December 10, 2017 17:27

ርዕስ አንብባችሁ አስተያየት ለመስጠት አትቸኩሉ፡፡ ሀሳቤን አንብቡት፡፡ ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ ሀጫሉ የዘፈነው ዘፈን ብዙ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ መልዕክቱ ጥሩ ነው ግን በጣም ጥሩ የሚባል አደለም፡፡ እኔን ሁሌ የሚሻክረኝ ነገር አለ፡፡ የኦሮሞም ሆኑ የሌሎች አርቲስቶች ከአሁን በኋላ ከዘር ዘለግ ያለ ሕዝብን ሁሉ ወደ አንድነት የሚያመጣ ዜማ ቢያዜሙ መልካም ነው፡፡ እኔ ሀጫሉን ከዚህ በፊት ያሉ ዘፈኖቹን ሰምቼ አላውቅም፡፡ ግን ብዙ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ዘፈኖች አሉት የሚሉ አሉ፡፡ ከእነዛ ውስጥ የትኞቹ ከኦሮሞ ፈቀቅ ያሉ እንደሆኑ አላውቅም፡፡ በትላንትናው እለት እኔን ቅር ያሰኘኝ ሲጀምር በዚህ መድረክ የኦሮሞ አርቲስቶች ብቻ ሳይሆኑ ፍቃደኛ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች አርቲስቶችም መሳተፍ ነበረባቸው፡፡ እንግዲህ ተጋብዘው አልመጡ እንደሆነ አላውቅም፡፡ አድማጩም ኦሮሞ ብቻ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ምን አልባትም ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑም አድማጮች ይኖራሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የእኔ መሠረታዊ ቅሬታ መጀመሪያ ችግራችንን አለመረዳት አሁንም ችግራችንን ልንፈታበት የምንሄድባቸው መንገዶች ራሳቸው ችግሩን በፈጠሩብን መንግድ መሆኑ አሁንም መፍትሄው እየታየን አልመሰለኝም፡፡ ኦሮሞም ይሁን ሌላው ብሄረሰብ ነህ ተብሎ የተለጠፈበት ሕዝብ ከታጠረበት የዘር ማንነት ሰብሮ መውጣት እስካልቻለ ድረስ አጥሩን በአጠሩለት እጅ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
ዛሬ በሱማሌ ታጣቂዎች እየተገደሉ ያሉ ወገኖቻችን ኦሮሞ መሆናቸው የተለየ አያደርጋቸውም፡፡ ተገልብጦ ሶማሌ ቢሆኑስ? ዛሬ በታጠርንበት የዘር ጉሮኖ ሆነን እኛ ነን ብለን ከምናስበው ዘር ውጭ እንዳናስብ አእምሮአችንን በድንብ 27ዓመት በተሰበክነው ስብከት ደንዝዘናል፡፡ ዛሬ በሱማሌ ታጣቂዎች እየደረሰ ያለው ግፍ በብዙ ኦሮሚያ በሚባው ክልልም ሲከሰት ነበር፡፡ ይለያል ልንል መቼም አንችልም፡፡ ቢያንስ የጉራ ፈርዳውና የበደኖው ግፍ ሊያውም የሚያደምጥ ሳይሆር ምን ያህል የከፋ እንደነበርና አሁን በሱማሌ ታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ግፍ የተለየ እንዳልነበር ምን ያህሉ ኦሮሞ ነኝ የሚለው እንደሚያምን አላውቅም፡፡ በቃ ችግሩ አንድና አንድ ነው፡፡ በዘረኝነት መመረዝ፡፡ መድሀኒቱ ደግሞ መርዙን ማርከስ እንጂ በዘርኝነት እንድንመረዝ ያደረጉንንና በየዘር ጉሮኖ ውስጥ ጨምረው የሚያፋጁንን ሴራ የሚያጠናክርና የታጠረብንን ጎሮኖ እኛው ድርብ አድርገን እንዲያጥሩብን የአጥር ሽቦና ግንብ እያቀበልን መሆን የለበትም፡፡
