ለአንዳንድ ወገኖች ይህ እውነት ሆኖ አይታያቸውም። አገራችን በአይናችን ስር እየጠፋች ነው። ይባስ ብሎ አገሬን እወዳለሁ ሚለው ክፍልም በማወቅ ካለማወቅ አለያም በፍልስፍና ድህነት የአጥፊወቹ አባሪ እና ተባባሪ ሆኖ ሲገኝ ይህችን አገር ማነው ሊያድን የሚችለው የሚል ጥያቄ ያጭራል። ለጥያቄው ግን መልስ የለም። ለአንዳንድ በዝምታ እና ገለልታ ለሚመለከቱ እንዴውም የሁሉም ጉዞ አንድ አቅጣጫ መሆኑ እና አዳማጭ መጥፋቱ ጸሎት ላይ እንዲያተኩሩ ሆኗል። ከሰበካ ቤተክርስቲያኔ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ለአገራችን እና ለሕዝባችን ተብሎ ጸሎት እና እግዞታ ከተጀመረ ሁለት አመቱን ይዟል። 
ዛሬ አገራችን መሪ ሳይሆን አፍራሽ የተከበረባት ናት። ይህ ጉዞ በሁሉም ቦታ በተመሳሳይ ይተገበራል። ተቃዋሚ ነኝ ይልና የሚቃወም እና ከልቡ የሚሰጋው ወያኔን ሳይሆን ሌላውን ተቃዋሚ ነው። ጀግና ሲፈለግ ፈሪ ጀግና ነኝ ብሎ ይወጣ እና ተከታዩን ወደጀግኖች ሰፈር ሳይሆን አሰር ባሰር ወደ ሚደበላለቅበት ይዞ ይሄዳል ሁሉም ከንቱ እንዲሉ መሳቂያና መሳለቂአም ያረጉናል። ትብብር ሲሉት መርጦ ሊተባበር የሚነሳው አንድ ሀሙስ የቀረውን እና የግራ እግሩን አንስቶ የቀኙን ለማስቀደም ሰአታት የሚያስቆጥረውን ይሆን እና ትግሉን ደም ተከፍሎ አገር ወደሚያድን ሳይሆን ጠላቶቻችን እንደሚመኙት ተስፋ ቆራጭነቱን ሲያነግሱት ይውላሉ።        
ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቆረቆር ካለ ከምር የሚያሳዝን እንጅ ሁሉም የሚታይ፣ የሚደመጥ እና የሚዳሰሰው ተስፋ የሚሰጥ አይደለም።

ይህ መለወጥ አለበት።

ህወሓት በቀይ ሽብር ተሳትፋለች

የእኛ እና የእነርሱ የትግራይ ጠባብ ብሄርተኞች ያመጡብን በሽታ መለወጥ አለበት። አሳዛኙ የያትውልድ ቀንዲል የነበሩ። ለሕዝብ እና ሀገር ሲሉ ህይወታቸውን በየአደባባዩ የሰጡት የእነ ተስፋየ ደበሳይ፣ ገብረ እግዚያብሄር (ጋይም በህወሐት የተገደለ)፤ የነጸሎተ ሕዝቅያስ፣ ዮሴፍ እና ብንያም አዳነ። ከአንድ ቤተሰብ አምስት ልጆቻቸው ለሀገር የተሰው የነዚያ ምርጥ የሀገር ልጆች ቀበሌ የነበረችው ትግራይ ዛሬ የጠባብዋን እና ዝቃጭ አተላዋን የህወሓትን መስመር አምነው እና ተጠምቀው በምሁር ማፍሪያ የትግራይ ዩኒቨርሲቲ ግቢወች ጠባብነት ቦታውን ወስዶ አማሮችን እና ኦሮሞወቹን በጠቅላላ ኢትዮጵያውያንን ከሀገራችን ውጡ ብሎ መግደል ከባድ የታሪክ ጠባሳ መጣሉ የሚያሳዝን ነው። ህወሓት ኦሮሞ እና አማራ ብላ ስታጋድል ኖረች ዛሬ እርሷ በተፈጠረችበት እና በምታስተዳድረው ክፍለሀገር ከናት አባቶቻቸው ተነጥለው እንማራለን ብለው የሄዱ ልጆችን መግደል ምን ያህል ብልግና ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ ነው። የዚህ እዳ ከፋዩስ ማነው?

