13/12/2017

“እኛ” እና “እነርሱ” … እያስባለ በህዝቦች መካከል የመለያየት ግንብ ያስገነባል – ዘ ረ ኝ ነ ት!

ዘረኝነት በሽታ ነው፤ ለዛውም ፈውስ ያልተገኘለት በሽታ፡፡ ዘረኝነትን መሠረት ያደረገ ግጭት ለዓለማችን አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ለዘመናት በዓለም ደረጃ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን አደገ ተመነደገ የሚባልለት የአውሮፓ አህጉርም ጭምር የዚህ በሽታ ሰለባ ነበር፡፡ ችግሩ ይበልጥ የዓለምን ትኩረት መሳብ የጀመረው ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ እንደሆነ የግጭት አፈታት ሙህራን በሰፊው በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ-ዘመን የጤና ተመራማሪዎች ለብዙዎቹ የሰውን ልጅ ለሚያጠቁ በሽታዎች ፈውስ የሚሆን ነገር አበጅተዋል፡፡ ሌላ ቀርቶ በገዳይነቱ እና በአስፈሪነቱ ወደር ለሌለው HIV/AIDS እንኳን ሳይቀር መላ ዘይደውለታል፡፡ ለዘረኝነት ማርከሻ መድሃኒት ግን እስካሁን የተገኘለት አይመስልም፡፡ በሽታው ለዘመናት በዓለም ደረጃ ተንሰራፍቶ የሰው ልጆችን ሲቀጥፍ የቆየ ቢሆንም በተለይ ከታላቋ ሶቭየት ህብረት መፈራረስ በኋላ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ ችሏል፡፡ የዘረኝነት በሽታ እንደሌሎቹ ገዳይ እና ተላላፊ በሽታዎች ሁሉ የትኛውንም የዓለም ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም በተለይ ደግሞ የምስራቅ አውሮፓን (የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ) እና ከሠሃራ በታች ያለውን የአፍሪካ ክፍል (ለአብነት ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ) …አጥቅቷል፤ያጠቃል፡፡ ዘረኝነት በገዳይነቱ ከተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች (ከጎርፍ፣ ከመሬት መንሸራተት እንዲሁም ከአውሎ ነፋስ በላይ) ተወዳዳሪ የማይገኝለት ገዳይ በሽታ እንደሆነ ለማወቅ ብዙም ምርምር ሳያስፈልግ የሩዋንዳንና የቡሩንዲን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ማየት በቂ ነው፡፡ ዘረኝነት በሩዋንዳ በ100 ቀናት ውስጥ ብቻ 800 ሽህ ዜጎችን ቀጥፏል፡፡ በቡሪንዲም እንዲሁ ለ300 ሽህ ዜጎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡
የኛዋ አህጉር አፍሪካ በተለይም ለዘረኝነት በሽታ መስፋፋት ምቹ አህጉር ናት፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ዘረኝነት እጅግ ስር የሰደደ በሽታ ነው፡፡ ይህንን በማስረገጥ ይመስላ በአነቃቂ ንግግራቸው የታወቁት ኬንያዊ ፕሮፌሰር (Motivational Speaker) Prof. Patrick Lumumba (PLO) በአንድ መሳጭ ንግግራቸው ወቅት ‘in Africa …the blood of ethnicity is thicker than the blood of Christ’ በማለት ተናግረዋል፡፡ ንግግራቸውን ለማዳመጥ ከፈለጉ ይህንን ሊንክ ይጫኑ፡፡https://www.youtube.com/watch?v=794pUQrjpVE
ልብ አድርጉልኝ እንግዲህ!!! በአፍሪካችን ውስጥ ዘረኝነት እዚህ ድረስ ነው ልኩ፡፡ በዘረኞች መንደር በክርሰቶስ አምሳያ ተፈጥረህ “ሰው” ሆነህ ሳለ የብሄር ደም (ethnicity) ከሰውነትህ ማንነትም በላይ ነው፡፡ በዘረኞች መንደር “የኛ ሰው” ትባላለህ፡፡ አንተ የትኛውንም አይነት ስህተት ብትሰራ ስህተት ሰራህ አትባልም ምክንያቱም አንተ የነርሱ ሰው ነህና፡፡ የነርሱ ሰው ከሆንክ አትሳሳትም፤ ደረጃህም ከሰውነት ተራ ከፍ ብሎ ወደ መልዓክነት ተራ ይጠጋልሃል፡፡ አንተ ብትዋሽም ሁሌ ትክክል ነህ፣ ብታጠፋም ሁሌ ትክክል ነህ፣ ምክንያት አንተ የነርሱ ሰው ነህ እና፡፡ የምትታይበት መነፅር የሰውነት መነፅር ሳይሆን “የኛነት” መነፅር ነውና፡፡ ምንም ያክል በስራህ ደካማ ብትሆንም ‘ግንባር’ ቀደም ነህ፤ ምክንያቱም አንተ የነርሱ ሰው ነህና፡፡ በዘረኞች መንደር አንተ የትኛውም ቦታ ላይ ለመቀመጥ፤ የትኛውንም ሥልጣን ለመያዝ ዋነኛ መመዘኛህ ተግባርህ አይደለም፡፡ ዕውቀትህ እና ክህሎትህ ያን ያህል ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም፡፡ ቦታው ላይ ተቀምጠህ ብታለማም ብታጠፋም ጉዳያቸው አይደለም ዋና ቁምነገሩ አንተ ብቻ የነርሱ ሰው ሆነህ ተገኝ፡፡ አለቀ ደቀቀ ዋናዋ ጉዳይ እርስዋ ናት፡፡ ሌላው በሁለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚታይ ነው፡፡ ብቻ በአጠቃላይ የነርሱ የተባለ ሰው የሰራው እና የነካው ሁሉ ቅዱስ፤ የሌላ ደግሞ በተቃራኒው ርኩስ ነው፡፡ በነርሱ ዘንድ፡፡
