November 12, 2017 10:21

ሁልጊዜም መንበረ ሥልጣናቸው በሕዝብ የበቃኝ እምቢተኝነት በራደ ቁጥር እየተሸበሩ አገርና ሕዝብን የባሰ ማሸበር እንጅ የትክክለኛ መፍትሄ አካል መሆን ጨርሶ ከማይሆንላቸው ጨካኝ ገዥዎቻችን ሰፈር ከሰሞኑ ከምንሰማቸውና ከምናነባቸው ክስተቶች መካከል የአቶ አባዱላ ገመዳ እና የአቶ በረከት ስምዖን ከያዙት ሥልጣን መልቀቅ በዋናነት ይገኙበታል ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕረዝደንት አቶ ለማ መገርሳም በሚያሰሟቸው ዲስኩሮች ውስጥ ፈጣሪና ጠርናፊ ድርጅታቸውን (ህወሃትን) የሚዳፈሩ የሚመስሉ ንግግሮችን እዚያም እዚህም ጣል ጣል ማድረጋቸው እና በድርጅታቸው ኢህአዴግ/ኦሆዴድ እንደ የፖለቲካ ነውር ሲቆጠር የነበረውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቁ ቃላትና ሀረጎችን ለምንም ወይም በምንም ምክንያት ይሁን በግልፅና በድፍረት መናገራቸው “ያልተለመደ” እስከሚባል ድረስ የጆሮን ቀልብ ከሳቡ የሰሞኑ ወሬዎች አንዱ መሆናቸው አልቀረም።

“ክቡር ፕረዝደንት” ዶክተር ሙላቱ ተሾመም የዚሁ ሰሞን ወሬ ሳይነካቸው የቀረ አይመስልም። ተፅፎም አንብበናል (ያልተረጋገጠ ወይም በእራሳቸው ያልተስተባበለ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ)። ነገርየዋ ትንሺም ብትሆን ዕውነትነት ኖሯት «እስከአሁን በህወሃት የፖለቲካ መጠንና ይዘት ተለክቶ ከተላበስኩት የሥልጣን ካባ ስር ያለውን የረከሰ ወይም እኩይ ፖለቲካዊ ሰብዕናየን ጨርሶ አውልቆ ለመጣል ወኔው ወይም ድፍረቱ ባይሆንልኝም ቢያንስ ማንገራገሬ አይቀርም» ዓይነት እራስን የመፈለግና የመፈተሽ ተነሳሽነት አድሮባቸው ከሆነ እሰየው ነው።

የአቶ በረከት ከያዙት ሥልጣን መልቀቅ ህወሀቶችና ግብረ አበሮቻቸው በሥልጣን ብልግና ከተቆጣጠሩት እና ከሚንበሸበሹበት የአገር ሀብት «ትንሽም ብትሆን ለምን ድርሻዬ ይቀርብኛል» በሚል በዚያው ገደብ የለሽ የብልግና መንገድ ዘመነኛ ቱጃር ባለሥልጣናት ከሆኑት አንዱ ለመሆን ሲደክሙ በመገኘታቸው ምክንያት እንደሆነ (ሊሆን እንደሚችል) ዜናዉን ሰምተናል። የትኞቹ የኢህዴግ በተለይ ግን የህወሀት ባለሥልጣናት (ሲቪልም ሆነ ወታደራዊ) የአደባባይ ምሥጢር ከሆነው እና አገርና ሕዝብን በብርቱ ካደቀቀው የሥልጣን ብልግና (ሙስና እና ዘረፋ) ነፃ ሆነው አቶ በረከትንና መሰሎቻቸውን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የያኔ «ጓዳቸውን» አቶ ታምራት ለአይኔን “ሲየቅለበልበኝ ስኳር ልሼ ተሳሳትኩ” ብለው እንዲናዘዙ ያደረጉትን ታሪክ እንደሚደግሙልን ወይም ደግሞ ምረመራው “እኛ የራሳችን ብርቅዬ አገልጋዮች እንኳ አንምርም ። በረከትም በዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ መሠረት ተመርምሮ ነፃ ሆኖ ተገኝቷል” የሚል ዜና ይነግሩን እንደሆነ የምናየው ይሆናል።

እይታዬ በምን ጉዳይ ላይ እንደሆነ ይህን ያህል ካልኩኝ የዓላማየን ይዘት ግልፅ ያደርጉልኝ ዘንድ እንደ መግቢያ የሚከተሉትን አንቀፆች በአጭሩ ልጠቀም፥

የሚኖረን የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ልዩነትና ግጭት አንዱ የሌላውን የግል ተፈጥሮአዊ ሰብዕና እና ሕይወትን ወደ ማጥቃቱ እንዳይጎትተን ስሜታችን መቆጣጠር ግድ ይለናልና እኔም በዚህች የእይታ ጽሑፌ የምችለውን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብኝ እገነዘባለሁ። ይህን ሆኖ ለመገኘት የሚጠይቀን ነገር ቢኖር የመነጋገሪያና የመከራከሪያ ርዕሰ ጉዳያችን መነሻና መዳረሻ በሰዎች ዙሪያ ሳይሆን በሰዎች አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ዙሪያ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግለሰቦች እንደማነኛውም ሰው ይሁን እንደ አንድ አገር ዜጋ (የሕወሕት/ኢህአዴግ አባላትን ፣ ደጋፊዎችንና ግብረ በላዎችን ጨምሮ) ያላቸውን ወይም የሚኖራቸውን አወንታዊም ሆነ አሉታዊ የግል ባህሪና ጉዳይን የመገምገምና የመኮነን ዓላማና ፍላጎትም የለኝም ። ተገቢነት ፣ ትክክለኝነትና ገምቢነትም የለውምና ።

በሌላ በኩል ግን ግለሰቦች ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑትን መብትና ጥቅም በማስከበር መሠረታዊ ዓላማ ዙሪያ የተሰባሰቡ ድርጅቶች ወይም ማህበራት በአንድ ወይም በሌላ መልክ የአገር ደህንነት ያስጨንቀናል እና የወገን ህመም ያመናል ብለው የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ አድናቆትና ድጋፍ የሚገባቸውን ያህል ፣ ከዚህ በተፃራሪ ሲቆሙ ወይም ምን አገባኝ ሲሉም ያለምንም ማመንታት ፣ በቀጥታ እና በማያወላዳ ሁናቴ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በተግባር መታገል ቢያንስ የውዴታ ግዴታ ነው የሚል ብርቱ እምነት አለኝ። ብዙ የምንናገርለትና በፅዕኑ የምንመኘው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመመሥረትና እና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያነትን የማስፈን ታላቅና የተቀደሰ ዓላማ ዕውን እንዲሆን ከምር የምንፈልግ ከሆነ ።

አዎ! ሩብ ምዕተ ዓመት ከተጓዝንበት ፣ ለሁለንተናዊ ቀውሳችን አይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ከሆነው እና ይኸው በዚህ ክፍለ ዘመንም ማቆሚያ ካጣው ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውድቀታችን መላቀቅ ካለብን ግልፅ ፣ ደፋር፣ ገንቢ እና የነገውን በግልፅና በቅንነት የሚየይ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሰብዕና ግድ ይላል።

