12/12/2017

 

” እኔ አሁን የ90 አመት አዛውንት ነኝ።ብዙ ውጣ ውረዶች አይቻለሁ።ከዛሬ 40 እና 50 ዓመት በፊትም ሆነ ዛሬ ከ80 በላይ ብሔሮች በዚህችው በኢትዮጵያ ስ ር ነው የምንኖረው። የተለወጠች የተቀየረች ሀገር የለችንም። የተለወጠ ው ፖለቲካው ብቻ ነው።ሀገሪቷም ሕዝቧም ያው ናቸው።አዲስ ሕዝብ የመጣ የለም።ለምሳሌ አሜሪካ ስንል ሃምሳ ሁለት ግዛት የሚለው ወደ አእምሯችን አይመጣም።ወደ አእምሯችን የሚመጣው ጠንካራዋ አንድ የሆነችው አሜሪካ ምስል ነው።በአድዋ ጦርነት ጠላትን አሽንፈን ኃያላንን ያስደነገጥነው በ10 ወይም በ11 ግዛቶች ተከፋፍለን አይደለም።በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ሥር ሆነን ነው።ጎሰኝነትና ዘረኝነት ኃያል እንሆናለን ብለው ለተነሱት ለጀርመኑ ሂትለርና ለጣሊያኑ ሞሶለኒም አልበጀም።ሺህ ጦር ና ጉልበት ቢኖር ፍቅርና አንድነት ካልሰበክ፣ ተከታዮች ሰይጣኖች ስለሚሆኑ የኋላ ኋላ የትም ተጥለው ነው የሚቀሩት ሂትለርና ሞሰሎኒ መጨረሻቸው ያላማረው አስተሳሰባቸውን የራሳቸው ሕዝብ ስለማይወደው ነው።ስለዚህ አንድነትን መስበክ የፈጣሪን ሥራ መሥራት ነው።ያስከብራል እንጂ አያዋርድም።ዘረኝነት ነው የሚያዋርደው።የሕዝብን አንድነት ለማምጣት የሚደረግ ጥረትን ሁሉ ከሰይጣን በስተቀር ሁሉም ይደግፈዋል።

አጼ ቴዎድሮስ ለ66 ዓመታት ኢትዮጵያን የከፋፈሉ መሳፍንቶችን አጥፍቶ አንድነትን የሰበከ ሰው ነው።ዛሬ በርካቶች በስሙየሚጠሩት ታሪኩ ኩራት ስለሆናቸው ነው።ዛሬ ኢትዮጵያ 10 ቦታ ነው የተከፋፈለችው።ይሄ ጥሩ አይደለም።ይህን ሀገርና ሕዝብ አንድ ማድረግ ያስፈልጋል።ይህን የሚያመጣ ሙሴ ያስፈልገናል።ኢትዮጵያ ክብሯን ጠብቃ የምትኖረው በመከፋፈል ሳይሆን በጽኑ አንድነት ብቻ ነው።
በአድዋ ጦርነት ምኒልክ መሪ ሆኑ እንጂ የተዋጋው ከየአቅጣጫው የተሰበሰበው ኢትዮጵያዊ ነው።እነሱ በአንድነት በአኩሪ ገድል ያስረከቡንን ሀገር ለመበታተን በመጠደፋችን አዝናለሁ።”