Sunday, 03 December 2017 00:00

Written by  አለማየሁ አንበሴ

*ፖለቲካዊ ችግሮች   

*የፌደራሊዝም አደረጃጀት   

*የሃይማኖት ተቋማት ሚና

*ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ይሣተፋሉ
*
ህዝባዊ ውይይቱ ለአንድ ወር የሚዘልቅ ነው ተብሏል

ሰማያዊ ፓርቲ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት!” በሚል መሪ አጀንዳ በአዲስ አበባ ለአንድ ወር የሚዘልቅ አለማቀፍ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ ስለ መርሃ ግብሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያንን በቪዲዮ ኮንፍረንስ በማሳተፍ በሚደረገው በዚህ ህዝባዊ ውይይት ላይ ታዋቂ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ፖለቲከኞች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ይሣተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 
ህዝባዊ ውይይቶቹ የሚካሄዱት በመጪው ታህሳስ ወር ባሉት 4 እሁዶች ሲሆን ታህሳስ 1815 እና 22 ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡ በአይነቱ የተለየ መሆኑ የተነገረለትን ይህን ህዝባዊ ውይይት፣ በአዲስ አበባ አምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ ለማከናወን አስፈላጊው ፍቃድ  መገኘቱንና የአዳራሽ ኪራይ ክፍያም መፈፀሙን አቶ ጌታነህ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የመጀመሪያው ህዝባዊ ውይይት በሚካሄድበት ታህሳስ 1 ቀን 2010 .ም ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎች “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት!” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል አቶ ጌታነህ፡፡ በዚህ መድረክ ላይ  የሃገሪቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ምንድን ናቸው? እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? በሚሉ እንኳር ጉዳዮች ላይ ፅሁፍ ቀርቦ በታዳሚው ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡ 
በቀጣዩ እሁድ ታህሳስ 8 ደግሞ ቋንቋን መሠረት አድርጎ በተዋቀረው የፌዴራሊዝም ስርአት ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን አሁን ያለውን የፌዴራል አደረጃጀት በሚደግፉ እና በሚቃወሙ  ምሁራንና ፖለቲከኞች መካከል ምክንያታዊ የሃሳቦች ክርክር የሚካሄድበት መድረክ መዘጋጀቱን ም/ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡ ታሕሳስ 15፣ የሃይማኖት ተቋማት ሃገሪቱ ከገባችበት አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ሚናቸው ምን ድረስ ነው? የሚጠበቅባቸውን ሚና ተወጥተዋልን? ለወደፊትስ ከሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ምን ይጠበቃል? በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የቤተ እምነት መሪዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡ 
ሠማያዊ ፓርቲ የተመሠረተበትን 6ኛ ዓመት በሚያከብርበት ታህሳስ 22  ደግሞ ፓርቲው በ6 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተጓዘበት መንገድ፣ ለህዝቡ ያበረከተው አስተዋፅኦበተሳታፊዎች ይገመገማል ያሉት አቶ ጌታነህ፤ቀጣይ የፓርቲው አዳዲስ የፖለቲካ ትግል ዕቅዶችም ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
የዚህ ህዝባዊ ውይይት ዓላማ በዋናነት፣ ሃገሪቱን ከጥፋት ሊታደጉ የሚችሉ አስተሣሠቦችን አንጥሮ ለማውጣትና በሃገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል /ሊቀመንበሩ፡፡  
የህዝባዊ ውይይት ጥሪው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀረበ ነው ያሉት አቶ ጌታነህ፤ ከአሜሪካና ከአውሮፓም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ምሁራን የሚሣተፉበት ዓለማቀፍ ህዝባዊ ውይይት መሆኑን ገልጸዋል፡፡