ታዲያ ይህን ለማድረግ ደግሞ የሥልጣን ደረጃን ፣ የንብረት ባለፀጋነትን ፣ የትምህርት ደረጃን ፣ የልደት ዘመንን እና ወዳጅነትን (ጓደኝነትን) እና ዝምድናን በራሳቸው እንደመመዘኛ እየተጠቀምን ከሆነ የትም አለመድረስ ብቻ ሳይሆን ተያይዘን ወደ ባሰ አዘቅት ልንወድቅ እንደምንችል ልብ ማለትም ይበጃል። እናም የምንለውና የምናራምደው አስተተሳሰብና አቋም ትክክለኛነት ፣ ተጨባጭነት ፣ አግባብነት እና ገንቢነት አለው ብለን በዕውን እስከአመን ድረስ ከመልካም ሰሪ ጋር ሳናወላውል አብረን ለመቆም ፣ ከክፉ አድራጊ ጋር ግን አግባብነት አለው በምንለው ስልትና ባልተቆጠበ አቅም የመፋለሙ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ልንፈቅድ አይገባም። ይህን የምናደርገው ደግሞ ወደፊት የሰመረ እንዲሆን ከምንፈልገው የአብሮነት ጉዞና መዳረሻችን ጋርም የተቆራኘ በመሆኑ ነው :: ከዚህ ጋር አብሮ መሄድ ያለበት ጉዳይ አጥፊዎችን አጥፊዎች በማለት ከጥፋት ከተመለሱ የለውጥ ግባት አመንጮችና አስተዋፅኦ አበርካቾች እንዲሆኑ ማገዝ ፣ ካልሆነ ግን የድንቁርና እና አፍራሽ የፖለቲካ ጨዋታቸውን ማምከን የግድ ነው። በአጭሩ በምንለውና በምናደርገው ጉዳይ (ነገር) እርግጠኞች እስከሆን ድረስ አካፋን አካፋ ብሎ መጥራት (call it as it is ) ትክክልና ተገቢ ነው።

የአስተሳሰባችንን እና ከእርሱ የሚወለደውን ተግባራችንን ምንነትና ለምንነት በግልፅና በቀጥታ ለመጥራት (ለማለት) ድፍረትና አቅም የምናጣ ከሆነ አለንና እንኮራበታለን የምንለው ዕውቀትና ተሞክሮ በከንቱ የባከነ ወይም የተበላሸ ወርቃማ ሃብት መሆኑን ማመን ባንፈልግም (ወኔ ብናጣም) ዕውነታውን ግን ጨርሶ አንለውጠውም። የሩብ ምዕተ ዓመት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ፣የማህበራዊና የሞራል ውድቀታቶቻችን አንዱ ምክንያት ይኸው አካፋን አካፋ ብሎ በመጥራት ወደ ትክክለኛው የመገናኛ መንገድ ለመምጣት በጎ ፈቃድና ጥረት በእጅጉ ስለጎደለን ነው። ይህንን ዕውነት በቅንነትና በድፍረት ተቀብለን እራሳችንን ለማረም ብርቱና አስቸኳይ እርምጃ ካልወሰድን በስተቀር የውድቀት አዙሪቱ ስፋትና ጥልቀት እየከፋ እና የአገርና የሕዝብ መከራና ውርደትም በዚያው ልክ እየባሰበት እንደሚሄድ ለማመን «ከአላምንም አሳምነኝ/አሳምኝኝ» ክርክር ውስጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም።

እናም ለዚህ ነው የሰሞኑን የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ከሥልጣን ለቀቁ እና አንዳንዶች ደግሞ በየአጋጣሚው በሚያሰሟቸው ዲስኩሮቻቸው ሕወሀትን መዳፈር ጀመሩ በሚለው ወሬ ዙሪያ ስንነጋገር አላስፈላጊ ከሆነ ዙሪውን የመዞር አስተያየት ፣ ትችት ወይም ትንታኔ ወጥተን አካፋን አካፋ እያልን መነጋገር ያለብን። ምክንያቱም የምንነጋገረው የተወሰኑ የገዥው ቡድን (ግንባር) ባለሥልጣናት በሚፈጥሩት የፖለቲካ ክስተት ላይ ብቻ ሳይሆን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የእነዚህን ባለሥልጣናት ብልግና እና የማንነት ውደቀት አቅፎና ደግፎ ስለያዘው ፣ እና በተቃራኒው ደግሞ አገርና ሕዝብን ረግጦና አዋርዶ ስለሚገዛው የፖለቲካ ሥርዓት ነውና።

ወደ ዋናው የእይታ ሃሳቤ ልለፍና በዚህ ሰሞን እገሌ የሚባለው የሕወሐት/ኢህአዴግ ባለስልጣን የነበረበትን ስልጣንና ሃላፊነት ለቀቅሁ አለ ፣ ወይም እለቃለሁ አለ ፣ ወይም ሊለቅ ነው ፣ ወይም መልቀቁ አይቀርም በሚለው ዜና ዙሪያ የሚቀርቡ የተለያዩ ትንታኔዎችንና አስተያየቶችን ታዝበናል ። እየታዘብንም ነው። በመሰረቱ ይህ የሚጠበቅ፣ መኖርም ያለበትና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጤናማ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ እንደለመደብን ከክስተታዊ (incidental) ነገሮች ጋር ብልጭና ድርግም ( on and off) የምናደርገው የፖለቲካ የሙቀት መጠን ( political temperature) የሸረኛና ሴረኛ ገዥዎቻችን ተጠቂዎች እንደሚያደርገን ግን ከራሳችን የፖለቲካ ታሪካና ተሞክሮ በላይ ነጋሪ የለንምና አስተዋይነትን የተላበሰና ስሜታዊነት ያልተጫነው የዕውቀትና የአስተሳሰብ ድባብ አስፈላጊነት የሚያስማማን ይመስለኛል ። በሌላ አገላለፅ የሰሞኑን የሥልጣን መልቀቅ «ሰበር ዜና» ማስተናገድ ያለብን እስከአሁን የሆነውን ፣አሁን እየሆነ ያለውን የፖለቲካችን ዕውነታ፣ እና ነገ እንዲሆን የምንፈልገውን የዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ባደረገ የፖለቲካ ግንዛቤና መርህ ላይ ቆመን መሆን አለበት ብየ አምናለሁ።

የህወሃት/ኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በተለይም ስልጣን ለቀቁ ወይም ሊለቁ ይሆናል ከሚባሉት ጋር ልዩ ግኑኝነት ( networking ) ያላቸው ክስተቱን «የፈቃደኝነት ጥልቅ ተሃድሶ አካል እንጅ የገዥ ፓርቲያቸውንም (የግንባራቸውንም ) ሆነ በቅርፅ ብቻ ከፓርቲያቸው የተለየ የሚመስል መንግሥታቸውን ድክመት (ውድቀት) የሚያመላክት ፈተና ወይም መረበሽ አይደለም» በሚል የጭንቀት ፕሮፖጋንዳ ሊያደነቁሩን ቢሞክሩም ዉስጠ ሕሊናቸው ግን አፍጥጦ የሚያዩት ሐቅ ከሚሞክሩት የጭንቀት ማስተባበያ ጋር ጨርሶ የተለየ መሆኑን አሳምረው ያውቁታል።

