Ilia Yefimovich

በተለይም ከንግስት ሳባ ታሪካዊው የእየሩሳሌም ጉብኝትና በእየሩሳሌም ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማት ጋር በተያያዘ ብዙዎች እየሩሳሌምን ያውቋታል።

ደጋግመውመም በአእምሯቸው ይስሏታል።

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ እየሩሳሌም ይሄዱ እነደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ዛሬ ደግሞ በተለያዩ የጉዞ ወኪሎች አማካኝነት በርካቶች ወደ እየሩሳሌም እየሄዱ ነው።

እየሩሳሌም የብዙ እናቶች አባቶችና ወጣቶች ህልም ነች።

“ህይወቷን ሙሉ ስለ እየሩሳሌም እየሰማች ስለኖረች እየሩሳሌምን ማየት ለእናቴ ትልቅ ነገር ነበር።ይህን ህልሟን ማሳካት ደግሞ ለእኔም እነደዚያው ነው” የሚለው ሄኖክ ፀሀዬ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል።

ወደ አሜሪካ ሲሄድ ይህን ፍላጎታቸውን እንደሚያሳካ ለእናቱ ቃል ገብቶላቸው ነበር።

ነገር ግን እሱ ቃሉን ጠብቆ ባለፈው አመት እናቱ ወደ እየሩሳሌም ሊሄዱ ባሉበት ወቅት አባቱ ከዚህ ዓለም በመለየታቸው እቅዱ ሳይሳካ ቀረ።

ሀዘን ውስጥ ቢሆኑም የእናቱ እየሩሳሌምን የመጎብኘት ህልም ግን ያው እንዳለ ነበር።

ስለዚህም እናቱን ለመጭው ገና ወደ እየሩሳሌም ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው።

እናቱም ጉዞውን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን፤ ለእናቱ ይህን በማድረጉ ደግሞ እሱም ከመጠን ባለፈ መልኩ መደሰቱን ይናገራል።

የአሜሪካ ለእየሩሳሌም በእስራኤል ዋና ከተማነት እውቅና መስጠትን በሚመለከት ያለውን አስተያየትም ሰንዝሯል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1917 የተደረገውንና ለእስራኤል መፈጠር መሰረት የሆነውን የባልፎር ስምምነት በመጥቀስ ያ ለዘመናት ያከራከረ ምድር ከመጀመሪያውም የፍልስጤም ነው ብሎ እንደሚያምን ይናገራል።

ስለዚህም ዛሬ ላይ “ምእራብ እየሩሳሌም ለእስራኤል ፤ምስራቅ ደግሞ ለፍልስጤም መሆን እንዳለበት አምናለሁ”ይላል።

አንዲት ህፃን ስትጸልይ
Ilia Yefimovich

ጋዜጠኛና በመንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የሆነው ሄኖክ ያሬድ ደግሞ “ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከሃይማኖት፣ ከታሪክ፣ ከባህልና ከቅርስ አንፃር ለኔ ልዩ ቦታና ትርጉም አላት፡፡ አንድም በባሕረ ሐሳባችን (ዘመን አቆጣጠራችን) የምንጠቀምበት ዓመተ ምሕረት እንዲሁም ዓመተ ዓለም መነሻውና መድረሻው ከቅድስት ሀገር ጋር ይያያዛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ የተመላለሰባት ናትና” ይላል።

ከአባቱ ጋር ወደ እየሩሳሌም የሄደው ከአምስት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያዊያንም ሆነ ለቤተ እስራኤሎቹ የዐዲስ ዓመት መጀመሩያ በሆነው በወርኃ መስከረም ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በታሪክ ትምህርቶችና በምስል፤ በመስማትም ጭምር የሚያውቃትንና የበርካታ ኢትዮጵያዊያን ሕልም እየሩሳሌምን ማየት ልዩ ስሜት እንዳሳደረበት ያስታውሳል፡፡

“ወሬ ባይን ይገባል እንዲሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ከምስልና ከንባብ ባሻገር ታሪካዊ ኩነቶች የተፈጸሙበት ሥፍራ ላይ መገኘት ምንኛ ደስ ይላል! ዕፁብን ዕፁብ ትለዋለህ እንጂ ምን ሌላ ቃል ታበጅለታለህ! እንዲል ያገሬ ሰው”ይላል ሄኖክ።

ከክርስቶስ ልደት በፊት የንግስት ሳባና ንጉስ ሶሎሞን ታሪክን እንዲሁም የቀዳማዊ ምኒሊክ መወለድን በማስታወስ እነዚህ ነገሮች ኢትዮጵያን ከእየሩሳሌም ጋር እንደሚያቆራኝ ይናገራል።

በተጨማሪም በእስራኤል የሚገኙት የኢትዮጵያ ገዳማት ኢትዮጵያውያንን ከእየሩሳሌም ያስተሳሰረ ሌላ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳል።

ተጓዦችን ወደ እየሩሳሌም ከሚወስዱ የጉዞ ወኪሎች መካከል ቀራኒዮ በእየሩሳሌም አንዱ ነው።

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የድርጅቱ መስራችና ስራ እስኪያጅ ናቸው። ድርጅቱ 2002 ዓ ም ላይ እነዴት ተመሰረተ?

