ ማህበረሰቦች በሀገር ግንባታና ብሄራዊ ተልእኮ አራማጅነት ተፈራርቀዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከብሄራዊ ማንነቱ ጠርዝ ላይ የነበሩ ወደ መሃል የሚመጡበትን እድል አግኝተዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ  ማዕከሉን ሲጋፉ የነበሩ በሂደት ለምደውና ተዛምደው ብሄራዊ አርበኛ ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው የኢትዮጵያዊነት አስኳል የነበሩ ማህበረሰቦች ፣ እምነቶችና እሳቤዎች ወደ ዳር የተገፉበትም ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ መፈራረቅ ወቅት መሃሉ ላቅ ደመቅ  ፣ ዳሩ ደግሞ ራቅ ፈዘዝ እያለ መታየቱ አልቀረም፡፡

ኢትዮጵያዊነት ካስተናገዳቸው ህልቆ መሳፍርት ለውጦች ሁሉ ሥር ነቀሉ ፣  የብሄራዊ ማንነቱ ገዢ ርዕዮተ ዓለም ከመንፈሳዊነት ወደ ዓለማዊነት መዞሩ ነው፡፡ ቢያንስ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ፣ ኢትዮጵያዊነት ከአንድ ብሄራዊ ኃይማኖት ማዕከላዊነት ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡  ኢትዮጵያ ትክለ ስብዕናዋ ከኦርቶዶክሳዊ እምነቷ ጠብቆ የተሰራ ፣ ህዝቧም ምድሪቱም መንግሥቷም በእምነት ድርና ማግ የተሳሰረ ፣ እጣ ፈንታዋ በመለኮታዊ ኃይልና ፀጋ የሚመራ  ‹‹የክርስቲያን ደሴት›› ሆና ዘልቃለች፡፡ ካህናዊው መደብ በጋራ አስተምህሮ ፣ ቀኖናና ቋንቋ የተሳሰረ የብሄራዊ አመለካከቱ ፅኑ አራማጅ ፣ የታሪኩ ዘጋቢ ፣ የባህሉ ፣ እሴቱና ትዕምርቱ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ኃይማኖትን የብሄራዊ ቤተሰብነት የልደት ካርድ በማድረግ ፣ ይህ ቀዳሚ ማህበረሰብ ራሱን ብሄረ ኢትዮጵያ ብሎ ሲገልፅ ኖሯል፡፡

ከ19ኛው ምዕት አጋማሽ በኋላ  መንግሥተ ኢትዮጵያ የጀመረው የዘመናዊነት ሽግግር የብሄረ ኢትዮጵያን ርዕዮተ ዓለም እያደር ያናጋና ፣ አጠቃላይ የማህበረሰቡን አቋምና ባህሪ በሥር ነቀልነት የለወጠ ሂደት ነበር፡፡ ቁምነገሩ የመንግሥቱ ቅርፅ ከአሃዳዊነት ወደ ፌዴራላዊነት ፤ ሥርዓቱ ከዘውዳዊ ወደ ወታደራዊ ወይም ዘውጋዊ መዋዠቁ ሳይሆን ፣ ብሄራዊ ተልእኮው  ከመለኮታዊነት ወደ ዓለማዊነት መቀየሩ ነው፡፡  እምነት አማካይ ቦታውን እየለቀቀ ፣ መንግሥትን ከኃይማኖት ነጥሎ በፖለቲካ ባህሪው እየወሰነ መሄዱ ነው፡፡   ‹‹ሀገር የጋራ ኃይማኖት የግል›› የሚለው  ቁልፍ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ከእምነታዊ ወደ ፖለቲካዊና ህጋዊ ማህበረሰብነት መለወጧን የሚያመለክት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ህልውና ቀጣይነት ላይ ተፅእኖ ያሳደሩ በርካታና ውስብስብ ምክንያቶች ቢኖሩም ፣ ከሁሉም በላይ ወሳኙ ግን  ኢትዮጵያዊነት በየዘመናቱ የሚፈጠሩ አስገዳጅ ሃይሎችንና ሁኔታዎችን ለማስተናገድ የነበረው አቅምና ቁመና ይመስላል፡፡ በተከታዩ ክፍል እንደምናየው በታሪክ የተፈራረቁ በጎም ሆነ መጥፎ ክስተቶችን ፣ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ኃይሎችን ፣ ርዕዮታዊ ወይም ሠራዊታዊ ጫናዎችን ፣ ህዝባዊና መደባዊ ንቅናቄዎችን ወይም ፖለቲካዊና ዘውጋዊ መቀናቀኖችን ፣ ወዘተ የማያቻችልና  በቅርፅም በይዘትም ግትርና ወርደ ጠባብ ብሄርተኝነት ቢሆን ኖሮ ፀንቶ ሊቆም ባልቻለ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ፅናት ቁልፍ ምሥጢር  አቻቻይና ባለ ሰፊ አውድ  ፣ ሀገራዊና ዜግነታዊ ብሄርተኝነት መሆኑ  ነው፡፡
(ይቀጥላል)
ቴዎድሮሥ ኃይለማርያም (ዶ/ር)