ባለፈው አርብ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን የተማሪዎች ግጭት ተከትሎ ለቀናት የዘለቀው ውጥረት ባለበት ሁኔታ በወልዲያ፣ በጎንደርና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ እንደሆነ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አርብ ኅዳር 29 ቀን 2010 በተነሳ ግጭት አንድ ተማሪ እንደሞተ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎችና የአማራ ክልል የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ቢያሳውቁም ተማሪዎች ቁጥሩን ከፍ ያደርጉታል።

በተጨምሪም ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሃኪም ቤት መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ግጭቱ የተነሳው የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦችን በዓል እየተከበረ ባለበት ወቅት ሁለት ተማሪዎች በመጋጨታቸው ምክንያት ነው። የልጆቹ ግጭትም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ በቡድን ተከፋፍለው ድንጋይ መወራወር እንደጀመሩ የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ከበደ ገልፀዋል።  ከጥቂት ሰዓታትም በኋላ የፀጥታ ኃይሎች ገብተው ነገሩን እንዳረጋጉት ቢናገሩም አሁንም በዩኒቨርሲቲው ውጥረት እንደነገሰ መሆኑን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ገልፀውልናል።  ይህንን ተከትሎም በወልዲያ ዪኒቨርሲቲ ከእሁድ ምሽት ጀምሮ ረብሻና ግጭት በተማሪዎች መካከል ተከስቶ አመሻሹ ላይ ጋብ እንዳለ እና ሰኞ ጠዋት መልሶ አገርሽቶ በተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ያናገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዩኒቨርስቲው ባልደረባ ተናግረዋል።  በጎንደር ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ተማሪዎች መንግሥትን ጭምር እያወገዙ ተቃውሞ ማሰማታቸውን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ገልፀዋል።

በተመሳሳይም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በአዲግራት በተማሪዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በመቃወም በዋናው ጊቢ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት (ሰኞ) ተቃወሞ ያሰሙ ሲሆን ትምህርትም እንደተቋረጠ ያናገርናቸው ተማሪዎች ነግረውናል። በሌላኛው የዩኒቨርሲቲው ግቢ ግን የተከሰተ ነገር እንዳልነበረና ትምህርት ሲካሄድ መዋሉ ተነግሯል።  በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭት ህይወቱ ያለፈው ተማሪ ሀብታሙ ያለው ስንሻው የተባለ የ2ኛ ዓመት የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረ መሆኑን መረጋገጡንና አስከሬኑም ወደ ቤተሰቦቹ እንደተላከ የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ገልፀዋል።  የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ከግጭቱ በኋላ ተማሪዎች ግቢውን ለመልቀቅ ጠይቀው ነበር። ጉዳዩ መረጋጋት እንደሚችልና ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ጣልቃ እንዲገቡም አድርገናልብለዋል።ነገሮች እየተረጋጉ መሆኑን የገለፁት አቶ ዮሐንስ ትምህርትም ተጀምሯል ብለው ቢነግሩንም፤ ያናገርናቸው ተማሪዎች ግን በስጋት ውስጥ መሆናቸውንና ትምህርት እንዳልጀመሩ ገልፀዋል።

የዩኒቨርሲቲው ግቢ በፌደራል ፖሊስ ጥበቃ ሥር ያለ ሲሆን በርካታ ተማሪዎች ወደቤተሰቦቻቸው መመልስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።  ከዩኒቨርሲቲዎች ርቀው የሚገኙ ወላጆችም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉና መንግሥት የልጆቻችንን ደህንነት መጠበቅ የማይችል ከሆነ ወደየቤታቸው መመለስ አለበትሲሉ ልጃቸው ዩኒቨርስቲ የሚማር የደሴ ነዋሪ የሆኑ እናት ተናግረዋል።

BBC