የቻይና ሠራተኞች በወደብ ግንባታ ላይ
Paula Bronstein

ቻይና ብዙ ሃገራዊ ጉዳዮችን በሚስጥር በመያዝ ትታወቃለች። አሁን ግን አጥኚዎች ከሃገሪቱ ሚስጥሮች መካከል አንዱ የሆነውን እና ቤጂንግ ለሌሎች ሃገራት በእርዳታ የምትሰጠውን የገንዘብ መጠን ማወቅ ችለዋል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ቻይና የውጭ እርዳታ ተቀባይ ሃገር ነበረች። አሁን ግን ዕርዳታ እና ብድር በመስጠት የረዥም ጊዜ ታሪክ ካላት አሜሪካ ጋር በመፎካከር ላይ ትገኛለች።

ለመጀመሪያ ጊዜም ከቻይና ውጭ ያሉ የአጥኚዎች ቡድን አባላት ቻይና ለተለያዩ ሃገራት የሰጠችውን የገንዘብ ድጋፍ የሚያሳይ መረጃ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማሰባሰብ ችለዋል። በ140 ሃገራት የሚገኙ አምስት ሺህ ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮርም፤ ቻይና እና አሜሪካ ለሃገራት በሚሰጡት ድጋፍ በመፎካከር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ሆኖም “በጀቱን በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። የእነዚህን ሰነዶች ስብስብ የተለያዩ ውጤቶች አላቸው” ሲል የፕሮጀክቱ ዋና አጥኚ ብራድ ፓርክስ ይገልጻል።

ብራድ የሚመራውና በቨርጂኒያ ዊሊያምና ሜሪ ኮሌጅ የሚገኘው ኤይድዳታ የምርምር ቡድን፤ ከሃርቫርድ እና ከጀርመኑ ሄደልበርግ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ነው ጥናቱን ያጠናቀቀው።

የቻይና ሠራተኞች
CARL DE SOUZA/AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የቻይና ሠራተኞች የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር መስመር ሲሰሩ

ሚስጥሩ እንዴት ሊደርበት ቻሉ?

በቻይና መንግሥት ምላሽ ያልተሰጣቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ኤይድዳታ የራሱን ዘዴ ተግባራዊ አድርጓል። ይፋዊ የኤምባሲ ማስረጃዎችን፤ የቻይናን የእርዳታና የእዳ መረጃዎችን እና ከቻይና ወደ ዕርዳታ ተቀባይ ሃገራት የሚደረገውን የገንዘብ ፍሰት ተጠቅመው ነው ጥናታቸውን ያካሄዱት።

አንድ በአንድ የተሰባሰበው መረጃ ሙሉ ቅርጽ ሲይዝ፤ የቻይና መንግሥት ድጋፍ የት እንደደረሰ እና ያመጣውን ለውጥ ሊያሳይ የሚችል ምስል ፈጥሯል።

“ዘዴው የማይታወቀውን ዓለም ይበልጥ ይፋ አድርጓል” ይላል ፓርክስ። “የቻይና መንግሥት አንድ ነገርን ለመደበቅ ከፈለገ እኛ አናገኘውም። ሆኖም ቻይና ወደ እርዳታ ተቀባዩ ሃገር የምትለከው ገንዘብ ከፍተኛ ከሆነ መረጃ መውጣት ይጀምራል” ይላል።

ቻይና ገንዘብ እንዴት ትሰጣለች?

መረጃው በተገኘባቸው ዓመታት ከፍተኛ እርዳታ በመስጠት የሚታወቁት አሜሪካ እና ቻይና ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ለተለያዩ ሃገራት መስጠታቸው ከጥናቱ ዋነኛ ግኝቶች አንዱ ነው። ገንዘቡን ያከፋፈሉበት መንገድ ግን በጣም የተለያየ ነው።

አብዛኛው (93%) የአሜሪካ የፋይናንስ ድጋፍ አሰጣጥ ቀደም ሲል በተለመደው እና በምዕራባዊያን ሃገራት የድጋፍ ስምምነት ትርጉም ውስጥ የሚጠቃለል ነው። የድጋፉ ዋና ዓላማ የተቀባይ ሃገራትን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል የሚሰጥ ነው።

ከዚህ ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆነው ቀጥታ ድጋፍ እንጂ ተመላሽ በሚሆን ብድር መልክ የሚሰጥ አይደለም።

በተቃራኒው ቻይና ከምትሰጠው ድጋፍ ትንሽ መጠን (21%) ያለው ነው በተለመደው የእርዳታ አሰጣጥ መሠረት ሌሎች ሃገራት ጋር የሚደርሰው። ሌላውስ? “የአንበሳውን ድርሻ” የሚይዘው ገንዘብ ግን በንግድ ድጋፍ መልክ ከወለድ ጋር ለቤጂንግ እንዲመለስ ተደርጎ የሚሰጥ ነው።

“ቻይና ከገንዘቧ ላይ ጥሩ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ማግኘት ትፍልጋለች” ሲል ብራድ ፓርክስ ይገልጻል።

ገንዘቡስ ምን ውጤት አስገኘ?

