October 19, 2017 06:50

ሐራ ዘተዋሕዶ

በአጠቃላይ ጉባኤው ያልተነሣ ጉዳይ በመግለጫው መስፈሩ ተቃውሞ ገጠመው
የቅዱስ ሲኖዶስ፣ የጥቅምት 2007 ዓ.ም ውሳኔ ሕገ ወጦችን የሚመለከት ነው
የማኅበረ ቅዱሳን የቴቪ ሥርጭት፣ በሲኖዶሳዊ ተልእኮው የተፈቀደ ሕጋዊ ነው
የመግለጫ አርቃቂ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ከፓትርያርኩ ጋራ መክረው ያስገቡት ነው
†††
የጣልቃ ገቡ መግለጫ፣በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚታይ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቆሙ
መግለጫው የሥራ መመሪያ የሚኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ መርምሮ ሲያጸድቀው ነው
ፓትርያርኩ: በድብቅ የጠሩት የአህጉረ ስብከት ሥ/አስኪያጆች ስብሰባ ጥያቄ አሥነሳ
ዓመታዊ ስብሰባው ተጠናቀቀ፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጉባኤተኞችን አሰናበቱ፤
†††

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ውሳኔው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ ብዙኃን መገናኛ፣ ፕሮግራም ስለሚያሠራጩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ማኅበራት ያሳለፈው ውሳኔ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ያላገኙ ሕገ ወጦችን የሚመለከት ቢኾንም፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በማያያዝ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ላይ በጣልቃ እንዲገባ መደረጉ፣ ፓትርያርኩንና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ዳግመኛ አነጋገረ፤ ከጉባኤው ተሳታፊዎችም ጠንካራ ተቃውሞ ገጠመው፡፡
ላለፉት አራት ቀናት ሲካሔድ የቆየው፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ጉባኤ 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ፣ ዛሬ፣ ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በንባብ ቀርቦ የተሰማ ሲኾን፤ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ሥርጭትን ሕገ ወጥ ለማድረግና ለማዘጋት በጣልቃ እንዲገባ የተደረገ የመግለጫው አንቀጽ፣ ከ970 በላይ ተሳታፊዎች በታደሙበት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ አዳራሽ ዳግመኛ አነጋግሯል፡፡
የጋራ መግለጫውና የውሳኔ ሐሳቡ ረቂቅ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊና የአርቃቂ ኮሚቴው ሰብሳቢ በኾኑት መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም የተነበበ ሲኾን፤ በማጠናቀቂያ አንቀጹ፣ በማኅበራት እየተላለፉ ያሉ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች እንዲዘጉ አጠቃላይ ጉባኤው እንደጠየቀ በማስመሰል አስፍሯል፡፡ ጉዳዩ፣ በተጠቀሰው መልኩ በስብሰባው ባልተነሣበት ኹኔታ በሥርዋጽ እንዲገባ ተደርጎ፣ የአጠቃላይ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ አስመስሎ መቅረቡን፣ “አሳፋሪ” በማለት ነው የገለጹት – ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ፡፡

“በአጀንዳነት ያልቀረበንና ጉባኤው ያልተነጋገረበትን ጉዳይ በቃለ ጉባኤ ጽፎ ማቅረብ ያሳፍራል፤” በማለት የተቃወሙት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የጋራ መግለጫውና የውሳኔ ሐሳቡ ረቂቁ፣ ጥቅምት 12 ቀን በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ታይቶ ከሕጉ አንጻር እርማትና ማስተካከያ እንደሚደረግበት ጠቁመዋል፡፡ ማኅበሩ፣ ሕግና ደንብ ተበጅቶለት፣ በአባቶቹ ሥር ኾኖ አገልግሎቱን እየፈጸመ ያለ አካል መኾኑን በመጥቀስ፣ አገልግሎቱን እንዲቀጥል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል፡፡
