Jews and Arabs on the Temple Mount/Haram al-Sharif
RRODRICKBEILER 

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአሜሪካው መሪ ዶናልድ ትራምፕ ለዘመናት አወዛጋቢ የሆነችው እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው ዕውቅና ሊሰጡ መሆኑ አሳሳቢ ነው ይላሉ።

አከራካሪ የሆነችው ከተማን በሚመለከት ማንኛውም ውሳኔ ሲወሰን ‘በእሥራኤልና በፍልሥጥኤም ስምምነት መሰረት መሆን አለበት” በማለት ማክሮን ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎችም ከተለያዩ አረብና ሙስሊም ሀገራትም እየተሰሙ ነው።

አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዪት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ በማድረግ ዕውቅና ሊሰጡ ይችላሉ።

ነገር ግን እስራኤል እና ፍልሥጥኤም ዋና ከተማችን ናት በሚል አቋማቸው እንደፀኑ ነው።

ከዋይት ሀውስ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትራምፕ ሰኞ ዕለት ቴልአቪቭ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም መዘዋወሩን አስመልክቶ ፊርማቸውን ማኖር የነበረባቸው ቢሆንም ቀኑ አልፏል።

ነገር ግን የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሆጋን ጊድሌይ እንደሚሉት ” ፕሬዚዳንቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ግልፅ አቋም ነው ያላቸው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ መዘዋወሩ ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ በአውሮፓውያኑ 1995 ኤምባሲው ወደ እየሩሳሌም እንዲዛወር ጥያቄ ከቀረበ በኋላ ትራምፕን ጨምሮ እያንዳንዱ ፕሬዚዳንት በየስድስት ወሩ መዛወሩን መቀበል አለመቀበላቸውን በሚመለከት መፈረም አለባቸው።

አከራካሪው ጉዳይ ምንድን ነው?

በእስራኤልና በፍልሥጥኤም ግጭት ዋነኛ የሚባለው ጉዳይ የእየሩሳሌም ጥያቄ ነው።

ከተማዋ በተለይም ምስራቅ እየሩሳሌም ለሶስቱ እምነቶች እስልምና፣ ክርስትናና አይሁድ የተቀደሰች ከተማ ተደርጋ ነው የምትታየው።

በአውሮፓውያኑ 1967 እስራኤል ከመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኋላ ከተማዋን የተቆጣጠረች ሲሆን የእሥራኤል ዋና ከተማ እንደሆነችም እሳቤ አለ።

ፍልስጤም ወደፊት ምስራቅ እየሩሳሌምን ዋና ከተማ የማድረግ ሃሳብ ያላት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1993 የተደረገው የእስራኤልና የፍልሥጥኤም የሰላም ስምምነት የመጨረሻ ደረጃ የከተማዋን ሁኔታ በሁለቱ ሥምምነት የሚወሰን ይሆናል።

እስራኤል እየሩሳሌም ላይ አለኝ የምትለው ሉአላዊነት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ያልተሰተጠው ሲሆን የእስራኤል ወዳጅ የሆነችው አሜሪካን ጨምሮ አገራት በሙሉ ኤምባሲዎቻቸውን ያደረጉት በቴል አቪቭ ነው።

እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ ከ1967 ጀምሮ በምስራቃዊ እየሩሳሌም 200 ሺህ ለሚሆኑ እስራኤላዊያን መኖሪያ ቤት ገንብታለች።

ይህ ምንም እንኳን ከዓለም አቀፍ ህግ አንፃር ህገወጥ ቢሆንም እስራኤል ግን አይደለም በማለት ትከራከራለች።

አሜሪካ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርጋ እውቅና ብትሰጥ በአሁኑ ወቅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዪ ላይ ያለውን አቋም ሊያዛባ ይቸላል።

እስራኤል በምስራቅ እየሩሳሌም የምታደርገው ሰፈራም ተቀባይነትን ያገኛል።

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ ምን ይመስላል?

ሳውዲ አረቢያ ሰኞ እለት የዚህ አይነቱ የሰላም ስምምነት ሳይጠናቀቅ የሚደረግ እርምጃ የሰላም ስምምነቱ ላይ ተፅኖ እንደሚኖረው ገልፃለች።

የፍልስጥኤሙ ፕሬዚዳንት ሙሃሙድ አባስ “የዚህ አይነቱ የአሜሪካ እርምጃ የሰላም ስምምነቱን ያበላሸዋል” በማለት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።

ዮርዳኖስ ከባድ ቀውስ እንዳይፈጠር ስታስጠነቅቅ የአረብ ሊጉ ዋና ፀሃፊ አብዱል ጊት የዚህ አይነቱ ነገር አክራሪነት እንዲሰፍንና ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ በር የሚከፍት እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

የቱርኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በኪር ቦዝዳግ ደግሞ ነገሩ “ከፍተኛ ጥፋት እንዳይሆን” ብለዋል።

BBC/Amharic