• 10 ኖቬምበር 2017

የኤርትራንና የሶማሊያን ጉዳይ እንዲያጠና በተባባበሩት መንግስታት ፅህፈት ቤት የፀጥታው ምክር ቤት ሃላፊነት የተሰጠው ተቆጣጣሪ ቡድን እስካሁን ባካሄደው ጥናት ኤርትራ ኣልሸባብን እንደምትደግፍ ማረጋገጫ እንዳላገኘ ኣስታወቀ።

ጥናቱም ለስምንት ዓመታት የተደረገ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ያቋቋመው የኤርትራ እና የሶማሊያ ተቆጣጣሪ ቡድን በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ምንም እንኳን ሁለት በስም ያልተጠቀሱ ጎረቤት ሃገራት ኤርትራ ለአሸባሪው ቡድን አልሸባብ ድጋፍ ታደርጋለች ብለው በመክሰስ መረጃዎችንም ቢያቀርቡም ተቆጣጣሪው ቡድን ግን ማረጋገጥ እንዳልቻለ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ ”በአሰብ ከተማ በቅርቡ የተመሰረተው አና እየተስፋፋ የሚገኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ወታደራዊ ካምፕ የጦር መሳሪያዎችን ስለሚያጓጉዝና ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመተባበሩ፤ በኤርትራ ላይ ተጥሎ ያለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የሚጥስ መሆኑን ተቆጣጣሪ ቡድኑ እሰታውቋል”በማለት ሪፖርቱ ያትታል።

ተቆጣጣሪው ቡድን ኤርትራ ለአልሸባብ ድጋፍ እያደረገች ነው የተባለውን ክስ ቢያጣራም ለ4ኛ ጊዜ ምንም አይነት መረጃ እንዳላገኘ አስታውቋል።

በተጨማሪም ከኤርትራ የሚገባ እና የሚወጣ የጦር ዝውውር የሚያሳይ መረጃ እንዳላገኘ ጨምሮ አስታውቋል።

አስመራ
Image copyrightAFP

ተቆጣጣሪ ቡድኑ በጅቡቲ አለመረጋጋትን ለመፍጠር የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖችን ግን ኤርትና እንደምትደግፍ ባቀረበው ሪፖርት አስፍሯል።

በሪፖርቱ ውስጥ ከኤርትራ ድጋፍ ያገኛሉ ተብለው የተጠቀሱ ቡድኖች መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ የሆኑት የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር፣ ግንቦት ሰባት፣ የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደምሕትና )የጂቡቲው ፍሮንት ፎር ዘ ሪስቶሬሽን ኦፍ ዩኒቲ ኤንድ ዲሞክራሲ ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያም በበኩሉዋ የኤርትራን መንግስት የሚቃውሙ የታጠቁና ያልታጠቁ ተቃዋሚዎች እንደምትደግፍ ይታወቃል።

በአረቡ ባህረ ሰላጤ የተፈጠረው ችግር በአፍሪካ ቀንድ ፀጥታና ደህንነት ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረና፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ በኤርትራና በጂቡቲ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለማርገብ እንደታዛቢ በሁለቱ ሀገራት ድንበር መካከል ጣልቃ ገብቶ የነበረው የኳታር ሃይል እንዲወጣ ተገዷል።

አሁንም ቢሆን በጂቡቲና በኤርትራ ድንበር መካከል የሚያከራከረው ራስ ዱሜራ የተባለው ግዛት አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሁለቱም ሀገራት እንደሚያደርጉና፤ በተጨማሪም ጂቡቲም በኤርትራ ተይዘውብኛል የምትላቸው የጦር ምርኮኞች ላይ ምንም መረጃ እንዳላገኘች ሪፖርቱ አክሎ ይገልጻል።

ይህ ተቆጣጣሪ ቡድን ለአራተኛ ጊዜ ኤርትራ አልሸባብን እንደምትደግፍ መረጃ ባለማግኘቱም ” በኤርትራና በሶማሊያ ላይ የተጣለውና ለዘመናት በአንድ አይነት መንገድ ሲታይ የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ስርዓት ለየብቻው ተለያይቶ እንዲታይ” ማሻሻያውን አስተላልፏል።

ሪፖርቱ በተጨማሪ በኤርትራ ላይ አሉ የሚላቸውን ችግሮች የጠቀሰ ሲሆን ከነዚህም ወስጥ በኤርትራ መንግስት ያለው ግልጽ ያልሆነ ኣካሄድ፤ የሀገሪቱን ተፈጥሯዊ ሃብት አስተዳደሩ በትክክል አልተጠቀመም ከሚልም ጋር ተያይዞ የግዳጅ ጉልበት ተጠቅሟል ተብሎ በተባባሩት መንግስት የሰብአዊ መብት ሪፖርት የሚከሰው ነቭሱን የሚባል የማእድን ኩባንያ ቢሻ ከሚባለው ማእድን ከሚያመርትበት ቦታ ብቻ 43.3 ሚልዮን ዶላር ገቢ ለኤርትራ መንግስት እንደሰጠም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የኤርትራና የሶማልያ ተቆጣጣሪ ቡድን በአውሮፓውያኑ በ2009 ዓ.ም የተመሰረተ ነው። በኤርትራና በሶማልያ የተጣለው የጦር ማእቅብ 1907 ማዕቀብ ይባላል።