በጣልቃ የገባው አንቀጽ በንባብ እንደተሰማ፣ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ጭብጨባም ጉርምርምታም የተሰማ ሲኾን፤ አንድ ተሰብሳቢ፣ “አንቀበልም፤ አንስማማም” ሲሉ በከፍተኛ ድምፅ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ ወዲያውኑ፣ በጸጥታ ሠራተኞች ቢከበቡም፡፡
ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ “የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ነው፤ ልብ ወለድ አይደለም፤” በማለት ሥርዋጹን ለማጠናከር ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ የጉባኤው ዋና ሰብሳቢ እንደመኾናቸው፣ በስብሰባው ውሎ ያልተነሣ ሐሳብ በቃለ ጉባኤ ሲሰፍር ማረም ይገባቸው እንደነበር የጠቀሱ ተሳታፊዎች፣ የቅዱስ ሲኖዶስን አመራርና የበላይነት መገዳደርን ልማድ አድርገውት ሳለ፣ አላገባብ የውሳኔው ተቆርቋሪ መስለው የታዩበት ግብዝነት ለትዝብት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የማኅበሩ የቴሌቭዥን ሥርጭት እንዲታገድ የሚጠይቅ አጀንዳ ለቋሚ ሲኖዶስ ሲያቀርቡ፣ መነሻ ያደረጉት የጥቅምት 2007 ዓ.ም. ውሳኔን እንደነበር ተሳታፊዎቹ አስታውሰዋል፡፡ ይኹንና ውሳኔው፣ ሕገ ወጦችን እንጅ ሕጋዊውን ማኅበር የሚመለከት አይደለም፤ አባላቱም በሥራችን የሚያገለግሉ ልጆቻችን ናቸው፤ ተብሎ በቋሚ ሲኖዶሱ ሲነገራቸው አቋማቸውን ማስተካከል ይገባቸው ነበር፡፡ በፈንታው፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ውጭ የራሳቸውን ቡድን እየሰበሰቡ ሥርጭቱን ለማሳገድ ሕገ ወጥ ትእዛዝ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ማስተላለፍን ነው የመረጡት፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚታወቀው ያለፉት 25 ዓመታት የማኅበሩ የአጠቃላይ ጉባኤ ሪፖርት፣ “ዘልማዳዊ ነው” በማለት እንዳይቀርብና ተወካዮቹም እንዳይሳተፉ ነው የከለከሉት፡፡
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁና አህጉረ ስብከቱ፣ ተቀባይነት ለሌለው ኢ-ሲኖሳዊነታቸው የተግባር ምላሽ በመስጠት የማኅበሩን ክንውኖች ለአጠቃላይ ጉባኤው ማቅረቡ ሲመራቸው ደግሞ፤ ከአምስት የቃለ ጉባኤው አርቃቂ ኮሚቴ አባላት የተወሰኑትን ለይተው በመምከር፣ በስብሰባው ሒደት ያልተነሣን ጉዳይና የሕገ ወጥ ትእዛዛቸው አካል የኾነን የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ ኾኖ በጣልቃ እንዲገባ አስገድደዋል፡፡
በመረጃ ደረጃ ቀደም ብሎ ተሰምቶ፣ ከቃለ ጉባኤ አያያዝና የጋራ መግለጫ ዝግጅት አኳያ አካሔዱ እንዲታረም በተደረገው ጥረት፣ ከአምስቱ የአርቃቂው ኮሚቴ አባላት ሦስቱ አቋማቸውን ቢያስተካክሉም፣ የተቀሩት ሁለቱ በተለይም በአድርባይነትና አቋም የለሽነት የሚተቹት ሰብሳቢው መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም የፓትርያርኩን ፍላጎት በመጥቀስና የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በማሳሳት በፈጠሩት ጫና በጣልቃ እንዲገባ አድርገው አባላቱን በማስፈረም ለአጠቃላይ ጉባኤው ማንበባቸው ታውቋል፡፡
አጠቃላይ ጉባኤው ከመናቅ ተለይቶ የማይታይና በተሳታፊዎች ዘንድ መጥፎ ስሜት መፍጠሩን የተናገሩ ተሳታፊዎች፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሰጡት አስተያየት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ 48/6 እና አንቀጽ 50/1 መሠረት፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ሲኾን፤ የሚያወጣው የጋራ መግለጫና የሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብም፣ የሥራ መመሪያ ኾኖ እንዲፈጸም የሚተላለፈው፣ ለጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ቀርቦ ከተመረመረና ከጸደቀ በኋላ ነው፡፡
