የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን መልቀቃቸውን የሀገሪቱ ፓርላማ አፈጉባኤ አስታውቀዋል። ይህ ያልተጠበቀ ውሳኔ የተሰማው የሀገሪቱ ህግ አውጪዎች በሁለቱ ምክር ቤቶች ጥምር ስብሰባ እርሳቸውን ለመክሰስ በሚያስችል ሁኔታ ዙሪያ እየተወያዩ ባለበት ጊዜ ነው።

ሙጋቤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በፈቃዳቸው እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄና ግፊት አልተቀበሉም ነበር። ዛሬ ግን ለ37 ዓመታት ከነበሩበት ሥልጣን ለመልቀቅ መፍቀዳቸው ተዘግቧል። በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ውሳኔያቸውን የቀየሩት በፈቃዳቸው እንደሆነና ጤናማ የሥልጣን ሽግግር እንዲካሄድ በማሰብ እንዳደረጉት ገልጸዋል።

ዚምባቡዌያውያንም ዜናውን ከሰሙ በኋላ አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።