November 14, 2017 07:00

ኢትዮጵያ ዉስጥ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ብር  የወረቱት ሼክ መሐመድ ሁሴይን አል አሙዲንም በመታሰራቸዉ፤ ዳፋዉ ከቱጃሩ ሐብት ለሚጠቀሙና በቱጃሩ ኩባንዮች ለሚሰሩ ኢትዮጵያዉያን ሐዘን እና ስጋት አትርፏል።

 


ኢትዮጵያዉያን የትልቁ ቱጃር የሼክ መሐመድ ሁሴይን አል አሙዲ መታሰርን ትልቅ ርዕሳቸዉ እድርገዉ እየተከራከሩ ነዉ።ሊባኖሶች ጠቅላይ ሚንስትራቸዉ ያሉበትን ሥፍራና ሁኔታ ለማወቅ ኃያላንን ሲማፀኑ፤ ፈጣሪያቸዉን ሲፀልዩ ሰንብተዉ ትናንት ማታ ተንፈስ አሉ።በቴሌቪዥን አዩቸዉ።የየመኑ ፕሬዝደንት ከነልጅ-ሚንስትሮቻቸዉ ያሉበት ትክክለኛ ሥፍራ አይታወቅም።የመኖችን ብዙ ያስጨነቀዉ የጦርነቱ አልበቃ ብሎ በኮሌራና ረሐብ ብዙ ወገኞቻቸዉ ማለቃቸዉ ነዉ።ቀጠሮች ያየር፤የምድር የባሕር ሕልቅታቸዉ ተይዞ እስትፋሳቸዉ በቱርክ እና ኢራኖች ደግነት ላይ ከተንጠለጠለች አምስተኛ ወራቸዉ።ሶሪያዎች መጋደል፤መጫረስ፤ መሰደዱን ለመዱት።ኢራኖች ለጦርነት እንደሚዛትባቸዉ ሁሉ ለጦርነት እየዛቱ ነዉ። ከኢትዮጵያዉያን ክርክር እስከ ቴሕራኖች ዛቻ፤ከየመኖች እልቂት እስከ ሊባኖስ ሥጋት ምክንያት የሆነች አንድ ትልቅ ግን በትንሽ ወጣት የምትመራ ሐገር አለች።ሳዑዲ አረቢያ።የለዉጥ ማዕከል ወይስ የትርምስ ምድር?

ጀርመናዊዉ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዩስቲን ሑግለር ጥቅምት 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደፃፈዉ የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት አሁን የሚሉ፤የሚያደርጉ፤የሚያቅዱትን የጀርመኑ የስለላ ድርጅት (BUNDES NACHRICHTEN DIENST-BND) የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ጠቁሞ ነበር።ሳዑዲ አረቢያ የአረቡ ዓለም ዋና «በጥባጭ» ኃይል ከመሆን አፋፍ ላይ ናት ይላል የስለላዉ ድርጅት ዘገባ።

«የሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዊ ቤተ-ሰብ አንጋፋ አባላት አሁን የሚያራምዱት ጥንቃቄ የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ አቋም፤ ጣልቃ ገብነትን በሚያራ

Jemen humanitäre Lage Sanaa (Getty Images/AFP/M. Huwais)ምድ መርሕ ይቀየራል» ይላል የሥለላዉ ድርጅት ማስታወሻ።BND ነባሩ የሳዑዲ አረቢያ ጥንቃቄ የተሞላበት መርሕ ወደ  «አበጣባጭነት» መለወጡ አይቀርም  ለማለቱ ምክንያት ያደረገዉ የያኔዉን የሰላሳ ዓመት ልዑል የመሐመድ ቢን ሰልማንን ፍላጎት፤ የሥልጣን ጉጉት እና  ሩጫን ነበር።የጀርመን የዉጪ መርሕ ማሕበረሰብ የተሰኘዉ ተቋም ባልደረባ ሴባስቲያን ዞንስ ግን የሐገራቸዉ የስለላ ድርጅት ጥቆማን ብዙም የሚቀበሉት አይመስሉም።ዞንስት እንደሚሉት ወጣቱ ልዑል በተለይ በእድሜ አቻዎቻቸዉ ዘንድ እንደ ለዉጥ አራማጅ ነዉ የሚታዩት።

«ወጣቱ ትዉልድ ዋና ደጋፊያቸዉ ነዉ።አብዛኞቹ ወጣቶች በእሳቸዉ ላይ ትልቅ ተስፋ አላቸዉ።ዕድሜያቸዉ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ሥለሆነ የእሳቸዉ ትዉልድ ወኪል ናቸዉ።ልዑሉ ሲናገሩ ግልፅ መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ነባሩን ሥርዓት ተቺም ናቸዉ።በጣም የተለጠጠ ዕቅድ አላቸዉ።እንደሚሳካላቸዉ እና ሕብረተሰቡን መለወጥ እንደሚችሉም ያምናሉ።ሰዎቹ (ተከታዮቻቸዉ) ሐገራቸዉን ወደፊት ለማራመድ ቆርጠዉ ተነስተዋል።»

