Share

ይድረስ  ለአቶ  ገዱ  አንዳርጋቸው  የአማራ  ክልል  ፕሬዚደንት

ከፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ (ፕሮፌሰር)

ጉዳዩ– ፍቅርን፣ሰላምን፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያዊነትን አስመልከቶ

በቋንቋ ላይ ከተገነባ ጎሰኝነት ይልቅ በደም፣ በተዋልዶ እና አብሮ በመኖር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነትን ክህዝባችሁ ጋራ ሆናችሁ አብስራችሁና አውጃችሁ በባህርዳር ከተማ ውስጥ ከኦሮሞና ከ ክአማራ ዘመዶቻችሁ ጋራ በቅርቡ ያደረጋችሁት ውይይት ልቤን ነክቶታል። በእዚህ ጉዳይ ዛሬ እኔ ክማንም ያላነሰ ሃሴት አደርጋለሁ። ቅድስት ኢትዮጵያ እንድትከበርና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ ባለፉት 28 ዐመታት አቅሜ የሚችለውን ሁሉ አድርጌአለሁና።  ኢትዮጵያዊነት እንደ አርኩስነት በተቆጠረበት በ ቀውጢዎቹ  28 ዐመታት ውስጥ፣ በትንሿ አቅሜ፣ ኢትዮጵያዊነት ቅድስና እና ልእልና መሆኑን ለማንፀባረቅ ሞክሬአለሁ።  ይህን በማድረጌ የዘለፋና የስድብ ውርጅብኝ ደርሶብኝ ስለነበር አሁን እናንተ በፍቅር ተገናኝታችሁ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ከፍ ስታደርጉ ሳይ ይሀ ክስተት አውነት በህልሜ ነው በውኔ፣ ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ።  የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያዛምድውና የሚያስተሳስረው፣ እንዲሁም  አብሮ ለመኖር የሚያስችለው ኢትዮጵያዊነት፣ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።  በእርግጥም እንደተራራ ለተቆለለው የኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት፣ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ስለሆነ እናንተ በትክክለኛው ጥርጊያ መንገድ ላይ መጓዝ ጀምራችኋል።  የጉዟችሁን መጨረሻ አግዚአብሄር ያሳምረው። ጅማሮአችሁ እንዳይጠለፍ ወይም እንዳይደመሰስ  ይጠብቀው። እናንተም ነቅታችሁ ጠብቁት።

ጉራጌ፣ አማራ፣ ተጋሩ፣ አፋር፣ ኦሮሞ፣  ከምባታ፣ ሀዲያ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ እና ሌሎቻችንን በኢትዮጵያም ሆነ በውጪ ሀገር የምንኖረውን ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያዛምደን ኢትዮጵያን በስሙ ያስጠራት የንጉሦች ንጉሥ የካህኖች ካህን የነበረው አባታችን ኢትዮጵ ነው። ኢትዮጵ የኖረው በጣና ደሴቶች ላይ ሲሆን ዘመኑም ከ 4000 ዐመታት በፊት ነው። እሱም 10 ወንዶች ልጆች ወልዶ ነበር። እነዚህ 10 ወንዶች ልጆች 10 ነገዶች ሆነው ለ 4000 ዐመታት በመባዛት እኛን የዛሬዎቹን ኢትዮጵያውያንን አስገኝተዋል።   የኢትዮጵ አስሩ ወንዶች ልጆች ስሞችም አቲባ፣ ቢዖር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክዚብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ፣ እና አዜብ ነበሩ። የዛሬ 4000 ዐመት ከወጡት ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ ወለጋ ውስጥ ይኖር የነበረው የኦሮሞው አጎቴ ስም ቶላ ነበር። ኢትዮጵ ከኦሮሞዎች ጋራ ዝምድና ስለአለው ነው የዛሬ 4000 ዐመት ለልጁ የሰየመው ስም ዛሬ የኦሮሞው የኔ አጎት እና የሌሎችም ኦሮሞዋች  ስም ሊሆን የቻለው። ከአባታችን ከኢትዮጵ በኋላ የተክተሉት ነገሥታት ልጆቹ የኢትዮጵያን ስልጣኔ በመላው አፍሪካ አስራጭተው ዛሬ አፍሪካ የሚባለው ሰፊ ምድር እስክ ዛሬ ሁለት መቶ ዐመታትት ድረስ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ ነበር። LOWER እና UPPER ETHIOPIA ብለው ከፍለውት ነበር።  ከእዚህም በላይ የህንድ ውቅያኖስ እና ከ ምእራብ አፍሪካ ብብት ስር ያሉት ውቅያኖሶች ሁሉ የኢትዮጵያ ውቅያኖሶች ይባሉ ነበር።  ለማመሳከርያ ከዚህ ፅሁፍ እግርጌ የሰፈሩትን ሁለት ጥንታዊ የአፍሪካ ካርታዎች ተመልከቱ።   አሁንም ቢሆን አፍሪካ፣ አፍሪካ የተባለችው በእኛው በአፋሮች ስለሆነ ደስ ይለናል እንጂ አንቆጭም። እስያም እስያ የተባለችው ንግሥተ ሳባ ዙፋኑን በተካችው በ ዐፄ እስያኤል ስለሆነ በእዚህም እንታበያለን። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ  “የተቃጠለ ፊት” ሳይሆን “ቢጫ ወርቅ” ስጦታ ለእግዚእብሄር ነው። ቅዱስ ስሟን ለመፋቅ ወይም ለመቀየር የተመኙ ሁሉ የኢትዮጵያ ስም ከእግዚአብሄር ጋራ የተያያዘ በመሆኑ ምኞታቸው ከሽፎ ቀርቷል። ኢትዮጵያን ሊያገንን የተነሳ ሁሉ ይገንናል። ኢትዮጵያን የሚያከብር ሁሉ ይክብራል።  ኢትዮጵያን ያኮሰሰ ሁሉ ይኮስሳል።  ኢትዮጵያን ያንቋሸሸ ሁሉ ይንቋሸሻል።

