Posted by | 10/11/2017

የኑስ ሙሃመድ

ሐውልቱ እንዲቆም ያደረጉት የጣልያን ባለስልጣናትም የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል

ሐውልቱ እንዲፈርስ ሲከራከሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እና ጣልያናውያን በሰሩት መልካም ተግባር ተሸልመዋል
***
የጣልያኑ ፋሽስት መሪ ቤንቶ ሞሶሎኒ ቀኝ እጅ የነበረውና ለበርካታ ኢትዮጵያውያንና ሊብያውያን ዜጎች ሞት ተጠያቂ የሆነው በሙሉ ስሙ ሩዶልፎ ግራዚያኒ /Rodolfo Graziani/ የተሰኘው ሰው ሐውልት እንዲፈርስ በጣልያን ሀገር የሚገኘው ፍርድ ቤት ወስኗል፡፡ ግራዚያኒ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኛ በመሆናቸው ድርጊታቸውን መኮነን ሲገባ ሐውልት ሰርተን የወጣቱ አርኣያ ልናደርጋቸው አይገባም፤ ይህ ሁኔታም በኢትዮ ጣልያን ወዳጅነት ላይ እንቅፋት ይፈጥራል ሲሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲከራከሩ የነበሩ እንደ ሀብቴ ኪዳኔ ዓይነት ሰዎችና ይህን ጉዳይ በሀላፊነት የያዘው ማህበር በጣልያን መንግስት ውሳኔ መደሰቱን የገለጸ ሲሆን ሲተባበሯቸው ለነበሩ ጣልያናዊዮችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የላዚዮ ባለስልጣናትና በሮም ደቡባዊ ግዛት የምትገኘው ቲቪሊ ከተማ ከንቲባ ኢርኮሊ ቪሊ የህዝብን ገንዘብ በዓለማቀፍ የጦር ወንጀለኛነት ለተፈረጀው ለፋሽስቱ ግራዚያኒ ሐውልት ማሰሪያ እንዲውል መፍቀዳቸውን ተከትሎ የተለያዩ ምርመራዎች ሲካሄድባቸው መክረሙ የሚታወቅ ሲሆን ባሳለፍነው ማክሰኞ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

በጣልያን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣታቸውና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዳቸው ክሱ ተቀባይነት አግኝቶ ሐውልቱ እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡

በጣልያን የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማህበር አባሎች የአንዳንድ አሽሟጣጮች ተረትና ንቀት ሳይበግራቸው በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ወኔ በመነሳት የግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ከማስወሰናቸውም በላይ ይህ ሐውልት እንዲሰራ በጀት የፈቀዱ ባለስልጣናትንም እንደየ ድርጊታቸው ከ120 ዩሮ ቅጣት ጀምሮ እስከ 8 ወር የሚደርስ እስራት አስፈርደውባቸዋል፡፡

ግራዚያኒ በሀገራችንና በሊብያ ላይ ከፍተኛ እልቂትና ጭፍጨፋ ያደረገ አለም አቀፍ የጦር ወንጀለኛ ነው፡፡ በተለይ የሀገራችን መዲና በሆነችው አዲስ አበባና አንዳንድ ከተሞች የተደረገው የየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎች የሞቱበት ሲሆን ዓለምም በጥቁር መዝገቡ ያሰፈረው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡ ኢጣልያ ለሁለት ጊዜ ያክል በሀገራችን ላይ ወረራ ብታደርግም ጀግኖች አርበኞቻችን አጥንትና ደማቸውን አፍስሰውን ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆነች ሉዓላዊት ሀገር አውርሰውናል፡፡ በዚህም ታሪክ ሁሌ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡

በአንፃሩ እንደ ግራዚና ሞሶሎኒ ዓይነት ጭራቆች በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሽንፈት ተከናንበው ከመዋረዳቸውም በተጨማሪ የሰሩትን መጥፎ ተግባር ዓለም ሲያወግዘው ይኖራል፡፡ ለእነሱ የመታሰቢያ ሐውልት ይቅርና መቀበሪያ ምድር እንኳን እንዳይኖራቸው ዓለምና ልጆቿ በጽኑ ይመኛሉ፡፡

ከሁሉም ከሁሉም ግን ያን ሁሉ ውጣውረድና የአይሳካላችሁምን አስተሳሰብ ሰብረው ይህ የግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ላደረጉት ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ይህ ድል በነሱ ፊታውራሪነት ለሶስተኛ ጊዜ ፋሽሽት ጣልያንን ድል የማድረግ ያህል የከበረ ሲሆን እነሱንም ልክ እንደ ጀግኖች አባቶቻችን ሁሉ ታሪክ በበጎ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡

አያችሁ አይደል…ኢትዮጵያዊነት ለተጠቀመበት ሁሌም የሚያሸንፍ ረቂቅ መለኮታዊ ኃይል ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ከፊትም ከሁዋላም አሸናፊነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ነፃነትና ጨዋነትም ነው….ንቁ!

Filed in: Amharic