ሙጋቤ እና ግሬስ ሙጋቤ
Reuters

የሰሞኑ የዚምባብዌ ፖለቲካዊ ቀውስ የጀመረው ሮበርት ሙጋቤ በባለቤታቸው ግፊት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋ ‘ታማኝ አይደሉም’ ብለው ከሥስልጣን ካባረሯቸው በኋላ ነበር።

የኤመርሰን ምናንጋግዋን መባረር ይፋ ያደረጉት የኢንፎርሜንሽን ሚኒስትሩ ሳይመን ካሃያ ሞዮ ምናንጋግዋ ”ታማኝ” አይደሉም ሲሉም ተደምጠዋል።

ባላቸው ብልህ አስተሳሰብ “አዞው” በሚል ስም የሚታወቁት ምናንጋግዋ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ “ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ አንተና ሚስትህ እንደፈለጋችሁ የምታደርጉት የግል ንብረታችሁ አይደለም” ሲሉ ሙጋቤን ተችተውም ነበር።

የቀድሞው የደህንነት ሹም የነበሩት ምናንጋግዋ ፕሬዝዳንት ሙጋቤን የመተካት ተስፋ የተጣለባቸው መሪ ነበሩ።

ምናንጋግዋ ከሥልጣን በመነሳታቸው የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት የሆኑት ግሬስ ሙጋቤ ባለቤታቸውን በመተካት ቀጣይ የዚምባብዌ መሪ እንደሚሆኑ በበርካቶች ዘንድ ተገምቶም ነበር።

ከዚህ በፊት ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከስልጣናቸው እንዲያነሱ ሮበርት ሙጋቤን በተደጋጋሚ ይወተውቱ እንደነበርም ይነገራል።

• ሙጋቤ ታማኝ አይደሉም ያሏቸውን ምክትላቸውን ከስልጣን አነሱ

ግሬስ ሙጋቤ እና ኤመርሰን ምናንጋግዋ
AFP
አጭር የምስል መግለጫ ግሬስ ሙጋቤ (ግራ) እና ኤመርሰን ምናንጋግዋ (ቀኝ)

ከቀናት በፊት ግሬስ ሙጋቤ በሃራሬ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ”እባቡ በሃይል ጭንቅላቱን መመታት አለበት። በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል እና አለመግባባትን የሚፈጥሩትን ማስወገድ አለብን። ወደ ቀጣዩ የፓርቲያችን ስብሰባ በአንድ መንፈስ ነው መሄድ ያለበን” ሲሉ በምናንጋግዋ ላይ ሲዝቱ ተሰሙ።

ግሬስ ሙጋቤ ይህን ባሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለህይወቴ ሰግቻለው ብለው ሃገር ጥለው ሸሹ።

የጦሩ ማስጠንቀቂያ

ሙጋቤ ምክትላቸውን ካባረሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር የሀገሪቱ ጦር በፓርቲው ውስጥ እየተደረገ ባለው ጉዳይ ጣልቃ ልገባ እችላለሁ ሲል ማስጠንቀቂያ የሰጠው።

ከ90 የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ነበር የዚምባብዌ ጦር ኃይል ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ገዢውን ፓርቲ ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ጦሩ ጣልቃ እንደሚገባ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያስጠነቀቁት።

• የዚምባብዌ ጦር “ጣልቃ እንደሚገባ” አስጠነቀቀ

የዚምባብዌ ጦር ኃላፊ ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ
AFP
አጭር የምስል መግለጫ የዚምባብዌ ጦር ኃላፊ ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ

ያልተጠበቀው መግለጫ

ምናልባትም ዕለተ ዕረቡ ለዚምባብዌያዊያን ታሪካዊ ቀን ነበረች ማለት ይቻላል። የሃገሪቱ ዜጎች ዕረቡ ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረባቸውን ያልተጠበቀ የቴሌዢን መግለጫ የተመለከቱት። ግመሹ በተፈጠረው ነገር ድንጋጤ ውስጥ ሲገቡ በደስታ የቦረቁም አልጠፉም ነበር።

