ለዚህም ምክንያቶቼ እንደሚከተለው ይሆናል:- ኢትዯጵያ መሆን አለበት ብሎ ሊያሳምን የሚያስችል መረጃ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ኢትዮጵያ መሆን አለበት በሚለው ለሚቀርበው መረጃ ላለመቀበል ጭምር ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትን እጋራለው:: ይሁን እና በአለም ላይ አብዛኛው ምሁራኖች እንደሚስማሙት ከሆነ ከየትኛውም ጥናታዊ ፅሑፎች፣

መፅሐፍቶ እና ስያሜዎች ጭምር ከመፃፋቸው በፊት ቅድመ ሐሳብ ወይም ፍላጎት (Presupposition) እንዳለ ይታመናል:: አፍሪካ፣ አል-ሐበሽ፣ ኤርትራ የጣልያን እና የአረቦች ለአንዳንድ አካባቢ እና ህዝብ የተሰጡት ስያሜ ሲሆን የግልም ሆነ የአንድ ሀገር ስም ስያሜዎች ታሪካዊ ሂደት ቢኖረውም ነገር ግን በራሱ የስም ስያሜዎች ሲሰየሙ እና ሲውጣ የግድ ቅዱስ ወይም እርኩስ፣ ትክክል ወይም ስህተት አለው በሚለው አላየውም:: በተለይ ከመፅሐፍ ቅዱሱ ስም በማውጣት ጥሩ ልምድ እና ምሳሌ ሆኖ ምናየው የአይሁድ ህዝብ ነው:: ይህ ህዝብ ስም ሲሰይም ከአንድ ክስተት (event) አና ከማንነት (Identity) ጋር በማያያዝ ነው:: ኩሽ የሚለው ቃል ቅዱስ አይደለም፤ በራሱ የሒብሩ ቃል እንጂ፤ ትርጉሙም የሚያዘነብለው ለሰው የተስጠ ስያሜ ሲሆን ከመልክ እና ከጥቁረት ጋር የተገናኘ ነው:: ኢትዮጶስ የሚለው የግሪክ ቃል ነው:: ይህ በግሪክ አቻው ቃል ኩሽ የሚለውን ትርጓሜውን ይተካል:: በራሱ የሒብሩን ቃል ቅዱስ የግሪኩን ስም [ቃል] ርኩስ ማድረግ ካልሆነ በስተቀር:: በአማርኛ እየተተረጎሙ ባሉ የመፅሐፍቅዱስ የትጉም ስራዎች በጣሙን እያበረታታሁ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ እረዳለው::