እነዚህ ወገኖቻችን በድፍረትና በግልፅ ድክመትን (ውድቀትን) አምኖ በመሬት ላይ ካለው ሐቅ ጋር በሚገናኝ ሁናቴ ተገቢውን የመፍትሄ መንገድ የመፈለጉና የማፈላለጉ ባሕሪና ጥበብ በእጅጉ ስለሚጎላቸው የሚመርጡት መንገድ የሥልጣንን ኪሳራ እያሰሉ እርሱኑ መከላከሉ ላይ ነውና ሰፋና ጠለቅ አድርጎ ማየትን ይጠይቃል ባይ ነኝ። ። ገዦቻችን ከዚህ እጅግ አደገኛ አዙሪት አለመውጣታቸው የመከራውንና የውርደቱን ፍፃሜ ለማፋጠን የሚደረገውን ሕዝባዊ ንቅናቄ(ትግል)ፈታኝ እንደሚያደርገው ከራሳችን የፖለቲካ ታሪክ የበለጠ አስረጅ የለንምና በክስተቶች ላይ እየተነሳን የምንሰጠው ግልብና የተሳሳተ ድምዳሜ (እንደሰሞኑ ማለት ነው) ሰፋ ያለና ጥልቀት ያለው ትኩረትን ይሻል ብየ አምናለሁ።

የሰሞኑን በተለይም በሁለቱ የሕወሐት የፖለቲካ ፍጡሮችና አገልጋይ አካላት(በኦሆዴድ እና በብአዴን) ባለሥልጣናት አካባቢ የሚስተዋለውን መያዣና መጨበጫ የሌለው የጋራ ሥልጣንን የመታደግ ብቻ ሳይሆን የየግልን የክፉ ቀን መጠለያ (መጠጊያ) ወዴትነትን ለመቃኘት የሚደረገውን ዘመቻ መሰል ጥድፊያ በጥንቃቄና በትዕግሥት ልናጤነው ይገባል ባይ ነኝ :: « የለውጥ ኅይሎች ወይም ለውጥ ናፋቂዎች ከኢህአዴግ ማህፀን ተገኙ» የሚል ዓይነት ከስሜታዊነት ፣ ከግልብነት እና ከሊሆን ይችላል ( IF) የሚቀዳ መልክተ ፖለቲካን በአግባቡ ልብ ልንለውና ወደ ዕውነተኛዉና ትክክለኛው መስመር ልንመልሰው ግድ ይለናል :: ያለዚያ ለበርካታ ዓመታት ከመጣንበት ለብርቱ የፖለቲካ ሕመማችን ምክንያት (cause) ትክክለኛውን መድሃኒት መፈለግና መጠቀም ይቅርና ጊዜአዊ የሕመም ስቃይ ማስታገሻ እንኳን ጥቅም ላይ መዋል አቅቶን እስከአሁን እግዚኦ! ከሚያሰኘን የፖለቲካ ደዌ አንገላገልም።

በመሬት ላይ ያለው ዕውነታ የሚነግረን የሰሞኑ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሥልጣን የመልቀቅ እና ሕወሐትን “የሚዳፈሩ” የሚመስሉ ቃላትንና ሐረጎችን በየዲስኩሩ የመቀላቀል ክስተት መነሻዎቹ የሚከተሉት ተጨባጭና ፈታኝ ሁኔታዎች መሆናቸውን ነው ፥

ሀ) ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ከመሻሻል ይልቅ እጅግ አስቀያሚና አደገኛ እየሆነ የዘለቀውና ንዑሳን (minority) የጎሳ ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ጠርንፈው በያዙት አምባገነናዊ ሥርዓት ምክንያት በሕዝብና በእነሱ (በገዥዎች) መካከል የነበረው (ያለው) ቅራኔ ከመሠረታዊ ለውጥ በስተቀር ከቶውንም መፍትሄ ሊያገኝ እንደማይችል ከበቂ በላይ ግልፅ መሆኑ ሕሊናው በድንቁርና ወይም መረን በለቀቀ የግል ጥቅም ላልታወረ ሁሉ በርቀት የሚታዘበው ሳይሆን እየኖረው ያለ ዕውነታ ነው ።

ለ) ይህን የለውጥ አይቀሬነት መሠረታዊ ምክንያት ተከትሎ ደግሞ ፥

በግንባሩ (ኢህአዴግ)ውስጥ አራጊና ፈጣሪ ነኝ በሚለው ህወሀት እና በሌሎች በተለይም የብአዴንና የኦሆዴድ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች መካከል የአሽከርነቱ(የአሻንጉሊትነቱ) ቀንበር “ይቅለልልን” በሚል ዓይነት የቅሬታ ምክንያት “በእረግጠን እንግዛው” ቃል ኪዳናቸው ላይ መንገጫገጭን ማስከተሉም የሚታይና የለወጥን ግድ ባይነት የሚያመላክት መሆኑ ግንዛቤ የሚነፈገው አይደለም።

በግንባሩም ሆነ በእያንዳንዱ አባል ድርጅት ውስጥ በላይኛው ካድሬ(ባለሥልጣን) እና በታችኛው የካድሬ ሠራዊት መካከል የነበረው የመጠርነፊያ ሰንሰለት ክፉኛ የመላላት ወይም የመወላለቅ ችግር እየገጠመው መሆኑንም ለማስተዋል የሚያስቸግረን አይመስለኝም።

በራሱ በሕወሐት ውስጥ ያለው ፍትጊያ የለውጥ ፍለጋ ሳይሆን ማን ከማን በሥልጣንና በሃብት ይበልጣል እና አብረን ከመውደቅ እንዴት አብረን እንዳን የሚል ቢሆንም በዚህ በሰሞኑ የመረበሽ ሽር ጉድ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ ግን ዕውነት ነው።

ሐ) በተለይም ከሦስትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ በመላው አገሪቱና በተለይ ግን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልልላዊ መስተዳድሮች እየታየ ያለው ሕዝባዊ የለውጥ ፈላጊነት ማዕበልን እሥር፣ ስቃይ፣ ግድያና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (መንግሥታዊ የሽብር አዋጅ) እንኳን ሊገታው ይቅርና ይኸውና አሁንም የሚዛናዊ ሕሊና ደሃ የሆኑትን ገዦቻችን መያዣና መጨበጫ እያሳጣቸው መሆኑን ለመረዳት ብዙ ማሰብን የሚጠይቅ አይደለም። እነደነ አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ በረከት ስምኦን ያሉት ሥልጣን ለቀቁ ፣ እና እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉት ደግሞ ህወሀትን “ተዳፈሩ” የሚል ዜናን በስሚታዊነት ወይም የለምንነትን፣የወዴትነትንና የእንዴትነትን ጥያቄ በአግባቡ በማይመልስ አቀራረብ ስናስተናግድ (በቅንነትም ቢሆን)ለሕዝብ የተሳሳት(misleading) መልክት እንዳናስተላፍ በተቻለ መጠን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብየ አምናለሁ። ጥንቃቄ ስል የውይይታችን አቅጣጫና ይዘት ነገሮችን ከእኛ እይታና እምነት አኳያ ብቻ ሳይሆን ከእኛ እይታ ዉጭም ሊኖር የሚችለውን እይታ እያሰብን ቢሆን ማለቴ ነው ። ይህን የምለው ከምንም ተነስቸ ሳይሆን የማነባቸውና የምሰማቸው አንዳንድ የፅሁፍና የሚዲያ ውይይቶች ተደጋጋሚነት ባላቸው የቋንቋ አገላለፆች እና በገታራ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አቋሞች የተገደቡ ናቸው የሚል ግንዛቤ ስለአለኝ ነው።

