ዘመኑ ተናኘ

16 November 2017

የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝብ የወደፊት ግንኙነት በተመለከተ ከሁለቱ አገሮች የተወከሉ ምሁራን በአዲስ አበባ ውይይት አካሂደዋል፡፡
‹‹የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች›› በሚል መሪ ቃል ሐሙስ ኀዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል በተካሄደው ውይይት ላይ፣ ኤርትራን በመወከል ከአውሮፓ የመጡና በአዲስ አበባ የሚኖሩ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡ በውይይቱም የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የገቱ ጉዳዮች ተነስተው ተመክሮባቸዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች ምሁራን ውይይት ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ የመሩ ሲሆን፣ ‹‹የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ሊያሻክሩ የሚችሉ ጉዳዮች አሹለው እየመጡ ስለሆነ፣ ምሁራን በጋራ ተግባብተው ለመጪው ትውልድ አንድ የሆነን ሕዝብ ማስረከብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሚዲያ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የሁለቱን አገሮች ምሁራን የጋራ ውይይት ያዘጋጀው ‹‹ሰለብሪቲ ኢቨንትስ›› የተባለ ድርጅት ሲሆን፣ በቀጣይም የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች አንድነት የሚያጠናክሩ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ለማዘጋጀት መታቀዱ ታውቋል፡፡

Source   –     Ethiopian Reporter