ሌላኛው የምርምር ቡድኑ ትልቅ ውጤት እንደሚያሳየው ቻይና በተለመደው የእርዳታ አሰጣጥ መንገድ የምትሰጠው ገንዘብ፤ በተቀባይ ሃገራት ዘንድ አስደሳች የኢኮኖሚ ውጤት አስገኝቷል።

ለረዥም ጊዜ በቻይና እርዳታ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ለቻይናዊያን ሠራተኞች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና ለሃገራቸው ትርፍ የቆሙ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር። በተጨማሪም በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ህይወት በመቀየር በኩል ያላቸው ድርሻ አነስተኛ እንደሆነ ይታመን ነበር።

እንደ ጥናቱ ከሆነ ግን ቻይና እንደ ሌሎች ምዕራባዊያን ሃገራት ለልማት የሚረዱ ዕርዳታዎችን ማቅረብ ችላለች።

የትኞቹ ሃገራት የቻይናን ገንዘብ እያገኙ ነው?

እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ የአፍሪካ ሃገራት ከቻይና ድጋፍ ከፍተኛውን ድርሻ ለማግኘት ችለዋል።

ከሴኔጋል ሆስፒታል ጀምሮ እስከ ፓኪስታን እና ሲሪላንካ ወደብ ግንባታ ድረስ ድጋፉ በመላው ዓለም ተከፋፍሏል። እ.አ.አ በ2014 ከቻይና ድጋፍ በማግኘት ሩሲያ ቀዳሚ ስትሆን ፓኪስታንና ናይጄሪያ ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን የኤይድዳታ መረጃ ያሳያል።

በተቃራኒው አሜሪካ በቀዳሚነት ድጋፍ የሰጠችው ለኢራቅ፣ አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ነው።

የፓኪስታን ሃይል
AAMIR QURESHI/AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በቻይና ፋይናንስ ፓኪስታን ወደብ ገንብታለች

ቻይና እና አሜሪካ ለሃገራት የሚሰጡት እርዳታ በአብዛኛው ፖለቲካቸውን መሠረት በማድረግ ነው። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሁለቱም ሃገራት እርዳታ በብዛት የሚሰጡት በተበበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ከጎናቸው ለቆሙ ሃገራት ነው።

ለቻይና ቁልፉን ቦታ የሚይዘው ኢኮኖሚ ነው። የኤይድዳታ ጥናት እንደሚያሳየው ቻይና ብድሩ ከነወለዱ እንደሚለስላት በምትፈልግባቸው ሃገራት የወጪ ንግድንና የገበያ ብድርን በማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ታደርጋለች።

ሰሜን ኮሪያ

የኢኮኖሚ ቀውስ ያጋጠማት ሰሜን ኮሪያ እንድትቋቋም በመርዳት በኩል ቻይና ቀዳሚዋ ሃገር መሆኗ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። ነገር ግን እንደ ኤይድዳታ አጥኚዎች ከሆነ ባለፉት 14 ዓመታት 210 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ 17 የቻይና ፕሮጀክቶች በሰሜን ኮሪያ መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ከሰሜን ኮሪያ መረጃ ለማግኘት ከባድ እንደሆነች ብራድ ፓርክስ ይጠቅሳል። ቻይና በገንዘብም ሆነ በተለያየ መንገዶች ለሰሜን ኮሪያ የምታደርገው ድጋፍ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ መረብ ውጭ ነው።

የቻይና ገንዘብ ለምን የሚያጓጓ ሆነ?

ከ1960ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ድረስ ምዕራባዊያን ሃገራት ከፍተኛ የወለድ መጠን ያለው ብድር ለሃገራት ይሰጡ ነበር። ሆኖም ተበዳሪ ሃገራት የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል አለመቻላቸው ስትራቴጂው ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል። አስደንጋጭ የሆነው የምዕራባውያን እርዳታ ሞዴል አሁን ተሻሽሏል።

“ለታዳጊ ሃገራት ዓላማውን ትርፍ ያደረገ፤ ወለድ ያለው ብድር መስጠት አያስፈለግም የሚል የጋራ መግባቢያ አለ” ይላል ብራድ ፓርክስ። “ቻይና ይህንን የተተው መድረክ ለመሙላት ብቅ ብላለች። መግባቢያው ላይም አልደረሰችም። በዚህም በዝቅተኛ ወይንም በከፍተኛ ወለድ ብድር ትሰጣለች” ብሏል።

“ሃገራትም የኢኮኖሚ መቃወስ ሲያጋጥማቸው ወደ ዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም ከማቅናት ይልቅ ቻይናን እየመረጡ ነው” ሲል ያስረዳል።

ቻይና ገንዘብ ማበደሯን ትቀጥላለች?