ሰዉዬዉ በርግጥ ለለዉጥ የቆሙ ይመስላሉ።በሳዑዲ አረቢያ የእስከ ቅርብ ዘመን ታሪክ ሐራም ወይም አይኔ ይመስል የነበረዉን አስተሳሰብ ጥሰዉ ሴቶች መኪና እንዲነዱ ፈቅደዋል።የሚወስዱትን እርምጃ ይቃወማሉ የሚባሉ አክራሪ የኃይማኖት መሪዎችን ሰብሰበዉ አስረዋል።የኃይማኖት ፖሊስ (ሙጠዋዕ) የሚባሉት  ኃይላት ያላቸዉን ተፅዕኖ ቀንሰዋል።ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክም ይሕን ማስተዋሉን ይመሰክራል።

አልጋወራሹ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም ሐገራቸዉ ሌሎች ሐይማኖችን የሚያከብር፤ መቻቻልን የሚቀበል፤ ፅንፈኝነትን የሚቃወም ለዘብተኛ የእስልምና አስተሳሰብን እንደምታሰርፅ መናገራቸዉ ሰዉዬዉ ለለዉጥ መቆማቸዉን ጠቋሚ የሚል አስተያየት አስከትሎላቸዋል።አልጋወራሹ የመከላከያ ሚንስትርነቱን ሥልጣን በ2015 እንደያዙ መጀመሪያ የወሰዱት ትልቅ እርምጃ የመንን መዉረር ነበር።ወረራዉ ብዙ ታዛቢዎች እንዳሉት አካባቢዉን በሚያተራምሰዉ ግጭት እና ጦርነት ላይ ሌላ ጦርነት ከመጫር ባለፍ በየትኛዉም መመዘኛ የተሐድሶ ለዉጥ አካል ሊባል አይችልም።

እርግጥ ነዉ የመን እንደሐገር ከቆመችበት ጊዜ ጀምሮ የሳዑዲ አረቢያ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ  ጣልቃገብነት ተለይቷት አያዉቅም።በቅርቡ የየመን ታሪክ የሳዑዲ አረቢያ ጣልቃ ገብነት ጎልቶ የነበረዉ የቀድሞዋ ሰሜን የመን የካፒታሊስትና ሶሻሊስቶች ጡንቻ መፈተሻ በነበረችበት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ነበር።በግብፅ እና በሶቭየት ሕብረት የሚደገፉት የሰሜን የመን ሪፐብሊካን ኃይላት የሐገሪቱን ዘዉዳዊ ሥርዓት ባፈረሱበት በዚያ ዘመን ሳዑዲ አረቢያ ዮርዳኖስ እና ብሪታንያ ለዘዉድ አራማጆቹ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲሰጡ ነበሩ።

የያኔዉ የግብፅ መሪ ገማል አብድናስር ከ70 በላይ ጦር ሲያዘምቱ የሪያድ ነገስታት ለታማኞቻቸዉ የገንዘብ፤የጦር መሳሪያ እና የስለላ ርዳታ ከመስጠት አልፈዉ ወታደር ለማዝመት አልደፈሩም ነበር።ልዑል

Jemen Kind Unterernährung (picture-alliance/AP Photo/H. Mohammed)መሐመድ ቢን ሳልማን ግን ያያት-አጎቶቻቸዉን ጥንቃቄ የተሞላበት ሥልት ጥሰዉ አሁን የመንን ካየር እና ከባር የሚቀጥቅጥ ጦር ነዉ ያዘመቱት።አዲሶቹ የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ጦር ያዘመቱበት ምክንያት እንደ አያት-አጎቶቻቸዉ  በሶሻሊስቶች የሚደገፉ ሪፐብሊካዊያን አስግተዋቸዉ አይደለም።የመንን እንኳ በቅጡ ያልተቆጣጠሩት ሁቲዎች ለትልቋ ሳዑዲ አረቢያ የሚያሰጉ ሆነዉ አይደለም።«በአካባቢዉ ፖለቲካ» የተበለጡ ሥለመሰላቸዉ ነዉ ይላል የጀርመኑ የስለላ ድርጅት ማስታወሻ።
«በአካባቢዉ ፖለቲካ ላለመበለጥ የፈለገዉ ኪሳራ ቢያመጣም ወታደራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ  ኃብታዊ እርምጃ ለመዉሰድ መቁረጣቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።» ይላል ማስታወሻ።