የእግዚአብሄር ዐይኖች ኢትዮጵያ ላይ ተተክለዋል። በቅዱስ መፅሃፉ ውስጥ እግዚእብሄር ኢትዮጵያን ደጋግሞ የሚጠራት ያለ ምክንያት አይደለም። ከማንም ይልቅ ኢትዮጵያን ስለሚወዳት ነው። በነቢዩ አሞፅ አፍ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡-

<<እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያውያን ልዶቼ አይደላችሁምን?>>  (አሞፅ 9: 7) ከእዚህ ጥቅስ የምንማረው እኛን ኢትዮጵያውያንን እግዚአብሄር ክአሰራኤላውያን ይበልጥ ወይም እኩል እንደሚወደን እና ልቡ ውስጥ እንደእለን ነው።  ስለእዚህ እሱ ጥሎ አይጥለንም።

የሁለቱ ትልልቅ ህዝቦች፣ ማለትም የኦሮሞናየ አማራ በሰላምና በፍቅር መኖር ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋስትና ነው። ኦሮሞና አማራ እየተጨራሱ እኔ ተገልዬ እና ተዘልዬ ገንብ አጥሬ ለዘላለም በሰላም እና በብልፅግና ለብቻዬ እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ጂል ብቻ ነው። የሁለቱ ጠብ ዳፋ ለሁሉም ስለሚደርስ። ደሞም ሁለት ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ መጎዳቱ ስለማይቀር።  እንግዲህ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትጎናፅፍ ዘንድ ኦሮሞና አማራ በፍቅር እና ሰላም አብረው እንዲኖሩ ግድ ይላል።  የአማራና ኦሮሞን ቤቶች የሚያነደው እሳት ካልጠፋ ወደ ሌሎቹም ሰዎች ቤቶች መዛምቱ አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት በእርግጥም በኢትዮጵያውያን ልቦች ሁሉ ሰርጎ የገባ ፍቅር ነው። ይህ ባለፉት 4000 ዐመት በቅሎ ስር የሰደደ ፍቅር በ 30 ዐመታት ውስጥ ሊተን አይችልም። ከእዚህ በተያያዘ የአቶ መለስ ዜናዊን ስህተት ያስታውሷል። አቶ መለስ ዜናዊ የአክሱም ሃውልቶች እና የ ጎንደር ቤተመንግሥቶች የተጋሩና የጎንደር አማራዎች እንጂ ለኦሮሞ እና ለጉራጌው፣ እንዲሁም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ምኑም አይደሉም፣ ብሎ ለሟቹ ለፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ቃለመጠይቅ ሰጥቶ ነበር። እኔም ለዚህ ስህተት እፃፋውን በዛው ሰሞን በ ኢትዮፒያን ሪሺው መፅሄት ላይ በእንግሊዝኛ መልሼለት ነበር። እንዲህ ስል << አቶ መለስ ተሳስትሃል። በኋላ በጉራጌነት የተጠሩ ህዝቦች በትግራዩ ተወላጅ በአዝማች ግርማይ መሪነት በዛን ጊዜ የትግራይ ክፍል ከነበረው ከጉራእ ተነስተው ሸዋ ላይ ሰፍረው ነበር። ስለዚህ አክሱም የጉራጌዎችም ነው። ኦሮሞም በጎንደር ቤተመንግሥት ውስጥ ከመጀመሪያው  አንስቶ አፄ ቴዎድሮስ  እነ ትንሹን ራስ አሊን ከ እቴጌዋ እናታችው ጋር አስወጥተው እስከ አባረሯቸው ጊዜ ድረስ ይፈነጭበት ነበር። ስለዚህ አቶ መለስ ሆይ ስህተትህ አጥፍ ድርብ ነው።>> አቶ መለስ ለ ዶናልድ ሌቪን ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት የላችውም የሚል ነበር። እንደ አሱ አባባል ትግራይ የተጋሩ ብቻ ስለሆነች ትግራይ ስትወረር ተጋሩ ያልሆኑት ኢትዮጵያውያን ለትግራይ ደማቸውን ማፍሰስ አልነበረባቸውም። እኛን ምን አገባን ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ማየት ነበረባቸው። ሀቁ ግን የድሉ ተጠቃሚዎች ሌሎች ቢሆኑም በሃገር ፍቅር ተቃጥለው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደማቸውን ለትግራይ  ነፃነት ገብረዋል።  ያኔ ኢትዮጵያውያን ለትግራይ ባይሞቱ ኖሮ ምናልባት ዛሬ ነፃዊቷ ትግራይ ባልኖረች ነበር።

አቶ መለስ ብሄራዊ ስሜት የለውም ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእርግጥም ኤርትራ ትግራይን በወጋች ጊዜ ህገሬ በጠላት ተወረረች ብሎ የብሄራዊ ስሜት ሲቃ ይዞት፣ ግር ብሎ አየተመመ ከድፍን ኢትዮጵያ ተነስቶ ትግራይ ላይ ተሰባስቦ ለሃገሩ ሉአላዊነት ደሙን አፈሰሰ። በእዚያን ጊዜ ለአቶ መለስ ዜናዊ በእንግሊዝኛ  ግልፅ ደብዳቤ ፅፌ ተበቀልኩት፡—<< ዐየህ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ሞትን ከመጤፍ የማያስቆጥረው እሳታዊ የእናት ሃገሩ የኢትጵያ ብሄራዊ ስሜት አለው፣>> ብዬ። አሁንም ቢሆን ይህ የኢትዮጵያዊነት እሳት በጎሰኝነት አመድ ቢዳፈንም አመዱ ሲበን ተገልጦ ዳግም እየተንቀለቀለ ይነዳል።  ሰሞኑንም መንደድ ጀምሯል።

ፕሬዚደንቶች ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ሆይ!