ዛሬ በሶማሌና ኦሮሞ አማራና ኦሮሞ፣ ብሔር ከብሔር ነው፡፡ ነገ ወለጋ ከባሌ፣ አርሲ ከሀረር ሊሆን እንደሚችል መገመት እንዴት አቃተን? ደግሞም እኮ ሆኖ አይተናልም፡፡ እንደወንድማማች የሚታዩት ጉጂና ቦረና መሀከልም እኮ ጦርነት ሆኖ አይተናል፡፡ የዘርን ነገር ከጀመራችሁት እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡ አሁን የገባንበትን አረንቋ ለመውጣት አማራጩ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ የታጠረብንን የዘር ማንነት ጉሮኖ ማፈራረስ፡፡ ለመሆኑ ኦሮሞ ምንድነው? አማራስ ምንድነው? ይገባኛል 27 ዓመት ስለዘር ሲነገረን ከርሞ ዛሬ እንዲህ ያለ ጥያቄ ማንሳቴ የሞኝ ነገር ያስመስልብኛል፡፡ ጥያቄዎቼ ግን ልክ ለመሆናቸው አልጠራጠርም፡፡ ብዙዎች በቀድሞው ሥርዓቶች የብሔር ጭቆና ነበረ ይሉናል፡፡ አሁን ላይ ያለነው ሰዎች ማናችንም የቀድሞዎቹን ሥርዓቶች ለመተቸት አለማፈራችን ነው እንጂ አንድም የኖራል ብቃት የለንም፡፡ ዛሬ ላይ በተፈጠሩልን የውሸት ታሪኮች ታጭቀን አንኳን  የቀደሙትን ዞር ብለን  ስናስብ በብዙ እጥፍ የዜጎችን መብት ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ዛሬ በብዙ ኦሮሞዎች ዘንድ የሚናፈሰው በዘሬ ምክነያት በቀድሞው ሥርዓት ተጨቁኛለሁ የሚለው አባባል ዛሬ ያለውን የኦሮሞ ትውልድ ብዙ ዋጋ እያስከፈለው እራሱን ባዶ እያደረገው ነው፡፡ በቀደሙት ሥርዓቶች በዋናነት ኢትዮጵያን የመሩት ዛሬ ኦሮሞ ከተባለው ሕዝብ የወጡ መሆናቸው ቢዋጥልንም ባይዋጥልንም ልንክደው ያልቻልንው በሕይወት ሳይቀር ኖረው ምስክር የሆኑብን አሉ፡፡ ሰሞኑን አንድ ምሁር በኦሮሚያ ቲቪ ቀርበው “ይሄ ድመት እኮ ነብር ነበረ አሉ ”  በሚል የተናገሩት አገላለጽ በግልጽ የዛሬውን ኦሮሞ ነኝ የሚለውን ኦሮሞ በምትባል ትንሽ አጥር ውስጥ የታጎረውን ትውልድ ይገልጸዋል፡፡ አዎ ኦሮሞ ነበር ነበረ ዛሬ ግን ከድመትም አንሷል፡፡ ኦሮሞ ገዥ ነበረ ዛሬ ግን ተገዥ ለመሆኑ የምናየው ነው፡፡ አማራም ተብዬው ያው ነው፡፡ ዛሬ ያለው ትውልድ ጎበና ጀግናው አደለም፣ ባልቻ ሳፎ፣ ገበየሁ ጎራ፣ እስከቅርብ በሕይወት አብረውን የኖሩት ጃጋማ ኬሎ ጀግኖቹ አደሉም፡፡ ጠላቶቹ እንጂ፡፡ ዛሬ ላለው የኦሮሞ ትውልድ ጀግና የሚላቸው ኦሮሞ ነህ እያሉ ለዘመናት ወደ አዘቅት የከተቱትን አሁንም እየከተቱት ያሉት ናቸው፡፡ ኦሮሞነት ምንድነው? እንደሕዝብ አንድ ማህበረሰብ የራሱ መገለጫዎች አሉት ቋንቋ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ባህል ሌሎች ማሕበራዊ እሴቶችም፡፡ እነዚህ ሁሉ ኦሮሞ አማራ ምናምን ተብለን የታጠርንበት ውስጥ ያሉ ይመስለናል፡፡ የሚያሳዝነው ይችን እንኳን ማስተዋል አቅቶን እንደተጋረደብን ሳስብ ነው፡፡ እነዚህ ቃላቶች ውስጥ ከዘረኝነት የዘለለ አንድም ማህበረሰባዊ እሴት የለም፡፡ ከፈይሳ የተወለደ ሰው ኦሮምኛ መናገር አለመናገር ባህሉን መሳተፍ አለመሳተፍ አደለም ዋናው የዘር ማንነት እንጂ፡፡ ኦሮምኛ የሚናገር ምን አልባትም ኦሮምኛ እንጂ አማርኛ በደንብ አጣርቶ የማይናገር ከጎጃሜ ቤተሰቦቹ የሚወለድ በላይ ቁምላቸው ምናምን ገና ሥሙ ሲጠራ ይገለላል፡፡ ይህ 27 ዓመት ያለፍንበት እውነት እንጂ ሰዎች የነገሩን ታሪክ አደለ፡፡
ብዙ ጊዜ ብያለሁ ኦሮሞ  ወደ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ እስኪመጣ ድረስ እራሱ ነጻ መውጣት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ሥቃይ መቀጠል ምክነያት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ትላንት የሀጫሉ ዘፈን በመልዕክቱ ጥንካሬ ቢደነቅም ኢትዮጵያያውያንን ሁሉ ጋባዥ የሚያደርጉ ቃላት ተጠቅሞ ቢሆን ምን ያህል ጉልበት በኖረው፡፡ የእሱም ሆኑ የሌሎቹ ግን ከኦሮሞ አላለፉም፡፡ የባሕር ዳሩ ላይ ማልቱ አዳን ኑባሴ ባለቤት አሊቢራም እዛው ኦሮሚያ ውስጥ ታስሮ ነው የሰማሁት፡፡ አሁን ላለፈው አለፈ ወደፊት ቢያስቡበት አመክራለሁ፡፡ አስተውሉ ኦሮሚያ የሚባል ቃል የፈጠሩልንን፡፡ የዛሬ 27 ዓመት በነጻነት ወለጋም፣ ጎጃሜም፣ ትግሬም ሌላም የትኛውም የኢትዮጵያ መሬት ለመኖር በማንነቱ የተነሳ ስጋት የለበትም፡፡  በበደኖ ተጀምሮ ይሄው እስከዛሬ ማንነታችን እየተለየ በኖርንበት ቀዬ እየተገደልን እየተሳደድን ነው፡፡ ነገም ይቀጥላል ይህን ሴራ ነቅተንበት ከታጠረብን የዘር ጉሮኖ እራሳችንን ማውጣት እስካልቻልን፡፡ ሁላችንም ከጎንደሬዎቹ እንማር፡፡ ጎንደሬዎቹ የበቀለ ገርባን ምስልና ለኦሮሞ ወንድሞቻቸው የአለሁልህ መልዕክት በከተማቸው ይዘው አደባባ የወጡበት ክስተት ምን ያህል የሴረኞቹን ሕልም እንዳጨናገፈ አስተውሉ፡፡ ዛሬ እነ ለማ በኢትዮጵያዊነት ድምጽ ሲመጡ ምን ያህል ድጋፍ እንዳገኙ አስተውሉ፡፡ ለተንኮልም ይሁን ለመልካም ግን ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን ሲያነሱ ሁሉም ሴራቸው ከተበላሸባቸው በስተቀር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዘር ሀይማኖት ሳይለየው ከጎናቸው እንደሆነ አስተውሉ፡፡ አስከ መቼ ነው የማይገባን፡፡ በተለይ ኦሮሞ ነን ለምትሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የኢትዮጵያውያንን የዘር ማንነትና አንድነት በሳይንስ በተደገፈ መረጃ ለማቅረብ የምንችልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ሌሎች ለሴራቸው በአዘጋጁልን ወጥመድ እየገባን አንሸወድ፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ አማራ ነን በለው የተነሱትንም ልዩ ሴራ  ሊኖራቸው እንደሚችል አስቡ፡፡ ይህን ስል ግን ለየወገናችሁ አታስቡ ማለት አደለም፡፡ ግን ሌላውም እኔ ወገኔ ለምለው እንዲያስብ ዘለግ ብሎም ኢትዮጵያዊነታችን ከዛም ስብዕናችን እንዲታይበት አሳታፊ እናድርገው ነው፡፡  በትላንትናውም እለት በቀጥታ የዝግጅቱም ምክነያት ዛሬ በሱማሌ ታጣቂዎች የተፈናቀለውን የኦሮሞ ሕዝብ ከመደገፍ አንጻር በመሆኑ ኦሮሞ ተብሎ በብዛት ቢጠራ ቅር አያሰኝም፡፡ በትንሹም ቢሆን ግን ሌሎችንም መጋበዝ የሚችሉ ዘፈኖች ንግግሮች ቢኖሩ አንዴት በተሳካ፡፡ የአቶ ለማን ንግግር ተቀንጭቦ ነው የሰማሁት ሙሉውን ስላልሆነ ምን እንዳሉ አላውቅም ግን በተቀነጨበውም ውስጥ አሁምን የተሰማው ኦሮሞን ለብቻው የነጠለ ነበር፡፡ ከሌላው ጋር ወንድም ነን እያሉ በወሬ ብቻ መልካም አደለም፡፡ ችግርም ሲደርስ ወንድሜ ሆይ እንዲህ ያለ ችግር ደርሶብኛልና ናና ተካፈለኝ ደስታም ሲሆን እንደዛው፡፡ ይሄን በተግባር ማድረግ ስንጀምር ዛሬ አይፈርስ የመሰለን ግንብ በሰዓታት ድርምስምሱ ወጥቶ ሸለቆ ሲሆን ታዩታላችሁ፡፡ እባካችሁ በተለይ ኦሮሞና አማራ ነን ብላችሁ ራሳችሁን የወሰናችሁ ግን ከሴራው ተባባሪ ያልሆናችሁ ከዚህ እንውጣ፡፡ ኦሮሞ መሆን ትችላለህ፣ አማራ መሆን ትችላለህ ግን ኢትዮጵያዊነትህን ከጣልክ ባዶ እንደሆንክ አስብ፡፡ ይህን የምለው የአንድነት ኃይል ከሚባሉ ጋር ተመሳሳይነት ኖሮኝ አደለም፡፡ ከታሪካዊ እውነታዎች አንጂ፡፡ በአባቶቻችን አጥንት ላይ እየቀለድን ነጻ እንሆናለን ብለን አናስብ፡፡ ሊያውም ደግሞ አባቶቻችን ተዋግተው ድል ያደረጓቸው የባንዳ ልጆች በሸረቡልን ሴራ ተጠልፈን፡፡

ኦፒዲዮና በአዴን አሁንም ጥርት ያለ ነገር የላችሁም፡፡ ሕዝብ ጥቂት ወራት ሊታገስ ይችላል፡፡ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በተወሰነ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን ገና ነው፡፡ የአማራ ሚዲያ ምን እንደሚል አላውቅም፡፡ በየከተማው የሕብረት የአንድነት ምናምን እያሉ መሰብሰብ በቂ አደለም፡፡ ሚዲያዎቹ በተለይ በይፋ ትብብሩንም በሕዝብ ለይ እየደረሰ ያለውንም መናገር አለባቸው፡፡
አመሰግናለሁ!

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ ይጠብቅ! አሜን!