December 14, 2017

ተስፋዬ ደምመላሽ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕወሓት አገዛዝ ጋር ዛሬ የሚያኪያሂዳቸዉ አካባባዊና ታክቲካዊ ትግሎች በምን መንገድ ነዉ ወደ ዘላቂ አገር አቀፍ ስልታዊ ንቅናቄ የሚሸጋገሩት? ከጽንሱም መሠረቱም ብልሹ የሆነዉና ዛሬ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነቱ ጨርሶ የተሟጠጠበት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ራሱን መለወጥ ቀርቶ መጠገን የማይፈልግ ወይም የማይችል መሆኑን ግልጽ ካደረገ ዉሎ አድሯል። ሕወሓት ሰሞኑን በዉስጡ ባኪያሄደዉ የፓርቲ አመራር ብወዛ (ሹም ሽር) ይህንኑ ግትርነቱን አባብሶና ጠባብነቱን “በአድዋ” ቅኝት ይበልጥ አጣቦ እንዳረጋገጠም ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በበኩሉ የጭቆናዉ ሥርዓት በቃ፣ አገር ከፋፋዩና ማኅበረሰቦች አጋጪዉ ዘረኛ አገዛዝ ጨርሶ ከጫንቃዬ ይዉረድ፣ ከሥር መሠረቱ ይመንገል እያለ ነዉ። አስተዉሎ ላይ በተመሠረተ ተስፋ ሳይሆን በመኞታዊ እሳቤ ብቻ ተመርተዉ ወይም ምናልባት የሥልጣን ፍርፋሪ መለቃቀም ፈልገዉ ከአገዛዙ ጋር “እርቅ” መግባት ይቻላል ባዮችን ሳይከተል የአገዛዙንም የተቃዉሞ ጐራዉንም ጐሣ ተኮር ፖለቲካ ኪሳራ እያሳየ ነዉ። ታዲያ ለዘለቄታዉ በኢትዮጵያ ሥርዓታዊ ለዉጥ የሚመጣዉና አማራጩ የሚገነባዉ በምን አይነት የትግል አነሳስና አኪያሄድ ይሆን? ጥያቄዉ ይህ ይመስለኛል።

የሙሉጌታ ኃይሉ መታሰቢያ ሆኖ በተቋቋመዉ የዉይይት መድረክ ከሁሉት አመት ተኩል በፊት በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። ዛሬ አገራችን ያለችበት ወቅት እርግጥ ሕዝባዊ አመጾችና እንቅስቃሴዎች እየተፋፋሙ ያሉበትና ተደጋጋፊ መሆን በጀመሩ እንቅስቃሴዎቻቸዉ የወያኔን ዘረኛ ፖለቲካ ፉርሽነት ይበልጥ ተከሳች እያደረጉ ያሉበት ወቅት ነዉ። ሆኖም የለዉጥ ትግሉን በሚመለከት ባለፈዉ ጊዜ ያቀረብኳቸዉ ሃሳቦች አሁንም አገባብ አላቸዉ። በኔ አተያይ የትግሉ አገራዊም አካባባዊም አነሳስ (ከየት ?)፣ አቅጣጫዉና መዳረሻዉ (ወዴት ?)፣ እንዲሁም አኪያሄዱ (እንዴት ?) አሁንም ዋና ጉዳዮች ናቸዉ።
እንዲያዉም ዛሬ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እየተጧጧፉ ባሉበት ወቅት ጉዳዮቹ ከመቸዉም ጊዜ ይበልጥ ብርቱ ሆነዋል። የዜጐች፣ የማኅበረሰቦችና የአካባቢዎች እምቢተኛነት እያየለ ሲመጣ፣ ሕዝብ በቃ ብሎ እንቅስቃሴዉን ሲያፋፍም፣ የትግሉ ስልታዊ ቅንብርና አቅጣጫ ሰጪ አገራዊ ሃይሎችም ተሰባስበዉ፣ ከሕዝባዊ ትግሉ ጋር ተመዛዝነዉ፣ ይበልጥ ድርጁና ተንቀሳቃሽ መሆን ይኖርባቸዋል።

ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት አገር ዉስጥና ዉጭ በኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ፣ የምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን አካባቢዎች የተደረጉት ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች ግልጽ ያደረጉት ነገር ቢኖር በስልታዊ ራዕይ የተቀረጸ፣ የተደራጀና የተመራ አገር አቀፍ የተቃዉሞ ትግል መገንባት አስቸጋሪነትን ነዉ። የተቃዋሚ ወገኖች፣ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን እጥረት ኖሮን አያውቅም፤ በተለይ በዳያስፖራዉ የተቃዉሞ ጐራ የድርጅትና ሚዲያ አርብቶ አደሮች እጥረት የለም። በሃቀኝነት ለአገር የሚቆረቆሩ ዜጐችና ስብስቦች ቁጥር አላነሰም። በአገራዊነትም ሆነ በነገዳዊነት ደረጃ የበደል ተቀባይነት ስሜት ወይም የተጐጂነት ስነልቦና አልተጓደለም።ነገር ግን አንድ ጉልህና መሠረታዊ ጉድለት ነበረ፤ አሁንም አለ። ይኸዉም የሕወሓትን አገዛዝ ተቃዋሚ የሆኑ ነገደ ብዙ አገር ወዳድ ግለሰቦችና ስብስቦች በተለያዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴዎቻቸዉን በጋራ ኢትዮጵያዊነት አገናኝተዉ፣ አዋህደዉና አማክለዉ መመሥረት፣ ማነፅና በሂደት ማዳበር አልቻሉም።
ይህ ያፈጠጠና ያገጠጠ ክፍተት ደግሞ የአገሪቱን የተለያዩ አካባባዊና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች፣ ብሶቶችና እንቅስቃሴዎች ለወያኔ ደባና አፈና ያጋለጠ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የዉስጥም የዉጭም ሰርጐ ገብ ሃይሎች ጥምዘዛ ይበልጥ ያመቻቸ ነዉ። ስለዚህም ነዉ ሃቀኛ ወይም ሙሉ (integral) ብሔራዊ ቅርጽና ይዘት ሳይኖራቸዉ ኢትዮጵያን ከመፈረካከስ እናድናለን በሚሉ የዉስጥም የዉጭም ዘር ተኮር ሃይሎችና ወገኖች እንቅስቃሴዎች የትግሉ ምህዳር የተጣበበዉ። በሻቢያ ድጋፍና ዋና ነጂነት የግንቦት ሰባት ድርጅት ለአስርተ አመት ባለበት ሲሽከረከርበት የቆየዉ የፖለቲካ ጐዳና፣ ኢትዮጵያን በአንድነትና ሉአላዊነት የትም የማይወስድ “ሁለ ገብ” የትግል መንገድ፣ በዚህ አገባብ የሚታይ ነዉ። በተጨማሪ ድርጅቱ ዛሬ ጥቂት የጐሣ ቡድኖች አሰባስቦ የሚነዳዉ አገራዊ ህልዉናችንንና ንቃተ ህሊናችንን ፈጽሞ የማይመጥን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ” እንዲሁ የምንገነዘበዉ ነዉ።

በኔ ግምት ይህ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ዉስብስብ ዉጥረት ለነገደ ብዙ ለዉጥ ፈላጊ አገር ወዳድ ዜጐች፣ የጐበዝ አለቆች፣ አርበኖች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ወገኖች የደቀነዉ ዋና ጉዳይ የትግሉ ሙሉ አገራዊ አነሳስና አቅጣጫ የሚረጋገጠዉ እንዴት ነዉ የሚል ነዉ። በሌላ አባባል፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ብሔራዊነት የዛሬዉ የለዉጥ ትግል መነሻም መድረሻም የሚሆነዉ በምን መንገድ ነዉ? በቀጥታና ባንዳፍታ ከረቂቅ አለም አቀፍ የፖለቲካ ሃሳቦች (በተለይ “ዲሞክራሲ” ከምንለዉ) ብድግ ተብሎ ይሆን? ከግዛታዊ/አካባባዊ ምንነት (ከጐንደር፣ ጐጃም፣ ወሎ፣ ሽዋ) ተነስቶ ወይም የዘር መለዮን አስቀድሞ (በኦሮሞነት፣ በአማራነት፣ ወዘተ) ነዉ? ወይስ ደግሞ በዘመናዊ የስቪክ ብሔርተኝነት ጽንሰሃሳብ ብቻ ተንደርድሮ? ኢትዮጵያዊነት እንደ እሴት መሃል (value center) እነዚህን ግብአቶች አገናኝቶ፣ አሸጋሽጐና አዋህዶ የአንድ ሕዝብና የአንድ አገር ትግል አካላት ማድረግ አይችልም ወይ?