በመሰረቱ በአማራ እና በኦሮሞ ክፍለሀገራት የንብረቱ ሁሉ ባለቤቶች ትግርኛ ተናጋሪ አይደሉምን?

ወያኔ ሀርነት ትግራይ በ1970 ዓም በደርግ በተከፈተው የቀይ ሽብር ዘመቻ ተባባሪ በመሆን ብዙ የጎንደር እና የጎጃም ልጆችን ገድላለች። አስገድላለች። ወደትግራይ አሲምባ የተጓዙ ወጣቶችን በየከተሞች ጸጉረ ልውጥ ናቸው የኢሕአፓ ፋኖወች ናቸው በማለት የወያኔ የከተማ ክንፍ ካድሬወች አስገድለዋል እነሱም ያጋጠማቸውን ሁሉ ገድለዋል። ከቀዩ ሽብር ዘመቻ ጋር በቀጥታ እነ ፍስሀ ደስታ፣ እነ ገብረህይወት ተሳትፈዋል። ድፍን የጎንደር አርሷደር የሚያውቀው ዘግናኝ ግድያወች በገብረህይወት ተፈጽመዋል። በሊማሊሞ ገደል የሰሜን ጎንደር ገበሬወች ኢሓፓ ናችሁ፣ ኢዲዩ ናችሁ ተብለው ልክ አርባ ጉጉ እና በደኖ እንደአደረጉት ቀደም ብለው በሊማሊሞ ገደል ሰው ወርውረዋል። በደርጉ ውስጥ የተሰገሰጉት ወያኔወች የእነ መቶ አለቃ አለማየሁን እና ሞገስን ያስገደሉ፣ ተቀዳሚ ሊቀመንበሩን ሻለቃ አጥናፉ አባተን እና ዋናውን ሊቀመንበር ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ካስገደሉ በኋላ በባዶው ቦታ የተሞሉት እንደነ ፍስሀ ደስታ አይነት የወያኔ ሰርጎ ገቦች በመሆናቸው ኋላ ለተከተለው አንድን ትውልድ የቀጠፈውን ቀይ ሽብር ምክር ሊለግስ የሚችል ህሊና በሌለበት እነዚህ ሰርጎገቦች ቀደም ብሎ በኢሕአፓ የከተማ ፋኖወች በተደናበረው ፈርጣጭ አማካኝነት አካሂደዋል። በጎጃም መቶአለቃ እሸቱ አለሙን በመላክ ዋና ካሳየ አራጋው ተቀምጦ ክፍለሀገሩን እየዞረ ያለፍርድ በየማታው ይገድል የነበረው ውርጋጡ እሸቱ አለሙ እንደነበር ሁሉ፣ ጎንደር ሰው በላው መላኩ ከሰው በላው ወያኔው ገብረ ህይወት ጋር በመሆን ትውልድ መትረዋል። በደቡብ አሊ ሙሳ የተባለ ምንም የማያውቅ ደንባራ ሰው በላ አሰማርተው እነፍስሀ ደስታ እና ፈርጣጩ ትውልድ ጨርሰዋል።

