4 ዲሴምበር 2017

የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ከቀድሞ ደጋፊዎቻቸው ጋር በነበረ ግጭት እንደተገደሉ የየመን ሚዲያዎች ዘግበዋል። በአማፂያኑ ሁቲ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ስር ያለው ሚዲያ ባለስልጣናቱን ጠይቆ እንደዘገበው የከሃዲው ሚሊሺያ የቀውስ መጨረሻ እና የመሪያቸው ሞትየሚል ነው። በሳሌህ ይመራ የነበረው ጄኔራል ኮንግረስ ፓርቲ የወጡ ምንጮችም መሞታቸውን እንዳረጋገጡ አል አረቢያ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ሳሌህን የሚመስሉ በከፍተኛ ሁኔታ የቆሰሉ ሰው ፎቶና ቪዲዮም በተለያዩ ድረገፆች ታይቷል። እስካለፈው ሳምንት ድረስ የሳሌህ ደጋፊዎች ከሁቲዎች ጋር በመጣመር ከየመን ፕሬዚዳንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ ጋር ጦርነት ላይ ነበሩ ። ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች በተጋጋሉበት ሁኔታ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር በሆነችው ዋና ከተማዋ ሰንአ ያለውን ዋነኛ መስጊድም ለመቆጣጠር በነበረ ከፍተኛ ግጭት ረቡዕ ማታ ጀምሮ 125 ሰዎች ሲሞቱ 238 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ቅዳሜ ሳሌህ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በየመን ላይ እያካሄደ ያለውን ጥቃት እና ከበባ ካቆመ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍለመጀመር ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር። ጥምረቱና የሚስተር ሃዲ መንግሥት የሰጡትን አስተያየት ተቀብለውትም ነበር። ነገር ግን ሁቲዎች ሳሌህ በማያምኑበት ትብብር ላይ መፈንቅለ መንግሥት እያካሄዱ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋለወ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት የጥምረቱ ኃይል በ2015 (እአአ) መጋቢት ላይ በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ ከገባ በኋላ ከ8670 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 50ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ቆስለዋል። የእርስ በርስ ጦርነቱና ሳዑዲ አረቢያ በየመን ላይ የጣለችው ከበባ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል። ይህም የዓለማችን ትልቁ የምግብ እጥረት እንዲከሰትና ከ2200 በላይ የመናዊያን ሞት ምክንያት የሆነውን የኮሌራ ወረርሽኝ እንዲቀሰቀስ አድርጓል።