ኢነዚህን ጥያቄዎች አማክዬ ነዉ ይችን ጽሑፍ በሃሳብ ፈጠር ዉይይት መልክ ያቀረብኩት። አቀራረቡ በንጹሁ ፈጠራ ሳይሆን እውን አመለካከቶችና አቋሞች ላይ የተመሠረተ ነዉ። የሚከተሉት ገጾችና ተከታይ ጽሑፎች የያዙትን ሃሳብ ወለድ ዉይይቶች ያዘጋጀሁት ከተዉኔት ወይም ሥነ ጽሑፋዊ አላማ ተነስቼ ሳይሆን ወሰብሰብ ያሉ የአገር ጉዳዮችንና ከጉዳዮቹ የፖለቲካ ቀረጻ ጋር የተያያዘ ጽንሳዊ ሃሳብን (conceptual thought) ቀለል ላለ ግንዛቤ ለማመቻቸት ነዉ። ይህ አቀራረብ ብዙዉን ጊዜ በድፍኑ ወይም በድብስብሱ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም ሰፋና ጠለቅ ባለ (ምሁራዊ) የዕዉቂያ ጉጉት ሳይፈተሹ ያአነጋገር ዘይቤ ሆነው ብቻ የሚዘዋወሩ “ሃሳቦችን” በጥይይቅና ምልልስ ከፈትፈት በማድረግ የላቀ ትርጉማዊ ይዘት ሰጥቶና አጣርቶ መጨበጥ ያስችለናል የሚል ግምት አለኝ።

የሃሳብ ወለድ ዉይይት መንገዱ ብዙዉን ጊዜ በመደበኛ ጽሑፎቼ በቀጥታ የማቀርባቸዉን ለአንዳንድ አንባቢያን በቀላሉ ተገንዛቢ ያልሆኑ ትንተናዎችና አስተያየቶች ለጥያቄዎች በመክፈት ይበልጥ ተደራሽና ተረጂ ለማድረግ የሚያግዙ ትችቶች ማስተናገድም ያስችላል። በዚህ መንገድ የፈጠራ ጭውውቱ አስተያየቶቹን ይበልጥ ጥራት ለመስጠትና ተገንዛቢ ለማድረግ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ። ጭውውቱ ሦስት የተያያዙ ክፍሎች አሉት። ይህ የመጀመሪያዉ ክፍል የዛሬዉ የለዉጥ ንቅናቄ ሙሉ አገራዊ አነሳስና አቅጣጫ ጉዳይ ላይ ያተኩራል። ሁለተኛዉ ደግሞ አማራጭ አካባባዊ/ማህበረሰባዊ ማንነት ወይም ራስነት ግንባታንና አገራዊ አገባቡን የሚቃኝ ነዉ። ሦስተኛዉ የውውይት ክፍል በሥርዓታዊ ለዉጡ ንቅናቄ ከብሔራዊ ህልዉናችን ጋር የሚናበብ የፖለቲካ አስተሳሰብና ስልት ጉዳዮችን የሚያነሳ ይሆናል።

የዉይይቱ ተሳታፊዎች

በዛሬ አንዳንድ ብሔራዊና ፖለቲካዊ የለዉጥ ጉዳዮች ዙሪያ ጭውውት የሚያደርጉት የአገራቸዉ ሁኔታ የሚያሳስባቸዉ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩና በቅርብ የሚተዋወቁ አራት ኢትዮጵያዊያን ናቸዉ። ውይይቱን የሚመራዉ ጋዜጠኛ ፋና አሰፋ አንዱ ተካፋይ ነዉ። ፋና በትምህርትና በልምድ የዳበረ የጋዜጠኛነት ሙያ ያለዉ ነዉ። በአንድ የዉጭ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ዉስጥ የሚሠራ ምሁር ሁለተኛዉ የዉይይቱ ታዳሚ ነዉ፤ ዶ/ር ነጸረ ጥሩነህ ይባላል። የሦስተኛዉ ተሳታፊ ስም ዘርይሁን አበራ ነዉ። አቶ ዘርይሁን የሰብአዊ መብቶች ድርጅት አባል የሆነ አገር ወዳድ አክትቪስት ነዉ። አራተኛዋ የዉይይቱ ታዳሚ በኮሌጅ የማኅበረ ሳይንስ መምህር የሆነች ፕሮፌሰር ልባዊት ጐበዜ ነች። ተዋዋቂዎቹ ታዳሚዎች ዶ/ር እገሌ፣ አቶ እንተኔ ሳይባባሉ በስሞቻቸዉ ብቻ ነዉ የሚጠራሩት። ይህ የሆነዉ አካዳማዊ ማዕረጐቻቸዉን በመርሳት ወይም የሚገባቸዉን ከበሬታ በመነፋፈግ ሳይሆን ጥይይቃቸዉንም ምልልሳቸዉንም ቀጥተኛና ግልጽ አድርጐ ለማቀላጠፍ ብቻ ነዉ።

