ዶር አብይ አሕመድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ምክትል ሲሆኑ በኦህዴድ ውስጥ ካሉ በሳል አስተዋይ መሪዎች መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዱ ናቸው። ዶ/ር አብይ አህመድ በዛሬ እለት (13/11/2017) ለOBN በአፋን ኦሮሞ በሰጡት ቃለ ምልልስ የኦሮሞ ማህበረሰብ በሁሉም ኢትዮጵያ ያለ፣ የየኢትዮጵያ ምሰሶ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ዶር አባይ በሰጡት ቃለ ምልልስ

“… ባለፈው የተደረገው የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ውይይት ህዝቡ ምን ያህል እንደተሳሰረ ለማየት በኮንፍረንሱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው አሳይቷል። በ15ኛውና በ16ኛ ክፍለ-ዘምን ሱሲንዮስ የተባለ ሰው በጎንደር አከባቢ ችግር ሲገጥመው ሸሽቶ መጥቶ በአምቦ አከባቢ በግንደበረት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ሲኖር ነበር። ይህ ሰው በኃላ ተሳክቶለት የጎንደር ንጉስ ሲሆን ባለቤቱ ኦሮሞ ስለነበረች ከዚህች ኦሮሞ ባለቤቱ ፋሲል የተባለ ልጅ ይወልዳል። ይህ በኃላ የጎንደር ንጉስ የሆነው ፋሲል ከኦሮሞዎች ጋር በመሆን የፋሲል ግንብ ገነባ።

ግን ኦሮሞ ገንብቶ ለሰው በመተው፣ ሠርቶ ለሌሎች በመስጠት እራሱን እያገለለ ድሎቹን በሙሉ ለሌላ እየሰጠ እራሱን ለአገሪቱ እንደባዳ እያየ ይገኛል። ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ ታሪክ መመርመር ነው። በአገሱማ ወይንም አክሱም በሚባለው ታሪክም ኦሮሞ አሻራ አለው። በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም ጭምር የኦሮሞ ህዝብ አለ። ህዝቡ የተቀላቀለ ነው። የተሳሰረ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ከኦሮምያ ውጭ በስፋት ያለው በአማራ ክልል ነው። ይህ በመሬት ላይ ያለ እውነታ ነው። መደበቅ አይቻልም። ….በአማራ ክልል ያለው ህዝባችን እንዴት በኦሮምኛ ቋንቋ ሊማር ይችላል የሚለው ጥያቄያችን የነበረ ሲሆን ከዚህ አንፃር አመርቂ ውጤት አገኝተናል። ይሄው በቤንሻንጉልና ጋምቤላ ይቀጥላል።

በዚህ ሁኔታ ከሁሉም ቦታ ካለው ደሃ ህዝብ ጋር አንድነት ፈጥረን ለዴሞክራሲና እኩልነት እንዲሁም ለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የምናደርገው ትግል በአንድነት እናፋፍማለን። በተናጠል ትግል ዬትም ስለማንደርስ ይህንን የጋራና አሁን ያለውን ችግራችንን ለመፍታት በጋራ መታገል አለበት።

በኢትዮጵያ በምናደርገው ትግል በልጠን ለመገኘት እንጂ በተለመደው አኳሃን ባለንበት ለመርገጥ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ ምሶሶ በመሆኑ ያለውን ፍረሃት ማስወገድ አለበት። የኦሮሞ ህዝብ በአገር ደህንነት በማስጠበቅ፣ ጣሊያንን ከመዋጋት አንፃር የእነ ባልቻ አባነፍሶን ታሪክ ማንሳት ይቻላል። የትናንትናውን ባድሜ ብንወስድ የኦሮሞ ህዝብ ልጆቹን ገብሯል።ይህ ሊካድ፣ ሊደበቅ አይችልም። በኢኮኖሚ ብንወስድ የኦሮሞ እርሻ፣ ቡና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። ይህ ሁሉ እውነታ እያለ ኦሮሞ እንደ ባእድ፣ እንደጎረቤት እራሱን ማየት አይችልም። ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመሆን ለማስተካከል መስራት ይኖርብናል። መታወቅ ያለበት ድሃ የአማራ ህዝብና ከብሄሩ የተገኘ አመራር ወይንም የወላይታውን ድሃ ህዝብና ከዛው ህዝብ የተገኘ አመራር አንድ አድርጎ ማየት ስህተት ነው።

ህዝቡ ትናንት አብሮ ነበረ፣ ዛሬም አብሮ አለ፣ ነገም አብሮ ይኖራል። ከእነዝህ ህዝቦች የወጡ ክራይ ሰብሳቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሌቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዝህ ተነስተን እነዛን ህዝቦች መጥላትና መራቅ ስለማይቻል፣ ወደ ህዝቡ ቀርበን አብረን አገሪቷን መገንባት ላይ አብሮ መስራት ይኖርብናል፤ ትግልም በዚህ መልኩ ከተመራ ብቻ ነው ስኬታማ ሊሆን የምችለው።”