October 20, 2017

ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው ተቀባይነት እያጣ መምጣቱ በብርቱ አሳስቧቸዋል የተባሉት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “መሥራት አልቻልኩም፤” ሲሉ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቃል ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡

ፓትርያርኩ ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ከኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ከሥራ አስፈጻሚው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ አካል ጋራ ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየታየ ባለበት ወቅታዊ ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡

መፍትሔ ሊሰጠኝ ይገባል፤” በማለት በሓላፊነታቸው ለመቀጠል እንደተቸገሩ በቃል ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መናገራቸውንና በቅርቡም በጽሑፍ እንደሚያሳውቁ ነው፣ ምንጮች የጠቆሙት፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የፓትርያርኩ ሢመትና ርደት ጉዳይ የሚወስነው ቅዱስ ሲኖዶስ ኾኖ ሳለ፣ ጥያቄያቸውን ለባለሥልጣናት ማቅረባቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘንድ በአስከፊ ኹኔታ እያጡ የመጡትን ተደማጭነትና ተቀባይነት በተጽዕኖ ለመመለስ፣ ከአማካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት መኾኑን እንደሚያሳይ ተነግሯል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ ከነገ በስቲያ፣ ጥቅምት 12 ቀን እንደሚጀመር እያወቁ፣ ከሓላፊነት ለመልቀቅ ጠይቀዋል መባሉ ይህንኑ ጫና የማሳደር ስልታዊነቱን እንደሚያረጋግጥ ነው የተገለጸው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በተያያዘ የሚያቀርቡት የእግድ አጀንዳ በቅዱስ ሲኖዶሱ አካላት(ቋሚ ሲኖዶስ እና ምልአተ ጉባኤ) ውድቅ መደረጉ፤ ቡድን ፈጥረው እየመከሩ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚያስተላልፉት መመሪያ መሸራረፉ ሕመም እንደኾነባቸው ነው የተስተዋለው፡፡

የማኅበሩ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሥርጭት ከቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭ እንዲታገድ ያስተላለፉት መመሪያ ተፈጻሚነት ሲያጣ፣ ከአጠቃላይ ጉባኤው 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳትፎ እንዲታገድ ወደ ማዘዝ ቢሸጋገሩም እንዳሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቶ፣ በተፃራሪው የማኅበሩ የማዕከልና የአህጉረ ስብከት ሥራዎች በጉልሕ እንዲስተጋቡ ምክንያት ኾኗል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው መክፈቻ ምሽት፣ የማኅበሩ ተወካዮች እንዳይሳተፉ በማድረጋቸው፣ “የእኛን ሥልጣን ማወቅ አለባቸው፤ ሥልጣናችንን መረዳት አለባቸው፤” በማለት ከእነብፁዕ አባ ሩፋኤል፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ እና ብፁዕ አባ ቶማስ ጋራ ውሎውን የገመገሙ ቢኾንም፤ በቀጣዩም ቀን ማኅበሩ ከአህጉረ ስብከት ጋራ በመቀናጀት ያከናወናቸው ተግባራት በድምቀት እየተነገሩ በመዋላቸው፣ በጋራ መግለጫና ቃለ ጉባኤው ላይ፣ ቴሌቭዥኑ ሕገ ወጥ እንደኾነና እንዲዘጋ የሚጠይቅ አንቀጽ በጣልቃ እንዲገባ አርቃቂዎቹን አዘዋል፡፡ ሐሳቡን የተቃወሙ የአርቃቂ ኮሚቴው ሦስት አባላት፣ “የማኅበር ተላላኪዎች”ተብለው በሰብሳቢው የተዘለፉ ሲኾን፣ ሥርዋጹም በግድ እንዲገባና በድፍረት እንዲነበብ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው ያልተነሣ ጉዳይ በቃለ ጉባኤ የውሳኔ ሐሳብ ተብሎ መስፈሩ አግባብነት እንደሌለው ወዲያውኑ ከጉባኤተኛው ተቃውሞ የተሰማበትና በምክትል ሰብሳቢው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም ተቃውሞ ቢሰነዘርበትም፣ ርእሰ መንበር የኾኑት ፓትርያርኩ ግን ሕገ ወጥነቱን የተከላከሉት፡፡ “የመዝጊያ ንግግር እንዳደርግ ስለ ፈቀዱልኝ አመሰግናለሁ፤” በማለት ስሕተቶችን በፍጥነት እያረሙ የአጠቃላይ ጉባኤውን ሒደት በጥብቅ እየተቆጣጠሩ ምክራቸውን ያፈረሱባቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን፣ በማጠቃለያ ቃለ ምዕዳናቸው በአሽሙር መናገራቸውም ተሰብሳቢዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡

የቤቱን ፈገግታ ያከሰመው፣ የፓትርያርኩ ክብረ ነክ ንግግር ግን ወዲያው ነበር የተሰማው፡፡ “ተናግሮ አናጋሪ የትላንቱ ሰውዬ” ባሏቸው ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ላይ ለአጠቃላይ ጉባኤውም ለመንበረ ፕትርክናውም በማይመጥን ንግግር፥ ደጋፊዎቻቸውን ጭምር ነበር ያሳፈሩት፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በእጅጉ አዝነዋል፤ ጥቂት የማይባሉትም ቁጣቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ፓትርያርኩ በሚሰጧቸው ሕገ ወጥና ረብሕ የለሽ መመሪያዎች እንዲጠነቀቁ፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አቅርበው ማነጋገርን እንዲያስቀድሙ ነበር ምሳሌያዊ ምክር የሰጡት፤ ቅዱስ ሲኖዶሱንም ያሳሰቡት፡፡ እንደተለመደው ግን፣ በዚያው ዕለት ማምሻውን፣ በተጠቀሱት ክፉ አማካሪዎች ምሳሌያዊ ምክሩ በአሉታ እየተነተነ የፓትርያርኩ ቁጣ እንዲጋጋም መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

አቡነ ፋኑኤል፣ በፈንጅና ጭስ መስለው የተናገሩትን [አማካሪዎቻቸው]ይዘው፣ ቅዱስነትዎ የሚጽፉት ደብዳቤ ከዚህ ግቢ ውጭ የማይሠራና አቅም የሌለው እንደኾነ፤ ምንም ቢጽፉ የትኛውም አካል የማያስፈጽመው ነው፤ ነገር ግን መነጋገርያ ብዙ ሰው እያደናገረ ነው፤ ብለው ተርጉመውላቸዋል፤ ይህም ሕመም ፈጥሮባቸው አድሯል፤”

ነውረኛ ንግግራቸው በአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊዎች ላይ የፈጠረውን ፍጻሜ ስሜት ቢያዩም፣ ይብሱኑ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከሀገረ ስብከታቸው ለማገድ ነው እየዛቱ የሚገኙት፡፡ በዚህ ረገድ በሀገረ ስብከታቸው ተቀባይነት ያጡትና የመባረር ዕጣ የሚጠብቃቸው ብፁዕ አባ ማርቆስ፣ “ሀገረ ስብከቱን ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ ሰጥቶታል፤” እያሉ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በማሳጣት በቦታቸው ለመተካት ፓትርያርኩን እየገፋፉ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ “ምን ሲኖዶስ አለ፤ ሲኖዶስ እኛው ነን፤” በሚል ፓትርያርኩ ሌሎችንም አባቶች እንዲያስተባብሩ እንዳሉ ተገልጿል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በበኩላቸው፣ ለተሰነዘረባቸው ውንጀላ ፓትርያርኩን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ እንደሚጠይቁና በስም ማጥፋትም እንደሚከሷቸው ነው የተጠቆመው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ርእሰ አበው እንደመኾናቸው መጠን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ አመራር የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንደተደነገገው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰኑና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋራ እየተማከሩ መሥራት የሚጠበቅባቸው ቢኾንም፣ ከዚህ ውጭ እየመከሩ የሚከተሉት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ አካሔድ፣ ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ፤ በባለሥልጣናትም ዘንድ አቅም ቢስ ተደርገው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ የመንግሥት ሹማምንትን ባገኙ ቁጥር፣ “ማኅበሩን ዝጉልኝ” የሚለው የዘወትር ውትወታቸው በእጅጉ እንዳስናቃቸውና ተደማጭነት እንዳሳጣቸውም ተጠቁሟል፡፡

በቃል አሳውቀውታል የተባለውና በቀጣይም በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ የተጠቆመው ከሓላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ መነሻዎች ባለሥልጣናቱን እያነጋገረ እንደሚገኝ ተነግሯል፤ ከሥልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ከማሳየት ይልቅ፣ ከመንግሥት ያጡትን ትኩረት ለመመለስ በዚህም፣ በቀጣዩ ሰኞ በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ጫና ፈጥረው ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም፣ ከእኩይ መካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት ስልት ሊኾን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾኖ የተሾመ አባት ከመዓርጉ የሚወርደው፡ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፤ በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ካልጠበቀ፤ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ ተቀባይነት ያጣ ከኾነና ይህም በተጨባጭ ተረጋግጦ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰን እንደኾነ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 33/1() እና () ተደንግጓል፡፡