ይህ ዛሬ የምናየው የትግራይ ጠባብ ብሄርተኞች እነርሱ በሚያስተዳድሩት ክፍለ ሀገር ሳይቀር ያለሀፍረት ከሌሎች ክልልሎች ለትምህርት በሄዱ ልጆች ላይ የተፈጸመው ግድያን ሳይ ከአርባ አመታት በፊት ወያኔ በትግራይ እና ከትግራይ ውጭ በቀይ ሽብሩ ተሳትፋ የፈጸመችውን ወንጀል ዳግም እንዳስታውስ አድርጎኛል። በነሀሴ 1973 አም እኔ እና አንድ ጓዴ ተያይዘን በታች አርማጭሆ ያጋጠመን ድንገተኛ ገጠመኝ በደርግ እጅ ብንወድቅም ለገብረ ሕይወት አሳልፈን አንሰጥም በማለት የጎንደር የአርሷደር የደርግ ታጣቂወች እንደለቀቁን እና ከህወሓቱ ገብረህይወት ስለት ማምለጣችን የታወቀኝ በኋላ ገብረ ሕይወት በሄሊኮፕተር አደጋ ሞቶ የወያኔ ሬዲዮ ጣቢያ ሙሾ ሲያወርድ ደርግ የተባለው የነፍሰበላ እንከፎች ስብስብ በክብር የቀበረውን የገብረሕይወትን እሬሳ ማውጣቱን እና መወርወሩን ከሰማሁ በኋላ ነበር። ዞር ብየ ሳስታውስ የጎንደር አርሷደርም ሆነ ወታደር ገብረሕይወት ወያኔ መሆኑን ቢያውቅም በደርግ ስም ይንቀሳቀስ የነበር ነፍሰበላ በመሆኑ ትንፍሽ ማለት አልተቻለም።

ለዚህ ነው ህወሓት ደም ጠጥታ ያደገች እስከ እለተ ህልፈቷም የንጹሀንን ደም አፍሳ የምታልፍ እንጅ ተለውጣ እና ታርማ የምታልፍ አይደለችም። ቀኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተቃውሞውን ከለት እለት የምታባብሰው ይህች ዘረኛ ድርጅት ስትሆን። እኔ ከሞትሁ በሚል የአህያዋ ተምሳሌ የትግራይ ምሁራንን ሳይቀር በጠባብ ጸበል ጠምቃ ይህ ስህተት ነው የሚል ማይት እስኪሳነን አድርጋዋለች። ሕወሐት ትሄዳለች (ትጠፋለች) የትግራይ ሕዝብ ግን ቀሪ እና ቀጣይ ነው። ይህ አሁን እየተሰራ ያለው በደል በይበልጥም በትግራይ ምድር ከሌላ አካባቢ ለትምህርት የሄዱ ለጋ ወጣቶችን መግደል እና ማስገደል ታሪካዊ ስህተትም ነው። ከዚህ በኋላ መፍትሄው ከወያኔ ካምፕ እንደሌለ ሁሉ ተቃዋሚ በሚል እራሳቸውን ስም ሰጠው የሚንቀሳቀሱ ፍሬ ማሳየት ይገባቸዋል። የተቃዋሚ ስብስቦች እኮ አብይ ተግባር ጦር ሰብቆ በሽሆች መርቶ፣ ታንክ አንከባሎ ላይሆን ይችላል። በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጠላታችን የትግራይ ጠባብ ብሄርተኛዋ ህወሓት ምንም መሳሪያ በሌላቸው ወጣት ታጋዮች በተነሳባት ሰላማዊ እና አመጻዊ ተቃውሞ መዳረሻ የጠፋት ግዜ ላይ ደርሳለች። በአንጻሩ የተቃዋሚ ስራው እጅግ የቀለለበት ግዜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው። ሕዝባችን የ logistics and moral support ብቻ ነው የሚፈልገው። እናም ይህ የሞራል እና ከጀርባ ድጋፍ ለመስጠት የሚቻለው የጋራ ትብብር ማሳየት ሲቻል ነው። አለበለዚያ ለትብብር ያልተመቸ ተቃዋሚ ሕዝብ እየሞተ አራት ኪሎ የሚመኝ ከሆነ ከወያኔዋ የተለየ ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!