አሁን እናንተ ኦሮሞዎችና አማሮች ወንድማማቾች በባህርዳር ተገናኝታችሁ ያረጋገጣችሁት ዝምድና  እና ትስስር ሁለታችሁም  ባነበባችሁት  የኦሮሞ እና የአማራ አውነተኛው የዘር ምንጭ በተሰኘው መፅሀፌ  በግልፅ ተንፀባርቋል።   ከመፅሀፌ እንደተገነዘባችሁት በእውነትም አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት እንጂ በቋንቋ ላይ የተገነባ ጎሰኝነት አይደለም። ጎሳ ማለት ቋንቋ ማለት ነው እሱውም <<ጎሰአ>>፣ ማለትም  ተናገረ  ከሚለው የግዕዝ ቃል የፈለቀ ነው። ስለዚህ ቋንቋ ማለት ጎሳ ነው። ጎሳ ማለትም ቍንቋ ነው።  በሌላ አነጋገር፣ ጎሳ የቋንቋ ክፍል እንጂ የደም ወይም የ ዘር ዘርፍ አይደለም። አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሞላ በዛ ቋንቋ አፍ ከፈቱ  የዛ ቋንቋ  ወይም ጎሳ አባላት ይሆናሉ። ይህን በምሳሌ ላሳይ።– እኔ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና አንግሊዝ ሃገሮች ኖሬ ሶስት ልጆች ብወልድና እነሱ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ  እና እንግሊዝኛ ቢናገሩ፣ የእኔ አፍ መፍቻ ደግሞ ኦሮምኛ ቢሆን ልጆቼ ሶስት የተለያዩ ቋንቋዎች በመናገራቸው ጎሳቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ቢሆንም የርስበርስ ዝምድናቸው አይፋቅም።  እኔም ኦሮምኛ ስለተናገርኩ ጎሳዬ ኦሮሞ ቢሆንም አባትነቴ አይሰረዘም። እኛን የሚያዛምደን የኔ ደም ወይም ዘር እንጂ ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለምና።  ስለእዚህ ስዎችን በስጋ የሚያዛምድ ደም ወይም ዘር ነው እንጂ  ቋንቋ ወይም ጎሳ አይደለም።  ደሞ ቋንቋ ሊረሳም ሊለዋወጥም ስለሚችል አስተማማኝ የማንነት መለያ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎች እንድአሉ ይንገራል። ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ስለሆነ በእዚህ ቁጥር መሰረት 82 ጎሳዎች አሉ ማለት ነው። በልጆቼ ምሳሌ እንደምናየው ደም አንጂ ቋንቋ አያዛምድም።  አነዚህ ሁሉ የቋንቋ ተናጋሪዎች በደም ወይም በዘር የሚዛመዱት ሁሉም ከኢትዮጵ ወይም ከእሱ 10 ልጆች አብራክ ስለፈለቁ ብቻ ነው። በተጨማሪ ደግሞ በጋብቻ ደም ስለተደበላለቁ  እና በኢትዮጵያ ግዛት ለ ሺዎች ዐመታት አብረው ኖረው በባህል፣ በልቦና እና እምነት ስለተሳሳቡ  እና ስለተወሳሰቡ፣ እንዲሁም የጋራ የማንነት አሴቶችን ስለአካበቱ  ነው።   አንግዲህ እናንተም የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚያዛምዳቸው እና አንድ የሚያደርጋቸው፣ ክዛም አልፎ የሚያኗኑራቸው ኢትዮጵያዊነት አንጂ ጎሰኝነት ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል አለመሆኑን እናንተም ተረድታችሁ ሁለታችሁም ከኢትዮጵ ዘር ከወረደው አባታችሁ ከፈላስፋውና ከ ነብዩ ደሸት የዛሬ 3600 ዐመት አካባቢ በተፈጠራችሁበት በጎጃም ተገኝታችሁ ኢትዮጵያዊነትን መዘመራችሁ ያስመሰግናችኋል። ይህ ሊሆን የቻለው የእግዚእብሄር መንፈስም ዘንቦባችሁ እንደሆነ አኔ አልጠራጠርም። የደም ወተቷን እያጠባች ያሳደገቻቸው ልጆቿ፣ ኢትዮጵያ አመድ-አፋሽ ሆና፣  ጡት ነካሽ ሆነውባታል።  ምንም እሷ ብታወፍራቸውና ብታፋፋቸውም፣ እንዲሁም ብታቶጅራቸውም፣ ርእሰብሄሮቿ እንኳ ሳይቀሩ ለ 28 ዐመታት ኢትዮጵያ ብለው ስሟን ለመጥራት ተፀይፈው <<ሃገሪቱ፣ ይች ሃገር>> ይሏት  የነበረችውን እናታችንን ኢትዮጵያን እናንተ ከፍ ከፍ አድርጋችኋታል።  ነገር ግን ተግባራችሁ በእዚህ ብቻ እንዲገታ አይገባም። አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ አለባችሁ።

