ከንቱ ውዳሴንና ኣጉል ወቀሳን ወደ ዳር

image_pdf
 iEmail
Share

ሰሞንኛው ሃገራችን ኢትዮጵያ ላይ የታየው ጉዳይ በጥሞና ለሚከታተለው ዜጋ የመከራችን መቆጫ የመጀመሪያው ምእራፍ ላይ መሆናችንን ለመረዳት ያስችላል። የኦሮሞ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኣቶ ለማ መገርሳ ከኣቻቸው ኣቶ ጎዱ ኣንዳርጋቸው ጋር ያደረጉት የሁለትዮሽ ኣስተዳድር የሰላምና የእርቅ ግንኙነት ለሃገራችን ፖለቲካ ኣዲስ ምርዓፍ ከፋች፤ ኢትዮጵያ የተጋፈጠባትን ህወሃት መሰረታዊ እምነቶች የሚሸረሽርና ወደ ተሻለ ጎዳና የሚመራን የአንድነት ኩራዝ ነው።

የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ኣባቶች ወደ ኣማራው መዲና ባህር ዳር መሄዳቸው በራሱ ለውጥ ነው ብዬ ከሚጮሁት ጋር ኣብሬ ኣላናፋም። እንዲሁም ለማ መገርሳ በህወሃት መልእክት ተሰጦት ነው፤ ድብቅ ዓላማ ስላለው ነው በማለት እንቅልፍ አጠዉ ከሚወቅሱት መደብ ሆኜም ኣልዘረጥጥም። የኔ እይታ ይህ ነው።

የለማ ኣስተዳደርና መልእክተኞች ወደ ባህርዳር መሄዳቸውንና ገዥና ነፍጠኛ እየተባለ ለዘመናት ሲዘለፍ፤ ሲወገዝ፤ ኣልፎም ከኖረበት ቀዬ ሲባረርና ሲገድለል ለሚኖረው ኣማራ ኑሮውን፤ ታሪኩን፤ ባህሉን ለላኡካኖች ማሳየታቸውን የሚቃወም ካለ የህወሃት ካድሬ መሆን ብቻ ኣለበት። ስለዚህ ጉዟቸው የሚመሰገን ነው።

ባህርዳር ላይ በተዘጋጀው መርሃ ግባር ላይም ርዕሰ ብሔር ገዱና ለማ ያቀረቡት ዲስኩር ይህ ኣዲስ ትውልድ ላለፉት 26 ዓመታት ከየትኛውም መሪ ያልተደመጠና ለትውልዳችን በጎ መልእክት የተላለፈት ኣንድነት የተሰበከበት ግሩም ዝግጅት ነው።

በተልይም ወያኔ ሆነ ብሎ የፈጠራቸውም ይሁን ወያኔ በፈጠረው ዘረኛ ስረኣት ተመርዘው ጽንፈኛ ብሔርተኞች እንደጉድ በበረከቱበት ሰዓት፥ ኢትዮጵያዊነትን እሳት ውስጥ በጣዱበት ወቅት፤ የኣንድነት ታሪክ እየተወሳ፤ የኣብሮነት ትርጉም እየተመረመረ፤ በኣማረና በተዋበ ኢትዮጵያዊ ቃላት ኣንድነትን ሲሰብኩ ላስተዋለ ትውልድ ለቀጣዩ ኢትዮጵያዊነታችን ጉዞ መሰረታዊ ችግሮቻችን የጠገነ ተግባር ነው።

ይህ ኣይነት መርሃ ግብር ላለፉት ሃያ ምናምን ኣመታት አልተሞከረም፤ ተሞክሯልም ከተባለ ኢትዮጵያን ኣፍርሰን ሰርተናታል በሚሉት “መለሳዊያን” የተከተበ የታሪክ ድሪቶ በተለይም በትግራይ ህዝብ የበላይነት ልእልና ላይ መሰረት ያደረገ በኣለማችን ብቸኛው የኣብዮታዊ ደሞክራሲ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ብሔር ኣዘል ጉባኤ ነው።