ቻይና ከከፍተኛ ወለድ ጋር በምታበድረው ገንዘብ ምክንያት የተበዳሪ ሃገራት ኢኮኖሚ አልተጎዳም። ሃገራቱ የኢኮኖሚ ዕድገትም እያስመዘገቡ አይደለም። አጥኚዎቹ በቀጣዮቹ 10 እና 15 ዓመታት ተበዳሪ ሃገራት ብድሩን መመለስ ስለሚከብዳቸው ይህ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው። ይህ ካጋጠመ ቻይና ስለሁኔታው በድጋሚ ልታስብ ትችላለች።

“ምዕራባዊያን እርዳታ ሰጪዎችና አበዳሪዎች የብድራቸው አለመመለስ የፈጠረባቸው አይነት ችግር ከ10 ወይንም 15 ዓመታት በኋላ ሊያጋጥም ይችላል። ይህ ካጋጠመ ደግሞ ቻይና ብድር የምትሰጥበትን ዘዴ ልትቀይር ትችላለች” ይላል ብራድ ፓርክስ።

የብሪትሽ ኮሎምቢያ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪው ዢአኦጁን ሊ እንደሚለው ቻይና ብድር የምትሰጥብት መንገድ እየተቀየረ ነው ይላል። ሃገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ ኤሽያ ኢንፍራስትራክቸር ኢንቨስትመንት ባንክ ባሉ ተቋማት በኩል በማበደር ለዓለም ባንክ ምላሽ እየሰጠች ነው።

ቻይና የዓለማችን ቁጥር አንድ አበዳሪ ብትሆን ምን ችግር አለው?

ቻይና የምትሰጠው ብድር በመላው ዓለም ተጽዕኖ እንዳለው እሙን ነው። በተለይ ደግሞ ቀደም ሲል አበዳሪ የነበሩ ሃገራት ገንዘብ ከመፍቀዳቸው በፊት ያስቀምጧቸው የነበሩትን መሥፈርቶች እንዲያቆሙ እያስገደደ ነው።

ቻይና ከዋና ዋናዎቹ አበዳሪ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗ ቀደም ሲል አበዳሪ በሆኑት ሃገራት መካከል ያለውን ፉክክር አጠናክሯል ይላል የኢኮኖሚ ባለሙያው ዲዬጎ ሄርናንዴዝ።

“አንድ የአፍሪካ ሃገርም በቻይና ስትደገፍ የዓለም ባንክ ለብድሩ የሚያስቀምጠውን መስፈርት ይቀንሳል” ሲል ይገልጻል። ቻይና ድጋፏን በአንድ በመቶ ባሳደገች ቁጥር፤ የዓለም ባንክ ብድር ለመስጠት እንደነጻ ገበያንና የኢኮኖሚ ግልጽነትን ያሉ መሥፈርቶቹን በ15 በመቶ ቀንሷል።

አንዳንድ ሃገራት የቻይና መንግሥት ብድርን በመተማመን የዴሞክራሲ ሥርዓታቸው ላይ ለውጥ እያመጡ አይደሉም ሲሉ ይተቻሉ። በተለይ ቀደም ሲል ከምዕራባዊያን ብድር ለማግኘት የሚቀመጡ መስፈርቶች እየቀነሱ መሆናቸውን በመጠቆም።

ካምቦዲያ ለዚህ ምሳሌ ናት፤ ዋሽንግተን የምትፈልገውን ነጻ ምርጫ ወደ ጎን በመተው ከቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነት ከፈጠረች በኋላ ነጻ መገናኛ ብዙሃንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ዘግታለች።

የቻይና ድጋፍ የአፍሪካ ሃገራትን ምን ያህል እንደለወጠ ዢአኦጁን ሊ አጥንቷል። ታዳጊ ሃገራቱ በምዕራባዊያኑ እንደመስፈርት የሚቀመጠውን የዴሞክራሲ ማሻሻያ ወደ ጎን በመተው ፊታቸውን ወደ ቻይና አዙረዋል። በዚህም የዴሞክራሲ ለውጥ አዝጋሚ ሆኗል።

“ቀደምት አበዳሪ ሃገራት የቻይናን የብድር አካሄድ ይተቻሉ። የአፍሪካ ሃገራት በበኩላቸው ብድሩን በጸጋ ተቀብለዋል ወይንም አዲስ አማራጭ ስላላቸው ደስተኞች ናቸው” ይላል ሊ።

ንጭ     –    ቢቢሲ /አማርኛ   ቢቢሲ ዜና