የሳዑዲ ገዢዎች በፖለቲካ ይበልጡናል ብለዉ የሚፈሩት የረጅም ጊዜ የአረብ ጠላት የምትባለዉ እስራኤልን አይደለም።እንደነሱዉ ሁሉ በእስልምና ግን በሺዓ ሐራጥቃ የሚመሩትን ኢራኖችን እንጂ።ያም ሆኖ ሪያዶች ለሰወስት ወራት አቅደዉ የተሞጀሩበት ጦርነት እነሆ ሰወስተኛ ዓመቱን ሊደፍን አራት ወር ቀረዉ።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ ከሐምሳ ሺሕ በላይ የመናዊ ረግፏል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቅሏል።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር እንደም በረሐብ፤ ሁለትም በኮሌራ ይሰቃያል።ሳዑዲ አረቢያም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየከሰከሰች ነዉ።እስከመቼ? አለመታወቁ ነዉ የክፋቱ ክፋት።

ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ።

በሪያዶች ግፊት የየመኑን ወረራ እኩል ከጀመሩት የአካባቢዉ መንግሥታት አንዷ የሪያድ ጠላት ከሆነች አምስተኛ ወሯን ያዘች።ቀጠር።የዶኻዎች ጥፋት ጋስ እየተዛቀ፤ ዶላር የምታፈስባት ትንሽ ሐገራቸዉን ከሪያዶች ፍላጎት እና ፍቃድ ዉጪ ከፍከፍ ማድረጋቸዉ ነዉ።የሪያድ ገዢዎች የአካባቢ ታማኞቻቸዉን አስከትለዉ በትንሽ ጎረቤቶቻቸዉ ላይ የጣሉት የአየር፤የየብስ እና የባሕር እገዳ እና ማዕቀብ የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ ሐገራት ትብብር (GCC) አንድነት ያናጋ፤ከሴኔጋል እስከ ሶማሊያ፤ ከግብፅ እስከ ኤርትራ ያለዉን የኃይል አሰላለፍ ያዛባ ነዉ።

ከሁሉም በላይ የሪያዶች እርምጃ የአረቦቹን (የይስሙላም ቢሆን) የአንድነት ግንብ በርግዶ ኢራንና ቱርክ ለቀጠር ወግነዉ በአረቦቹ መሐል ሰተት ብለዉ እንዲገቡ የፈቀደ ነዉ።የቢን ሠልማን ቤተሰቦች ቀጠርን መቅጣት-ማግለላቸዉን «የተሐድሶ ለዉጥ» እርምጃችን ሊሉት በርግጥ አይቃጣቸዉም።

አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ይመሩታል የተባለዉ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ በቅርቡ ልዑላንን፤ ሚንስትሮችን፤ የጦር አዛዦችንን እና ቱጃር ነጋዴዎችን ጠራርጎ አስሯል።በእስራት ዘመቻዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ብር  የወረቱት ሼክ መሐመድ ሁሴይን አል አሙዲንም በመታሰራቸዉ፤ ዳፋዉ ከቱጃሩ ሐብት ለሚጠቀሙና በቱጃሩ ኩባንዮች ለሚሰሩ ኢትዮጵያዉያን ሐዘን እና ስጋት አትርፏል።

ለእርምጃዉ የተሰጠዉ ምክንያት ሙስናን መዋጋት የሚል ነዉ።ሙስናን መዋጋትን የማይደግፍ ካለ እሱ ሙሰኛ ነዉ።ድጋፉ ምክንያታዊ የሚሆነዉ ግን አሳሪዎቹ ከታሳሪዎቹ ይበልጥ ከሙስና የፀዱ መሆናቸዉ ሲረጋገጥ ነዉ።
ብዙ ታዛቢዎች እንደተስማሙበት ወጣቱ አልጋወራሽ በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ ነዉ የገደሉት።ሥልጣን ሊቀናቀኗቸዉ የሚችሉ የንጉስ አብደላሕ ልጆችን አይነት ልዑላንን እና ደጋፊዎቻቸዉን አሽመድምዶ መጣል ቀዳሚዉ ነዉ።ልዑላኑም ሆኑ ቱጃሮቹ የሚቆጣጠሩትን ሥልጣንና የሥራ መስክ ለታማኞቻቸዉ በማደላደል የታዛዦቻቸዉን ቁጥር ማበራከት ሁለት።ለወደፊቱም ቀና የሚል ተቺ ተቀናቃኛቸዉ ካለ «እነሱን አይተሕ ተቀጣ» ሌላዉ ምክንያት ነዉ።