• ጦሩ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያውን ከተቆጣጠረ በኋላ ”መፈንቅለ መንግሥት አይደለም” ሲል አስታውቋል

የዚምባብዌ ጦር ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነውን ዜድ ቢ ሲን ተቆጠጠረ። ጦሩ በሰጠው መግለጫ “ይህ መፈንቅለ-መንግሥት አይደለም፤ በፕሬዝዳንት ሙጋቤ ዙሪያ የሚገኙ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ የመውሰድ ተልዕኮ እንጂ። ጦሩ የመንግሥትን ስልጣን ለመቆጣጠር አልተንቀሳቀሰም” ሲል በመግለጫው ጠቅሶ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ቤተሰቦቻቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አረጋገጠ።

እስካሁን የጦሩን እንቅስቃሴ ማን እየመራው እንደሆነ የታወቀ ነገር ባይኖርም ጦሩ በሚሰጠው ተደጋጋሚ መግለጫ እያደረገ ያለው ‘መፈንቅለ-መንግሥት’ እንዳልሆነና ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ ነገሮች ወደቀድሞው እንደሚመለሱ ማሳወቁን አላቋረጠም።

የዚምባብዌ ጦር አባላት በሃራሬ ጎዳና ላይ
አጭር የምስል መግለጫ የዚምባብዌ ጦር አባላት በሃራሬ ጎዳና ላይ

”መፈንቅለ-መንግሥት አይደለም”

ጄኔራል ሲቡሲሶ ሞዮ ጦሩን ወክለው በሰጡት መግለጫ “ማሳወቅ የምንፈልገው ጦሩ መንግሥት ገልብጦ ስልጣን አልያዘም” በማለት እየተካሄደ የለው መፈንቅለ-መንግሥት አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩም ተሰምተዋል።

ሰራዊቱ መፈንቅለ-መንግሥት የሚለውን ቃል ለምን ፈራው?

ጄኔራሉ መፈንቅለ-መንግሥት አይደለም ማለትንም ይመረጡ እንጂ የጦሩ እንቅስቃሴ መፈንቅለ-መንግሥት ይመስላል ስትል የቢቢሲዋ ሪፖርተር ከሃራሬ መዘገቧ አይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት የጦሩ እንቅስቃሴ መፈንቅለ-መንግሥት ይመስላል ሲል ተደምጧል።

የፖለቲካ ተንታኞች ጦሩ መፈንቅለ-መንግሥት የሚለውን ቀል መጠቀም ያልፈለገበት ምክንያት የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማሕበረሰብ (ሳድክ) መፈንቅለ-መንግሥት አካሂደው ስልጣን ለያዙ አካላት ዕውቅና ስለማይሰጡ ነው በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ከግራ ወደ ቀኝ ሮበርት ሙጋቤ፣ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፣ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተባረሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌጋAFP/Reuters/EPA
አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ወደ ቀኝ ሮበርት ሙጋቤ፣ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፣ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተባረሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌጋ

አራቱ ቁልፍ ግለሰቦች

በዚምባብዌ ፖለቲካዊ ቀውስ መስተዋል የጀመረው ሮበርት ሙጋቤ ምክትላቸው የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከስልጣን በማንሳት በምትካቸው ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤን ሊተኩ ካቀዱ በኋላ ነው።

የሃገሪቱ የጦር አዛዥ ጀነራል ኮስታንቲኖ ቺዌንጋ ባሳለፍነው ሰኞ በዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ካልቆመ ጦሩ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል አስጠንቅቀውም ነበር። በዚህ ሁላ ውጣ ውረድ ውስጥ የአራት ሰዎች ስም ተደጋግሞ ሲደመጥ ይሰማል። የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መሪ ተውንያውያን እንደሆኑም ይነገራል እኚህ አራት ሰዎች።