ይሁን እና በአንፃሩ ግን የዚህን የትጉም ስራ ላይ “ኢትዮጵያ በሚለው በኩሽ” በመተካቱ በዚህ ላይ የሀሳብ ልዩነት አለኝ ለመቀበልም እቸገራለሁ:: ከሞያዊነቱ ይልቅ የታሪክ መፋለስ እና ባልተገባ እና ወቅታዊ ፖለቲካዊ ይዘት ባዘነበለ መልኩ ለመቶርገም መሞከሩ የትርጉሙን ስራ ተአማኝነቱን ያሳጠዋል:: ሁሉም የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሲተረጎሙ ከኦሪጅናል ቋንቋ ማለትም ከሒብሩ እና ግሪክ ቋንቋዎች ሲተረጎም ሁሉም ትርጉሞች የራሳቸው [የራሱ] የሆነ ጠንካራ እና ደካማ ጎን አላቸው:: የዚህም የትጉም ስራ ደካማ ጎን ነው ቢዬ የማየው ሀገራችንን ኢትዮጵያ በተመለከተ ኢትዮጵያ በሚለው ፋንታ ኩሽ በመተካቱ ነው:: ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ሊያሰኛት ወይም ሊያስጠራት ሚችለው የሴሜትክ: የኩሽ: የኦመቲክ: እናም የናይሎሳህራ ህዝብ ታሪክ ጭምር እንጂ የሴሚቲክ ብቻውን ወይም የኩሽቲክ ብሎ መነጠሉ እና ማሰቡ የኢትዮጵያን የሺዎች አመታቶችን ታሪክ ሙሉ አያደርገውም ተብሎ በአብዛኛው ታሪክ ተማራማሪዎች(historian) ይታመናል:: በአሁኑ ጊዜ በአለም ላይ ከአስር በላይ የታወቁ የእንግሊዘኛ የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይኖራሉ:: ከዚህም መሐከል የ king James ትርጉም ብንመለከት የእንግሊዝ ንጉስ የነበረው ኪንግ ጄምስ ይህንን የትርጉም ሲያስተረጉም ኩሽ በሚለው ፋንታ ኢትዮጵያ ብሎ ነው የተረጎመው:: በራሱም ይህ ስያሜ ቅዱስ ባይሆንም መረጃ ላይ እና እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ያሳያል እንጂ፤ ይህ ከሌሎች ትርጉሞች ይልቅ የተሻለ ሆኖ በግሌ አገኘዋለው:: ይህንን እመርጠዋለሁ:: የኪንግ ጄምስ መፅሐፍ ቅዱስ መመልከት ይቻላል:: የዚህ ኢትዮጵያ ሚለው ስም ወጥቶ በኩሽ መተካቱ ከዚህ ኪንግ ጄምስ ትርጉም ስራ ጋር ይቃረናል::
ኢትዮጵያ የሚባለው የት አካባቢ እና ግዛቶችን በተመለከተ በርካታ መረጃዎች ይኖራሉ፤ ይሁን እና ይህ አካባቢ የቱን እንደሆነ ለሚለው ሀሳብ፤ ከግብፅ መለስ ወዲህ ባሉ አካባቢዎች ሲሆን የአሁንን ሱዳን (ኑቢያ) ጨምሮ እስከ አክሱም ድረስ ያለውን ያጠቃልላል:: በርግጥም የአለም ኢኮኖሚ ለውጥ (shift) በሚያደርግበት ጊዜ ፓለቲካውም ጨምሮ በዚህ ለውጥ ምክንያት አንድ ያልነበሩ ሀገራት ሲዋሐዱ፤ በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሀገር የሆኑት ሲለያዪ የሚታይበት ነባራዊ ክስተት ነው:: ይህንን ታሪክ እንዴት እንደሆነ ለመመልከት ከክርስቶስ ልደት በፊት እንዲሁም በኅላ ያለውን የአለምን እንዲሁም የአፍሪካን ታሪክ መመልከት ይቻላል:: ግብፅንም ጨምሮ እስከ አሁኗ ኢትዮጵያ ግዛት የጥቁር አገር ነው:: በነገራችን ላይ ግብፅ ከሚለው ስም በፊት ኬሚስ ሚል የጥቁሮች አገር ነበር:: አሁን የአረብ እና ኤዢያ ዝርያዎች አካባቢውን ከመቆጣጠራቸው በፊት ማለት ነው : : ያው እንደሚታወቀው በአለማችን የታሪክ ሽሚያ እንዳለ ሆኖ የጥቁሩ ህዝብ ታሪክ፣ አገር እና ባህል በሌሎች አገራት ማለትም ጉልበት ባላቸው ሰዎች ተቀምተዋል:: ለምሳሌ ከፈርኦን ፒራሚድ ሐውልት ብንነሳ አርኪዮሎጂስቶች እንዳረጋገጡት የጥቁር ሰው ምስል ነው :: አሁን ተጨባጩ አለም የሚያምነው እና የሚያየው ግን የነጭ ወይም የሌላ እንደሆነ ነው:: የግብፅ ግዛት እና አካባቢው ጭምር የጥቁር ህዝብ አገር እና ታሪክ ነበር::

ነገር ግን በአለማችን ላይ በሚከሰቱት ተፈጥሮአዊ እና ኢተፈጥሮዊ ለውጦች ምክንያት የአገራት ቅርፅ እና ታሪክ እየተለወጠ የመጣ እና የሚሄድ ነው:: በአለማችን ላይ ከፍችተኛ የኢተፈጥሮዊና የባህል ሽሚያ እንዲሁም ዘረፋ አለ። ይኸውም ጉልበት ያለው ህዝብ ነው በአለማችን ላይ የሚደመጠው:: እናም ለዚህ እንደማሳያ የሚሆንው የፈርኦን ፒራሚድ በራሱ ጥቁር እና የጥቁር ህዝብ ታሪክ ሆኖ ሳለ ግን ጉልበት ባለው በመውሰዱ ነው፣ በተጨማሪም ግብፅ ውስጥ ካለው የፈርኦን ፒራሚዶች ይልቅ በጥቁር ህዝብ በሱዳን ውስጥ ያሉት የፈርኦን ፒራሚዶች ይበዛሉ:: በተጨባጭ የአለም መድረክ ግን ከዚህ ከጥቁር ታሪክ፣ ግዛት እና ባህል ይልቅ ጥቁር ላልሆነው ህዝብ እንደሆነ ነው የሚያሳየው:: ስለሆንም የኢትዮጵያ (ጥቁር ህዝብ) አካባቢ ከግብፅ ጀምሮ የአሁኑን ሱዳን (ኑብያ): አክሱም እስከ አሁኑ የኢትዮጵያ ግዛት ያካታል::