ነፃ ዉይይቶች

ክፍል አንድ

የዛሬዉ የለዉጥ ትግል አገራዊ አነሳስ/አቅጣጫ
(ፋና አሰፋ፣ ነጸረ ጥሩነህ፣ ዘርይሁን አበራ፣ ልባዊት ጐበዜ)
ፋና  ለዉይይታችን መግቢያ ያህል አንድ ነገር ለማስታወስ፣ ማንኛዉንም ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ አላማ ስንከተል አነሳሳችንን በተገቢዉ መንገድ ሁሉ አረጋግጠን ካጠናከርን አኪያሄዳችን ዘላቂና ፍሬያማ የመሆን ዕድሉ ከፍ እንደሚል እንገነዘባለን። ዛሬ በኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል የአንድነት ወይም የአገራዊ አነሳስ ችግር አለ ትላላችሁ? ካለስ ምንድን ነዉ ተግዳሮቱ? ነጸረ፣ እስቲ ካንተ ልጀምርና ምን ትላለህ?

ነጸረ  አዎ፣ መሠረታዊ ችግር አለ። ችግሩን በቅጡ ለመጨበጥ አንድነት ወይም አገራዊነት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ መጀመሪያ ግልጽ ማድረግ ይጠቅማል። የቃሉን ትርጉም የሚመለከቱ ሃሳቦችና መልክቶች በየጊዜዉ በጽሑፎቼ አቅርቤያለሁ ግን ፍችዉ ይበልጥ አጣሪ ዉይይት ስለሚያስፈልገዉ የናንተን አስተያየቶች መስማት እፈልጋለሁ። በቅድሚያ ግን እኔ ስለተጠየኩ አንድ ሁለት ነገሮች ማለት እችላለሁ?

ፋና  እንዴታ! ቀጥል።

ነጸረ  ከጥቂት አመታት በፊት፣ በፈረንጆቹ 2011 ዓ.ም ይመስለኛል፣ የግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበረዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ “የዲሞክራሲን ጉዳይ ሳናነሳ አንድነት የሚለዉን ቃል መጠቀም አንፈልግም” ያለዉ ትዝ ይለኛል፣ ድርጅቱን ወክሎ ሲናገር። ለምን ሲባል ፋሺስታዊም የሆነ አንድንት ስላለ፣ ወያኔም በአንድነት ስም ፕሮፓጋንዳ ስለሚሠራ የዲሞክራሲን ጥያቄ ማስቀደም ያስፈልጋል በማለት ነበር የመለሰዉ። በተመሳሳይ መንገድ ሌላዉ የግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ ብሔራዊ ታሪካችንን መሠረት አድርገን የዛሬዉን አገራዊ ማንነታችንን ወይም አንድነታችንን ማረጋገጥ የማይቻል እንደሆነ ነግሮናል። ለዚህም የሰጠዉ ምክንያት የታሪክን እዉነትነት ወይም አተረጓጐም አስመልክቶ በአንድነት ደጋፊ ሃይሎችና “በታሪክ ተጐጅዎች” መካከልም ሆነ በታሪክ ተመራማሪዎች ጐራ ስምምነት የለም የሚል ነበር። እንግዲህ…

ልባዊት  ይቅርታ ነጸረ፣ ላቋርጥህና አስተሳሰቡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥልቅ ታሪካዊ ሥሮች ያሏቸዉ አገሮችን ተጨባጭ ህልዉና ከታሪካቸዉ የአመለካከት ልዩነቶችና ክርክሮች ጋር የሚያምታታ ነዉ። የአስተሳሰቡ ቅርብ ምንጭ የግንቦት ሰባት ድርጅት ቢሆንም ዋና ፍልቀቱ በአገሪቱ የሰፈነ የአብዮተኝነት ባህል እንደነበረ እናዉቃለን። ባህሉ ወሰንና ቅጥ ባጣ ፖለቲካዊ “ተራማጅነት” የአገሪቱን ነገዳዊ ማኅበረሰቦች ድፍን የበደል ተቀባይነትና የተጐጂነት ማንነት ሰጥቶ በጋራ ካዳበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልዉና የመለየትና የማግለል አዝማሚያ የነበረዉ ነዉ። ልምዱ ዛሬም በጥሬ ዘረኝነት ተባብሶ አገር ጐጂና ተቃራኒ በሆነ የወያኔ ቅጂዉ ነግሦብናል።

