October 19, 2017 06:33

“ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክር መግባቱ አግባብ አይደለም” አቃቤ ህግ
የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ይግባኝ አቃቤ ህጉ “ፊልድ ወጥቷል” በሚል ሰበብ ሳይሰማ ቀርቷል
ተከሰውበት ከነበረው የ”ሽብር ክስ” በብይን ወደ መደበኛ ወንጀል ህግ ተቀይሮላቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የዋስትና ጥያቄ አቅርበው ውድቅ የተደረገባቸው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ይግባኝ ክርክር ዛሬ ጥቅምት 9/2010 በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሰምቷል።
የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን በአቶ በቀለ የተጠቀሰው አንቀፅ በመርህ ደረጃ ዋስትና እንደማያስከለክል፣ የእስር ፍርድ ቤቱም አቶ በቀለ በውጭ ከሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያደርጉ ስለነበር በእነዚህ አካላት በኩል ወደ ውጭ ይወጣሉ እንዲሁም የዋስ መብት ተፈቅዶላቸው ቢፈቱ ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ በሚል አቃቤ ህግ ባቀረባቸው ነጥቦች የዋስትና መብታቸውን መከልከሉ ትክክል እንዳልሆነ በመግለፅ ክርክራቸውን በዝርዝር አቅርበዋል።
አቶ አምሃ አቃቤ ህግ ለዋስትና መከልከያነት ያቀረበው መቃወሚያ እና የእስር ፍርድ ቤቱም ዋስትና የከለከለበት ጉዳይ የሽብር ክሱ በብይን ሲወድቅ የወደቀ መሆኑንም አስረድተዋል። በውጭ ከሚገኙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር የተባለውም በብይን በውጭ ከሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ወንጀል አይደለም ተብሎ እንደተበየነ አስረድተዋል። በመሆኑም ወንጀል ያልሆነ ነገር መሰረታዊ የዜጎች መብት የሆነውን የዋስትና መብት ሊያስከለክል አይገባም ሲሉ ክርክራቸውን አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ካቀረበው ነጥብ ውጭ የዋስትና መከልከያ ነጥብ ሳያገኝ የዋስትና መብት የከለከለ ከመሆኑም ባሻገር አቶ በቀለ ዋስትና የተከለከሉበት ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ በመጥቀስ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ አቶ በቀለ የሽብር ክሱ ውድቅ ሳይደረግ ዋስትና ተከልክለው ስለነበር የእስር ፍርድ ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ የዋስትና መብት ሊያይ አይገባውም ብሎ ለልደታ ፍርድ ቤት አቅርቦት የነበረውን መቃወሚያ በማስታወስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ክርክሩን እንዲያግደው ጠይቋል። ” ፍርድ ቤቱ ወደ ክርክር መግባቱ አግባብ አይደለም” ሲልም ተቃውሞ አቅርቧል። ይሁንና ፍርድ ቤቱ ክርክሩን እንዲቀጥል ከወሰነ በሚል ከአሁን ቀደም ለእስር ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን የዋስትና መቃወሚያዎች ደግሞ አቅርቧል። አቶ በቀለ ይከላከሉ የተባሉበት ወንጀል ከባድና እስከ 10 አመት የሚያስቀጣ ነው በሚል የእስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲፀና ጠይቋል።
አቶ አምሃ በበኩላቸው እነሱ በጠየቁት ይግባኝ አቃቤ ህግ ” ክርክሩ መደረግ የለበትም!” ብሎ ተቃውሞ ማቅረብ እንደማይችል፣ እስከ 10 አመት ያስፈርዳል የሚባለው በተጠቀሰው ወንጀል ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ መሆኑን፣ አቶ በቀለ ይከላከሉ ተባለ እንጅ ጥፋተኛ እንዳልተባሉ በመግለፅ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ለአቃቤ ህግ መቃወሚያ በሰጡት መልስ አስረድተዋል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክሩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 20/ 2010 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት የነበረው እና 6 አመት ከ6 ወር የተፈረደበት የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ይግባኝም ዛሬ ጥቅምት 9/2010 ቀጠሮ ተይዞለት የነበር ቢሆንም ለአቶ በቀለ ገርባ ክርክር መልስ የሰጠው አቃቤ ህግ “ለዮናታን ጉዳይ መልስ የሚሰጠው አቃቤ ህግ ፊልድ ወጥቷል። ፍርድ ቤቱ አጭር ቀጠሮ ይስጠን” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ “መልስ መስጠት ያለበት ተቋም እንጅ ግለሰብ አይደለም” ሲሉ በአቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱም እንዲህ አይነት አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት መቅረብ እንደሌለበት ገልፆ ለጥቅምት 24/2010 ቀጠሮ ሰጥቷል።