እያስተዋልን ያለነውን የሥልጣን መልቀቅና ህወሃትን “የመዳፈር” ፖለቲካዊ ክስተትን ምንነትና እንዴትነት በአወንታዊ ወይም አሉታዊ ፣ ይታመናል ወይም አይታመንም ፣ ሰዎቹ ለዓመታት ከተዘፈቁበት እኩይ የፖለቲካ ሕይወታቸው ለመውጣት ቆርጠዋል ወይም አልቆረጡም ፣ የመሠረታዊ ለውጥ አካል ይሆናሉ ወይም አየሆንም ፣ ወዘተ ከሚል ደምሳሳ እሰጥ አገባ ዓይነት ክርክር በእጅጉ በተሻለ የሃሳብ ስፋትና ጥልቀት ማየት የሕዝብን አስተያየት ( public opinion) ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ከመቅረፁም በላይ ወደፊት ልንሠራው የሚገባንን ሥራና ልንጓዝበት የምንፈልገውን መንገድም የሰመረ ያደርገዋል።

መ) ምንም እንኳ ለሩብ ምዕተ ዓመት ከተከማቸውና ከተወሳሰበው (ካከማቸነውና ካወሳሰብነው) ሁለንታዊ ውደቀታችን አንፃር ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚታየው የኢትዮጵያውያን የጋራ እጣ ፈንታን በጋራ ትግል የመወሰኑ ግንዛቤ ፣ ተነሳሽነትና የቁርጠኝነት ሥነ ልቦና በተሻለ ሁኔታ ላይ መገኘቱ ለሰሞኑ «ሥልጣን ለቀቅንና ሕወሐትን አንፈራም» ፖለቲካዊ ክስተት ለአደባባይ መብቃት የራሱን ተፅኖ እንዳሳረፈ ለመገንዘብ ብዙ መመራመርን የሚጠይቀን አይደለም።

ሠ)) የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግለሰብም ይሁን በቡድን (በድርጅት) ደረጃ በመረጠውና እችለዋለሁ በሚለው መንገድና አቅም ጥረት በማድረጉ ይህን የሰሞኑን በሕወሐት/ኢህአዴግ ሰፈር እየታዘብን ያለነውን ሕዝባዊ አጀንዳን በማጮህና ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ፈላጭና ቆራጭ ሥልጣንን ለማሰንበት እንሞክር ዓይነት ዘመቻ መሰል እንቅስቃሴ ወደ አደባባይ እንዲወጣ አስገድዶታል ። በዚህ ረገድ ከተግባራዊ ፈተና ፣ ከረጅሙ የፖለለቲካ ታሪካችን ተሞክሮ ፣ በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ግምገማና ውሳኔ ሁለገብ የትግል ሥልት አገራችን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ የተሻለ መሆኑን አምነው ወደ ትግሉ ሜዳ የወረዱ ወገኖቻችን ሚና ወይም አስተዋፅኦ እጅግ ጉልህ ድርሻ አለው ። በገዥዎች ላይ መርበትበትን ፣ በሕዝብ ዘንድ ግን ተስፋን ፣ ተነሳሽነትን እና አይበገሬነትን ፈጥሯል ብየ አምናለሁ ።

ረ) ምንም እንኳ ወታደራዊው አምባገን አገዛዝ የራሱን መቃብር የቆፈረው በእራሱ ኢሰብአዊ ባህሪና ድርጊት ቢሆንም የዛሬ ገዦቻችንን አቅፈወና ደግፈው ቤተ መንግሥት ያስገቧቸው የምዕራባዊያን መንግሥታት መሆናቸው የታወቀ ነው። ይኸውና የሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት አገዛዛቸውንም ያሳስበናል እና ግፊት እናደርጋለን (We are concerned and we urge) ከሚል የተለመደና ትርጉም ያጣ እስኪመስል ድረስ የሰለቼ ዲፕሎማሲዊ መግልጫ ከማውጣት ባለፈ መቆጣታቸውን አይተንና ሰምተን ባናውቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየያለ የመጣውን የሕዝብ አልገዛም ባይነት በማየት ይመስላል በአንፃራዊ መልኩ ጠንከር ያለ መልክት እያስተላለፉ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይህም ሰሞኑን በገዥዎቻችን ሰፈር ለምንሰማውና ለምናየው የተረበሸ ፖለቲካዊ ክስተት የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ ዕውነትነት አለው።

እዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ልጨምር። ኅያልነታቸውን ለማስጠበቅና ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ብርቱ ጥረት በሽርከኝነት ወይም በጠበቀ ወዳጅነት ፈፃሚና አስፈፃሚ የሆነ መንግሥት ወይም የገዥ ቡድን እስከአገኙ እና እሱም በሕዝብ እምቢተኝነት ህልፈተ ህልውናው ጫፍ ላይ መድረሱን እስከአላረጋገጡ ድረስ ይቀጥሉበታል ።

ለሕዝብ ውርደትና መከራ ፍፃሜ ብለው የምር የፖሊሲ ለውጥ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ ቀርቶ ማሰብ ከገሃዱ የዓለም ፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ጋር በእጅጉ የተራራቀ ነው። ይህንን በሚገባ ተረድቶ ከመንቀሳቀስ አኳይ አጥጋቢ ነው ባይባልም አሁን ካለው እጅግ ወሳኝ ግን ፈታኝ የአገራችን ሁኔታ አንፃር በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስከአሁን ያደረጉት የተቃውሞ፣ የዲፕሎማሲ ፣ እና የሎቢ (የማግባባትና ሃሳብን ወደ የራሳችን ጉዳይ የመሳብ) ጥረት የራሱ አስተፅኦ ያለው መሆኑ ግን ዕውነት ነው ።

ይህን ጥረት ይበልጥ በታሰበበት፣ በተደራጀ ፣ በታቀደ እና ከአገር ቤቱ የነፃነት ፣የፍትህ፣ የእኩልነት ፣ የአስተማማኝ ሰላምና የዘላቂ ሁለንተናዊ ልማት ትግል ወሳኝነት ጋር በተቀናጀ መንገድ ማስኬድ የግድ ነው ። ይህ ዓይነት የአጋርነትና የአብሮነት ትግል ብቻ ነው በሕዝብ ውርደትና መከራ ላይ የሚቀልዱ ጨካኝ ገዥዎቻችን ጋር በአጋርነት (ሽርከኝነት)የሚተሻሹ መንግሥታት ኅላፊነት የጎደለው ፖሊሲ ላይ አስገዳጅ ተፅዕኖ መፍጠር የምንችለው ። ያለዚያ በደብዳቤ አቤት ብለን እናስብበታለን እየተባልን፣ ባለሥልጣን አነጋግረን የማውቀው መረጃ ይበልጥ ስለተብራራልኝ አመሰግናለሁ ስንባል ታላቅ ሥራ እንደሰራን ሁሉ ኩራት እየቃጣን ፣ በስብሰባ ተሳትፈን ሸጋ ሪፓርታዥ እያስነበብን፣ በየብዙሀን መገናኛው የእዩልኝና ስሙልኝ ዓይነት ወግ እያወጋን ፣ በየሶሺያል ሚዲያው የስድብ እሺኮለሌ እየገጠምን ፣ ተሰልፈንና ጬኸን ወደ የቤታችን ስንመለስ እየተጠፋፋን ፣ የሰብአዊ መብት ተሚጋች የሚሰኙት ድርጅቶች ገዦቻችን ከሚፈፀሙት ገድብ የለሸና እጅግ ኢሰብአዊ ወንጀል ውስጥ በአደባባይ የሆነውንና ሊደብቁት የማይቻላቸውን እያዘጋጁ ይፋ የሚያደርጉትን ሪፖርት ባስነበቡን ቁጥር ስለሱ እያወራንና አጃይብ እየተባባልን ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የዚህ ወይም የዚያ አገር መንግሥት ኤች አር (HR) ቁጥር ይህን ያህል የተሰኘ ህግ ሊያሳልፍ ነው በተባለ ቁጥር እሱን እንደ ትልቅ የድል የምስራች እያወራንና እያስወራን ወደፊት መራመድ ቀርቶ የቆምንበትን ይዘን መቆየታችንም እርገጠኞች ልንሆን አንችልም።