ነጸረ  ልክ ነሽ፤ የተወሰኑ የአንድነት ደጋፊዎች፣ የጐሣ ፖለቲካ ወገንተኞችና የታሪክ ተመራማሪዎች በክርክር ሆን ብለዉ የሚይዟቸዉ የታሪክ ግንዛቤዎችና አተረጓጐሞች በአንድ እርከን የሚታዩ ሲሆኑ፣ ታሪክ በተጨባጭ ሂደት የሚፈጥረዉ የአገር መኖር ሁኔታ ደግሞ ራሱን ችሎ የሚታይ ሌላ የታሪካዊነት ደረጃ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር ናት ስንል በዚህ የመኖር (existential) አገባብ ነዉ። ልባዊት እንዳስተዋልሽዉ የግንቦት ሰባት መሪዎች አቀራረብ የአገር ታሪክ አመለካከትንና አገነዛዘብን ከእዉን ታሪካዊ የአገር ህልዉና ጋር ይደባልቃሉ።

ፋና  አያይዘዉም የፖለቲካ ሃሳቦችን፣ በተለይ ዲሞክራሲን፣ ከአገር ህልዉና ያስቀድማሉ። ወይም አገራዊነትን ከሆነ ያልሆነ ርዕዩተአለማዊ ሥርዓት ወይም ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ጋር እኩል አድርገዉ ያያሉ። አገር ከተለዋዋጭ ፖለቲካና አገዛዝ ይቀድማል፣ ይተልቃልም። ዘሪሁን እዚህ ላይ የምትለዉ አለህ?

ዘርይሁን  አዎ፣ ለነጸረ ጥያቄ አለኝ። ለብዙ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ አገራዊ ምንነት ወይም አንድነት ልቆ ትርጉም አዘል የሆነዉ በጥንት የጥዋቱ ታሪካዊ-ባህላዊ ምንጮቹ ወይም ባለፉ ድርጊቶቹና ክንዉኖቹ ሳይሆን ዛሬ ሊያደርግ በሚችለዉ፣ በሚገባዉም፣ የስቪክና የፖለቲካ ለዉጥና እድገት ነዉ። ታሪካዊ የአገር ማቅናት ሂደትን በተጐጂነት ስሜት በማስታወስ ዘመናዊ ሃሳቦች ላይ ብቻ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ለሚሹ የፖለቲካ ሊህቃንና የዘዉግ ስብስቦች ምን ትላለህ?

ነጸረ  ጥሩ ጥያቄ ነዉ፤ የአንድነታችን ጥልቅ ታሪካዊነትም ሆነ ወደፊት ተመልካች የፖለቲካ መርሆች ላይ የተመሠረተ ዘመናዊነት ለብቻዉ ወቅታዊዉን የኢትዮጵያ/ኢትዮጵያዊነት እዉነታ በብቃት ሊይይዝ ወይም ሊገልጽ አይችልም። አገራዊ ቁም ነገሩ ያለዉ በተናጠል ከታሪካዊዉ ወይም ከዘመናዊዉ የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችን ገጽታ ላይ ሳይሆን በሁለቱ የኢትዮጵያዊነት መለያዎች ተዋህዶ ሊፈጠር የቻለዉ፣ ወደፊትም ይበልጥ ሊዳብር የሚችለዉ የርስ በርስ ተጐለባባችነትና ተደጋጋፊነት ነዉ።

ልባዊት  ዘመናዊ ሃሳቦች በዛሬዉ የለዉጥ ትግል አስፈላጊ ናቸዉ፣ በትግሉ ወሳኝና ተገቢ ቦታ አላቸዉ፣ ግን ታሪካዊ ህልዉና የሌላት፣ ኖራ የማታዉቅ “አዲስ” ኢትዮጵያ ከዜሮ ተነስተዉ አይፈጥሩም ማለትህ ነዉ?
ነጸረ  አዎ…