1. ሮበርት ሙጋቤ

ዚምባብዌ በአውሮፓውያኑ 1980 ነጻነቷን ከቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ከተቀዳጀች በኋላ በተደረገ ምርጫ ነበር አሸንፈው ወደ ስልጣን የመጡት።

ሙጋቤ በስልጣን ዘመናቸው ከከወኗቸው ተግባራት በ1990ዎቹ መባቻ ላይ ያከናወኑት ሁሌም ይወሳል። በወቅቱ ሙጋቤ በጥቂት ነጮች ተይዞ የነበረውን ሰፊ መሬት በመንጠቅ ለጥቁር ዚምባብዌውያን አከፋፈሉ።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆዩት የ93 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ሙጋቤ ስልጣን ለመልቀቅ ምንም አይነት ፍላጎት ባያሳዩም ጤናቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ የሚተካቸው ማነው የሚለው ጥያቄ በበርካቶች ዘንድ ነበር።

በተለይም ደግሞ በቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤና በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት በኤመርሰን ምናንጋግዋ መካከል ለፕሬዝደንትነት በሚደረገው ፍጥጫ ውጥረት ተፈጥሮ ቆይቷል።

2. ግሬስ ሙጋቤ

የሮበርት ሙጋቤ ሁለተኛ ሚስት የሆኑትና ከሙጋቤ በ40 ዓመት የሚያንሱት ግሬስ ሙጋቤ ከፕሬዝዳንቱ የቢሮ ፀሐፊነት በመነሳት በሃገራቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት ለመሆን በቅተዋል።

ወዳጅና ደጋፊዎቻቸው “የድሆች እናት” እያሉ የሚጠሯቸው ግሬስ በነቃፊዎቻቸው ዘንድ ደግሞ ለሥልጣንና ሃብት እንደሚስገበገቡ ተደርገው ሲሳሉ ይስተዋላል።

ግሬስ ሙጋቤ ከሥልጣን የተባረሩትን ምናንናግዋ “እባብ ስለሆነ ጭንቅላቱ በኃይል መመታት አለበት” ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም።

3. ኤመርሰን ምናንናግዋ

ግሬስ ሙጋቤ ብቅ ብቅ ከማለታቸው በፊት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሙጋቤ ‘ትክክለኛ’ ምትክ ተደርገው ነበር የሚቆጠሩት።

ከምክትል ፕሬዝደንትነታቸው ከተባረሩ በኋላ ለሕይወቴ ያሰጋኛል በማለት ሃገር ጥለው ሸሽተውም ነበር።

ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ግን ጦሩ ሃገሪቱ ከተቆጣጠረ በኋላ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ወደ ዚምባብዌ ተመልሰዋል።

በዚምባቡዌያን ዘንድ ‘አዞ’ እየተባሉ የሚጠሩት ኤመርሰን የደህንነት ሚኒስቴር ሆነው ከመሥራታቸው አንፃር የሃገሪቱን ጦር ኃይልና የደህንነት ኤጀንሲውን በደንብ እንደሚያውቁት ይነገራል።

4. ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ

የምናንጋግዋ ቅርብ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት የ61 ዓመቱ ጄኔራል ኮንስታንቲኖ የዚምባብዌን ጦር ኃይል ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ መርተዋል።

የዚምባብዌ ጦር ኃይል በፖለቲካ ኡደቱ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ በሰጡ በማግስቱ ነበር የዚምባብዌ ጦር ሃገሪቱን የተቆጣጠረው።


ከቁም እስር በኋላ

ሙጋቤ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ@ZimMediaReview
አጭር የምስል መግለጫ ሙጋቤ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ

የሃገሪቱ ጦር ከሶስት ቀናት በፊት ስልጣን ተቆጣጥሮ ሙጋቤን በቁም እስር ካቆየ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓርብ ከሰዓት ሙጋቤ በአደባባይ ታይተዋል።

