November 11, 2017 22:56

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ዛሬም እንደ ትናንቱ ከምሁራን እስከ እኔ ቢጤ ተራ ዜጎች ስለብሔራዊ እርቅና ይቅር ባይነት ይደሰኩራሉ፡፡ የብሔራዊ እርቅንና ይቅር ባይነትን ጠቀሜታ ለማሳየትም በአፓርታይድና በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የተፈፀመውን እርቅ በማስረጃነት እንደ ውዳሴ ማርያም ይደግማሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ “እርቅ” እንደሰፈነ በምዕራባውያን አቀንቃኝነትና በእኛ ተቀባይነት ተዘፍኗል፡፡ ስለዚህ እርቅ ዘፍነን ባናባራም ፍትህ ግን እንጦሮጦስ እንደ ወረደች ደም የጎረሱት የደቡብ አፊርካ ወንዞች፣ የሕዝብን ጩኸት ያስተጋቡት የደቡብ አፍሪካ ተራሮች፣ የታጋዮችን ስቃይ ያዳመጡት የደቡብ አፍሪካ ከርቸሌዎች ብቻ ሳይሆኑ የአፓርታይድ መሪዎችም ያውቁታል፡፡ በዚህ ፍትህ እንደ ጭቃ ተረግጣ እርቅ እንደ ጎርፍ ወረደበት በሚባለው ደቡብ አፍሪካ ዛሬም ገዳይና የገዳይ ወገን እንደ ሥጋጃ ተንፈላሶ፣ የተገዳይ ወገን ግን እንደ ቆርበት ተቆራምዶ ይኖራል፡፡ ይህ ፍትህ አልባው የደቡብ አፍሪካ እርቅ ገዳዮችን ጠቅሟል፤ የተገደሉትን ግን ከመቃብር በጦር ወግቷል፡፡ ከመቃብር በጦር የተወጉትን ዜጎች እንደ ውቃቢ ዶሮዎች ለኢፍትሐዊ እርቅ ገብረው የሟች ወገኖች እርምን እየጠሸቀሙ መኖርን ቀጥለዋል፡፡ እንደ ዓባይ የፈሰሰው ደም ፏፏቴ ግን ዛሬም “የፍትህ ያለህ!” እያለ ይጮኻል፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እኛም አራጅና ታራጅ ሆነን አራጆች ደማችንን እንደ ፋሲካ በግ ሲያፈሱት ታራጆችም እንደ ፍሪዳ ስንሰዋና ስንበላ ኖረናል፡፡ የሰማእታት ወገኖችም የደቡብ አፍሪካን እርቅ እየጠቀስን አራጆችን ነፃ እሚያወጣውን የእርቅ ዘፈን ከሰማእታትን አስከሬኖች በተሰራ ደረጃ መዝፈንና መደለቅ ጀምረናል፡፡ ከድለቃው በስተጀርባም ካራጆች ጋር ውል አስረን የታረዱትን እርም ለመብላት የቋመጥን ይመስላል፡፡ ይህንን ለመብላት የቋመጥነውን እርም የተባረከ ጮማ ለማስመሰልና የእርቅ ሐዋርያ ለመባልም መጽሐፍ ቅዱስ መጥቀሱን ቀጥለናል፡፡

“የእርቅ” ሐዋርያት ሆይ! መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛው ምዕራፉ እርቅን ከፍትህ ነጥሉ ሲል ያስተምራል? “ኢፍትሐዊ እርቅን ፈጥሙ!” የሚልን ምዕራፍ የትኛው መጋቢ ብሉይና መጋቢ ሐዲስ ሊጠቅስ ይችላል? ቅዱሱ መጥሐፍ እርቅን ከፍትህ ነጥሉ ካላለስ ካራጆቻቸው ውል አስረን ኢፍትሀዊ እርቅን እንድንፈጥም የታረዱት ሰማእታት መቼ ፈርመውልናል? አራጆች ከነነፍሳቸው ገደል የወረወሯቸው፣ የአራጆችን ካራ ሲሸሹ አውሬ የበላቸው፣ በአረመኔዎች ብትር ማሰብ የተሳናቸውና ሌሎችም ያካል ጉዳተኞች በእነሱ ስም ፍትህን ረግጠን “የእርቅ” ውል እንድናስር መቼ ቃላቸውን ሰጥተውናል? በማን ህይወት ማን ከአራጆች ኢፍትሐዊ ውል አስሮ ሰላሙን ይተኛል? በማን የስቃይ ማገዶ ማን ከአረመኔዎች እርሾ ተበድሮ እንጀራውን ይጋግራል?