ፋና  ይቅርታ ነጸረ፣ የአገር ህልዉና ከፖለቲካ ሃሳብ ጋር ስላለዉ ወይም ሊኖረዉ ስለሚችል ግንኙነት በውውይታችን ሦስተኛ ክፍል ሰፋ አድርገን የምንነጋገርበት ጉዳይ ስልሆነና ከዚህ የመጀመሪያዉ ክፍል ውይይታችን ርዕሰ ነገር ብዙ እንዳንወጣ ለልባዊት ጥያቄ የምትሰጠዉን ምላሽ አጠር ብታደርገዉ ይመረጣል።
ነጸረ  መልካም፤ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ሌሎች ተያያዥ እሴቶች በዛሬዉ ኢትዮጵያን የመታደግ፣ የማደስ እና መልሶ የማጠናከር ንቅናቄ ተገቢ ቦታ እንዳላቸዉ አይካድም። ግን በንጹሁ ፖለቲካዊ በሆነ አነሳስና አኪያሄድ “አዲስ” አገር ሊፈጥሩ አይችሉም። ታሪካዊ ሥሮች ያዳበረ ብሔራዊ ባህል በሌለበት ሁኔታ (ለምሳሌ በኤርትራ) ግልብ ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት አዲስ አገር ፈጣሪ ሊሆን ይችል ይሆናል። ግን አገራዊነት ወይም አንድነት አይነት አይነት አለዉ። በሻቢያ አፈጣጠሩ የኤርትራ “ብሔራዊ” ሕይወት ከጽንሱም ከቅርጹም በብቸኛ ወገንተኝነትና ፈላጭ ቆራጭ ፖለቲካ የተጨናገፈ ነዉ። እንደ ኢትዮጵያና ቻይና ያሉ ረጅም ታሪክ ወለድ ህልዉና ያላቸዉ አገሮች ግን የአምባገነናዊ አገዛዝ ችግር ቢገጥማቸዉም ዘመናዊ የተባለ ፖለቲካ ፈጠራ ዉጤቶች ሊሆኑ አይችሉም።

ዘርይሁን  ሆኖም ግን የብሔራዊ ባህላችንን ድክመቶችና ጉድለቶች በፖለቲካ ሃሳብ ተነሳስቶ ከመተቸትና ከመገምገም፣ ባህሉ በመላ የአገሪቱ ዜጐችና ባህላዊ ማህበረሰቦች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት በሚያፈራ መልክ የሚለወጥበትንና የሚሻሻልበትን መንገድ ከመፈለግ ወደ ኋላ ማለት የለብንም። እንደ አገር “ይበልጥ እንከንየለሽ አነድነት” ለመፍጠር የማያቋርጥ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ተሸጋጋሪ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ እንስማማለን?

ፋና  እርግጥ እዚህ ላይ ምንም ያህል የሚያከራክረን ነገር የለም። ኢትዮጵያዊነት እንደ አገር  የሚሰማንና የምንኖረዉ (our felt and lived experience) ብቻ ሳይሆን በንቁ ሃሳብ አዙረን የምናየዉ፣ ለችግሮቹ ተገቢ መፍትሔዎች የምንፈልግለት፣ አሻሻይ ለዉጥ የምናመጣለትና የምናጠናክረዉ ብሔራዊ ማንነታችን ነዉ። ግን ነጸረ ወዳንተ ልመለስና የዚህ የመጀመሪያ ዉይይታችን ክፍል ዋና ርዕሰ ነገር ላይ ይበልጥ ለማተኮር፣ የዛሬዉ የለዉጥ ትግል አገራዊ አነሳስ እንከኖች ምንድን ናቸዉ እንላለን? ሙሉ ኢትዮጵያዊ አነሳስስ ምን ይመስላል?
ነጸረ  ችግሮቹን በሁለት ደረጃዎች ወይም ሁኔታዎች ለይተን ማየት እንችላለን። አንዱ ሁኔታ የተለያዩ የፖለቲካ፣ የስቪክ፣ የምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ወገኖች በሚያደርጓቸዉ የአገርም የነገድም አድን ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች በአገራዊ መንፈስ እርስ በርስ አለመጠያየቅና ቅን መልስ አለመሰጣጣት ይከሰታል። በእንቅስቃሴዎች አለመገናዘብ፣ አለመጣጣምና አለመተባበር ጐልቶ ይታያል። ተቃዋሚ ወገኖች በጋራ የክርክርና ዉይይት መድረኮች ከመገንባት ይልቅ በብቸኝነት በየፊናቸዉ ብን ብን ይላሉ፤ ሚዲያና ድርጅት አርብቶ አደሮች በመሆን ወገንተኝነትን ቅድሚያ ይሰጣሉ። ይህን አዝማሚያ የሚያሳይ ባለፈዉ ሰሞን ያጋጠመኝን ጽንፋዊ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። የአማራ ማኅበረሰብ ራስ አድን ንቅናቄ ከአገራዊ የለዉጥ ትግሉ ጋር ያለዉ ትስስር ላይ ያተኮሩ ሃሳቦች በቅን አማራነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻ ሳይሆን በምሁራዊ የዕዉቂያ ጉጉትም ተነሳስቼ ለአንባቢያን አስተያየቴን አካፍዬ ነበር። ነገር ግን በብቸኛ ወገንተኝነት ራሱን የአማራ ማንነት ፖለቲካ ጐራ ካደረገ አንድ ግለሰብ ጽሑፌ በምላሹ የጫረዉ “ካድሬያዊ” የቃላት ጥይቶች ተኩስ (polemical reaction) ከጽሑፌ አላማና መንፈስ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረዉም። ሰዉዬዉ ነቀፋ ማቅረብ መብቱ ነዉ፣ ግን ሊነቅፈዉ የተነሳዉን ነገር በቅጡ መገንዘብ ያልፈለገ ወይም ያልቻለ ነበረ። ይህን ስትል ምን ማለትህ ነዉ ብሎ ከኔ ጋር ዉይይት ማድረግና ሃሳቤን በሃሳብ መግጠም ግድ አላለዉም። ይህን ከማድረግ ይልቅ ለአማራዉ ተቆርቋሪነቴን የካደ፣ እንዲሁም የአገር ጉዳዮችን በሚመለከት ትንተናዬን ምንም ያላስተዋለ፣ “ሌሎችን ዝቅ አድርጐ ራስን ከፍ ማድረግ የምሁርነት ሙያ አደለም” የሚል እዚህ ግባ የማይባል የወቀሳና የዉንጀላ ናዳ አወረደብኝ።