እይታየንና አስተያየቴን እንደሚከተለው ልቀጥል፥

የቀድሞው (ዘመነ ደርግ) ወታደር ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ምርኮኛ ፣ በህወሃት (ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ) እስትንፋስ «ኦህዴድ (የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) ሁኑ!» ተብለው «ከተቀቡት» መሥራች አመራር አባላት አንዱ ፣ ለጥሩ ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸው የጀኔራልነት ማዕረግ የተቸራቸው ፣ ኦሮሚያን የሚገዛ ታዛዥ ሲቭል ካድሬ የታጣ ይመስል ወታደራዊ መለዮአቸውን አውልቀው የህወሃት ታማኝ የኦሮሚያ ገዥ የነበሩት ፣ እና በመጨረሻም በብሔረሰብ ማንነት ላይ የተመሠረተው አብዮታዊ ዴሞክራሲ «ሊቅና» አርክቴክት በነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ መልካም ይሁንታ የህወሃት/ኢህአዴግን አጀንዳና ህገ አገዛዝ ለማፅደቅ እጅ ከማውጣት ያለፈ ሚና የሌለው ፖርላማ አፈ ጉባኤ የሆነቱ (የነበሩት) አቶ አባዱላ ገመዳ «ሕዝቤ እየተዋረደ ስለሆነ የያዝኩትን ሥልጣን ለቅቄ በሌላ ድርጅቴ በሚመድበኝ ቦታ የወከለኝን ሕዝብ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ “ ማለታቸውን በደምሳሳው ማጣጣል ወይም ውድቅ ማድረግ ትክክልና ተገቢ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አቶ አባዱላ ገመዳን ያለምንም ሂሳዊ ተጠየቅነት ( critique and challenge ) “አበጀህ!” ብለን እንቀበል የሚለው አስተሳሰብ ጨርሶ የትክክለኛነትና የገንቢነት ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም።

እንደዚህ አይነት በበሁለት ጫፎች ላይ ተንጠልጥለው የሚገፋፉ ሀሳቦችን (አመለካከቶችን) ወደ መሃል አቀራርቦ በብርቱ የምንመኘውን የነፃነት ፣ የፍትህ ፣የእኩልነትና የጋራ ብልፅግና ሥርዓት ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ዕውነተኛ ፣ ሚዛናዊ እና ገንቢ የጋራ ግንዛቤና መግባባት ለመፍጠር አቶ አባዱላ ገመዳን የሚከተሉትንና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በማስተናገድ እራሳቸውን በቅንነትና በሃቅ ግልፅ እንዲያደርጉ መጠየቅ ይኖርብናል።

ጥያቄዎችን በአግባቡ፣ በድፍረት እና በቅንነት(በሚዛናዊ ህሊና) ለሕዝብ ውርደትና መከራ ዋነኛው ምክንያት (root cause) ከሆነውና በምርኮኝነት ከያዛቸው ኅይል (አካል) እንደስጦታ ተረክቦ ለእኩይ ፖለቲካው በአሻንጉሊትነት አገልጋይ ባደረጋቸው ህወሃት የበላይነት የሚመራው የአገዛዝ ድርጅታቸው ወይም መንግሥታቸው ከመሆኑ አኳያ ጋር እያገናዘቡ ግልፅ ካደረጉልን አንድ ትልቅ እርምጃ ነው። ይህን የሰቆቃ ሥርዓት አስወግዶ በዕውነተኛ ሕዝባዊ ሥርዓት ለመተካት ሁሉም (እራሳቸውንና መሰሎቻቸውን ጨምሮ) ሃላፊነትና ተጠያቂነት በተላበሰ አኳኋን መረባረብ እንዳለበት ጨምረው ግልፅ ካደረጉልን ደግሞ የውርደትና የመከራውን ፍፃሜ ለማሳጠር ረድተውናልና «ሕዝቤ ተዋርዷል» ያሉት እጅግ መሪር ዕውነት ከምራቸው መሆኑን ለመቀበልና የሚገባቸውን አድናቆት ለመቸር የማያስችል ምክንያት አይኖርም። እናም ተስፋ እያደረግን ወደ ጥያቄዎች እንለፍ::

1) «ሕዝቤ እየተዋረደ ነው» የሚለውን እጅግ መሪር የሆነ ዕውነት በዕራይም ይታየዉ ወይም በዕውን ከህሊናዎ ጋር ተሟግተውና ተማክረው ይድረሱበት ትክክለኛና ተገቢ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ነገር ግን እርስዎ የበላይ አካል አባል የሆኑበት ገዥ ፖርቲና መንግሥት ለድፍን ሩብ ምዕተ ዓመት ገደብና ርህራሄ በሌለው አኳኋን በፖሊሲ ቀርፆና በእቅድ ቀምሮ ሲተገብረው ለምንና እንዴት አስችሎዎት ከሥልጣን ሥልጣን ሲቀያይሩ እንደቆዩ ተዋረደ ለሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ ቢያደርጉለት?

2) “ህዝቤ ተዋርዷል» የሚለውን መሪር ሀቅ እንዲሁ በደምሳሳው ወይም «በአንድምታ ድረሱበት» በሚል ዓይነት አገላለፅ ለማለፍ መሞከር የበሽታውን ማንነትና እንዴትነት አውቆ ተገቢውን መድሀኒት ለማግኘት አይረዳምና የአዋራጁን አካል ምንነት ወይም ማንነት ግልፅ ቢያደርጉት? “አይ ! እሱንስ ሆድ ይፍጀው እንጅ አልናገርም” ካሉ የተናገሩትን መሪር ዕውነት ባለቤት የሌለው ማድረግዎ ነውና ለመተማመን አይበጅም። “ስለሕዝቤ” የሚሉትም በሕዝብ ውርደትና መከራ ላይ መሳለቅ ነው የሚሆነው።

3) «አፈ ጉባኤነቱን ለቅቄ ድርጅቴ በሚመድበኝ የሥራ ሃላፊነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ» ለሚሉት መብቱ የእርስዎ ፣ ሥልጣኑ (authority) ደግሞ የድርጅተዎ ስለሆነ እዚያው እንደሚሆን አድርጉ። ። ነገር ግን እንዴትና በምን ሁኔታ? አፈ ጉባኤነቱን በመልቀቅና በሌላ መንበረ ሥልጣን ላይ በመቀመጥ እንዴት ነው የተዋረደውን ህዝብ ክብሩን ለመጎናፀፍ የሚያደርገውን የበቃኝ ትግል የሚያግዙት ? የኖሩበትን (ያሉበትን) ሥርዓት በጎ በሚመስሉ ሽርፍራፊ የጥገና መደለያዎችን ሥራ ላይ በማዋል ወይስ የህዝብን መሠረታዊ የለውጥ ጥያቄን በማገዝ?

4) የኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶችንና ወጣቶችን እስከ ታችኛው አካባቢያዊ መስተዳድር ድረስ እየወረዱ በማደራጀት (ከጎነዎ እንዲሰለፉ በማድረግ) ጥሩ ችሎታ እንደነበረዎ ይነገራል። ይህ ችሎታ ዛሬ ማን እንዳዋረደው ገልፀው ሳይነግሩን በደፈናው ተዋረደ የሚሉትን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስዎና ድርጅተዎ ድፍን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ካደረሳችሁበት ውርደትና መከራ እንዲገላገል የሚያደርግ አነሳስ፣ ተልእኮ ፣ እና ግብ ቢኖረው ኖሮ እንዴት እድለኞችና ደስተኞች በሆን ነበር።

እስከአሁን ያለው የየግላችሁም ሆነ የድርጅታችሁ/የመንግሥታችሁ ፖለቲካዊ ተፈጥሮ፣ ባህሪ እና ድርጊት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ግን የምታደራጁት ባለሃብት በስልጣን ብልግናችሁ አይዞህ ባይነትና ጥቅም ተጋሪነት የአገርን/የህዝብን አንጡራ ሃብት ለማጋበስ መሆኑን ነው ። ወጣቱንም ቢሆን የሥራ አጥነቱንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የሞራል ቀውስ በመጠቀም የእናንተው እኩይ ሥራ አጫፋሪና አስፈፃሚ ከማድረግ የዘለለ አንዳችም እራሱን እንዲሆን የፈቀዳችሁበት ጊዜና ሁኔታ የለም። ታዲያ አሁን ያንን “በተካኑበት» የማደራጀት ችሎታዎ ያደራጁትን ባለሃብትና ወጣት ከነበረበት (ካለበት) እጅግ የተሳሳተ አደረጃጀትና አካሄድ አውጥተው(መልሰው) ዕወነተኛ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግና ሥርዓት ምሥረታ አካል የሚያደርጉት እንዴትና በምን እንደሆነ ቢያስረዱን ?

5) ተዋርዷል ብለው ሀቁን የተናገሩለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውርደትና ከመከራ መውጣት አለበት የሚል የምር እምነት ካደረበዎ፥

የድርጅተዎ ወይም የመንግሥተዎ ጨካኝ አገዛዝ አብቅቶ ዕውነተኛ ሕዝባዊ ሥርዓት ይመሠረት ዘንድ ስለጠየቁና ስለታገሉ ብቻ መተኪያ የሌለውን ህይዎታቸውን ላጡ በብዙ ሽዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች እና በመሪር ሃዘን ለተመቱ ቤተ ሰቦቻቸው ምን ይላሉ?

የአገርና የሕዝብ ውርደትና መከራ አብቅቶ ለዘመናት ከኖርንበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሞራል ቀውስ አዙሪት መውጣት አለብን ብለው በፃፉ ፣ በተናገሩ፣ እና በግልም ይሁን በድርጅት ተሰባስበው በታገሉ የእናንተ፣ የካድሬዎቻችሁና የጥቅም ተጋሪዎቻችሁ እኩይ ሴራ ሰለባ በመሆን በየማጎሪያ ማዕከሉ (ከእይታ ውጭ የሆነውን ጨምሮ) እና በየወህኒ ቤቱ የሚሰቃዩትን ዜጎች ሙሉ የዜግነት መብታቸው ሳይሸራረፍ ነገ ሳይሆን ዛሬ እንዲለቀቁ የማድረግን ወይም የማስደረግን ግዴታነት እንዴት እንደሚረዱት ጠቀም ያለ ሃሳብዎን ለህዝብ ግልፅ ቢያድርጉ? እርስዎ «በቀጥታ የምወክለው (የምወለድበትና የመረጠኝ)» የሚሉት የኦሮሞ ሕዝብ የዚህ አስከፊ ወርደትና መከራ ሰለባነቱ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን ከዚያ ሕዝብ እንደተገኘ ወይም እንደዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የማነኛውም ሰው መከራና ውርደት እንደሚሰማው ሰብአዊ ፍጡር በዕውን የሚሰማዎት ከሆኑ ይህን ጥያቄ በድፍረትና በቅንነት ማስተናገድ ግድ ይለዎታል።

ከያዙት መንበረ ሥልጣን መልቀቀዎን «ይህ ዓይነቱ በፈቃድ ሥልጣንን መልቀቅ መለመድ አለበት » ያሉት እንደአባባል እንከን የለውም። ምርምር የማይጠይቀውና መሬት ላይ ያለው ዕውነታ የሚነግረን ግን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ከሥልጣን ላለመውረድ እንኳንስ መንግሥታዊ ተቋማትን ይቅርና ከመንደር የመረዳጃ ማህበራት እስከ ሌሎች የሲቪክ ፣የዕምነት ተቋማትና የሙያ ማህበራት ድረስ በመቆጣጠር (በመጠርነፍ)፣ የህዝብን ድምፅ በመስረቅ ፣ በየሰበቡ የጅምላ እስርን ፣ አካላዊና አእምሯዊ ስቃይን ፣ የተናጠልና የጅምላ ግድያን በመጠቀም ሥልጣን ላይ መቆየታችሁንና አሁንም በዚያው ክፉ መንገድ ላይ መሆናችሁን ነው።

እናም ካለሁበት «ወርጄ ሌላ ቦታ ላይ መድቡኝና ሕዝቤን ከውርደት ልታደገው» የሚሉት ደምሳሳና ልፍስፍስ አገላለፅ እንዴት ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ተምሳሌት እንደሚሆን ለመረዳት ይቸግራልና ግልፅ ቢሆኑ ?

6) በጣም በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳትና መጠየቅ ቢቻልም ቅንነቱና ድፍረቱ ካለዎት (ካላችሁ) በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ብዙ ማለት ይቻላልና እንደሚያደርጉት (እንደምታደርጉት) ተስፋ እናድርግ። እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ግዙፍና ፈታኝ ጉዳዮችን የተሸከሙትን ጥያቄዎች በአግባቡ (ገንቢ ተፅዕኖን በሚያስከትል አኳኋን) የማስተናገዱ ነገር ለቀጣዩ የነፃነት ጉዞ መንገድ ጠራጊነቱና አመቸችነቱ እንዳለ ሆኖ ሊከተል የሚችለውን ኅላፊነትና ተጠያቂነት እንደየድርሻችን ለመውሰድ መዘጋጀት ይኖርብናል:: ከምር ዝግጁ መሆናችን ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን መልስ በመስጠት የጀመርነውን መንገድ ጠረጋ ወደ እምንመኘው ውርደትን በክብር የመተካት ተልዕኮ(ግብ) ለማድረስ ይረዳናል ። በፍፁም ለነገ ይደር የሚባልም አይደለም ። ይኸ ፈታኝ ግን መደረግ ያለበት የለውጥ ፍለጋ ሂደት መጀመር ያለበት ከየውስጥ ህሊናችን ጋር በመሟገት ፣ ለውስጥ ግጭታችን ትክክለኛውንና ገንቢውን የግጭት መፍቻ ተጠቅመን በመፍታት፣ ራሳችንን ይቅር በማለት እና የወደፊቱን ጉዟችንና እጣ ፈንታችን ስኬታማነት ዕውን ለማድረግ ከራሳችን ጋር የምር ቃል በመግባት ነው። ይህ ዓይነት የተቀደሰ ፖለቲካዊ ሰብዕናችን ነው በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ትክክለኛው የህዝብና የአገር ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋ መንገድ የሚወስደን። ይኸ ዓይነት ፖለቲካዊ ሰብዕና ነው አገርንና ሕዝብን ከተዋረዱበት (ከገቡበት ሁለንተናዊ ቀውስ) ለማውጣት የሚያግዘን ። ታዲያ እርሰዎና ድርጅተዎ/መንግሥተዎ በዚህ ረገድ ምን ያህል በድፍረት፣ በቅንነት፣ ለነገ ዴሞክራሲያዊት አገር ምሥረታና እና ባለነፃነትና ባለፍትህ ትውልድ ለማፍራት ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?

