mail

Share

የዘመኑን ፈሊጥ የመኖርን ምስጢር

ሳስተውለው ውዬ ቆሜ ስመረምር

ጥበቡ ገብቷቸው መሄጃውን አውቀው

መላ የጨበጡት ስሌት አስተካክለው

ከተጠቀሙበት ኃያል ብልሃቶች

አንዱ ማስመሰል ነው ለመኖር ከሰዎች

እንደውም አንዳንዱ ከማስመሰል አልፎ

በረቀቀ ጥበብ በተንኮል ቆልፎ

ለተዘጋጀበት ላሰበበት ዕቅድ

ማሰለፍ ይችላል በግድና በውድ

እንዲሁም ሌላውን አድርጎ መሰላል

ሁሉንም አሟልቶ እላይ በመንጠልጠል

ሲፈልግ አጣልቶ፤ ሲሻው በማስታረቅ

ሌላን እየጎዳ ጥቅሙን በማስጠበቅ

በተገኘው መላ ባዘጋጀው መንገድ

መረቡን ዘርግቶ ገንዘብ ለማሳደድ

ምንም ጊዜ – የትም እሱን አስበልጦ

አምሮ ተሽቀርቅሮ በአልባሳት አጊጦ

ድሮውንም ያለው የቱጃር ቤተሰብ

ገና በልጅነት ያየ ብዙ ገንዘብ

ሃይማኖት አክባሪ ጿሚ ጸሎተኛ

እጁ እማይታጠፍ ካየ ችግረኛ

መምሰሉ አስገርሞኝ በማውቀው ቀንቼ

ልመስል ተነሳሁ እጆጄን ዘርግቼ

ብዙም ሳልገፋበት ገና ከጅምሩ

አላምርብህ አለ በኔ ላይ ነገሩ

በማያስለቅሰው አስቤ ለማልቀስ

መስዬ ቁጭ አልኩኝ የተራበ ፈረስ

ደስተኛ ለመምሰል ሳቁንም ብስቀው

ፊቴ መስሎ ታየ መርፌ ‘ሚወጋ ሰው

ሳላዝን አዝኜ ብሆን እንደራራ

መስዬ ታየሁኝ ትያትር ‘ምሰራ

አንዱን ካንዱ ጋራ በወሬ አስማምቼ

የራሴን ቆጥቤ የሰው አድፋፍቼ

ከሌላ እንዳየሁት ለማድረግ ብነሳ

ሸክሙ የከበደ መጣብኝ ወቀሳ

ካንዱ ተበድሬ ለሌላ በመክፈል

ብዙ ገንዘብ ያለው ለመባል ለመምሰል

እንደ ጮካዎቹ መንገድ ብዘረጋ

ልወጣው የማልችል ገጠመኝ አደጋ

ደግሞም አሰኝቶን ተጋብዞ መጋበዝ

በእዳ ደፈቀኝ አመጣብኝ መዘዝ

በፖለቲካው መስክ ገብቼ ልመራ

ተመራጭ ሆንኩና ያዝኩኝ ትልቅ ስፍራ

እሱም አልቀናኝም ወራትም አልዘለኩ

አጎብዳጅ ተብዬ ተዋርጄ ወረድኩ

ሁሉም አልሆን ብሎኝ ብመለስ ቦታዬ

አንድ ነገር ወድቆ ቆየኝ ከገላዬ

ምንድነው የጠፋኝ እያልኩኝ ስዋትት

ለካስ ሌላ ሰው ነኝ ራሴን አጣሁት

ማስመሰል ሳልጀምር በፊት የምታውቁኝ

ወሮታ እከፍላለሁ “ያን እኔን አፋልጉኝ!”