ዲሴምበር 2017 –

አባቶች “ሥራ ለሠሪው እሾህ ለአጣሪው” እንዲሉ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ ለመግዛት ዘረኝነትን ፖሊሲው ያደረገው ህወሃት ለሃያሰባት ዓመት ኮትኩቶና ውሃ እያጠታ ያሳደገው ዘረኝነት ወይም የጎሰኝነት ገመድ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ መተንፈሻ እያሳጣው ነው። ሰው በሰውነቱ ከዚያም ዝቅ ሲል በዜግነቱ ወይም በኢትዮጵያዊነቱ መከበር ሲኖርበት፣ ህዝቡን በጎጥ አጥር ከትቶ እርስ በርሱ እንዲጋደል ወያኔ ሌት ተቀን ሠርቷል። ለዘመናት የቆየው ኢትዮጵያዊ ትስስርና ባህሉ ህዝቡን በአንድነት ቢያቆየውም  ብዙ ዜጎች በማንነታቸው ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ተሰደዋል፣ ተንገላትተዋል። ጊዜ ይውሰድ እንጂ ኢትዮጵያውያን የወያኔ ተንኮል ከመረዳት አልፈው በቃህ በሚል ፍጻሜውን ለማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ነው።

ዓለምን ያስደነገጠው የሩዋንዳ እልቂት ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ያላቸውን ሩዋንዳውያን ቅኝ ግዥዎቹ  በፊት ገጽታ፣ በፍንጫ ቅርፅ ልዩነት ብቻ ከፊሉን ቱትሲ ቀሪውን ሁቱ ብለው በመከፋፈል መታወቂያ ካወጡላቸው በሁዋላ አንድ እንዳይሆኑ ያስፋፉት የልዩነት ቅስቀሳ ነበር የሚሊዮኖችን እልቂት ያስከተለው። ጎረቤት ሶማልያ ህዝብዋ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ባህል እያለው ሰላሳ ዓመት የተጠጋ ብጥብጥ፣ መጋደል፣ መሰደድና እንደሃገር ያለመኖር ጦስ ውስጥ የገባው የጎሳ ልዩንትን እንደወያኔ ያሉ የስልጣን ጥመኞች ስለአጦዙት ነው። የዘር ፖለቲካ አጥፊ ለመሆኑ ብዙ የዓለም አገራትን ምሳሌ ማቅረብ የሚያስፈልገን አይደለም። ከየቀየው የተፈናቀሉ፣ ገደል የተጣሉና የተዘረፋ አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ሲዳማዎች፣ በቅርቡ የተፈናቀሉ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ኦሮሞዎች፣ ዛሬ በየዩኒቨርስቲው የሚገደሉ ኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ ወጣቶች ምስክር ወይንም ትምህርት አይሆነንም ወይ? በዚህ ግድያ፣ በዚህ ስደት፣ በዚህ መፈናቀል ማን ነው የሚደሰትው? ዘረኝነትን ከሚያቀነቅነው ከይሲ ወያኔ በቀር!

ወያኔዎች ኢትዮጵያውያንን በመታወቂያቸው ላይ እያስገደዱ ብሄራቸውን ሲያስሞሉ ህዝቡ እንደሩዋንዳ እየተነጣጠለ እንዲጫረስ ነበር። የኦሮምያ አስተዳደር መታወቂያ ላይ የሚሰፍረው ብሄር የሚለው እንዲቀር በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል።

የትምህርት ምኩራብ በሆኑ ዩኒቨርስቲዎች ለጋ ወጣቶች ከተለያዩ የአገራቸው ልጆች ጋር እንዳይገናኙ በዘር ሸንሽነው ያደራጁት ይህንን ልዩነት ይዘው እንዲያድጉና በጥላቻ ተለያይትው ለመገዛት እንዲመቹ ነበር። የወጣቶችን ትኩስ መንፈስና ስሜት ተጠቅመው የዘሩት ዘር ሙሉ በሙሉ ባያፈራም የሚያሳዝኑ ጉዳቶች ማድረሳቸው አልቀረም።በነዚህ ዩኒቨርስቲዎች የሽማግሌው የስብሃት ነጋና የዘመዶቹ ልጆች፣ የአባይ ፀሃዬ፣ የስዩም መስፍን፣ የአርከበ እቁባይ፣ የጌታቸው አሰፋና የሌሎችም ዘራፊ ወያኔ ልጆች የሉም። እነሱማ አባቶቻቸውን ተክተው ልጆቻችንን ሊገዙ በቻይናና በምዕራቡ ዓለም ትልልቅ ትምህርት ቤቶች በተዘረፈ የህዝብ ሃብት ይማራሉ። ከፊሎችም በሀሺሽ ናውዘዋል።