ግን ምን ዐይነት አርምጃ?   ከዝምድናችሁ በተጨማሪ፣ በቁጥር ብዛታችሁና ክእዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ህልውና አብራችሁ የተሰለፋችሁትን መለስ ብላችሁ በማጤን የአመራር ሚና እየተጫወታችሁ ሌሎቹንም ኢትዮጵያውያንንም፣ ማለትም ብዙሃኑን የአፋርን፣ የተጋሩን፣ የሲዳማን፣ የጉራጌን፣ የሃዲያን፣ የከምባታን፣ የሱማሌን፣ የክፋን እና ሌሎቹን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋብዛችሁ ተመካክራችሁ  ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና ርትእ፣ የሰብአዊ እና የሃብት እኩልነትን አስከብሩ። የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ በድፍን ኢትዮጵያ የመንቀሳቅስ እና የመኖር መብትን አስተግብሩ። በጎሰኝነት ጦስ በከንቱ የሚፈሰውን ደም አስቁሙ። የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ በአስቸኳይ አስፈቱ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ የአሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰባዊ ማህበራትን ሳትንቁ በማሰባሰብ ከእናንተ ጋራ ሆነው እነሱም የሃገራቸውን እጣ ፈንታ እንዲወስኑ እድል ስጡአቸው። የእንቅስቃሴአችሁንም አርማ እስከመጨረሻው ኢትዮጵያዊነትን አድርጉ። አሁን በሃረር የሶማልያ ክልል በእብሪተኞች መሰሪነት ከመኖሪያቸው የተፈናቅሉት አሮሞዎችና ከነሱ ጋር በሰላም ለዘመናት የኖሩት ሶማሌዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው አንዲመለሱ ጣሩ። የጎንደር ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ የተቻላችሁን ፈፅሙ።  ይህን ሁሉ ብትፈፅሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅር፡ አንድነት፣ እኩልነት፣ የንግግርና የፅሁፍ ነፃነት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሰብአዊ መብት፣  ዲሞክራሲ እና የህግ የበላይነት ይሰፍናሉ። ኢትዮጵያም በነፃነቷ ለዘላለም ትኖራለች።

ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በልብ እና ደም ስር ውስጥ መገኘቱን እና እንደሚያሰክር ልዩ እፅ መሆኑን ለመግለፅ  ሞክረው ነበር። እኔ ከእዚህ ቀደም ስለ ኢትዮጵያዊነት በጥልቅ እስቤበት የደረስኩበትን መደምደሚያ ከእዚህ በታች አያይዤዋለሁ። የኢትዮጵያዊነት ማኒፌስቶ ወይም መግለጫ ብዬዋለሁ። ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለምን በኢትዮጵያዊነታችን  መኩራት እንደሚገባንም ዘርዝሬአለሁ።  በኢትዮጵያዊነት ጉዞአችሁ ይህ መግለጫ ፋና ይሆናችሁ ዘንድ አበርክቼላችኋለሁ። ከእሱ በተጨማሪ፣ አናንተ ከዚህ ቀደም ባነበባችሁት የኦሮሞ እና የእማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በተሰኘው መፅህፌ፣ እና አሁን ስሞኑን ባሳተምኩት ሥራዬ  ውሰጥ፣ ማለትም የተሰወረውና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክበሚለው መፅሀፌ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ፍንትው ብሎ ስለሚታይ በእነሱም ልትመረኮዙ ትችላላችሁ።  በእዚሁ በአይሁዳውያን እና አትዮጵያውያን የታሪክ መፅሃፌ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ምንነት ዝርዝር በተቀፅላ በቋሚነት ስለተቀመጠ መፅሃፉን እንደ አሻችሁ እየገለጣችሁ  እሱን ለመመልከት የሚያግዳችሁ ነገር የለም።

የኢትዮጵያዊነት ምንነት መግለጫ እና ለምን በኢትዮጵያዊነታችን መኩራት እንደሚገባን

MANIFESTO OF ETHIOPIANISM

                        ክፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ የጽፈት ጠረጴዛ

ኢትዮጵያዊ መሆን እጅግ የሚያኮራ ነገር መሆኑን ባለመገንዘባችን እና “አትዮጵያ” የሚለውን ቃል ትክክለኛ ፍቺ ባለማወቃችን፣ አንዳንዶቻችን በኢትዮጵያዊነታችን አናፍራለን።

“ኢትዮጵያዊነት” ምን ማለት እንደሆነ  ለማብራራት የቃሉን ትርጉም  ምንጭ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ “ኢትዮጵያ” ማለት ቢጫ ወርቅ ስጦታ (ለእግዚአብሄር ማለት) ነው፡፡ ይህ ስም የተሰጠው ለኢትዮጵያ መስራችና የኢትዮጵያውያን አባት ለሆነው ለ ኢትዮጵ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ወርዶ፣ ወርዶ  ወደ እኛ የደረሰው ከሱ ስም ነው ማለት ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊ” ማለት በግሪክ ቋንቋ የተቃጠለ ፊት ነው  የተባለው ነጭ ውሸት ነው። በግሪክ መዝገበ ቃላት ውስጥ እንደዚህ የሚል ቃል የለም። ደሞም የኛ ፊት የተዋበ እንጂ የተቃጠለ አይደለም።

ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው፣ ከፍ ሲል ኢትዮጵያን በስሙ ካስጠራው ከካህኑና ከንጉሠነገሥቱ ከኢትዮጵ፣ ዝቅ ሲል የሱ ዘር ከሆነው ከነቢዩና ከፈላስፋው ከደሸት መውረዳቸ ነው፡፡ ኢትዮጵ የዛሬ 4000 ሺ ዐመት አካባቢ ዐስር ወንዶች ልጆች ወልዶ ነበር፡፡ ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፡፡–