‘የኛ’ የሚል ሲኖር ‘የነርሱ’ የሚል ወገን ደግሞ መፈጠሩ የግድ ነው፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ዘረኝነት ምቹ ሁኔታ የምታገኘው፡፡ ያኔ ዘረኝነት ውሃ የሚያጠታት እና እየኮተኮተ የሚንከባከባት ታገኛለች፡፡ ከሁለቱም አቅጣጫ፤ ከ ’እኛ’ እና ከ ’እነርሱ’ ወገን፡፡ ያኔ ዘረኝነት ትለመልማለች፣ ታብባለች፣ ፍሬም ታፈራለች፡፡ ያንጊዜ ታጫርሳለች፡፡ ሩዋንዳ (በHutus እና Tutsis ) እና ዩጎዝላቪያ( በCroats እና Serbs ) መካከል እንደሆነው፡፡
በነገራችን ላይ የዘረኝነት ምንጯ ብዝሃነት (diversity) እንዳትመስላችሁ፡፡ ይኸ ውሸት ነው፡፡ ብዝሃነት በምንም መልኩ የዘረኝነት እና እሱ የሚወልደው ግጭት ምንጭ አይደለችም፡፡ ይልቁንም ይህንን የበለጠ የሚጠቀምበት የፖለቲካ ኤሊቱ ነው፡፡ ፖለቲከኞች የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ ዘረኝነትን ነጋ ጠባ ይሰብካሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይወጡት ዳገት እና የማይወርዱት ቁልቁለት የለም ፡፡ በሰላም አብሮ የሚኖርን እና የኖረን ህዝብ ለራሳቸው ርካሽ የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ያናክሳሉ፤ ለዘመናት አብረው ተቻችለው በኖሩ ህዝቦች መካከል የጥርጣሬ እና የዘረኝነትን መርዝ ይረጫሉ፡፡ አቧራ የለበሱ እና ዕውነትነት የሌለቸውን የ’እንዲህ ተደረገ’ ታሪክ አቧራዋን እፍ እፍ ብለው አራግፈው ውሸት ደባልቀውባት መርዛቸውን ይረጫሉ፡፡ ዓላማቸው ሲሳካ የዘሩት የዘረኝነት ዘር ሲያፈራ በህዝቦች መካከል ውጥረት ይነግሳል፣ አንዱ ሌላን የጎሪጥ ይመለከታል፡፡
Mariana Tepfenhart የተባለች ፀኃፊ እ.ኤ.አ በ2013 ‘The Causes of Ethnic Conflict’ በተሰኘ ፅሁፏ ማጠቃለያ ላይ… የፖለቲከኞቹ ሴራ ግቡን ሲመታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲህ ብላለች… as their message succeeds, tension increases between groups, communication between the groups fails, and fear dominates the minds of the people. ጉዳዩ በዚህም አያበቃም ፡፡ ፀሀፊዋ ቀጠል አድረጋም ይህንን ብላለች… taken to an extreme, morality does not apply any more to society. People may begin to react with the belief that self-defense is justified and this requires annihilating the other group first. Violence, cruelty and inhumane acts are accepted. That is the beginning of genocide.
ሰው በዘረኝነት በሽታ ሲለከፍ ትላንትና አብሮት ለኖረው፣ ሲቸገር አብሮ ለተቸገረው፣ ሲያዝን አብሮት ላዘነው፣ ለተዋለደው እና ለተካበደው ህዝብ እንኳን የሚራራ አንጀት አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም በዘረኝነት በሽታ አይኑም ይታወራል የርህራሄ ልቡም ይደፈናል፡፡ ፀኃፊዋ እንዳለችው morality የሚባለው ነገር አይኖርም፡፡ በሽታው አቅል ያሳጣል፤ ያሳብዳል፡፡ አንዱ ሌላን ይጠራጠራል፣ አንዱ ሌላን የጎሪጥ ያያል፣ መተማመን ብሎ ነገር ደብዛው ይጠፋል፡፡ “እኛ” እና “እነርሱ” … እያስባለ በህዝቦች መካከል የመገናኛ ድልድይን ሳይሆን የመለያየት የባቢሎን ግንብ ያስገነባል፡፡ ዘ ረ ኝ ነ ት!
እምቢ ለዘረኝነት!!!
Say No to Racism !!!