ውል አሳሪዎች ሆይ! በግፍ የረገፉት ሚሊዮን ዜጎች እንኳን ለናንተ ለወላጆቻቸው፣ ለልጆቻቸው፣ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸውስ ኢፍትሐዊ እርቅ እንዲፈጸምብቻው ባውራ ጣታቸው ፈርመው አልፈዋል ወይ? የፍትህ መብታቸውን እንደ ገዳዮቻቸው እንድትገፉ ለናንተ መብቱን አስረክበዋል ወይ? “ያለፈው አልፏል! የሞተ ሞቷል” ብላችሁ በ “እርቅ” ከረጢት ቋጥራችሁ እንደ ፍሪዳ ፈርስ ከወረወራችኋቸው እናንተስ ካራጆቻቸው ትሻላላችሁ ወይ? “ያለፈው አልፏል! የሞተ ሞቷል” በሚል ኢሞራላዊና ድውይ አስተሳሰብ እስራኤላውያን ዜጎቻቸውን እንደ ፍሪዳ ፈርስ በእርቅ ቋጥረው ቢወረውሩ የሂትለር ጀኔራሎች ዛሬም እየታደኑ ለፍትህ ይቀርቡ ነበር ወይ?

የዛሬውን አያርገውና እርቅን፣ ሽምግልናን፣ ፍቅርንና ሰላምን “ተኛ ወዲያ ፉጨት ማሞጥሞጥ” እስተሚያሰኝ ቀደምት አባቶቻችን ተክነውባቸው ነበር፡፡ እነዚህ የተካኑባቸው መንፈሳዊ እሴቶችም ድንቅነሽ ሰው መሆን ከጀመረችበት ወይም አዳም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለምንም ፖሊስ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ አስችለዋቸው ነበር፡፡

እነዚህን የፍትሀዊ እርቅ እሴቶች ከሰው አራጅ ወንበዴዎች፣ ከእንጨት ሽበት ሽማግሌዎችና  ከቀበኛ የሃይማኖት መሪዎች ብንጠብቅ ኢፍትሀዊ እርቅ ሽመታ ደቡብ አፍሪካ ባልኳተን ነበር፡፡ ኢፍትሐዊ እርቅ ሽመታ ደቡብ አፍሪካ መኳተናችን “የዓባይን እናት ውሀ ጠማት” አሰኝቶ አስቆዘመኝ፤ በትዝታ መንገድም ወደ አደኩበት ፍትሐዊ እርቅ ወሰደኝ፡፡

