በየዓመቱ የሚያጋጥመን የመማሪያ መፃሕፍት እጥረት የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው እንደሆነ በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ት/ቤቶች መምህራን እና ወላጆች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ከ1-8ኛ ክፍል ድረስ ያሉ የመማሪያ መፃሕፍት ከጀርባቸው ከተለጠፈው ዋጋ ከእጥፍ በላይ እየተሸጡ ይገኛሉ። ለመጥቀስም ያህል ከዚህ ቀደም የ3ኛ ክፍል የማሕበራዊ ሳይንስ መፃሕፍት በ33 ብር መግዛት ይቻል ነበር። አሁን ግን ገበያ ላይ ያለው ዋጋ ከ160-200 ብር ድረስ ነው። ለገሃር አካባቢ መጽሐፍ በመሸጥ የሚተዳደረው ግለሰብ የመፃሕፍት እጥረት መኖሩን ጠቁሞ የ3ኛ ክፍል የአማርኛ መጽሐፍ በ350 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ይናገራል። አቶ ዳዊት ሰለሞን ለልጆቻችው አራት የተለያዩ የትምህርት አይነት መጽሐፍት ለመግዛት ቢመጡም አንድ መፅሐፍ ብቻ ለመግዛት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

”መንግሥት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መጽሐፎችን እንዳከፋፈለ ይናገራል፤ ትምህርት ቤቶች ግን ለተማሪዎቻቸው መፃሕፍት ማቅረብ አልቻሉም። የስድስት እና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ለሆኑት ልጆቼ ት/ቤታቸው መፅሐፍ ሊያቀርብ አልቻለም። አማራጭ ስለሌለን በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደድን ነው” ሲሉ አቶ ዳዊት ይናገራሉ። አቶ ዳዊት ጨምረውም ”የዚህ ችግር ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግሥት ነው” ይላሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ግን የግል ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጋቸውን መፃሕፍት ብዛት አላሳወቁንም ስለዚህ ችግሩ ያለው እነሱጋር እንጂ እኛ ጋር አይደለም ይላል።

”እጥረት እና ድብቅ ገብያ”

በመዲናችን የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መፃሕፍት እጥረት አጋጥሞናል ሲሉ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያሳተማቸው መማሪያ መፃሕፍት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በውድ ዋጋ እየተሸጡ እንደሚገኙ ይገልፃሉ። ትምህርት ቤቶቹ እጥረት አጋጥሞናል ቢሉም ቢቢሲ ያነጋገራችው የመፃሕፍት ነጋዴዎች መፃሕፍቱን የሚረከቡት ከጅምላ አከፋፋዮች እንደሆነ ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ስሜ አይጠቀስ ያሉ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ውስጥ በሃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ”የመፃሕፍት እጥረቱ ያጋጠመው መፃሕፍቱን እንዲያትም ሃላፊነት የተሰጠው ማተሚያ ቤት ስህተት ያለባቸውን መፃሕፍት በብዛት በማተሙ ነው” ብለዋል። የመፃሕፍት እጥረቱ ያጋጠመው ስህተት ያለባቸውን መፃሕፍት በብዛት በመታተማቸው ነው ከተባለ፣ በገበያው ላይ በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጡ የሚገኙት መፃሕፍት ከየት መጡ? እንዲሁም ህትመቶቹ ስህተት እንዳይኖራቸው የሚቆጣጠረው ማነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለሆኑት አቶ አበበ ቸርነት ቢቢሲ አቅርቦላቸው ነበር። ”ጉዳዩን እያጣራን ነው” ሲሉ አቶ አበበ መልሰዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የሚፈልጉትን የትምህርት አይነት እና ብዛት በማሳወቅ በሐምሌ ወር ከትምህርት ቢሮ ይገዛሉ። አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ምዝገባ የሚያካሂዱበት በሐምሌ ወር በመሆኑ የመማሪያ መፃሕፍት ቁጥርን እና ከተማሪዎች ቁጥር ጋር አመጣጥኖ ለመግዛት አዳጋች እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የግል ትምህርት ተወካይ ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት ከ1-8ኛ ክፍል የሳይንስ፣ የስነምግባር፣ የስነዜጋ እንዲሁም የአማርኛ መማሪያ መጻሐፍት እጥረት መኖሩን ጨምረው ይገልጻሉ። ያነጋገርናቸው ወላጆች በበኩላቸው መንግሥት በበቂ ሁኔታ መፃሕፍትን አሳትሞ ማሰራጨት የሚሳነው ከሆነ የግል ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን መጽሕፍት እንዲያሳትሙ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። መፃሕፍት የማሳተም ሐላፊነት የአዲስ አባባ ትምህርት ቢሮ መሆኑን አስታውሰው “ይህ ችግር ጊዜያዊ ነው በቅርብ ጊዜ መፍትሄ ያገኛል” ሲሉ አቶ አበበ ቸርነት ይናገራሉ። ለገሃር አካባቢ የሚገኙ የመፃሕፍት ነጋዴዎች ግን ዛሬም የመማሪያ መፃሕፍት በውድ ዋጋ መሸጣቸውን ቀጥለዋል።