እንደሚታወቀው አሁን በቅርብ እንኳን የኢትዮጵያ ግዛት ከ70 አመታት በፊት የአሁኑን ጅቡቲ እናም በሰላሳዎቹ አመታት ኤርትራን ኢትዮጵያ ግዛቷን ታሪኳን እያጣች መታለች:: ከዚህም የተነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን እና ማንነታችንን ብሎም ለአለም ህዝብ ያደረግነው አስተዋፅኦ በአለም አቀፍ መድርክ ራሳችንን በበጎ መልኩ ከማቅረብ : ጥቃትን ከመከላከል: ጥቅማችንን ከማስጠበቅ አንፃር: ይልቅ እርስ በርስ ጉዳዮች እና እርስ በርስ በምናደርገው የራሳችንን ታሪክ አለመቀባበል: አለመግባባት፣ ብሎም ግጭት ላይ በማተኮር እና በመጠመድ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአለም መድረክ ያለንን የታሪክ እና ሀገራዊ ገፅታ(Image) እያጣን የመጣንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል:: ስለዚህም ታሪካችንን፣ ግዛታችንን እና ባህላችንን አቅም ያለው እየዘረፈ እና እየተቀማን ይገኛል::

እኛ ኢትዮጵያውያን የነበረንን፣ ያለንን እና የሚኖረንን ማስጠበቅ ካለመቻል የተነሳ ደካማ ሀገራቶች ሳይቀሩ ኢትዮጵያን በማጥቃት ያሉንን ግዛቶች፣ ሐብቶች፣ ባህል: ብሎም ወረራ በመፈፅም ጥቃት እና አደጋ ላይ እየወደቀች ትገኛለች:: በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ደካሞች እና አዳዲስ አገራት ሳይቀሩ አጋጣሚውን በመጠቀም ተፅዕኖ ስር ከምንጊዜውም በላይ ሀገሪቷ እየወደቀች ትገኛለች። ለምሳሌ የአሁኒቷ ሱዳን፣ የመን፣ ሶማሌ: የትላንቷ ኤርትራ ሌላም ግዛታችንን፣ ታሪካችንን፣ ባህላችንን እናም ማንነታችንን በቀላሉ በመዝረፍ እና በመውሰድ በመከፋፈል እና የራሳቸው በማድረግ ይጠቀሙበታል:: ስለሆነም በዚህ በአዲሱ የመፅሐፍ ቅዱስ ትርጉም ስራ ላይ በኢትዮጵያ ፋንታ በኩሽ የተለወጠው ትርጉም ወደነበረበት ወደ ኢትዮጵያ ቢመለስ የተሻለ ነው ብዬ በግሌ አጥብቄ አምናለሁ:: በተጨማሪም የመፅሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን የተፃፈው በሒብሩ ቋንቋ ሲሆን ኩሽ ሚለው ቃል ደግሞ የሒብሩ ቃል ነው:: ይህ በጣም አስፈላጊ እንኳን ሆኖ ቢገኝ በቋንቋው በተፃፈው በብሉይ ኪዳን ውስጥ ቢካተት ወይም ቢተካ ምክንያትነቱ በመጠኑም ቢሆን ልክ መሆን በቻለ::

ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ጭምር መለወጡ የዚህን የትርጉም ስራ ሞያዊ በሆነ መልኩ ከመሰራቱ ይልቅ ተአማኝነቱን ስጋት ላይ ይጥለዋል:: ምክንያቱም አዲስ ኪዳን የተፃፈው በሒብሩ ሳይሆን በግሪክ ነው ስለሆነም ኩሽ በሒብሩ ስለሆነ በሒብሩ በተፃፈው በብሉይ ላይ መኖር ሲገባው በአዲስ ኪዳን በግሪክ ተፅፎ ሳለ በግሪኩ አትዮጶስ አለመደረጉ የዚህን የመፅሐፍቅዱስ የትርህጉም ስራ ምክንያታዊነቱን ያሳጠዋል::በነገራችን ላይ የአለም አቀፋ የመፅሐፍ ቅዱስ ማህበር አካላት ወይም የመፅሐፍቅዱስ አዋቂዎች (Bible scholars) በግሪክ ቋንቋ የተፃፈው ከመፅሐፍቅዱስ ክፍል በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሀሳብ ልዪነት ወይም ክርክር በሚነሳበት ወቅት ሶስት ጥንታዊ የአለም ቋንቋዎችን መመልከት እና ማመሳከር (Refer) እንዲደረግ እና ዋናውን ሀሳብ ለማግኘት እንዲረዳ ይመከራል :: እነሱም የግሪክ ቋንቋ: ኢቶፒክ(የኢትዮጵያ ግፅዝ ቋንቋ) እና አራማይክ የሲሪያ ቋንቋ ናቸው ::

ኤርምያስ በላቸው

Share
Tweet
Pin
Email
Share