ወያኔ ህወሃት ኢትዮጵያዊነትን ኣይወድም። ለዚህን ያህል ዘመናት ስልጣን ላይ የመቆየቱ ምስጢርም በትግራዋይ መቀናጀቱ፤ የሃገሪቱን ወሳኝ ቦታዎች በትግራይ ሰዎች መያዙ ብቻ ኣይደልም። ዋናው ስልጣን ላይ የቆየበት ምክንያቱ የኣማራውንና የኦሮሞውን ልሂቃን እንዲቀራረቡ ኣለማድረጉና ሁለቱን ብሔሮች እርስበርስ እያናከሰ ብሎም ለዘመናት ወያኔ የሃገራችንን ሃብት እየጠራረገ ትግራይን ሲገነባ የፖለቲካችን ውይይቶች በነፍጠኝነትና ጠባብነት የተፈረጀ ጉንጭ ኣልፋ ንትርክ ላይ ያተኮረ የዜሮ ድምር ጨዋታ እንጅ የእኩልነትና የሃገራችንን ሃብት በተገቢው የመጠቀም ሁናቴ ኣልነበረም።

አቶ ለማና ገዱ የቀደዱት የፍረሃት ግርግዳ ወያኔን ክፉኛ ኣሳብዶታል። ከዚህ በሃላ ብአዴንና ኦህዴድ ስለ ኢትዮጵያዊነት እየዘመሩ በትግራይ የበላይነት ተጨፍልቀው ይኖራሉ የሚል እምነት የለኝም። የሁለቱ ህዝቦች ኣንድ መሆን ለሃገራችን ብቻ ሳይሆን ለኣፍሪካ ቀንድም የሰላም ዋስትና መሆኑን አመራሮቹ የተረዱ መሆናቸዉን ከቃላቸዉ ሰምተናል። ለማና ገዱ እንደተናገሩትም ከለሎች ሃገሮች መፍረስና አደጋዉን የተማሩና በመሰረታዊ ሃሳቦች ላይ የተስማማሙ ይመስላሉ።

በተጨማሪም እነዚህ የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሃይል እንዳላቸውም ሊሰመርበት ይገባል። ሃገራችንን ኢትዮጵያ ፖሊስን፥ደህንነትንና መከላከያን ጨምሮ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ሰራዊት እንዳላት ይገመታል። ምንም እንኳን የኣመራሩን ቦታ በትግራይ ተወላጆች ቢያዝም፤ የክልል ፖሊስ ፥ ልዩ ሃይል እና ደህንነት ግን በገዱና በለማ ስር መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። በኣማካኝም ሃገራችን ካሏት የሰራዊት ቁጥር ሁለቱ ክልልሎች ብቻ ከግማሽ ፐርሰንት በላይ መሆኑን ማወቅ ኣለብን።

የገዱንና የለማን ኣስተዳድር ማጠናከር፤ ኣልፎም ጥርስ ካላቸው የዲያስፖራ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ጋር ኣብረው የሚሰሩበት ሁነታን መፍጠሩ ኢትዮጵያ የገጠማትን መከራ የማሳጠሪያ ቁልፍና ዋናው ነው ብየ አምናለሁ።

በማንኛውም መልኩ ጠላትን መቀነስ ውጤታማ ያደርጋል። በግሌ ኣዲሱ ለገሰን ወይም ተፈራ ዋልዋን በማይበት ኣይን ገዱ ኣንዳርጋቸውን ወይም ለማ መገርሳን ኣላይም። ቢያንስ ኣሁን በሰሩት ስራ እመዝናቸዋለሁ። ይሄን ስል ግን ከወንጀል ነፃ ናቸዉ ማለቴ አይደለም ወንጀለኛ ናቸዉ የማለቱም ሃቅሙም የለኝም። ይህ ወደፊት በምትገነባዋ የኛ ኢተዮጵያ ዉስጥ በሚፈጠሩ ገለልተኛ ዳኞች የሚወሰን ይሆናል።