ከሁለት ዓመት በፊት የተነበበዉ የጀርመኑ የስልለላ ድርጅት ማስታወሻ «ሥልጣን በወጣቱ ልዑል እጅ መከማቸቱ፤ የአባታቸዉ ዙፋን ብቸኛ ወራሽ መሆናቸዉን እስኪያረጋግጡ ድረስ ከአቅማቸዉ በላይ እርምጃ ለመዉሰድ ሊነሳሱ ይችላሉ።» ብሎ ነበር።የመናገርም ሆነ የመደራጀት ነፃነት በሌላባት ሳዑዲ አረቢያ  ሥለ እስራቱ ዘመቻ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ከሚዘግቡት በስተቀር ሌላ ነገር መስማትና ማየት ከባድ ነዉ።ሕዝቡ በነፃነት አስተያየት መስጠት አይችልም።ጋዜጠኛ ነብዩም «ግልፅ» የሆኑ ነገሮች የሉም ከማለት ሌላ ብዙም የሚለዉ ያለ አይመስልም።

ሳዑዲ አረቢያ ሰነዓ ቤተ-መንግሥት ልትዶላቸዉ የምትዋጋላቸዉ የየመኑ ፕሬዝደንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ፤ ልጃቸዉ እና ሚንስትሮቻቸዉን አስከትለዉ ሳዑዲ አረቢያ ከመሸጉ ቆይተዋል።ባለፈዉ ነሐሴ ወደ አደን-የመን ለመሔድ ከሪያድ ተነስተዉ ነበር።አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ግን የፀጥታ ኃይሎች ከሳዑዲ አረቢያ እንዳይወጡ አገዷቸዉ።አረብ ኒዉስ አንድ የየመን ጦር አዛዥን ጠቅሶ ባለፈዉ ሳምንት እንደዘገበዉ ሐዲ እና ተከታዮቻቸዉ ሪያድ ዉስጥ በቁም ታስረዋል።

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሰዓድ ሐሪሪም ባለፈዉ ሳምንት ወደ ሪያድ የተጎዙት ያዉ እንደከዚሕ ቀደሙ ቤተሰብ ጥየቃ፤

Saad Hariri (picture-alliance/AP Photo/H.Malla)የሥራ ጉብኝት ወይም እረፍት መስሎ ነበር።ሪያድ ሆነዉ ሥልጣን መልቀቃቸዉን አስታወቁ።ሥልጣን ለቀቅኩ ካሉ በኋላ አንድ ሳምንት  ጠፉተዉ ትናንት ቴሌቪዢን ፊት ቀርበዉ ለሥልጣናቸዉም፤ለሕወታቸዉም፤ ለሐገራቸዉም ኢራንን ወነጀሉ።የሐሪሪ መግለጫ እነ ሳልማን ያስጠኗቸዉ መሆኑን የጠረጠረ የለም።

ጥቅል መልዕክቱ ግን አሸናፊ እና ተሸናፊዉ ባለየበት ጦርነት የየመንና የሶሪያን  ሕዝብ የሚፈጁት፤ ሪያድ ፤ ቴሕራኖች እና ተባባሪዎቻቸዉ ሊባኖስ ዉስጥ ሰወስተኛ የዉጊያ ግንባር እንዳይከፍቱ ማስጋቱ ነዉ።ሁለቱ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ኃያል ሙስሊም ሐገራት ቀጥታ ዉጊያ ለመግጠም መፈለጋቸዉን  ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ይጠራጠራሉ።ጦርነት ከተጫረ ግን ሴባስቲያን ዞንስት እንደሚሉት ለአካባቢዉም ለመላዉ ዓለምም ትልቅ ጥፋት ነዉ።

«አካባቢዉ አሁንም በሁሉም ማዕዘናት እየነደደ ነዉ።በኢራንና ሳዑዲ አረቢያ  ቀጥታ ዉጊያ ቢገጥሙ ደግሞ መካከለኛዉ ምሥራቅን በሙሉ ያጋያዋል።ከጦርነቱ የአካባቢዉም ሆነ ከአካባቢዉ ዉጪ ያሉት ኃይላት የሚጠቀሙ አይመስለኝም።»

አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን የጀመሩት የተሐድሶi ለዉጥ በርግጥ የብዙዎችን ድጋፍ አትርፏል።ከዉስጥም ከዉጪም ባንድ ጊዜ ብዙ ቁልፍ መነካካታቸዉ ግን የተሐድሶ ለዉጥ ሳይሆን ሥልጣን የመጥቅለል፤ የኃያልነት እና ምናልባት ያለማወቅ  ሥሕተት እንዳይሆን ያሰጋል።ምናልባት ዋሽግተኖችን አይዞሕ አይዞሕ አምነዉ ከሌላ ጦርነት ከተሞጀሩ ደግሞ መዘዙ መመለሻ ማግኘቱ አጠራጣሪ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