አቲባ፣ ቢኦር፣ ተምና፣ አቴር፣ አሻን፣ አክሲብ፣ በሪሳ፣ ቴስቢ፣ ቶላ እና አዜብ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስሞች ውስጥ አሻን፣ በሪሳ፣ ቶላ እና አዜብ አሁንም ድረስኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።

የኢትዮጵ ዘር፣ የነቢዩ ደሸት ልጆች ደግሞ መደባይ፣ መንዲ፣ ጂማ እና ማጂ ይባሉ ነበር፡፡ ማጂ ማራ (አማራ) ን እና ጀማን ወለደ፡፡ ሰዎቹ የተሰየሙት የዛሬ 3600 ዐመት ቢሆንም፣ እነዚህ ስሞች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡

የኢትዮጵ 10 እና የደሸት 4 ልጆች ተባዝተው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉት ሰዎች በሞላ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያና በመላው ዐለም ባሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የደም ስሮች ውስጥ የኢትዮጵ እና የደሸት ደም ይዘዋወራል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በሞላ ምንጫቸው አንድ እና አንድ ነው፡፡ ስለዚህም ቋንቋቸው  ቢለያይም ደምና ዘራቸው አንድ ነው፡፡ ቋንቋ ደግሞ የመግባቢያ መሳሪያ እንጂ ዘርን አመላካች ወይም የዘር ክፍል አይደለም፡፡ ቋንቋ ማለት ጎሳ ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ጎስአ(ጎሳ)  ልብየ ሰናይ ይላል፡፡ ልቤ መልካም ተናገረ፣ ማለት ነው፡፡ አገሳ ወይም ከውስጥ አወጣ፣ የተሰኘውም ቃል ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ጎሳ ማለት አንድ ዐይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ነው፡፡ ዘር ማለት አይደለም፡፡  ለምሳሌ አንድ አባትና እናት ወደ ፈረንሳይ ሃገር ሄደው ልጅ ቢወልዱና ፈረንሳይኛ ቢናገር፣ ከዛም ወደ አሜሪካን አገር ተጉዘው ሌላ ልጅ ወልደው እንግሊዝኛ ቢናገር፣ ልጆቻቸው ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ስለተናገሩ ወንድማማችነታቸው አይፋቅም፡፡ ወላጆቹም አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም አፋርኛ በመናገራቸው ወላጅነታቸው አይደመሰስም፡፡ ደምና ዘራቸው አንድ ናውና፡፡ ስለዚሀ ወሳኙ ቋንቋ ሳይሆን ደምና ዘር ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ ወይም ጎሳ ወሳኝ አይደለም፡፡ መግባቢያ ነው እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ከ 80 በላይ ቋንቋዎች  የሚናገሩ ጎሳዎች አሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ ጎሳዎች በቋንቋ ቢለያዩም በደማቸው አንድ የኢትዮጵ ልጆች ናቸው፡፡ የሚያገናኛቸውም ኢተዮጵያን በስሙ ያስጠራው ኢትዮጵ አባታቸው ነው፡፡

ክ 200  ዐመታት በፊት መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ይባል ነበር። የእዚህ ምክንያቱ የኢትዮጵ ተወላጆች በመላው አፍሪካ ተሰራጭተው፣ አፍሪካን አሰልጥነው ስለኖሩበት ነው። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በቅኝ መግዛት ከጀመሩ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ቀርቶ አህጉሩ አፍሪስካውያን በተባሉት አፋሮች አፍሪካ መባል ጀመረ። አሁንም ድረስ ስሙ ክእኛው ስለ አልወጣ ቅር አንሰኝም።

እንድ ኢትዮጵያዊ ውስጥ የተወለደ ወይም ትውልደ-ኢትዮጵየዊ ሰው በሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያዊ ይሆናል። አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዱ። ሁለተኛ፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ በመሆኑ።  ሁለቱንም የሚያገናኛቸው በደምና በዘራችው ክኢትዮጵ መውረዳቸው ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት በዐለም ልዩ የሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ  የሚገኝ ዮጵ የተባለ ቢጫና ብርቅዬ ወርቅነት ማለት ነው። ክዚህም በላይ፣ ለዐለሙ ፈጣሪ ለእግዚአብሄር ብቻ የሚቀርብ ልዩ ገጰበረከት ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የህይወት ምንጭነት፣ የሰብእና  መገኛ ስፍራ ማለት ነው።

ኢትየጰያዊነት ማለት የስነመለኮት ክፍታ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ፣ የሰው ዘር አርአያ፣ የስነምግባር ልእልና ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የህርነት፣ የጀግንነት እና የፍትሀዊነት ተምሳሌነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የእኩልነትና የሰው ልጅ ክቡርነት አርማ ነው።

እትዮጵያዊነት ማለት የታማኝነት እና የተአማኒነት እንዲሁም የመለኮት ማህደርነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የፅናትና የብርታት እና የትእግስትና የዘላቂነት ምልክት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀቀኝነትና የእውነተኛነት ምሳሌ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የርህራሄና የችርነት ናሙናነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት ሰው አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ይሉኝተኝነት እና አዙሮ ተመልካቸነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት የጥበበኝነት ቁንጮ፣ የብልህነት እራስ ማለት  ነው።

ኢትዮጵያዊነትማለት የቅድስና እና የብጱእነት ጫፍ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣ የመተዛዘን ማማነት                                      ነው።

ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትጵያውያን በሞላ በሚክተሉት ምክንያቶች በኢትዮጵያዊነታቸው ሊኮሩ ይገባል። የኩራቶቹን ሁሉ ምክንያቶች ለመዘርዘር ጊዜ ስለሚፈጅ ጥቂቶቹ ብቻ ይቀርባሉ።  

