የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ትላንት በኦሮሚያ ውስጥ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱም ሰባት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ዛሬም በስፍራው ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት መሆናቸውን በዓይናቸው እንደተመለከቱ የገለጹት ነዋሪዎች፣ በቀጣይም ለደህንነታቸው እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                                                                      File Photo

በጥቃቱ ከተገደሉ ሰዎች በተጨማሪ የቆሰሉ ሰዎች ስለሞኖራቸውም እየተነገረ ይገኛል፡፡ የክልሉ ልዩ ጦር ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ከአካባቢው ብዙም ርቆ እንዳልሄደ የሚናገሩት የዓይን እማኞች፣ ሁለተኛ ዙር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት በማኅበረሰቡ ዘንድ መፈጠሩንም ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ የልዩ ኃይሉ አባላት፣ ሰባት ሰዎችን ከገደሉ በኋላ አንድ ትምህርት ቤት በጥይት እንዳጋዩ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በተጨማሪም ሁለት የመኖሪያ ቤቶች በልዩ ኃይሉ አባላት እንዲቃጠሉ መደረጉንም ነዋሪዎቹ ያክላሉ፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባለቱ ጥቃቱን የፈጸሙት በስፍራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ባሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ጥቃቱ ሲፈጸም የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን የዓይን እማኞቹ ይገልጻሉ፡፡ ከሟቾች መካከል አራቱ ዕደሜያቸው ገፋ ያለ ሲሆን፣ ከ60 እስከ ሰባ ዓመት ይገመታሉም ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በአሮሚያ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎችን መግደሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ቆሟል ተብሎ በመንግስት እየተገለጸ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ ልዩ ኃይሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ዘልቆ ጥቃት የፈጸመበት ምክንያት አልታወቀም፡፡

BBN News November 15, 2017