ልጅ ሳለሁ ሁለት ጎረምሳ ወንድማማች ያጎቴ ልጆች መንገድ ገፍተው የተከሉትን ተክላቸውን የረገጠ አንድ ሰው ፈነከቱ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ፈንካቾችና ተፈንካቹ ለእርቅ ተስማሙ፡፡ የፈንካቾቹ አባትና ሌሎች አጎቶቼ ሽማግሌ የመምረጡን ዕድል ሙሉ በሙሉ ለተፈንካቹ ሰጡ፡፡ ይህንን ሽማግሌ የመምረጡን እድል የተረከበው ተፈንካችም የፈንካቾችን አባት፣ አጎታቸውንና የእኔን አባት ለሽምግልና መርጧቸው እርፍ አለ፡፡ ተፈንካቹ ለሽምግልና የመረጣቸው የፈንካቾች አባት፣ ሌላው አጎታችንና አባቴ የተጣለባቸው አደራ ከሰማይ የወረደ ያህል ተሰማቸው፡፡ ይህ አደራ የከበዳቸው እነዚህ ሽማግሌዎች ባንድ ድምፅ በልጆቻቸው ፈርደው ከዚያ በፊት በዚያ ዘመን ለእንደዚህ ዓይነት እርቅ ተከፍሎ የማይታወቅ ገንዘብ እንዲከፍሉና ድንጋይ ተሸክመው እግሩ ስር ወድቀው ተፈንካቹን ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገው አስታረቁ፡፡ በሽማግሌዎች ፍትሐዊ እርቅ የረካው ተፈንካችም “ፍትህ ይበቃኛል” በሚል መንፈስ የሰጡትን ገንዘብ አልቀበልም ብሎ መለሰው፡፡ ፈንካቾችም ገንዘቡን አንቀብለም ብለው ትተውለት ሲሄዱ ሌላ ጊዜ ከደጃፋቸው ጣለለቻው፡፡ ሽምግልናው እርቅን ወለደ እርቅም ፍትህን አነገሰ፡፡ ፍትህን ያነገሰው እርቅም ሰላምና ፍቅርን አሰፈነ፡፡ የሰፈነው ፍቅርም ለጋብቻ አደረሰ፡፡

ይኸንን የመሰለ ሰላምና ፍቅር የሚያነግሱ የእርቅ እሴቶቻችን በገዳይ ገዥዎች፣ ገዳዮች እንደ ችግኝ በተከሏቸው የሃይማኖት መሪዎችና ገዳዮችን በሚላላኩ ሽማግሌዎች ጥቅሙ እንዳለቀ ድሪቶ ተወርውረዋል፡፡ በእነዚህ እሴቶች ምትክም  ጉልበተኛ እንዲያሸንፍበት ፈረንጅ የሸመነውን የድርድር (ሚዴሽን) ሸማ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ ሸምተው ዘርግተዋል፡፡ ይህንን ከምዕራባውያን የሸመቱትን የድርድር ሸማ እየጎተቱም ወንጀልን መሸፋፈን ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ በግፍ የተገደሉትን ወገኖቻችንን ፍትህ ነፍገው ከምዕራባውያን በሸመቱት የድርድር እራፊ አጥንታቸውን እንደ ችቦ አስረው፣ እንደ ጎርፍ የወረደውን ደማቸውን እንደ ስፖንጅ መጠው እንደ ወጥ ቤታቸው ቆሻሻ ጥለውታል፡፡ ይኸንን ፍትህን የገደለ ድርድራቸውንም ብሔራው እርቅ ብለው ሰይመው ሽምግልናንና እርቅን እስተንፋሳቸውን አፍነው ሰውተዋቸዋል፡፡ እነ ኤፍሬም ይስሃቅ እንደ እኔ አባትና አጎቶች ጥጋበኛ ፈንካቾችን በግፍ ከተፈነከተው እግር እንዲወድቁ ሳይሆን በግፍ የተፈነከቱትን ከአረመኔ ፈንካቾች እግር ወድቀው ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገዋል፡፡ በዚህ ኢሰብአዊና ኢሞራላዊ ድርጊታቸውም በሞቱት ነፍስ፣ በተጎዱት ህይወት፣ በእኛ ህሊናና በመለኮት ኃይል ቀልደዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱን ኢፍትሀዊ እርቅ የሚያዳውሩ የእርቅ ሸማ ሰሪዎች ዛሬም እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ኢፍትሐዊ እርቅ በሙታን ነፍስ፣ በሰው ህሊናና በመለኮት ኃይል ከመቀለዱም ባሻገር የወንጀለኛን እድሜ ያራዝማል፤ የፍትህ እጦትን ህመም ያባብሳል፤ የተበዳይን መከራ ያራዝማል፣ ዋንጫ ተቀባይ ወንጀለኞች እንዲፈጠሩም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ኢፍትሀዊ እርቅ የዛሬዎቹን አራጆች ነፃ ካወጣቸው ኢፍትሐዊ እርቅን የሚተማመኑ አራጆች ዋንጫውን ላለመቀበላቸው  ዋስትናችን ምን ይሆናል? መለኮት የፈጠረውን ሰው ያረደ ነፍሰ ገዳይስ እንዴት በኤፍሬም ይስሃቃዊ እርቅ ነፃ ይወጣል?