  1. ኢትዮጵያ በሳይንስም ሆነ በመፅሃፍ ቅዱስ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ፣
  2. ክ 4500 ዐመታት በፊት በንጉሥ ስብታህ አማካኝነት የጋዜጣን እና የፖሊስን ሥራ ከዐለም ቀድማ ኢትዮጵያ በማቋቋሟ፣
  3. በዐለም ላይ የሌለ ከኖህ ጀምሮ ስሞቻቸውና የነገሡበት አዝማናት የተመዘገበ ነገሥታት በመኖራቸው፣
  4. አባችን ኢትዮጵ እና ሚስቱ እናታችን ሲና እንቁዮጵግዮን መሲሁ እየሱስ ሲወለድ ልጆቻችው ወደ እስራኤል ተጉዘው ገዳ እንዲያበረክቱለት በእግዚአቤሄር ትአዛዝ ከኢየሩሳሌም  ወደ ኢትዮጵያ መምጣታችው እና ጣና ጎጃም ላይ በተልእኮ በመስፈራቸው፣
  5. የኢትዮጵና የእንቁዮጳግዮን ልጆች ታላላቅ ነገሥታት ሆነው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና እስያ በመንሰራፋታቸው፣ ስልጣኔአቸውን በማሰራጨታቸው እና መላውን አፍሪካ ኢትዮጵያ በማሰኘታቸው፣
  6. አጼ እስያኤል እስያን አሰልጥኖ በስሙ አህጉሩን እስያ በ ማስኝቱ፣ እጽዋትን እና እንስሳትን አዳቅሎ አዲስ ውጤት ያስገኘው በዐለም የመጀመሪያው ጄኔቲክ ኢንጂኔር በመሆኑ፣ ክ3000 ዐመታት በፊት ይኽው ትልቅ ስው ምናልባት በዐለም የመጀመሪያ የሆነውን ሰንደቅአላማችንን በመፈልሰፉ፣
  7. በንግሥተ ሳባ ተልቅነት— ኢትያኤል የተባለች የሳባ ንግሥት በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰች፣ የዐለሙ ፈጣሪ እየሱስ ክርስቶስ ስሟን ጠርቶ፣ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበበኝነት ለመፈተን ኢየሩሳሌምን መጎብኝቷን የመሰከረላት ትልቅ ሰው በመሆኗ፣
  8. በአፋሮች ትልቅነት—አፍሪካ በአፋሮች አፍሪካ ስለተባለች። ከ 3000 ዘመናት በፊት አፋሮች ታላቅ መርከብ ገንቢዎችና መርክቦኞች እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና በእስራኤል ስመጥር የኦፊር ወርቅ ነጋዴዎች ከመሆናቸውም በላይ ተጽእኖ አሳዳሪዎች በመሆናቸው፣
  9. የኢትዮጵ ዝርያዎች 12 ጠበብት ነገሥታት ሆነው እሴራኤሎቹ የሚጠብቁት መሲህ መወለዱን ሳያውቁ የእኛዎቹ ክሩቅ ሆነው የመሲሁን መወለድ ተረድተው፣ ከኢትዮጵያ ተነስተው በኮከብ እየተመሩ ቤተልሄም ደርሰው ለመሲሁ ለእየሱስ ክርስቶስ ገዳ በማቅረባቸው፣
  10. በዐለም ላይ ከአሉት ነገሮች ሁሉ በጣም ውድ እና ብርቅ የሆነው የታቦቱ ማረፊያ እና መኖርያ አድርጎ እግዚአብሄር ከእስራኤል ይልቅ ኢትዮጵያን በመምረጡ፣
  11. ኢትዮጵያ በዳዊት መዝሙርና በሌሎችም መጽሃፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ በእግዚአብሄር በመጠራትዋ፣
  12. ከእግዚአብሄር በታች ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን በእግራችው ስለማቆማቸው፣ ከነብዩ ከሙሴ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ አይሁዳውያንን ወደ ግዛትዋ እያስገባች ጥገኝነት፣ መሬት እና ንግሥና ሳይቀር እየሰጠቸ አስተናግዳለች። በሌላ ሃገራት ግን እስራኤላውያንን ያሳድድዋቸው፣ እንዲሁም ይገድሏቸው ነበር። በእኛ በጎ አድራጊነት እንኮራለን። ክዚህ በተጨማሪ፣ እሴራኤላውያን በባርነት በባቢሎን 70 ዐመት ሲሰቃዩ ቆይተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተመቅደሳቸውን ካደሱ በሁዋላ መጻህፍት አጡ። መጽሃፍ ቅዱስን እና ሌሎች ብርቅዬ መጻህፍትን ኢትዮጵያ ስለላክችላቸው እንታበያልን።
  13. ትልቅ ለሚባለው ለሙሴ ጥገኝነት እና ሚስት ኢትዮጵያ ሰጥታ የፍትህን እና የሕግ አስተዳደርን እንዲሁም ነገረመለኮትን ስለአስተማረችው፣
  14. ከባለፉት 3800 ዐመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ በርካታ የሴት ነገሥታትን በኢትዮጵያ እና በግዛቶቿ ላይ ሾማ የሴቶችን መብት በማስከበር በዐለም ግንባር ቀደም በመሆኗ፣
  15. ኢትዮጵያ ክጣና ሃይቅ ተነስታ ወደ ኑብያ እና ገብጽ ወርዳ የግብጽን እና ኑብያን ስልጣኔ በመፍጠርዋ፣ ሕልቆመሳፍርት ወንዶች ፈርኦኖችን እና ህንድኬ በሚል ማእረግ 19 የሴት ነገሥታትን ብግብጽ፣ ብሊብያ እና ኑብያ ላይ በመሾሟ፣
  16. አጼ አክሱማይ የዐለም አባት፣ የነገሥታት አራስ ተብሎ ከባቢሎን ሳይቀር በንጉሦች የተበደሉ ዜጎቹ ለአቤቱታ ወደ እሱ ሲመጡ እምባቸውን ስለአበሰላቸው፣
  17. እየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ በኢትዮጵያ ግዛት በግብጽ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት አግኝተው በመኖራቸው፣
  18. እየሱስ ራሱን ለዐይሁዳውያን ሳይገልጽ በ22 ዕድሜው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለኛ ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን ለኛ ገልጾ እስከ 25 ዕድሜው ድረስ ሲያስተምርና ሲፈውስ ሃገራችን ውስጥ በመኖሩ፣
  19. እየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ሲል ግብጽ ሳለ ጥገኝነት የሰጠውን ንጉሥ አማናቱ ተትናይን እግረመንገዱን ጎብኝቶ ለአንድ ሳምንት እሱ እልፍኝ ውስጥ ሰንብቶ ነበር። እየሱስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንደተሻገረ አልፍኙን ንጉሥ አማናቱ ተትናይ ቤተክርስትያን አደረገው:። እየሱስ ክርስቶስ በህይወቱ እየአለ እኛ በዐለም የመጀመሪየውን  ቤተክርስቲያን በመመስረታችን፣