በጋራ መግለጫውና የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ ላይ የሚኖሩ አስተያየቶችና ማስተካከያዎች፣ በጽሑፍ ለአርቃቂ ኮሚቴ አልያም ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ መስጠት እንደሚቻል የተናገሩት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ በቃለ ዐዋዲውና አባቶች ባቆዩት ሥርዓት መሠረት፣ የአጠቃላይ ጉባኤው 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ እንደተፈጸመ በመግለጽ ልኡካኑን ወደየመጡበት አሰናብተዋል፡፡ ቀደም ሲል በተሠራጨው ደብዳቤ፣ ስብከተ ወንጌልን ጨምሮ በሦስት አርእስት ላይ የተዘጋጀና ለኹለት ቀናት የሚካሔድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደሚኖር ተገልጾ የነበረ ቢኾንም፤ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦና ውሳኔ አግኝቶ ኹሉን አሳታፊና ውጤት ያለው ኾኖ ሲዘጋጅ ጥሪ እንደሚተላለፍና እንደሚካሔድም ጠቁመዋል፡፡ አህጉረ ስብከት እንደየሥራ አፈጻጸማቸው ባገኙት ደረጃ በሚከናወነው የሽልማት መርሐ ግብር፣ በሚሰጠው አቅጣጫና የማጠቃለያ ቃለ ምዕዳን፣ ጉባኤው ቀትር ላይ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ መርሐ ግብሩ ያመለክታል፡፡
ይኹንና ፓትርያርኩ፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ነገ፣ ዓርብ፣ ጠዋት 3 ሰዓት በድብቅ ስብሰባ መጥራታቸው ታውቋል፡፡ በጽ/ቤታቸው በኩል በግል ለሥራ አስኪያጆቹ በተላለፈው ጥሪ የሚካሔደው ይኸው ስብሰባ፣ “በማኅበረ ቅዱሳን ላይ መመሪያ የሚሰጡበት ነው፤”ተብሏል፡፡ ሕገ ወጥ ትእዛዛቸው ተቀባይነት አጥቶ የማኅበሩ የሥራ ክንውን በአጠቃላይ ጉባኤው መቅረቡ፣ ስብሰባውን በድብቅ ለመጥራት ምክንያት እንደኾናቸው ተገልጿል፡፡ ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ ከእኩይ መካሪዎቻቸው ጋራ በየምሽቱ ሲዶልቱ፣ “ሰርጎ ገብ ነው” ያሉትን ማኅበረ ቅዱሳንን ከአህጉረ ስብከቱ መዋቅር ጋራ እንዳይሠራ ለማድረግ ስለሚቻልበት ኹኔታ እንደመከሩ ተጠቁሟል፡፡ ለሥራ አስኪያጆቹም ከዚሁ ጋራ የተያያዘ መመሪያ እንደሚሰጡና ክትትል እያደረጉ በሪፖርት እንዲያሳውቋቸው የተለመደውን ሕገ ወጥ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፤ ተብሏል፡፡
ሕገ ቤተ ክርስቲያኑና ቃለ ዐዋዲው፣ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነት ለሊቀ ጳጳሱ እንደኾነ ሲደነግግ፣ በማንኛውም ጉዳይ ከሊቀ ጳጳሱ መመሪያ እየተቀበለና በአስተዳደር ጉባኤው እያስወሰነ እንዲሠራ ያዝዛል፡፡ የሊቀ ጳጳሱም ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደኾነና በበላይ ሓላፊነት የሚመራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም መዋቅራዊ/ተዋረዳዊ ግንኙነቱ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋራ እንደኾነ ይደነግጋል፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅርና አደረጃጀት ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ የተካሔዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩትና ቀደም ብሎም እንደሚታወቀው፣ ለፓትርያርኩ የአስተዳደር አገልግሎት ድጋፍና ጽሕፈት ነክ ሥራዎች የታሰበው የፓትርያርኩ ጽ/ቤት፣ ራሱን አላግባብ ከፍተኛ የመዋቅርና የሥልጣን አካል አድርጎ የሚሠራ በመኾኑ፥ ለሕግና ሥርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ተጠቃሽ መንሥኤ ነው፡፡ ፓትርያርኩ ደረጃቸውን በማይመጥኑ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ እየገቡ የአሠራር ሥርዓትን ከማፋለስ አልፈው፣ በቋሚ ሲኖዶስ እያስወሰኑና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን እያማከሩ መሥራት የሚገባቸውን ጉዳዮች፣ በራሳቸውና እኩይ መካሪዎቻቸው ግፊት አላግባብ እየወሰኑ ለቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ አመራርና ኹለንተናዊ አንድነት የከፋ አደጋ እየጋረጡ ይገኛሉ፡፡