በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ውስጥ እርስ በእርስ የመጠቃቃት ሁኔታ እንዳለ ተገለጸ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ የዝምድና አሰራር መኖሩንም ፓርቲው ራሱ ተናግሯል፡፡ ረዥም ጊዜ የፈጀ ስብሰባ እያካሔደ ያለው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በፓርቲው ውስጥ የተጠቀሱት አዝማሚያዎች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ህወሓት ለሁለት መከፈሉ ሲነገር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው ላይም ይህን ሀሳብ በሚያረጋግጥ መልኩ፣ በፓርቲው ውስጥ እርስ በእርስ የመጠቃቃት ሁኔታ መኖሩን ይፋ አድርጓል፡፡

ሌላው በማዕከላዊ ስብሰባው ላይ የተነሳው አጀንዳ የዝምድና አሰራር ሲሆን፣ ይህ መንፈስም በፓርቲው ውስጥ እንደሚንጸባረቅ ተገልጿል፡፡ ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወገኖች ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፣ በፓርቲው ውስጥ አንዱ አመራር ሌላኛ ዘመዱን ሲጠቅም እና ጉቦ ሲያበላ መኖሩ በተደጋጋሚ የተነገረ ሐቅ ነው፡፡ በተለይ የቀድሞ የህወሓት ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ስብሓት ነጋ፣ በፓርቲው ውስጥ ሰፊ የዝምድና ሰንሰለት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ እህታቸው፣ ባለቤታቸው፣ የባለቤታቸው ወንድምን ጨምሮ ሌሎች ዘመዶቻቸው በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሲሆን፣ ከኤፈርት ጋር በተገናኘም በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ መመዝበራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የህወሓት አመራሮች በስብሰባው ላይ መግባባት ስለተሳናቸው ስብሰባው ለአንድ ተጨማሪ ሳምንት የተራዘመ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት ለመቋጨት ዕድቅ መያዙም ታውቋል፡፡ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳለው ከሆነ፣ አሁን ያለውን የፓርቲ አመራር በቀጣይ በአዲስ መልክ ለማደራጀት እና ለውጥ ለማድረግ ዕድቅ ተይዟል፡፡ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል፣ የክፍፍሉ አንደኛው መሪ የሆነው የእነ ስብሰሓት ነጋ ቡድን፣ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱን ከህወሓት ሊቀ መንበርነት አንስቶ፣ በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የመተካት ፍላጎት እንዳለው መረጃዎችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ አዲስ የአመራር ቡድን አዋቅራለሁ ያለው፣ በእነ ስብሓት ነጋ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡

ትላንት በመቀሌ ሲካሔድ በነበረው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ሌላ አንድ የፓርቲው አባል ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውም ታውቋል፡፡ ፓርቲው በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ትርምስ ላይ ሲሆን፣ አመራሮቹም እርስ በእርስ መግባባት እንደተሳናቸው ከስብሰባው አዳራሽ የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ናቸው፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን ወደማጠናቀቁ ተቃርቧል ቢባልም፣ በአንዳንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ መግባባት እንዳልተቻለም ታውቋል፡፡

BBN News November 17 , 2017