እንደማስገንዘቢያ ይወሰድልኝና እዚህ በላይ ያቀረቡኳቸው ጥያቄዎችና እነሱን ግልፅ ለማድረግ የተጠቀምኩባቸው አስተያቶች ከነበራቸው የሥልጣን ቦታና ያን የሥልጣን ቦታ ለመልቀቅ በደምሳሳውም ቢሆን ካቀረቡት «ሕዝቤ ተዋርዷል» ምክንያት አኳያ በማየት ለአቶ አባዱላ ገመዳ ቢሆንም ከመሠረታዊና ሁለንተናዊ የአገራችን ቀውስ አኳያ ግን በተለይ የሰሞነኛው የመረበሽ ሽር ጉድ ወሬ ባለቤት (ምክንያት) ለሆኑትና በአጠቃላይ ደግሞ ለገዥው ቡድን ባለሥልጣናትና ካድሬዎችም ጭምር መሆኑ ልብ ይባልልኝ::

የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ገዥ አቶ ለማ መገርሳ በርከት ያለውን የወጣትነት እድሜ ሥራቸውን በዋናነት ያሳለፉት የአገርንና የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ወይም ማስጠበቅ ሳይሆን በሕዝብ ጥላ ወጊነት (ገዥዎቻችን ይቃወማሉ የሚባሉትን ንፁሀን ዜጎችን በመሰለልና ለአፈና መረቡ ሰለባነት በማዘጋጀት) በሚታወቀው “የደህንነት” መሥሪያ ቤት ማገልገል መሆኑ ዕውነት ነው ። የመጀመሪያቸው መሆኑን እርግጠኛ ባልሆንም ረጅሙና ትልቁ የሥራ ልምዳቸውም ይኸው ነው።

ኦሮሚያ ክልል በቀለሙም ሆነ በዕድሜና በሥራ ልምድ የበሰሉ ዜጎችን ያጣች ይመስል አቶ ለማ መገርሳ አሁን ያሉበትን የክልል ገዥነት ሥልጣን መጎናፀፋቸው የግላቸው የሆነ ጠንካራ ጎን ( strength/quality) ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ቢቻልም አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ትልቅና ዘመን የማይሽረው የማንነት መገለጫ በየዲስኩሮቻቸው እያስገቡ ሲያሰሙን ብርቅዬና ታሪካዊ እስኪመስለን ድረስ እየተቀባበልን «የኢትዮጵያ የዳግም ትንሳኤ» የሚል ዓይነት እልልታ ቀረሽ ወሬ መሰለቁን ተያይዘነዋል። ይህን ስል የአቶ ለማን የኋላ የሥራ ታሪክ ለአሁኑ ሥራቸው ብቸኛ መገምገሚያ በማድረግ እና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማለታቸውን ደግሞ ፈፅሞ ውሸታቸውን ነውና በደምሳሳው ውድቅ መሆን አለበት የሚል የድንቁርና ክርክር ውስጥ ለመግባት አይደለም። በመግቢያዬ ላይ እና አግባብነት አለው ባልኩት የዚህ ጽሁፌ ክፍል ደጋግሜ እንደገለፅኩት የዚህ ዓይነት አቀራረብ አይጠቅምም።
እያልኩ ያለሁት ፥
ከሦስትና ሁለት ዓመታት ወዲህ በተልይም የአማራና የኦሮሚያ ክልል መስተዳድሮች ህዝብ የገዥው ቡድን የአፈና እና የግድያ ዘመቻ ጨርሶ ሊገታው በማይችልበት ሁኔታ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ዕውን ይሆን ዘንድ ከመጠየቅ አልፎ ወደ አስገዳጅና ሁለንተናዊ የትግል ዘርፎች ተሸጋግሯል።

እንግዴህ በዚህ ወቅት ነው የአቶ ለማ መገርሳ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን አይገሰሴነት ደፍረው ተናገሩ ከሚል ይነሳና አሆዴድ ከህወሃት የፖለቲካ ጠርሙስ ወጣ ፣ የጣና እምቦጭ አረም ብቻ ሳይሆን የህወሃት የጎሳ ልዩነት ፖለቲካም ተነቀለ ፣ህወሃትም ግራ ገባው፣ እነ አቶ ለማ ለህወሃት አንታዘዝም አሉ ፣ የሃያ ስድስት ዓመቱ የህወሃት የልዩነት አጥር እየፈራረሰ ነው ፣ ወዘተ የሚል ከአፍንጫ ሥር የማይርቅ አስተያየት ወይም አመለካከት በሰፊው እየሰማንና እያነበብን ያለነው:: ሰከን ብሎ እና ከግልብ ስሜትና ምኞት ወጥቶ ለሚያስተውል ግን ዕውነትም ገዥዎቻችን መቼና እንዴት የማስመሰል የፖለቲካ ጨዋታቸው ሰለባዎች እንደሚያደርጉን ከማንም (ከራሳችንም ጭምር) በላይ እንደሚያውቁን ለመገንዘብ የሚቸገር አይመስለኝም። ። በኢአሀዴግ /ህወሃት ሃሳብ አመንጭነትና ዕቅድ ነዳፊነት የተዘጋጅው እና በአቶ ለማ መገርሳና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስፈፃሚነት በባህር ዳር ተካሄደ የተባለውን “ታሪካዊ ኮንፈረንስ” እነ አቶ ለማ መገርሳ «የህወሃትን የዘውግ ፖለቲካ ሰበሩት» ለሚለው «የምሥራች» እንደ ትልቅ ማሳያ ወስዶ እውነት ነዉና እመኑ ማለት ዕውነታውን እየተነገረው ሳይሆን እየኖረው የሚያወቀውን ህዝብ የግንዛቤና የዕውቀት አቅም ከማሳነስ አልፎ ጨርሶ እንደ ደንቆሮ መቁጠር ይሆናል ።

