የጅቡቲ ደረቅ ወደብ አስተዳደር በሁሉም የወደብ አገልግሎቶቹ ላይ የ45 በመቶ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ የዋጋ ጭማሪ የተረደገባቸው አገልግሎቶች የጠቅላላ ካርጎ፣ የደረቅ ወደብና የተሽከርካሪዎች አገልግሎትን ያካትታሉ፡፡

የጅቡቲ የደረቅ ወደብ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዋሂብ ዳሂር ኤደን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ የዋጋ ማስተካከያዎቹ የተደረጉት ከአንድ ሳምንት በፊት በጅቡቲ መንግሥት ውሳኔ መሠረት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በመርከቦች ጭነት የመያዝ አቅም ላይ ተመስርቶ የክፍያ ዋጋዎቹ ከ17 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ዶላር ድረስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የጅቡቲ ወደብ ከተመሠረተ አንስቶ 200 ያህል መርከቦችን 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርጎ ጭነት አስተናግዷል፡፡

አሁን ላይ ማሪያ የተባለችው መርከብ በወደቡ ላይ ከሞሮኮው የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኦሲፒ አፍሪካ የተጫነ 50 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እያራገፈች ትገኛለች፡፡