  20. የንግሥት ሕንደኬ ዣን በጅሮንድ በቅዱስ ፊሊፖስ መጠመቁና እሱ ከአውሮፓውያን ክርስትያንነት ቀድሞ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባቱ፣
  21. አውሮፓውያን ወደ ክርስትና የተሽጋገሩት ክ አረማዊነት ሲሆን ኢትዮጵያውያን ግን ክኦሪት ሃይማኖት ነው። ይህ በመሆኑም የክርስትና እውቀታችንን ከአውሮፓውያን ለማጥለቅና ለማበልጸግ አስችሎናል። በእዚህም እንኮራለን።
  22. እየሱስ ክርስቶስ፣ ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው የኖርኩ ዘመዶቼ ናችው፣ በእኔ ያምናሉ፣ እናንተ እነሱን ለማሳመን ሳትደክሙ አጥምቃችሁ አቁርቡአቸው፣ ብሎ ደቀመዛሙርቱን በርጠለሚዎስን፣ ማቴዎስን፣ ቶማስን ናትናኤልን፣ እንድርያስን እና ማርቆስን ወደ ኢትዮጵያ ልኳቸው፣ ክሃዋርያቱ ግማሾቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለአስተማሩ በእግዚአብሄር እንደተከበርን ስለሚሰማን፣
  23. ኢትዮጵያውያን ክርስትያናት እና አይሁዳውያን ያለደም መፋሰስ ተስማምተው የኦሪትን እና የክርስትናን አምልኮ ስርዐቶች የሚተዉትን ትተው የተረፉትን ወደ ክርስትና በማሸጋገራቸው፣
  24. ክኢትዮጵ እስክ አጼ እስያኤል ድረስ የኢትዮጵያ ነገሥታት ክእግዚአብሄር ጋራ በቀጥታ የሚነጋገሩ ሊቀካህናት መሆናቸውና በፈሪሃ እግዚአብሄር ህዝባቸውን በፍትህ እና ርትህ በማስተዳደራቸው እና ይህ ክስተት በዐለም ላይ የሌለ በመሆኑ፣
  25. ነብዩ መሃመድ በችግር ላይ ሳለ ዘመዶቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ኢትዮጵያ ጥገኝነት ስለሰጠቻቸው፣ መሃመድ ራሱ ሙስሊም ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ በመካና በመዲና ውስጥ የራስዋ ቤተክርስትያን ስለነበራት እና እሱ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ተጠቃሚና የሊቀካህናቱ ወዳጅ በመሆኑ፣ እንዲሁም በመጀመሪያ አላሁ አክበር ብሎ የጮኸው ድምጸ-መረዋው ኢትዮጵያዊው ቢላል ሃበሽ በመሆኑ፣ ነብዩም ካልነኳችሁ ኢትዮጵያውያን ላይ ጂሃድ አታኪያሂዱ በማለቱ፣
  26. በዐለም ላይ በሌለ አኳኋን ኢትዮጵያ ውስጥ  ሙስሊሞችና ክርስትያኖች በሃይማኖት ልዩነቶች ካለመጋጨታቸውም በላይ ተፋቅረውና ተባብረው ቤተክርስትያኖች እና መስጊዶች አንዱ ለሌላው በመገንባታቸው፣ አብረው በመጸለያቸው እና ከተዋደዱ ያለብዙ ችግር መጋባት በመቻላቸው፣
  27. ቀዳማዊ አባቶቻችን በዐለም ላይ የሌሉ ብርቅዬ የሱባ እና የሳባ ፊደላትን ፈጥረው ስለአቆዩልን፣
  28. እንደ አክሱም እና ላሊበላ ዐይነት ያልተለመዱ ቤተክርስትያናት መኖራቸው፣ ክነሱ የተገኘው ቅዱስ ያሬድ ልዩ ማህሌትን በመድረሱ እና ክአውሮፓውያን 700 ዐመታት አስቀድሞ የዜማ ምልክቶችን በመፈልፈሰፉ፣ እንዲሁም  የማንንም የማይመስል ቅዳሴ እና ስርዐተ ዐምልኮ ስለአለን፣
  29. በቀለማችን እና በተክለሰውነታችን የተቅለመለምን አበቦች ከመሆናችንም በላይ የተለያዩ አልባሳት፣ ዳንኪራዎች እና ባህላዊ እሴቶች ስለአሉን፣
  30. ከተለያዩ የምግብ አሠራር ሙያዎች በተጨማሪ ለዐለም ምግቦች የእበርክትናቸው እንደ ቡና አና ጤፍ የመሳስሉ አዝእርት ስለአሉን፣
  31. ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 4000 ዐመታት ጠላቶችዋን ሮማውያንን፣ ገብጾችን፣ አረቦችን እና ሌሎችንም በጦርነቶች ድባቅ እየመታች ነጻነታችንን እና ክብራችንን በማስጠበቋ እና ለዐለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት እና የድል አድራጊነት ዐርማ እና ተምሳሊት በመሆንዋ እንኮራለን። አባቶቻችን በኮሪያ ዘምተው፣ በተሰማሩበት የጦር ሜዳ ሁሉ ድል-አድራጊዎች ክመሆናቸውም በላይ አንዳቸውም ባለመማረካቸውና ጠላት እሬሳችውን አንኳን ለመያዝ ባለማቻሉ ደጋግመን እንኮራለን።
  32. ቀጥሎም፣ ደረታችንን የሚያስነፋን በእየሱስ ክርስቶስ የደም ስር ውስጥ የእኛ የኢትዮጵያውያን ደም መፍሰሱ ነው። እንዴት ቢሉ፣ እየሱስ ክርስቶስ የቅዱስ ዳዊት ዘር በመሆኑ እና የእሱም እናት አይሁዳውያን አዶልያ ወይም አዴል የሚሏት፣ እኛ ደግሞ ሀብሌ የምንላት የኢትዮጵ የቀጥታ ተወላጅ ኢትዮጵያዊት በመሆኗ።
  33. በመጨረሻም በቀዳማዊ ወላጆቻችን ክህነታዊ ማእረግ እና ክብር እንኮራለን። እግዚአብሄር ሁለት ዐይነት የክህነት ማእረግ ሰጥቶአል። አንደኛው ዝቅተኛው እና ለዐይሁዳውያን ብቻ የሰጠው የአሮን ክህነት ሲሆን ሁለተኛው እጅግ ከፍተኛው ለኢትዮጵ አባት ለሳሌሙ ንጉሥ ለመልከጸዲቅ ያቀደው ነው። የአሮን ሹመት ካህንነት ብቻ ሲሆን የመልከጽዲቅ ግን የንጉሥ ንጉሥነት እና የካህን ካህንነት ነው። መለኮታዊ እና ዐለማዊ ማእረግ ነው። ራዕየ ዮሃንስ አንድሚተነብይልን የዐለሙ ፈጣሪ እየሱስ ከርስቶስ ወደፊት በመልከጸዲቅ ስርዐት የካህን ካህን፣ የንጉሥ ንጉሥ ሆኖ በእየሩሳሌም ላይ የራሱን ምድራዊ መንግሥት መስርቶ ይነግሣል። በዛም ጊዜ አባታችን ሆይ መንግሥትህ ይምጣ፣ ብለን የጸለይነው ይፈጸማል። የእየሱስ ክርስቶስ ክህነትና ንግሥና በአባቶቻችን በመልክጸዲቅ፣ በኢትዮጵ እና በልጆቹ ስርአት ስለሆነ እጅግ እንኮራለን።