በየዩኒቨርስቲና ልዩ ልዩ ተቋማት ያላችሁ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሆይ እንደ እናንተ ባሉ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ላይ እጃችሁን አታንሱ! ጥላቻን የዘራው፣ ተስፋችሁን ያጨለመው የወያኔ ዘረኛ ስርዓት ነው። ይህ እንዲያበቃ የምታደርጉትን ትግል አቅጣጫው እንዲቀይር በተዘጋጀ ወጥምድ ውስጥ አትግቡ።

ህወሃቶች ኢትዮጵያውያን በየጎጣቸውና ጠባብ መንደራቸው ግርግም እንደገባ ክብት በአካባቢያቸው ተወስነው፣ የየክልሉ የወያኔ አሽከሮች ተሹመውባቸው፣ እንዳይንቀሳቀሱ ሲያግዱ ወያኔዎችና ቤተሰቦቻቸው መላ ኢትዮጵያን የመዝረፍ መብት ተጎናፅፈዋል። ለኦሮሞው አጥንቱን ከስክሶ ያስጠበቃት ኦጋዴን እንዳይኖርባት ሲገደልና በግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠረው ሲፈናቀልባት ለህወሃት መኳንንትና ከሲአድባሬ ተባብረው ለወጉን ባለስልጣናት የግላቸው ናት። አማራው ከጠላት እየተዋደቀ እስከ ኦሜድላ ላስጠበቀው አገሩ ለጉቫ፣ ለዳንጉር፣ ለፓዊ ባዕድ ሆኖ የባንዳ የሹምባሽ ልጅ መሬቱንና ማዕድኑን ከአድዋ መጥቶ ይዘርፋል፤ አሶሳ ለኦሮሞው ውጭ አገር ሆና ይፈናቀልባታል፤ ጋምቤላን አኝዋኩ ጠብቆ መቆየቱ ሃጢያት ሆኖበት በመቶዎች ተገድሎ የተረፈው ተባርሮ የህወሃት ባለስልታናትና ዘመዶቻቸው በብቸኝነት (እንዳጋጣኢ ሆኖ ብለዋል) ኢንቭስተር ሆነውበታል። የምክር ቤት አባልም ናቸው። ጉራጌ ሠርቶ ያሳደጋት አዲስ አበባ ባዕዱ ሆና ከመርካቶ ተባርሮ እነሃጎስ ሱቆቹን የነጠቁት መሆኑን መናገር ሀቅ አንጂ ዘረኝነት አይደለም።

ለአንድ ኦሮሞ እንኳን ኦሮምያ ኢትዮጵያ ትጠብበዋለች። ልክ ለወያኔና ለቤትሰቦቻቸው እንደጠበበቻቸው። ለአማራው፣ ለጉራጌው፣ ለሲዳማው፣ ለወላይታው …ለሁሉም እንኳን አባቶቻቸው ተዋድቀው ያቆዩአት ኢትዮጵያ ይቅርና አፍሪካም፣ ዓለምም ይጠብባቸዋል። ቻይናና ወያኔ ከነዘመዶቹ የሚፏልልባት ኢትዮጵያ እንዴት ለዜጎቿ አትሆንም? ሁሉም በጠባብ የዘር አጥር ውስጥ ታስሮ ወያኔና አገልጋዮቹ መላ አገሩቱን ሲዘርፉ ለምን ይፈቀዳል?

የኦሮሞ ቄሮዎች፣ የአማራ ፋኖዎች የጠየቁት “እናንተ ማን ናችሁና ነው ሌሎችን አስራችሁ አገር የምትዘርፉት?” እያሉ ነው። በዚህም ሳያበቃ ለሶስት ዓመት በተካሄደው ህዝባዊ ትግል የተደናገጡትና የጌቶቻቸው አልጠረቃ ባይነት ያሳሰባቸው፣ አገልጋይነታችውም የሰለቻቸው የኢህአዴግ አባላት የህዝባቸውን ሮሮ ከመስማት አልፈው ወያኔን እየተገዳደሩ ነው። ለህወሃት ወፍራም ድመቶች በኦሮምያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ ወዘተ እንደወትሮው መዝረፍ ይቅርና መንቀሳቀስም ይክብዳቸዋል። በዚህም አያበቃም፤ የወያኔን አገዛዝ ህዝቡ በቃህ ስለአለው ፍፃሜው ቅርብ ነው።

አርባ ኪሎሜትር ድንበር አልፎ የገባን ሱዳን ተመለስ ማለት የፈራው ወያኔ እስክርቢቶ ብቻ የያዙትን የዩኒቨርስቲ ልጆች በመግደልና በመቀጥቀጥ የሰራዊቱን ሃያልነት ለማስመስከር ይታትራል። “በሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ” እንዲሉ። ህወህት የዘራው የዘረኝነት መርዝ እንዲጋተው ይገደዳል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም ጊዜ በቆየ የአብሮነት ባህሉ ዘረኝነትን አርክሶታልና። ወያኔ በሰፈረው ቁና ይሰፈርበታል።