ልባዊት  እንዳነበብኩት መጣጥፍህ የጫረዉ የተንዛዛ “እጥፍ ድርብ” ተቃርኗዊ መልስ በግልቡ ጽሑፍህ ላይ ያነጣጠረ ይምሰል እንጂ እዉን ኢላማ የለሽ ሆኖ ነዉ የታየኝ። የዉንጃላዉ ግርድፍ ዲስኩር ደስኳሪዉን ራሱን ነዉ ያጋለጠዉ። ያንተ ተቺ ትንተና ወዲህ የሰዉዬዉ ቅጥ ያጣ ተራ የትንተናህ ነቀፋ ደግሞ ጨርሶ ወዲያ ነበር። ሰዉዬዉ ራሱን (ከነተቀጣይ ድርጅቱ) ብቸኛ የአማራ ተቆርቋሪ አድርጐ አይቶ ሌላዉ ሁሉ እኔን/ድርጅቴን ተቀናቃኝና አጥቂ ነዉ በሚል ፈሩን የለቀቀ እሳቤ ነዉ “ምላሽ” የሰጠህ። ምላሹ (ምላሽ ከተባለ) ያቀረብከዉን መሠረተ ሃሳብ እንደ ሃሳብ ለመጨበጥና ለመተቸት ምንም ያህል ጥረት ያደረገ አልነበረም። እንደገባኝ፣ በተለይ ወጣቱ የአማራ ትዉልድ ላይ ያተኮረ መልክት ማስተላለፍ የፈለገዉ ጽሑፍህ የአማራ ህልዉና ወይም ራስነት ከኢትዮጵያዊነት ወርድና ስፋት ጋር የተያያዘ እንደሆነና ይህ ደግሞ ለአማራዉ ማኅበረሰብ ራስ አድን ትግል ስልታዊ እንድምታ እንዳለዉ ሊያሳይ የሞከረ ነበር። ወንጃይህ ግን ይህ ሙከራህ  ትክክል ነዉ ወይም አደለም የሚል ሃሳብ አዘል መልስ ሊሰጥህ አልፈለገም ወይም አልቻለም። የአማራዉ የህልዉና ተጋድሎና ኢትዮጵያን የመታደግ ትግል በተናጠል፣ በሁለትዮሽና በልዩነታቸዉ የቅደም ተከተል አኪያሄድ ያላቸዉ ናቸዉ ወይ የሚል ተቺ ጥያቄ አነሳህ። ጥያቄዉን ማንሳትህ ራሱ በሰዉየዉ ቤት ለአማራዉ አለመቆርቆር ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡን መቃወምና ለጥፋት መዳረግ ነዉ። ትልቁ የአማራ ማኅበረሰብ እንደ ሰዉዬዉ አይነት ደጋፊ እያለዉ ምንስ ተቃዋሚ አስፈለገዉ?