የሚያኮሩንን ሁሉ ነገሮች በእርግጥ ዘርዝረን አንጨርሳቸውም። ክብዙ በጥቂቱ አላይ የሰፈሩት ናቸው። አነሱን መስፈንጠሪያ ኢድርገን፣ ደረታችንን ነፍተን በኢትዮጵያዊነታችን ታብየን፣ እርስ በርሳችን ተከባብረን፣ ተፋቅረን እና ተቃቅፈን  በእኩልነት ወደፊት እመር! እንላለን። እንግዲህ ጥንታዊ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ትልቅ ከነበሩ እኛም የእነሱን አርአያ እና ፈለግ ተከትለን በመነሳሳት ወደፊት ትልቅ የማንሆንበት ምክንያት የለም።

መላው አፍሪካ ድሮ ኢትዮጵያ ይባል እንደነበር የሚመስክሬ ጥንታዊ ካርታ እታች ሰፍሮአል። ያኔ አፍሪካ የታችውና የላይኛው አፍሪካ ተብሎ ነበር የተከፈለው ። ዝቅ ብለው አሱን ከማየት አይዘናጉ።

በሚቀጥለው ገፅ የአለው ካርታ ደግሞ ከምአራብ አፍሪካ ብብት በታች ያለው ውሃ ሁሉ የእትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል አንደ ነበር ያሳብቃል። ዛሬ የህንድ ውቅያኖስ የሚባለውም ጥንት የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ይባል እንድነበር የሚያሳይ ካርታም ዐይቻለሁ።

ከ ምእራብ አፍሪካ ብብት ስር በእንግሊዝኛ የኢትዮፕጵያ ውቅያኖስ የሚለውን ፅሁፍ ያስተውሉ።

 
Share
Tweet
Pin
Email
Share
Sponsored by Revcontent

The Scary Truth Behind This German WW2 Photo – This Will Leave You Speechless
Natural Health Response

x

Doctors Are Stunned by This Strange Link Between Diabetes and Eggs (Try This)
Life Advice Daily

x

Chumlee’s Yacht Makes The Titanic Look Like A Raft
Weight Loss Groove

x

20 Photos of Ivanka Trump That’ll Make You Cringe
MedicareGranny

x

Alzheimer’s Discovery That is Leaving Doctors Speechless (Watch)
Medical Health Advice

x

Ottawa Casino Expert Analyzes 5 Unbelievably Common Mistakes: Read to Win Big
The Tribune

x

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Shares
Share
Tweet
Pin
Email
Share

close