በዚምባብዌ መዲና በሆነችው ሃራሬ በተማሪዎች የምረቃት ፕሮግራም ላይ ነበር ለህዝብ የታዩት።

ሬውተርስ የዓይን እማኝን ጠቅሶ እንደዘገበው ሙጋቤ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ካደረጉ በኋላ ከተመራቂዎች ሞቅ ያለ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ሙጋቤ በአደባባይ ታዩ

ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሙጋቤ በቀይ ምንጣፍ ላይ በዝግታ እየተራመዱ ወደ መድረኩ ሲወጡ ሞቅ ያለ ድጋፍ እና ጭብጨባ ሲደረግላቸው ነበር ሲል የቢቢሲው ሪፖርተር አንድሪው ሃርዲንግ ከሃራሬ ዘግቧል።

የሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤም ሆኑ የትምህርት ሚንስትሩ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ አልተገኙም።

ሙጋቤ በየዓመቱ በዚህ የምርቃት ፕሮግራም ላይ መገኘትን ልምድ ያደረጉ ቢሆንም በቁም እስር ላይ እንደመቆየታቸው በፕሮግራሙ ላይ ይገኛሉ ተብሎ አልተጠበቀም ነበር።

ስለ ዚምባብዌ እና ሙጋቤ ምን ተባለ?

የአፍሪካ ሕብረት ”ሕገ-መንግሥታዊ ላልሆኑ የመንግሥት ለውጦች የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማሕበረሰብ (ሳድክ) እውቅና አይሰጥም ሲሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ የተናገሩት ጦሩ ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ነበር።

የቀድሞው የዚምባብዌ የተቃዋሚ ፓርቲ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አሌክስ ማጋኢሳ ደግሞ ”ሙጋቤ እራሳቸው በፈጠሩት አውሬ ተበሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።

የደቡብ አፍሪካ መሪ ጃኮብ ዙማና የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ”ሰላም፣ መረጋጋት እና መከባበር” በዚምባብዌ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

ቻይና በበኩሏ”ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው” ስትል ሃሳቧን አሰምታለች።

የሙጋቤ ቀጣይ እጣ ፈንታ

ሙጋቤ ከጦሩ ጋር
The Herald

ዓርብ ጠዋት ዘሄራልድ የተሰኘው መንግሥታዊ ጋዜጣ ሙጋቤ ለቁም እስር ከዳረጓቸው የሀገሪቱ የጦር ኃላፊ ጋር ሲጨባበጡና ሲወያዩ የሚያሳይ ፎቶ ይዞ ወጥቷል።

የዚምባብዌ የረጅም ጊዜ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ዛሬም ከሥልጣናቸውን በፍጥነት እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልቀበልም ስለማለታቸው በሰፊው እየተዘገበ ቢሆንም ጦሩ በሰጠው መግለጫ ከሙጋቤ ጋር እያካሄደ ያለው ውይይት ውጤታማ እየሆነ አንደሆነ ገልጿል።

• ሙጋቤ ከሥልጣን አልወርድም እያሉ ነው

የረዥም ጊዜ የሙጋቤ ተቃዋሚ የሆኑት ሞርጋን ሻንጋራይ ሙጋቤ የህዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት አሁኑኑ ከሥልጣናቸው መውረድ አለባቸው ይላሉ።

የቢቢሲው ዘጋቢ አንድሪው ሃርዲንግ ከሙጋቤ ጋር ተደራድሮ የሽግግር መንግሥት ማካሄዱ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ይላል።

በሌላ በኩል የዛኑ-ፒ ኤፍ ፓርቲ መሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ታህሳስ እስከሚካሄድ ድረስ ሙጋቤ የመሪነት ስማቸውን ይዘው መቆየት እንደሚችሉና ያኔ ግን ምናንጋግዋ በይፋ የፓርቲውና የሀገሪቱ መሪ እንደሚሆኑ ገልጾ ነበር።

Source   –   BBC/AMHARIC