15 November 2017

ዘመኑ ተናኘ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኳታር በመሄድ፣ በማግሥቱ ከኳታር አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማቶች ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ ተስማሙ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ከኳታር በስልክ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሁለቱ አገሮች በ1987 ዓ.ም. የጀመሩትን ግንኙነት ለማጠናከር፣ ዲፕሎማቶች ያለ ቪዛ በሚንቀሳቀሱበት ዝርዝር ጉዳይ ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ በቱሪዝም፣ በኢነርጂና በኢንቨስትመንት መስኮች ተባብረው ለመሥራት መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ የኳታሩ አሚር ኢትዮጵያ የኳታር ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ማለታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገቧን ለኳታሩ አቻቸው እንደገለጹላቸውና በዚህም የኳታር ባለሀብቶች በአገሪቱ ኢንቨስት ቢያደርጉ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ የኳታር ባለሀብቶችና መንግሥትም በኢትዮጵያ ውስጥ በሆቴልና በቱሪዝም፣ እንዲሁም በፓታሽ ልማት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር እያደረገቸው ባለው ጥረት ኳታር ከፍተኛ አድናቆት እንዳላት አሚሩ መግለጻቸውንም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኳታርና ባህረ ሰላጤው አገሮች መካከል ያለው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መጠየቃቸውን፣ በዚህም ኢትዮጵያ የኩዌት አሚር የጀመሩትን የሰላም ጥረት እንደምትደግፍ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ኳታር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጋር እንደተወያዩ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ አገሪቱ  አሁን ያለችበት የፀጥታ ሁኔታ ምን እንደሚመስል፣ በኳታር የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ለምን አይገነባም? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ኳታር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው አገሪቱ ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋት መመለሷንና ይህን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግም፣ ከመላ የአገሪቱ ሕዝብ ጋር ውይይት ሊደረግ መታቀዱን እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱን በተመለከተ የኳታርን መንግሥት እንጠይቃለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በ2009 ዓ.ም. ለህዳሴ ግድቡ 4.9 ሚሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው  እንደተገኘ አስታውሰው፣ የተሻለ የተገኘው ግን ከመካከለኛው ምሥራቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ደግሞ ኳታር ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተገኘ እንደሆነም አክለዋል፡፡  በኳታር ከ23 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡ ኳታርና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት በ1987 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ‹‹አልጄዚራ›› የተሰኘው የኳታር ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያስተላልፈው በነበረው ዘገባና ሌሎች ምክንያቶች ግንኙነቱ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ የኳታሩ አሚር ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ መጥተው በነበረበት ወቅት ደግሞ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተሻሽሎ በአሁኑ ወቅት በትብብር ለመሥራት የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ በቅርቡም ‹‹አልጄዚራ›› በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መክፈቱ ይታወሳል፡፡

ኳታር ከባህረ ሰላጤው አገሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ በመግባቷ በኤርትራና በጂቡቲ ድንበር መካከል አሰማርታው የነበረውን ጦሯን ማንሳቷ አይዘነጋም፡፡

ሪፖርተር