በቀዳማዊ ሐይለስላሴ ስልጣን ዘመን የተመሰረተና ወደ እየሩሳሌም ለኢትዮጵያዊያን ጉዞ የሚያመቻች ማህበር አባል ነበሩ ወ/ሮ እጅጋየሁ።

አሁንም የዚሁ ማህበር አባል ናቸው።

በዚህ ማህበር ወደ እየሩሳሌም ጉዞ ሲያደርጉ በነበረበት ጊዜ የኢትዮጵያዊያን ወደ እየሩሳሌም የመሄድ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ማስተዋላቸው ድርጅቱን ለማቋቋም መነሻ እንደሆናቸው ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ዛሬ ላይ የተለያዩ የጉዞ ወኪሎች ቢኖሩም ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተጨማሪ የጉዞ ወኪሎች ወደ ስራው ሊገቡ እንደሚችሉ እምነታቸውን ይገልፃሉ።

“ዓላማዬ ትርፍ አይደለም።ብዙዎች ያችን ምድር ረግጠው እንዲመለሱ እፈልጋለሁ።እንጀራ ሸጣ ያሳደገች እናትን እንዴት ላስደስት የሚሉ ልጆች ለእናቶቻቸው የሚያደርጉት ነገር ነው”ይላሉ።

ቀራኒዮ በእየሩሳሌም ስራ ሲጀምር ወደ እየሩሳሌም የወሰደው 180 ሰዎችን ነበር።

ያኔ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ጉዞ የሚያዘጋጀው አሁን ግን በዓመት አራት ጉዞዎችን የሚያዘጋጅ ሲሆን ለምሳሌ ለገና በአል 122 ሰዎችን ለመውሰድ መዝግቧል።

እስከ 430 ተጓዦችን የወሰዱበት ጊዜም እንዳለ ወ/ሮ እጅጋየሁ ይናገራሉ።

መስቀል ተሸክመው ሲጓዙ
AFP

መሄድ የማይፈቀድላቸው

ሄደው ይቀራሉ ብለው የሚገምቷቸውን ወጣቶች አይወስዱም።

መጓዝ እንፈልጋለን ብለው ወደ ቢሯቸው የሚሄዱ ወጣቶችን የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲሁም ማስረጃ እንዲያቀርቡ በመጠየቅ እንደማይቀሩ ካላረጋገጡ እንደማይወስዱ ወ/ሮ እጅጋሁ ይናገራሉ።

“የወጣቶች እዚያ ሄዶ መቅረት በእስራኤልና በኢትዮጵያ መንግስትም ተጠያቂ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት የተዘጉ የጉዞ ወኪሎችም አሉ።”የሚሉት ወ/ሮ እጅጋየሁ ብዙ ጊዜ የሚሄዱት ሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።

በተመሳሳይ የትምህርትና የስልጠና እድል አግኝተውም ይሁን ለጉብኝት ቪዛ ለማግኘት የተለያዩ ኤምባሲዎች የሚገቡ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ሄደው ይቀራሉ ተብሎ ስለሚገመት ቪዛ ለማግኘት ይቸገራሉ።

በዚህ መልኩ ካገኙት የትምህርትና የስልጠና እድል የተስተጓጎሉ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ጥቂት አይደሉም።

ጥሩ የሚባል የትምህርትና የስራ ደረጃ ላይ ያሉ ሆነው በተለያዩ ኤምባሲዎች የጉብኝት ቪዛ የተከለከሉ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ ጥቂት አይደሉም።

የእየሩሳሌም ገዳም
THOMAS COEX

የኢትዮጵያ ገዳሞች በእየሩሳሌም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእየሩሳሌም ሰባት ገዳማት አሏት።

እነዚህም ዴር ሱልጣን ፣ኪዳነ ምሕረት፣ቅዱስ ፊሊጶስ፣ ቅድስት ሥላሴ፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ አልዓዛርና ቤተልሔም ናቸው፡፡

ከእነዚህ አንዱ የሆነው ዴር ሡልጣን ገዳም በግዕዝ ደብረ ሥልጣን የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ከጌታ ቅዱስ መቃብር ቤተመቅደስ በስተምሥራቅ ይገኛል።

ሄኖክ እንደሚለው ዴር ሡልጣን ጥንት ንጉስ ሰሎሞን ከኢትዮጵያ ለተለያዩ በዓላት ወደ እስራኤል የሚሄዱ ጎብኚዎችና መልዕክተኞች ማረፊያ ይሆን ዘንድ ለንግስት ሳባ የሰጣት እነደሆነ የቤተ ክርስትያን ታሪክን በመጥቀስ ይናገራል።

ኋላም ገዳም ተመስርቶበት በኢትዮጵያ ነገስታት ሲረዳ መቆየቱን ይገልፃል።

ከቀራንዮ በእየሩሳሌም የጉዞ ወኪል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እጅጋየሁ ንግግር መረዳት የሚቻለው ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ገዳሙን እንደሚረዱ ነው።

የመውደቅ ችግር ለተጋረጠበት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ኢትዮጵውያን እርዳታ ማድረጋቸውን ወ/ሮ እጅጋሁ ይናገራሉ።

ለዘመናት ያወዛገበች ከተማ

ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንም መዲናችን ነች እንደሚሏት እየሩሳሌም በመካከለኛው ምስራቅ ለዘመናት አወዛጋቢ የሆነ ጉዳይ የለም።

እየሩሳሌም በአለም ዓቀፍ ደረጃም በተመሳሳይ መልኩ አወዛጋቢ ናት።

አሁን ደግሞ የአሜሪካ እየሩሳሌምን በእስራኤል መዲናነት እውቅና መስጠትን ተከትሎ የእየሩሳሌም አወዛጋቢነት አይሏል።

እየሩሳሌም በተለያዩ ምክንያቶች ለክርስትና፣ለአይሁድና ለሙስሊሙ የተቀደሰች ምድር ናት።

በዚህ መልኩ የሶስቱም እምነቶች ትኩረት መሆኗም ለዘመናት እየሩሳሌም አከራካሪ ሆና እንድትዘልቅ አድርጓል።

SOURCE    –