ፍትሀዊ እርቅ ብቀላን አስወግዶ በፍቅርና በሰላም ስለሚያስኖር ልንፈፅመው ይገባል፡፡ ፍትህን ያገለለ እርቅ ግን ገዳዩን አድኖ ተገዳዩን ደጋግሞ ስለሚገድል የህሊና እረፍትና ሰላምን ይነሳል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በእኛ ባቅመ ቢሶች ባይሳካም አቅም ያለው ሲፈጠር ሰማእታት የዛሬ ሚሊዮን ዓመትም ቢሆን ፍትህ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እየለገምን አቅም አጥተን ከቀረንም ፍትህ የሚከበርባቸው እንደ ሆላንድ ያሉ አገሮች ከፍትህ ችሎት ያቀርቧቸዋል፡፡

ወንጀለኞች ከፍትህ ችሎት ለመቅረብ በሰው ደም እንደ ቅንቡርስ ያበጡት ሥጋዎቻቸው ቆመው መሄድ አይኖርባቸውም፡፡ ወንጀለኞች ከመቃብር ምስጥ እየበላቸውም ስማቸውና ሰይጣናዊ ግብሮቻቸው እየተዘረዘሩ ከፍትህ ችሎት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ፍትህ ከፍትህ ችሎት ስትገኝ የፍትህ አባት መለኮትና ፍትህ ናፋቂ ሕዝብም ይደሰታል፡፡ መለኮትና ሕዝብ ሲደሰቱም ፍቅር እንደ አበባ ይፈካል፤ ሰላምም እንደ መንፈስ ይሰፍናል፡፡

ፍቅርን እንደ አበባ የሚያፈካና ሰላምን እንደ መንፈስ የሚያሰፍን እውነተኛ እርቅ ከፍትህ ይመነጫል፡፡ ይኸንን ፈር ስተን በኢፍትሐዊ እርቅ ገደል እንደ ነፋስ ከነጎድን “እዘጭ እምቦጭ” ብቻ ሳይሆን መንደባለልም ይመጣል፡፡

ልግመኛነታችንን፣ አቅመ ቢስነታችንን፣ ፍርሀታችንን፣ መሐል ሰፋሪነታችንን፣ አድርባይነታችንንና ከርሳምነታችንን ለመሸፋፈን የሰማእታትን አፅም በእርቅ እራፊ ጠቅልለን እንደ ማድ ቤት ቆሻሻ ለመጣል መንፈራገጡን ማቆም ይኖርብናል፡፡ ይኸንን መንፈራገጥ ካላቆምን እንደ ቆሻሻ የጣልነው የሰማእት ህይወትና ታሪክ በጥኑ ይወቅሰናል፡፡ በአሰመሳይ ሃይማኖተኛነት፣ በአጉል ሽምግልና፣ በስመ ምሁርነት፣ በእታይ እታይ የአገር አውራነት ወይም ከእውነት በሚያላትም ይሉኝታ ወገባችን አደግድገን የኢፍትሀዊ እርቅን ዘፈን በከበሮ ከደልቅን የሰማእታት ነፍስ በምድርም በሰማይም ይፋረደናል፡፡

እውነተኛ እምነት ከሥራ ውቂያኖስ እንደሚቀዳው እውነተኛ እርቅ ከፍትህ ባህር ይጨለፋል፡፡ ይህ ካልሆነ ያዕቆብ በመልክቱ “ሥራ የሌለው እምነት … የሞተ … (፪፡፲፯) እንዳለው ፍትህ የሌለው እርቅም የሞተ ይሆናል፡፡

ሰማእታት የፍትህን ፍሬ ይቀምሱ ዘንድ ሥኖር ሥጋዬ ሳልፍም ነፍሴ ይጮኻል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ታህሳስ ሁለት ሺ አስር ዓ.ም.