ኣቶ ለማ መገርሳና ኣቶ ገዱ ኣንዳርጋቸው በዚህ የወያኔ ከፋፍለህ ግዛው ዘመን የተፈጠሩ ክስተቶች ናቸው። ኦህዴድና ብአዴን ድርጅቶች መሪ እንደፈጠሩ ያሳዩበት በነዚህ ሰዎች ነው። በኣንጻሩ ህወሃት-ወያኔ ቅጠሉን እንደረገፈ ዛፍ እድገታቸውን የገቱ መሆንኑን የተመለከትንበት፤ ትግራይም ህዝብ በጠባባ ህወሃት ተውጦ ለመጭው የትግራይ ወጣት ኣደጋን እየደገሱለት ለሚገኙ የህወሃት ባለ ስልጣናት ግልጹን የወጣበት እውነታ ነው።

በሳይንሱ የኣንድ ዛፍ ቅጠል ሲረግፍ ወይም ሲደርቅ ዛፉ ዋጋ ኣይኖረውም ምክንያቱም ዛፉ ምግቡን ቅጠሉ ላይ ስለሚያዘጋጅ፤ ህወሃትም ያ ነው። ወደ ስልጣን ሲመጡም እነ ኣቦይ ናቸው ኣሁንም እነሱ።

ስለዚህ ገዱና ለማ ወደሃላ እንዳያፈገፍጉ ሊደገፉ ይገባል ባይ ነኝ። ኣንዳንድ ምስኪኖች ገዱ ወይም ለማ ዛሬውኑ ተነስተው ወያኔ ጥፋ እንዲሉ የምንመኝ የዋሆች አንጠፋም። ያደሞ እንዲሆን ሂደት ያስፈልገዋል፥ መደጋገፍና መናበብ ያስፈልገዋል። እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር ግን ብአዴን ውስጥም ሆነ ኦህዴድ ውስጥ ያለው ወጣት የትግራይ የበላይነት ያንገሸገሸው ለውጥ ፈላጊ ሃይል መሆኑን ግንባሬን ሳላጥፍ መናገር እችላለሁ።

የጽሁፌ መዝጊያ ምልዕክት

ለማ መገርሳና ገዱ ኣንዳርጋቸው ጊዜና ታሪክ ከዚህ የተሻለ ኣደራ ልትሰጣጭሁ ኣትችልም፤ የዚህ ሁሉ ትውልድ ዕጣ-ፋንታ በኣመዛኙ እናንተ እጅ ላይ ነው። በማስተዋል ሃገራችንን ወደተሻለ ጎዳና ማድረስ እንደምትችሉ ተረድታችጛል ብየም ኣምናለሁ። ኣንድ ሆናችሑ ይህን ለውጥ ፋላጊ ህዝብ ኣንድ ማድረግ ትችላላችሑና በርቱ ነው የምለዉ። ምሁራንና የድያስፖራ ፖለቲከኞች ደግሞ ከራስ ወዳድነት ወጣችሁ ከሁለቱ ሃይሎች ጋር ምክክር ብትጀምሩ መልካም ነው። ዋስትና ተሰጣጡ። ያኔ ለውጡ እውን ይሆናል ኣልያ ግን እንዳለፈው ሃያ ምናምን ኣመት ኦህዴድንና ብአዴንን ከደም መጣጩ ህወሃት ጋር እየደባለቁ ማበራየት ትርፍ ባርነትና ስደት ነው።

በጎ ያሰማን!
አ.ን

No widget added yet.

← “ያን እኔን አፋልጉኝ!” – ወለላዬ ከስዊድን የኦሮሞ #ኢትዮጲያዊነት ጠበቃና ምስክር አይሻም! – (ስዩም ተሾመ) →

Leave A Reply

Comments are closed