Wednesday, 15 November 2017

በይርጋ አበበ

ያለፉትን 26 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በደንብ ላጤነ ሰው የሚያገኘው እውነታ መልኩ ጉራማይሌ አካሄዱ የሰካራም እርምጃ የሚሉት አይነት ነው። በተለይ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉት ኃይሎች አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተራመዱ ሲባል ሁለት እርምጃ ወደኋላ እየተመለሱ፤ ሄዱ ሲባል ሲመለሱ፣ ቆሙ ሲባል እየወደቁ እዚህ ደርሰዋል። ህዝቡም ከገዥው ፓርቲ ውጭ ያሉ አማራጭ ሃሳቦችን ለማግኘት የተቃዋሚዎችን ጓሮ ሲመለከት የአንዳንዶቹ በራሳቸው በፓርቲዎቹ አባላትና አመራሮች እሾህና አሜኬላ ተዘርቶበት በቅሎ ጓሮውን ወሮታል። የተወሰኑት ደግሞ ከፓርቲው ውጭ በሆኑ ኃይላት (እንደ ፓርቲዎቹ እምነት የመንግሥት ሥውር እጆች) በዘሯቸው አራሙቻዎች ተውጠዋል። በዚህ የተነሳም የተቃውሞውን ጎራ የፖለቲካ አካሄድ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ ሊቀበለው አልቻለም። በመሆኑም ተደጋግሞ እንደተባለው “ወይ ተባበሩ አለዚያ ተሰባበሩ” ሲል አቋሙን በግልፅ ሲያሰማ ቆይቷል።

ወዲህ ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “እንዳለመታደል ሆኖ ጠንካራ ተቃዋሚ የለንም” ብለው መናገራቸው ይታወሳል። የፖለቲካ ልሂቃኑ ግን “ኢህአዴግም ሆነ አቶ መለስ ሞጋች ሃሳቦችን ተቀብሎ ማስተናገድ አይችሉም። ለዚህ ደግሞ አመላካቹ በ1997 ከቅንጅትና ከኅብረት የገጠማቸውን ፈተና መቋቋም ሲሳናቸው ታይተዋል” ሲሉ የአቶ መለስን ሃሳብ ውድቅ ሲያደርጉት ተስተውሏል። የዚህ ሃሳብ አራማጆች አስተያየታቸውን ሲያጠናክሩም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2002 እና 2007 የተካሄዱ ሁለት አገር አቀፍ ምርጫዎችን ጠራርጎ ማሸነፉን ያስታወሱና በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል ለተነሳው ግጭት አንዱ እና ዋናው ምክንያት የሁለቱ ምርጫዎች ውጤት ነው ሲሉ ይናገራሉ። የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ተሾመ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ይህን ሃሳብ ከሚያራምዱ ፖለቲከኞች መካከል ይመደባሉ።

አቶ ሙላቱም ሆነ አቶ የሽዋስ ገዥውን ፓርቲ በሚተች ንግግራቸው “ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል” ይላሉ። ከ2001 እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ የነበረው አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በአንድ ጀምበር ክፍልፍሉ ወጥቶ የቀድሞ አመራሮቹ ፓርቲውን ለቀው ወጡ። በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት የዳኘው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የባለቤትነት ተገቢነቱን በእነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በመተካቱ እነ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፍራውን፣ እነ አቶ ተክሌ በቀለን ጨምሮ ከ250 በላይ የፓርቲው አመራሮች (ከወረዳ እስከ ፌዴራል ባሉ መዋቅሮች) ፓርቲውን ለቀው ወጡ። እነዚያ አመራሮች ሰሞኑን ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በአባልነት ታቅፈው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መሳተፍ እንደሚፈልጉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ይህን ተከትሎም የሰሞኑ አብይ የፖለቲካ ዜና ለመሆን በቅተዋል።

የቀድሞ የአንድነት አመራሮች በሰማያዊ ፓርቲ አባልነት ታቅፈው ለመታገል ምን አነሳሳቸው? የሰማያዊ ፓርቲ ምላሽስ ምን ይመስላል? እንዲሁም ቀጣይ የፓርቲው ጉዞስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ሃሳቦች እያነሳን ከዚህ በታች እንመለከታቸዋለን።

ጉዞ ወደ ዳግም ፓርቲ ምሥረታ እና የከሸፈ ጥረት

በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፓርላማ መግባት የቻሉት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ከቀድሞ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት የሥልክ ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር። አቶ ግርማ ስለ አዲሱ ፓርቲ ምሥረታ ጅማሮ ከተናገሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ይመሠረታል የተባለው ፓርቲ ቀርቶ አመራሮቹ (ከወረዳ እሥከ ፌዴራል ያለው የቀድሞ አንድነት አመራር) ከሌላ ፓርቲ ጋር በአባልነት ታቅፈው መታገልን እንደ አማራጭነት ወሰዱ።

