የተከበሩ አቶ ዓባይ ወልዱ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት፣
ክቡራን ሚኒስትሮች፤
የተከበራችሁ የአማራና የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ልዩ ልዩ አመራሮች፣
የተከበራችሁ የሁለቱም ክልሎች የሃገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች
የተከበራችሁ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላችሁ የመድረኩ ተሳታፈዎች፣
ክቡራትና ክቡራን
===
ከሁሉ አስቀድሜ በዚህ በአማራና በትግራይ ብሔራዊ ክልሎች ሕዝቦችና የሃገር ሽማግሌዎች ሲካሄድ የቆየው የህዝብ ለህዝብ ምክክር ሁለተኛ መድረክ ላይ በመገኘት መልእክት ሳስተላልፍ የተሰማኝን ደስታ እየገለጽኩ የተከበራችሁ እንግዶቻችን እንኳን ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በሰላም መጣችሁ፡፡
=
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የአያሌ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ባለቤት፣ የበርካታ ማንነቶች ማእከልና የብዝሃነት መነሃሪያ የሆነች የመቻቻል አገር መሆኗን ከእኛ አልፎ ማንም የሚያውቀው ህዝቦች በዘመናት አብሮነት የገነቡት የጋራ እሴታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄር በሄረሰቦች እና ህዝቦች በተለያየ መልኩ የሚገለፁ ልዩነቶች ያላቸው ቢሆንም ከጥንት እሰከ ዛሬ በአጥንትና በደማቸው የገነቡት ኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ ሆኖ በአንድነት አስተሳስሯቸው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ቀደምት አባቶቻችን እነዚህ ብዙ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ከሁሉም በላይ የጋራ ማንነታቸው በሆነው ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ተሳስረው በአንድነት የታፈረችና የተከበረች አገር አቆይተውናል፡፡
=
እኛ ኢትዮጵያውያን ዓለም በምርምር ምጥቀቱ በደረሰበት እወቀት የሰው ዘር መገኛ ምድር ማእከላዊ ህዝቦች መሆናችን፣ ከአንድ ምንጭ ከእነሉሲ መንደር ፈልቀን ወደ ሰሜንና ደቡብ፣ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሎም በዓለም ዳርቻዎች እንደ ተስፋፋን የአርኪዮሎጂ ምርምር ባለቤቶቹ አረጋግጠው ለዓለም በምስራችነት ያበሰሩት በመሆኑ መቼም እና በምንም ሁኔታ የማንለያይ አንድ ህዝብ ስለመሆናችን መሠረታዊ ማሳያ ነው፡፡ ይህንን የእውነት መነሻ ይዘን በተረዳነው ልክ ጥቂት ለማብራራት እንንደርደር ብንል በጥንተ ስልጣኔ ገናና የነበረችው አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ እዚህ በተሰባሰብነው የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ማንነት ዙሪያ ያጠነጠነና ተስቦ ፣ ተስቦ የማያልቅ ረዥም የትስስርና የአብሮነት ቱባ ታሪክ ልንመዝ እንችላላን ፡፡ ይህ እጅግ የረዘመና በአንድ የተገመደ የማንነት ጥንድ ድርብ ገመድ በአብረቅራቂ የስልጣኔ ዘመን ፈክቶ የታየ፣በሌላውም ጊዜ በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ውስጥ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቆ በወጣው ፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ጀብድ ከመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በአንድነት ፈክቶና ጎምርቶ የወጣ የአርበኝነት ታሪክ ባለቤት ነን፤
የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች የሚያኮራ የግንኙነት ታሪክ ስናወሳ የጥንቱን ብቻ አይደለም በቅርብ ጊዜ በተካሄደው የሰላምና የዲሞክራሲ የትግል ሂደትም እነዚህ በጋራ ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት በአንድ ላይ ቁመው አኩሪ መስዋእትነት ከፍለው ጨቋኙን መንግስት ገርስሰው ከመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በአንድነት አዲስ ስርአት መስርተዋል፡፡ የእነዚህ ህዝቦች ማንነት ሲጀመርም በብዙ መልኩ የተቆራኘ ነው ፡፡ የአማራና ትግራይ ህዝቦች በመልካም ጉርብትና ለዘመናት አብረው ከመኖራቸው ባሻገር በእምነት፤በባህል፤ በአኗኗራቸውና በአይነተ ብዙ የጋራ እሴቶቻቸው ተሳስረው የጋራ ታሪክ የገነቡ ህዝቦች ናቸው፡፡
=
በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከላይ ከላዩ ብቻ በጨረፍታ ማስቃኘት ቢፈቀድልኝ ደግሞ የአማራ ህዝብ በስራ ወዳድነቱ ተማምኖ ጥሮ ግሮ በላቡ ውጤት የሚኖር፤ የራሱን ማንነት ጠብቆ በስርአት አክባሪት ከሌሎች ህዝቦች ጋር በአብሮነት ተሳስሮና ተከባብሮ የመኖር ባህላዊ እሴትን በረጅሙ የታሪክ ጉዞው የገነባ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ሃይማኖቱን አጥባቂ፤እንግዳ ተቀባይና ለወደደውና ላመነው ሟች ነፃነቱን አፍቃሪ እና የኢትዮጵያን አንድነት ከራሱ ህልውና አልቆ የሚመለከት አገር ወዳድ ህዝብ ነው፡፡ይህ ህዝብ ከነዚህ ካዳበራቸው ባህላዊ እሴቶች በመነሳት ከጎረቤቶቹ ክልሎች ማለትም ከቤንሻንጉል፤ ከኦሮምያ፤ ከአፋርና ከትግራይ ክልል ህዝቦች ጋር ተከባብሮ፤ችሎና ተቻችሎ ለዘመናት በአንድነት ፀንቶ የኖረና እየኖረ ያለ ህዝብ ነው፡፡
=
ይህ እውነታ ትላንት ያለፈና ዛሬ በህዝቦቹ የማንነት እሴት ውስጥ ፈጽሞ የሌለ ጉዳይ በመሆኑ ለንግግር ማሳመሪያ እንዲሆነኝ ብዬ በትዝታ ብቻ የምጠቃቅሰው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዛሬ በእኩልነት ማህተም በደመቀ የህዝቦች የጋራ ቃል-ኪዳን በሆነው ሕገ-መንግስትና ሕገ-መንግስታዊ ስርአት ውስጥ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ታሪክ ዛሬም፣ ነገም እስከመጨረሻውም ተጠብቆ እንዲኖር የሚሞግትና ለዚህም እንደ አንድ ታላቅ ባለድርሻ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የበኩሉን ሲያበረክት እንደኖረው ሁሉ አሁንም እያበረከተ በመቀጠል ላይ ያለ ህዝብ ነው፡፡
=
በቀጣይም የጋራ ቤታችን የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ እኩልነት የሰፈነባት፤ ህዝቦቻ በነፃነት የሚኖሩባት፤ዴሞክራሲና ማህበራዊ ፍትህ የተረጋገጠባት የሰላምና የልማት አገር ትሆን ዘንድ የሁሉንም ህዝቦች ግንኙነቶች ማጠናከር ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር በትኩረት መስራት ለአገራችን ናቸው ስንል በአንድ በኩል በዚህ ወድድር በበዛበት አለም በብቃት ተወዳድሮ በህብረተሰባችን እያደገ የመጣውን የመለወጥ ፍላጎትና ተስፋ በተጨባጭ እውን ለማድረግ እንደ ሃገር መላው ህብረተሰባችን በአንድነት መንፈስ መንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚታየውን መጠራጠር የወለደውን ክፍፍልና በህዝቦች ሰላምና ደህንነት ላይ የሚያሳድረውን ፖለቲካዊ ችግር ለማስወገድ አንድ ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የአማራና የትግራይ ህዝቦች የጋራ የምክክር መድረክ በአንድ በኩል የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነትን የሚያሻክሩ ችግሮችን በቀጣይነት እየፈቱ የጎበጠውን በማረቅ፤የተጣመመውን በማቃናት ግንኙነታቸውን ለማዳበር በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችንን እጣ ፈንታ በሚወስኑ ጉዳዮች ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ በመሰለፍ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት የዚህ አይነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
=
ስለሆነም በአማራ ክልል በኩል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ አድማሱን በማስፋት በቀጣይም ከሌሎች ህዝቦች ጋር በተለይም የወጣቶችና የምሁራን ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ አትኩረን የምንደግፍ ይሆናል፡፡ በዚህ አይነቱ የህዝብ ለህዝብ ምክክርን በማጠናከር ችግሮችን እየፈቱ መሄድ በቀጣይም እንደ መልካም ልምድ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት ለማጠናከር ሳይታክቱ የሰሩትን የሁለቱን ህዝቦች ሃገር ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሜ አመሰግናለሁ፡፡
=
በመጨረሻም የምክክር መድረካችን እንደ መጀመሪያው ሁሉ በሁላችንም የነቃ ተሳትፎና የተደራጀ የአብሮነት መንፈስ ለዘላቂ ሠላማችን ልማታችንና ለጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችን ተደማሪ ውጤት የምናስመዘግብበት ይሁንልን እያልኩ ለተከበራችሁ እንግዶቻችን የጎንደር ቆይታችሁ ያማረ እንዲሆን ልባዊ ምኞቴን ደግሜ እገልፃለሁ፡፡ ዛሬ የሁቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር በሃላፊነት መንፈስ የሰራችሁ የመንግስት አመራሮች፣ የሃገርሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች በክልላችን መንግስትና በራሴ ስም አመሰግናችኋለሁ፡፡
=
እንግዶች በመጡበት መንገድ ሁሉ ደማቅ አቀባበል በማድረግ እንግዶቻችን ላስተናገዳችሁ ጎንደር ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ታላቅ አክብሮትያለኝ መሆኑን እየገለፅኩኝ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ እላለሁ ፡፡
አንድነታችን ለሰላማችን፤ ሰላማችን ለአንድነታችን!
አመሠግናለሁ!

BY