November 11, 2017 07:56

ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ አንድነቷ፣ ሉዓላዊነቷ ህልውናዋና እንደ አገር የመቀጠል እድሏ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት የዚያ የመከራ ዘመን እግዚአብሔር ለዚች ታላቅ አገር ታዳጊ መስፍን አስነሳላት፣ እርሳቸውም የቋራው አንበሳ ዳግማዊ ቴወድሮስ ነበሩ። አፄ ቴወድሮስ በዘመነ መሳፍንት የተከፋፈለቸውንና የተዳከመችውን ኢትዮጵያ አንድና ታላቅ አገር አድርገው ወደ ስልጣኔ ማማ ለማውጣት ታላቅ ራዕይ ሰንቀው ሲነሱ ህልም አጨናጋፊዎች ከሩቅ አልመጡም ነበር። ይልቁንም በተከፋፈለችው ኢትዮጵያ የግል ጥቅምና ምቾታቸውን አስጠብቀው ለመቀጠል የፈለጉ የቅርብ ወንድሞቻቸው ናቸው ጠላት ሆነው የተነሱባቸው። ያለጊዜያቸው የተፈጠሩት ታላቁ ባለራዕይ መሪ አፄ ቴዎድሮስ ህልማቸው ባይጨናገፍ ኖሮ ዛሬ የምናያት ኢትዮጵያ ከአሁኑ እጅግ የከበረ የስልጣኔ፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት አገር በሆነች ነበር።

ትናንት አልፎ ዛሬ ሲመጣ የዘመናት ሁሉ ጌታ የሆነው አምላካችን ህዝቡን ያለ ታዳጊና መሪ ምድረ በዳ ስለማይጥለው ዛሬም ዘመን ቆጥሮ በጎሳ ፓለቲካ፣ በዘረኝነት፣ በጥላቻ፣ በዘረፋ፣ በሰላም እጦት፣ በፍቅር እጦት፣ በመከባበር እጦት፣ በፍትህ እጦት በጨለማ እየዳከረች ላለችው ኢትዮጵያ ፈጣሪያችን እንዲህ ብሎ ታዳጊ መስፍን አስነሳላት፣ ” በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፣ በመድሃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፣ እጠብቅህማለሁ፣ ምድርንም ታቀና ዘንድ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ የተጋዙትንም ውጡ፣ በጨለማ የተቀመጡትም ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለህዝቡ ሰጥቼሃለሁ።” ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 49 ቁጥር 8_9። ይህ እውነት ነው አሁን በምድረ ኢትዮጵያ ሰማይ ምድሩን ሞልቶ የጨለማውን ብርታት በብርሃን እየሰነጣጠቀው የሚገኘው፣ ይህ መለኮታዊ ጥሪ ነው ሁለቱን ታላላቅ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ወደ እውነተኛ ማንነታቸው እየጠራቸው የሚገኘው፣ ይህ መለኮታዊ ጥሪ ነው የኦሮሞ መሪዎችን፣ ሽማግሌዎችን፣ አባ ገዳዎችንና ወጣቶችን ከመኝታቸው ቀስቅሶ እውነተኛ ወንድማቸው ወደ ሆነው የአማራ ህዝብ ጉያ ወስዶ አንገት ለአንገት አስተቃቅፎ በፍቅር የሚያስለቅሳቸው።

በመሆኑም አሁን የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ባለፉት ሀያ ስድስት ዓመታት በልባቸው ጠላት የዘራባቸውን መራራ ስርና እንክርዳድ ነቅለው ለእውነተኛ አንድነት፣ ለእውነተኛ ወንድማማችነት፣ ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት እንዲነሱና የጥላቻንና የዘረኝነትን በር ዘግተው የፍቅርንና የአንድነትን በር በመክፈት የኢትዮጵያን እውነተኛ ትንሳኤ ለማዎጅ እጅ ለእጅ እንዲጨባበጡ ያስቻላቸው የዚህ ክቡር ብላቴና ለማ መገርሳ የከበረ የኢትዮጵያዊነት ራዕይ ብቻ ነው። ይህን ታዳጊ መንከባከብ፣ መደገፍ፣ ከጎኑ መቆም ነገ ከፍ ብላ በነፃነት ልናያት ለምንናፍቃት እናት አገራችን ኢትዮጵያ ዘብ መቆም ነውና ምክንያታዊ ካክሆነ ትችትና ነቀፋ ነፃ ወጥተን ይህን የቴዎድሮስ አልጋ ወራሽ ታዳጊ ልዑል ሆ ብለን ወደ ዙፋን ልናመጣው ይገባል።

ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የትንሳኤ ድምፅ፣ የአንድነት ድምፅ፣ የፍትህ ድምፅ፣ የእኩልነት ድምፅ፣ የመከባበር ድምፅ፣ የመወንድማማችነት ድምፅ፣ የሰላምና የብልፅግና ድምፅ የሚያሰማላት ነብይና ሐዋርያ እንጅ የጦርነት ነጋሪት፣ የጥፋት ነጋሪት፣ የእልቂት ነጋሪት፣ የጥላቻ ነጋሪት፣ የዘረኝነት ነጋሪነትና የመለያየት ነጋሪት የሚጎስምላት የጥፋት መልዕክተኛ አይደለም። እስካሁን በተጓዝንበት የተሳሳተ የችግር አፈታት እየተጓዝን ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና ብልፅግና አንወስዳትም፣ ይልቁንም ወደ መበታተንና መፈራረስ እንጅ። በመሆኑም ሁላችንም ሰከን ብለን እውነተኛ ድምፆችን ከአስመሳይ ድምፆች እንለይ፣ እውነተኛ የፍቅርና የአንድነት መሪዎችን ከአስመሳዮችና ከአድር ባዮች እንለይ።

በእኔ የግል እምነት ታዳጊው ብላቴና ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ለዚች አገር ፈጣሪ ቀብቶ እንደ ዳዊት ህዝቡን ከጎልያድ ተግዳሮት እንዲታደግ ያስነሳው ጀግና ስለሆነ በንፁህ ልብ፣ በፍቅርና በደስታ እንቀበለው። ለብዙ ዓመታት ስለ ኦሮምያ መገንጠል በተሰበከባት ኢትዮጵያ ከኦሮምያ ተወልዶ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ትንሳኤ ከመስበክ የበለጠ ምን አዲስ ነገር በዚች አገር ለመስማት ትፈልጉ ነበር? ትናንትን በታሪክ ተምረንበት ነገን በፍቅር፣ በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በእውነተኛ ወንድማማችነትና በኢትዮጵያዊ አንድነት እንድንኖር የሚታወጅልንን የፍቅር ወንጌል መስማት የሚያመን ከሆነ ምን ዓይነት ወሬ ለመስማት እንፈልጋለን?
በአጠቃላይ አሁን ጊዜው የፍቅር ነው፣ የአንድነት ነው፣ የመከባበር ነው፣ የነፃነት ነው፣ የፍትህ ነው፣ የኢትዮጵያዊነት ነው። የዚህ የከበረ ጊዜ አዎጅ ነጋሪ ሆኖ ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ ተነስቷል። በመሆኑም ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በጎሳ ፓለቲካ ለምትታመሰው አገራችን አንድነትና ፍቅር ለመፍጠር ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሆነው ተነስተዋልና ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ፣ ዓይን ያለው ሁሉ ይይ፣ አንደበት ያለው ሁሉ ይመስክር፣ መጪው ዘመን ዘረኝነትና ጥላቻ ተቀብሮ ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም በኢትዮጵያ የሚነግስበት ይሆናል።
__________________________________________________
የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ድምፅ ኢትዮጵያን ከወደቀችበት አንስቶ ቀደ ከፍታ ያወጣታል!!
ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ነብይ፣ ሐዋርያና መሐንዲስ ሆኖ ተነስቷል!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ዳርቻዋንም ያስፋልን!!
Credit to:Z-Metaphors ጥበብ