07/11/2017

ኢትዮጵያ 
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ!!

ይሄ ስም ሲጠራ፥
ፀጉሩን የሚነጭ – ፊቱን የሚቧጭር
ድንጋይ እያፋጨ – እሳቱን የሚጭር
ምነው ግልፍተኛው – ተናካሹ በዛ
አረ ……….ወደዛ!!

በጨለማ ዘመን – ክፉ ቀን ላይ ወድቀን 
የጥላቻ ሀውልት – ከፍቅር መግዘፉ – ሰርክ ሲያስጨንቀን
“ኢትዮጵያ” የሚል ስም – መስማት ሲናፍቀን
ድንገት ታምር ሆኖ፥
ስሟ በትንሳኤ – መቃብር ፈንቅሎ – ሁሉንም ሲገዛ
እንደባኦል ነብይ – ፀጉሩን የሚነጭ – ምነው አልቃሽ በዛ?
አረ ………. ወደዛ!!

ዳግማዊው ዩሃንስ – አንገቱን የሰጠው
ካሳ የሞት ፅዋን – ጨክኖ የጨለጠው
ባልቻ በስተርጅና – ዳግም የተነሳው
አብቹ በቁጣ – ገና በልጅነት – ምንሽር ያነሳው
በየሰርጣ ሰርጡ – ነፍስ የተቀጠፈ – ሬሳ የወደቀው
ለዚህ ስም አይደል ወይ – ሐገሬው ያለቀው?

ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ

የሚል የፍቅር ስም፥
ሁሉን ሲያንበረክክ – ሁሉንም ሲገዛ
ምነው ተራጋሚው – ተናዳፊው በዛ
አረ ………..ወደዛ!!

ስሟ ምስክር ነው – የአንድነት ማህተም
ቀደን የማንጥለው – ነፍስ ላይ ሚታተም
የጥላቻ ነፋስ – ጠርጎ እንዳይወስደው
ከደም ካጥንታችን – ታሪክ ያዋሃደው!
ልክ እንደከንአን፥
ማር ባይሞላ ደጇ – ወተት ባታፈልቅም
ይሄን ስም አልለቅም!!
የሚል ሃያል ትውልድ – ከማህፀን ሲወጣ
ሙሴን የሚገድል – የፈሮ’ን አዋላጅ – ሰይፍ ይዞ መጣ!
ምን ሰይፉን ታምኖ – ሊገድለው ቢለፋም
ሙሴን የሚጠብቅ – የሃበሻ ረቢ – ከቶ አያንቀላፋም!

ይታየኛል ከሩቅ፥
ባህሩን ሲከፍል – በትሩን ዘርግቶ
ካለት ውሃ ሲያፈልቅ – እጆቹን አንስቶ
ደመናም ባይታይ – ሰማዩም ቢነጣ
የፈርኦን ምርኮ – ቀንበሩን ሰባብሮ – ነፃ እንደሚወጣ
በዮርዳኖስ ባህር፥
ያደፈውን ሸማ – በጋራ እንደሚያጥብ

ይኸው ነው ሚታየኝ … አስራሰባት ነጥብ!!