ይህ ለምን ሆነ? ብለን የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የቀድሞውን ተጠባባቂ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለን ጠይቀናቸው ነበር። አቶ ተክሌ ሲመልሱም፤ “አንድነት ፓርቲ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰፊ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ይታወቃል። ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ካዳከመው በኋላ እንደገና በሌላ ፓርቲ ተመልሰን በመንቀሳቀስ ከአራት ክልሎች ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጋ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ችለን ነበር። የተለያዩ አክቲቪስቶችንም በፓርቲው ምሥረታ ሂደት እንዲቀላቀሉን ጥያቄ አቅርበንላቸው ተወያይተናል። ነገር ግን የአብዛኛው ሰው አስተያየት አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ይልቅ ያሉትን አጠናክሮ መሄድና የተለመደውን አሰራር ትቶ እውነተኛ ፓርቲዎችንና በርዕዮተ ዓለም የሚመሳሰለንን መቀላቀል ይሻላል የሚል ስምምነት ተደረሰ። በዚህ ምክንያት አዲስ ፓርቲ የመመስረት እቅዳችንን ትተን ወደዚህ ሃሳብ ልንመጣ ችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞዎቹ የአንድነት አመራሮች አዲስ ፓርቲ ለመመስረት የአምስት ክልል ድጋፍ የግድ ያስፈልጋቸው ነበር። ከአራት ክልል ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጋ ድጋፍ ያገኙት እነ አቶ ተክሌ የአምስተኛውን ክልል ድጋፍ ለማግኘት ዝግጅት አድርገው ነበር። ፊርማም ማሰባሰብ ጀምረው እንደነበር ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ሆኖም ይላሉ አቶ ተክሌ፤ “ሆኖም በአገር ውስጥና ውጭ አገር ባለን መዋቅር ባደረግናቸው ውይይቶች የተሳታፊዎች፣ የምሁራንና የደጋፊዎቻችን ፍላጎት አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ይልቅ ያሉትን ማጠናከር እንደሚሻል ስለነገሩን የአዲሱን ፓርቲ ምሥረታ ወደጎን ልንለው ችለናል” ብለዋል።

51 የቀድሞው አንድነት አመራሮችም ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ለመግባት ውሳኔ ላይ የደረሱት በዚህ መልኩ ነው ማለት ነው።

ሰማያዊን ለመቀላቀል የተደረገ ቅድመ ዝግጅት

አቶ ተክሌ በቀለ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የቀድሞዎቹ አመራሮች ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሁለት ዓመታትን የፈጀ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም ሌሎች አማራጭ ፓርቲዎችን ሳይቀር ተቀላቅሎ ለመሥራት ፍላጎትና ጥረት ተደርጎ ነበር። በተለይ ለዚህኛው አማራጭ ተቀዳሚ ምርጫ ሆኖ የቀረበው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ነበር። ሆኖም መድረክ አባል ፓርቲዎቹ ክልላዊ ስለሆኑ በዘውግ ፖለቲካ መሳተፍ አግባብ አለመሆኑን ተወያይተው ሃሳባቸውን ሊቀይሩ ችለዋል። ከዚህ ሌላ አማራጭ ሃሳብ ሆኖ የቀረበው መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ወይም ሰማያዊ ፓርቲ ጋር አብሮ መሥራት የሚለው ሆነ። የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው ይህን ውሳኔ የሰማያዊ ፓርቲ ፍላጎትም እንደነበረ ተናግረዋል። አቶ አበበ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “አቶ የሽዋስ የፓርቲውን አመራር ቦታ ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው አንደ እነሱ ያሉ (የአንድነት የቀድሞ አመራሮችን) የፖለቲካ እውቀትና የትግል ልምድ ያላቸው ፓርቲውን ተቀላቅሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ስለሚሰፋበት መንገድ መምከር ነበር። በመሆኑም በግልና በተናጠል ከማነጋገር ጀምሮ ‘ለቀድሞ የአንድነት አመራሮች’ በሚል የደብዳቤ መጥሪያ አዘጋጅተን እስከመጥራት ደርሰን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ተክሌ በቀለ ደግሞ፤ “እኛ በተናጠልም ሆነ በቡድን ሰፊ ውይይት አድርገናል። ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የእኛ አመራር አባላት በራሳቸው ወጭ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ተወያይተናል፤ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ውሳኔ የገባነው” በማለት ሰፊ ጊዜ ወስደው እንደተወያዩ ተናግረዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ቀጣይ ጉዞ

