የማለዳ ወግ …የከልታማዋን አህት ገንዘብ መልስ … – ነቢዩ ሲራክ

image_pdf

December 5, 2017

የማለዳ ወግ …የከልታማዋን አህት ገንዘብ መልስ

ከልታማዋ እህት ሪያድ ላይ የሁለት ወር በኮንተራት ሰርታ ያጠራቀመቻት ደመወዝዋን ወደ ቤተሰቦቿ ለመላክ ታስብና ጓደኛዋን ታማክራለች ። ጓደኛዋም ታማኝ የተባለውን ሰው አድራሻ ሰጠቻት ። ብዙም ሳይቆይ ” በትክክል ገንዘቡን አደርሳለሁ ” የተባለው አንድ አባወራ ገንዘቡን ትሰጣለች ። ለእህቶቿ ትምህርት ቤት ክፍያ በአስኳይ የተላከው ገንዘብ ግን ሳይደርስ ቀረ … ለታዳጊዎች ትምህርት ቤት ክፍያ የላከችው ገንዘብ ሳይደርስ ቀናት ተቆጠሩ ፣ ሳምንት ነጎዱ ፣ ከሳምንት ተሸጋግረው በወራት ልዩነት ገንዘቡ ሊደርስ አልቻለም …

ይህ ታሪክ ወደ እኔ የደረሰው ከወራት በፊት በአንድ ሀገረ አሜሪካ በሚገኝ የፊስ ቡክ ወዳጄ አማካኝነት ነው ። ወዳጄ አዝኖ ችግሯን ሲያጫውተኝ የምችለውን ለመተባበር ቃል ገባሁ ። ብዙም ሳልቆይ በወዳጄ አማካኝነት ከተገፊዋ እህት ጋር በመልዕክት ተገናኘን ። በመልዕክት ስልክ ተለዋውጠን በተወሰደባት ገንዘብ ዙሪያ የላከችበት የባንክ አድራሻና ካላኪው ወንድም ጋር ያደረገችውን የድምጽ መረጃ አቀብላኛለች። በዚህ አጋጣሚ ስለ ሳውዲ አመጣጧና ስለምትሰራበት ስራ ጠይቄያት ፣ ታሪኳን ታጫውተኛለች ።

ይህች ዛሬ ስለ ገንዘቧን መነጠቅ የምትነግረኝ እህት በምስቅልቅሉ የኮንትራት ስራ ህይዎት ያለፈችው በቀላል መንገድ አይደለም ። ከአዲስ አበባ ድንበር ከተማዋ ጀዛን ፣ ከጀዛን ሪያድ ያደረሳት ስደት በአጭሩ በሞትና በድህነት መካከል ያለፈችበት ነበር ማለት ይቻላል። በደረቁ በርሃ ለቀናት በርሃንና ውሃ ጥም ተገርፋለች … መራራውን የስደት መከራ እዚህ መድረሷን ስታጫውተኝ ልቤ በሀዘን ቢሰበርም በጽናት ብርታቷ ተገርሜያለሁ ፣ ተደንቄያለሁ ! ለእኔ ከተቀማችው ገንዘብ ይልቅ የደረሰባት የስደት እንግልት ብዙ የሚባልለት አሳዛኝ የእህቶቻችን ህይዎት አንዱ ገጽታ ነው ። እዚህ ያደረሳት ህይዎት ሊሰሙት ያጓጓል …

የዚህችን መከረኛ ድሃ አደግ እህት ዛሬ እንደ ሰው እኩል ቆማ መናገሯ ስታብ ስለተቀማችው ገንዘብ መጠየቋ አስደምሞኛል ። ከሞት ተርፋ ስለተወሰደባት ገንዘብ አምርራ መከታተሏ በራሱ እድለኛ ያደርጋታል ። ያም ሆኖ የደከመች ባት አንዲት ሳንቲም ለዚያውም “ለሀበሻ ቃልአባይ አሳልፊ አልሰጥም ” የምትለው በእልህ ነው … ” አረቦች የሰራሁበትን ቢቀሙኝ አያውቁኝም ይሁን ይባል ፣ ደክሜና ለፍቸ ያመጣሁትን ገንዘብ ለምንስ በራሴ ዜጋ እቀማለሁ ? ” ትላለች ክልታማዋ እህት … እውነት አላት !

ከዚህችው እህት በዋትሳፕ የደረሱኝን መልዕክቶችና መረጃዎች ተከትዮ መኖሪያውን ጅዳ አድርጓል የተባለውን ወንደም አገኘሁት። በወሰደው የአደራ ገንዘብ ጉዳይ አነጋግሬው እውነቱን ዝንፍ ሳያደርግ አጫወተኝ ። ጉዳዩን በክስ ከሚታይ እኔው በመካከላቸው ልሸመግል ፈቃደኛ መሆኔን በማስረዳት ተግባባን ። ከሳሽ ሪያድ ተከሳሽ ጅዳ ፣ ሸምጋይ እኔው በስልክ ኮንፈረንስ ተነጋግረን ገንዘቡን አባክኘዋለሁ ያለው ወንድም ባሳለፍበው ወር ገንዘቧን በሁለት ጊዜ ክፍያ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ተስማምተን ስልኩን በመዝጋት ተለያየን !

ቀኑ ደረሰ ከልታማዋ እህት ” ቀጠሮው ደረሰ ” በሚል ደጋግማ ከሰሞኑ ብትደውልልኝም ከተሰጠን ቀጠሮ አንድ ሳምነት ጠብቄ ወደ ወንድማችን ደወልኩ ። ስልኩ ዝግ ነው ፣ እሱ የለም ! ግራ ተጋባሁ … አድራሻውን ጠይቄ ሳፈላልግ የወሰደውን ገንዘብ ለመመለስ ቀጠሮ የሰጠን ወንድም ሀገር ቤት መግባቱን ማረጋገጥ ቻልኩ ! እጅግ በጣም አዘንኩ 🙁 ተገፊዋ እህትም ደጋግማ ” ምን አደረግክልኝ ” ለማለት ደውላልኝ ነበር ። ዛሬ ያለውን እውነት አሳውቄያት እጅግ በተጎዳ ስሜትና መልዕክት ልካልኛለች …. መልዕክቱን ሰምቻ ላሰማችሁ አልፈቀድኩም ። ዛሬ የምለው የከልታማዋን አህት ገንዘብ መልስ ብቻ ነው ! በቀጣይ የማደርገው የሁሉንም ምስክርነት በመረጃ ማስረጃ ማቅረብ ይሆናል 🙁

የሰው ሀቅ ለዚያውም ልጅቷን በበላበት ፣ እድሜዋን በፈጨባት የአረብ ሀገር ስደት በላቧ የሰበሰበችውን ገንዘብ መልስ … እደግመዋለሁ ፣ የከልታማዋን አህት ገንዘብ መልስ ! ! !

ቸር ያሰማን

ነቢዩ ሲራክ

ህዳር 26 ቀን 2010 ዓም

No widget added yet.

← Ethiopia Plans to Close 27 Refugee Camps የህወሓት መግለጫ በራሱ ምላስ ሲዳሰስና ሲታመስ (+video) – ሀሰን ሁሴን →

Leave A Reply

Comments are closed

Visit Us On TwitterVisit Us On FacebookVisit Us On YoutubeVisit Us On Linkedin