እስርና ግድያው የምናውቀውን የህዝብን የመብት ጥያቄ የማስከበር ብቻ ሳይሆን የሞትና የሺረት ጉዳይ እየሆነ የመጣውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ማስቆም ባለመቻሉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ስም «የፍቅር ፣የሰላም እና የመቻቻል» ሰባኪ ሃሳዊ መሲህ እና የእንተዋወቅ የልኡካን (“ሐዋርያት” ) ቡድን በማሰማራት የእንሞክረው ፖለቲካዊ ድራማን እየታዘብን ነው ። ተማርኩ የሚለው ወገንም ይህ የገዥው ቡድን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ እንዲከሸፍ ህዝብን የማስተማር (የማንቃት) እና የማደራጀት ሥራ ለመሥራት ቀርቶ ይኸ ሁሉ መከራና ውርደት ሞልቶ ሲፈስ የአንዲት ቀን የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ሀዘኑንና የህዝብ ልጅነቱን ለመግለፅ ቢያንስ የሞራላዊ ሰብዕናን ምንነትና እንዴትነት ለማሳየት ጨርሶ ተስኖታል ። ለትውልድ ማንነትና ምንነት የሚጨነቅ ህሊና ላለው ሰው በእጅጉ የሚሳዝንና የሚያሳስብ ጉዳይ ነው።

የሚገርመው ደግሞ የሰሞኑን ከሥልጣን መውረድና የነአቶ ለማን «ሀወሃትን የመዳፈርና ኢትዮጵያዊነትን የማፅደቅ» ዲስኩር እንደታሪካዊ እርምጃ እያጮኸው ያለውም ይኸው ተምሬያለሁና ተመራምሪያለሁ የሚለው ወገን መሆኑ ነው ። ገዥው ቡድን (ግንባር) በተላላኪዎቹ (በኦሆዴድና በብአዴን) ፈፃሚነት የሚያካሄደውን ህዝብን የመምሰልና የህዝብን ህመም የታመሙ መስሎ የመታየት ዘመቻን « የኢትዮጵያ ትንሳኤ « የምንል ከሆነ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን ህዝብ በአፋችን እንጅ በልቦናችን ወይ አልተረዳነውም ወይም ደግሞ እንደገዥዎቻችን እየኖረው ስለአለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወቱ ያለውን ዕውቀት ከምንም አልቆጠርንለትም ማለት ነው። እንዴት ከነችግሩም ቢሆን የሽዎች ዓመታት እና የአያሌ ሥርኦ _መንግሥታት ባለታሪክ የምንለው (የሆነው ) ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የገዥው ቡድንና ግብረ በላዎቹ የብልግና እና የዝርፊያ ዕድሜያቸውን ለማራዘም ከመጋረጃ ጀርባ ሆነዉ በአገልጋዮቻቸው አማካኝነት “አታስቡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የማንደራደርበት ኩራታችን ነው” ሲሉን ቢያንስ እንዴት? ከመቸ ወዲህ? በየትኛው ተግባራዊ የለውጥ ተምሰሳሌትነታችሁ ? በየትኛው ለሥርዓት ለውጥ ዝግጁነታችሁን? ወዘተ ብለን መሞገት ብዙም የተሳካልን አይመስልም።

.
እንዴት እንሞግታቸው ? ካላችሁኝ ቢያንስ እንዲህ እንሞግታቸዉ፥

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ልብ ገዝታችሁ በአግባቡ ከተረዳችሁትና እንኑረው ካላችሁ ደስታውን አንችለውም። ነገር ግን ሁላችንም ማየት የምንፈልገው በሁላችን ገደብ የለሽ ተሳትፎ ለሁላችን የምትሆነዋን ኢትዮጵያን እንጅ እናንተ ጨፍልቃችሁና ዘርፋችሁ የምትገዟትን ኢትዮጵያን ከቶ አይደለምና በዚህ ረገድ እራሳችሁን አሁን ከምታደርጉት ጊዜ ያለፈበት፣ የድብብቆሽና የሴራ ፖለቲካችሁ እራሳችሁን በንስሃ ( confession and apology) አንፁና ከዛሬ ጅምሮ በይቅር ባይነትና በአብሮነት ዕውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰብአዊ መብትና ክብር ፣ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና የሚሰፍንባትን ኢትዮጵያን እንገንባ ። ከዚህ ያነሰ ወይም አሁን ከፍና ጎላ አድርጋችሁ ለመጫወት የምትሞክሩት ጨዋታ የባሰ የአገርንና የወገንን ውርደትና መከራ ከማራዘም ያለፈ መንፈስም አቅምም የለውም።

ስለአቶ በረከትና ስለ “ክቡር ፕሬዚደንት” ዶክተር መላቱ ተሾመ ለጊዜው በመግቢያየ ላይ ከገልፅኩትና እንደማስገንዘቢያ በሚል ካስቀመጥት አንቀጽ በላይ ብዙም የምለው የለኝም። ለነዚህና በአጠቃላይ ለገዥው ፖርቲ ባለሥልጣናት ፣አባላት ፣ ደጋፊዎችና ግብረ በላዎች ደግሜ ለማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ይኸ ጠመንጃውንና ሰሞኑን የምታደርጉትን የህዝብን አጀንዳ ቀምቶ የማታለሉን ድራማ እያቀያየራችሁ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የመጣችሁበትን የውርደትና የመከራ መንገድ በመተው የሥርዓት ለውጥ አካል በመሆን እራሳችሁንም ከተጨማሪ ወንጀል አድኑ ፣ ልጆቻችሁንም የእነዚያ አገርና ወገን አጥፊዎች ልጆች ከመባል ታደጓቸው የሚል ነው ።

እንግዴህ ከዚህ አሁን ከደረስንበት ግዙፍ፣ ፈታኝና ሁለንተናዊ ቀውስ ምክንያትና ውጤት ተነስተን ነው የሰሞኑን የገዥዎቻችን ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ዓይነት ሙከራቸውን መረዳት፣ መተንተንና በተቻለ መጠን ትክክለኛ የአቋም ምንነት ላይ መድረስ ያለብን። ይህን ስናደርግ ደግሞ በማይናወጥ መርህ ላይ መቆም ያለበትን የእራሳችን አጀንዳና ተልኮ እየተውን እነርሱ ሥልጣናቸውን የማጣቱ አይቀሬነት ባቃዣቸው ቁጥር (እንደ ሰሞኑ ማለት ነው) የሚተውኑት መያዣና መጨበጫ የሌለው ዘመቻ መሰል የፖለቲካ ክስተት ወጥመድ ሰለባ ላለመሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ። አዎ! የማይናወጠው አጀንዳችን፣ መርህአችንና ተልዕኳችን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ለአገርና ለወገን ልክ የሌለው ውርደትና መከራ ዋነኛ ተጠያቂ የሆነውን የገዥ ቡድን ሥርዓት አስወግዶ በዕውነተኛ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት ነው።

ከዚህ ያነሰና አሁን እንደሚተወነው አስቀያሚነትን በርካሺ የፖለቲካ ቅብ ኳኩሎ የማስቀጠል ጨዋታ የደረስንበትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሞራል ቀውስ ለመፍታት ፈፅሞ አይመጥንም። ወርቃማና ሕዝባዊ አጀንዳችንን እና ተልዕኳችንን ገዥዎቻችን ሆን ብለው (የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም) በሚሰብኩን እጅግ አሰልች እና መነሻውና መዳረሻው ያንኑ የውርደትና የመከራ ሥርዓት ከማስቀጥል በማያልፍ «የጥልቅ ተሃድሶ» የምናስነጥቅ ከሆነ ደንቆሮዎቹና ተሸናፊዎች እኛ እንጅ እነርሱ አይደሉም ። የሰሞኑንም የገዥዎቻችን ሥልጣንን በማንኛውም ዘዴ ለማታደግ የሚተውኑትን ፖለቲካዊ ድራማ ማየትና መመዘን ያለብን ከዚሁ መሪር ዕውነት አኳያ ነው።