በአቶ ይልቃል ጌትነት ይመራ የበረው የሰማያዊ ፓርቲ ካቢኔ በፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ከተሰናበተ በኋላ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መርጦ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት አልፎታል። የአቶ የሽዋስ አሰፋ ካቢኔ ወደ ሥራ መግባቱን ባሳወቀበት የመጀመሪያ ሳምንት ሊቀመንበሩ አቶ የሽዋስ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደው ነበር። በወቅቱ በሰጡት ቃለምልልስም “ሰማያዊ ፓርቲ በቀጣዮቹ የትግል ጉዞዎች የሚያካሂደው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እስከ ውህደት ተጉዞ ጠንካራ የአማራጭ ኃይል ሆኖ መቅረብ ነው” ብለው ነበር። በዚህ መሠረትም በወጣቶች የተዋቀረው ሰማያዊ ፓርቲ እና በልምድም በዕድሜም ከገፉት የመኢአድ መሪዎች ጋር በመነጋገር ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች ተስማምተው አብረው መሥራት ከጀመሩ አንድ ዓመት ሊሆናቸው ነው ። የሁለቱ ፓርቲዎች አብሮ የመሥራት ሂደት በተግባር የታየበትን አብይ ተግባርም እያከናወኑ ነው። የሰማያዊ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በሰሜን አሜሪካ ጉዞ አድርገው ከደጋፊዎቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል። በዚህ ጉዟቸው ከሁለቱ ፓርቲ ደጋፊዎችና የፖለቲካ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ምሁራን መቼ ነው ተጠናክራችሁ የምትቀርቡት? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

አቶ የሽዋስም ሆኑ ዶ/ር በዛብህ ሲመልሱ “መኢአድና ሰማያዊ ለውህደት የሚያደርጉት ጉዞ እየተጠና ነው” ብለው ነበር። ይህን አባባል የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉም ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል።

ሆኖም የቀድሞ አንድነት አመራሮች ወደ ሰማያዊ ሲመጡ በመኢአድ በኩል ምን አይነት ስሜት አሳደረ? ውህደቱን በተመለከተስ ምን አንድምታ አለው? ብለን ለአቶ አበበ እና አቶ ተክሌ ጠይቀናቸዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች ሲመልሱም “መኢአድና አንድነት ለመዋሃድ ሙከራ አድርገው ያልተሳካው በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት ነው። አሁን ደግሞ ያ አጋጣሚ ሲፈጠር መኢአድ በደስታ የተቀበለው ጉዳይ ነው። እኛም (ሰማያዊ ፓርቲም ሆነ ወደ ሰማያዊ የገቡት የቀድሞ አንድነት አመራሮች) አጥብቀን የምንፈልገው ነበር” ብለዋል። ሁለቱ አመራሮች አክለውም፤ መኢአድና ሰማያዊ ወደ ውህደት ሄደው የሚፈጠረው ፓርቲ ጠንካራ ሆኖ ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት ይኖረውና ገዥውን ፓርቲ መገዳደር የሚችል እንደሚሆን እምነታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃዋሚው ጎራ ከሚታማባቸው ዘርፈ ብዙ ድክመቶቻቸው አንዱ የሥልጣን ጥመኝነት ነው። በተለይ አንዳንዶቹማ መሪዎቻቸው ለረጅም ጊዜ በመሪነት ስለቆዩ ፓርቲውን ከግለሰቦቹ ለይቶ ማየት እስከሚቸግር ድረስ ተዋህደዋል። የአንድነት የቀድሞ አመራሮች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ሲገቡ የሥልጣን ጉዳይ እንዴት ይታያል? ስንል መጠየቃችን አልቀረም። አቶ ተክሌ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ “እኛ ወደ ሰማያዊ የገባነው ‘በተራ አባልነት’ ፓርቲውን ለማገልገል እንጂ ወደ አመራርነት ካልመጣን ብለን አይደለም” ሲሉ ሥልጣን ሳይሆን ሥራን እንዳስቀደሙ ተናግረዋል።

አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው “የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አመራርነት ቦታ የሚሰጠው በእውቀትና በችሎታ በ(Merit) ነው። በመሆኑም የተሻለ ሰው ከመጣ ወደ አመራርነት አሳድጎ እንዲሰራ ለማድረግ የማይቸገር ሥራ አስፈፃሚ ነው ያለን። በመሆኑም ከቀድሞ የአንድነት አመራሮች መካከልም ወደ ሥራ አስፈፃሚነት ሊመጡ የሚችሉ ይኖራሉ” ብለዋል።

ሰማያዊ ፓርቲ እና የቀድሞ አንድነት አመራሮች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተከትሎ አብሮነታቸው የውሃ እና ዘይት ጥምረት ወይስ የሥጋና የደም? የሚለውን ለማየት ጊዜው ገና ቢሆንም ሂደቱ እና እቅዱ ምን መልክ እንዳለው ጠይቀናቸው ነበር።

የአቶ አበበ አካሉም ሆነ የአቶ ተክሌ በቀለ ምላሽ፤ በአመራሮቹ መካከል ሰፊ እና ጥንቃቄ የታከለበት ውይይት መካሄዱን፣ በእውቀትና በአገራዊ ስሜት የተሞላ ኃላፊነትን ለመወጣት ቁርጠኝነት ያለበትና የሕዝብ አደራ ሳይቀር የተቀበሉበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ከዚህ በመነሳትም ጠንካራ አንድነት በመፍጠር የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋት ለሕዝብ ጥያቄ ጥሩ አማራጭ ሆነን እንቀርባለን ብለዋል።

ስንደቅ