13/12/2017

ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ሙሉ በሙሉ በቀጥታ የመከላከያ እዝ ስር እንዲሆን እራሱን የፀትታ ምክር ቤት ሲል የሰየመው አካል መወሰኑን ተከትሎ ከብአዴን ጋር እስጥ አገባ የተፈጠረ ቢሆንም ህወሓት ውዝግቡን ወደ ጎን ትቶ በሳሞራ ቀጥተኛ አመራር ሰጪነት መከላከያ ሰራዊቱን ቦታ እያስያዘ ሲሆን ደቡብ ወሎ ደንቆሮ ጫካ እና ደንሳ ከፍተኛ ሰራዊት እንዲሰፍር ተደርጎ የእዝ ማዕከል መደረጉ ተሰምቷል። ሰሜን ወሎ የመከላከያ ሹማምንት የአስተዳደር ቢሮዎችን እየተረከቡ አስተዳደሮች በየደረጃው ከማን አመራር መቀበል እንዳለባቸው እየተነገረ የመኮንኖች እዝ ሰንሰለት እየተዘረጋ መሆኑን የውስጥ ምንጮች አረጋግጠዋል።

ባህርዳር ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል ፤ የክልሉ ፖሊስና ልዩ ኃይል ቦታ ቦታቸውን እንደያዙ ቢሆንም መከላከያና ፌደራል ፖሊስ በእያንዳንዱ የመንደር መታጠፊያ ጭምር ተመድበዋል። ከትግራይ የተመደቡ ተማሪዎች በከተማው ወዳለው “አዲስ አምባ” ወደተባለ ትልቅ ሆቴል ተወስደው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑ ተነግሯል። ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም በርካታ ኦራሎች ወታደር ጭነው በየወረዳው እየተሰማሩ ነው። ከብአዴን ለተሰነዘረው ቅሬታ ህወሓት በኢህአዴግ ፅ/ቤት በኩል ብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ከፍተኛ አደጋ እንደሚፈፀም የታጠቁ ኃይሎች ሰርገው መግባታቸውም መረጃ አለው የሚል ምላሽ በመስጠቱ በአንዳንድ የብአዴን አመራሮች ከቅሬታ ከፍ ያለ ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ እየተሰማ ነው። ለሊቱን መከላከያና ፌደራል በርካታ ተማሪዎችና ወጣቶችን እያሰሩ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ለማጋዝ ማቀዳቸው ብርሸለቆ ድንኳኖች እየተተከሉ መሆኑ ተጠቁሟል።