ፋና  ከኔም አነባበብ ሰዉዬዉ የምናገረዉን ሁሉ አዉቃለሁና በጥያቄም ሆነ በምክንያታዊ ሃሳብ አታደናግሩኝ ባይ ይመስላል። በአንድ በኩል አማራዉ በማላ አገሩ ኢትዮጵያ በነፃነትና በሰላም ኗሪ ሆኖ የመቀጠል መብቱን ማረጋገጥ እንዳለበት ይነግረናል። ግን በሌላ በኩል አማራዉ ነገዳዊ ማንነቱን ከኢትዮጵያዊነቱ ለይቶ “በማስቀድሞ” ነዉ ለዘለቄታዉ ደህንነቱን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚጠብቀዉ ይላል። እነዚህ አባባሎች ከሥነ አመክንዮ አኳያም ሆነ በታሪካዊ አመለካከት የሚፃረሩ ናቸዉ። የአማራዉ አስፈላጊ ራስ አድን ተነሳሽነትና ኢትዮጵያን የመታደጉ ንቅናቄ ጉዳዮች ከአማራ (በሰፊዉ ደግሞ ከኢትዮጵያ) አገር ወዳድ ወገኖች የትግል አቅጣጫና ስልት የሚያዳብሩ ቀጣይ ዉይይቶችና ምክክሮች ይጠይቃሉ። ነገር ግን ባመዛኙ ግለሰባዊ በሆነ “ድርጅታዊነት” ተንቀሳቃሹ የጽሑፍህ “መላሽ” ለነዚህ አይነት ዉይይቶችና የሃሳቦች ልዉዉጥ አዝማሚያም ሆነ ትዕግሥት ያለዉ አይመስልም…

ዘርይሁን  ፋና፣ ያነሳኸዉ ዋና ጥያቄ ላይ መልሰን እናተኩርና፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ወገኖች ከሚያሳዩት በፖለቲካ አስተሳሰብና እንቅስቃሴ አለመገናዘብና አለመግባባት ባሻገር ምን አይነት ሌሎች የአገራዊ አነሳስ ችግሮች አሉ? ነጸረ በሁለተኛ ደረጃ የፈረጅካቸዉ እንከኖች ምንድን ናቸዉ?

ነጸረ   ለዛሬዉ የለዉጥ ትግል ዘላቂ ስኬታማነት አገራዊ አቅጣጫና አነሳስ ወሳኝ እንደሆኑ ተስማምተናል። ሆኖም ወደ ሰላሳ አመት ከሚጠጋ አገር ከፋፋይና አሰናካይ ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ ዘመን በኋላ ሙሉ ብሔራዊነት ወይም ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ዝግጁ ሆኖ ባንዳፍታ የቀረበልን የትግል መነሻና መንደርደሪያ ወይም መሣሪያ እንዳልሆነ አንዘነጋም።

ልባዊት  ምን ማለትህ ነዉ? መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጋራዉ ብሔራዊ ሕይወት በአገዛዙ የተቀናበሩ ዉስጣዊ ድርጊቶችና ጥቃቶች እርግጥ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፤ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ግን አገራዊ ሕይወታችን አካቶ ጠፍቷል ማለትህ አይመስለኝም።

ነጸረ  የለም፣ እንደሱ ማለቴ አደለም። ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ሕዝብና አንድ አገር አለን፣ ጨርሰን አልጠፋንም። ከወደቅንበት ሁኔታ ተንገዳግደንም ቢሆን የምንነሳዉ በታሪክ ሂደት በዳበረ፣ ግን ለአስርተ አመታት አፈናና መከራ በበዛበት የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችን ነዉ። ላሳስባችሁ የፈለኩት የጋራ ብሔራዊ ባህላችንንና ንቃተ ህሊናችንን ማደስ፣ መልሶ ማጠናከር፣ አገራችንን ከጥፋት የማዳኑ ተጨባጭ ትግል ዋና አካል መሆኑን ነዉ። መሉ ኢትዮጵያዊነት የዛሬዉ የለዉጥ ንቅናቄ መነሻ ብቻ ሳይሆን መድረሻም እንደሆነ፣ የተግሉ መሣሪያ የምናደርገዉም የወያኔ ሞገደኛ አገዛዝ ያጠበበዉን አድማሱን እያሰፋን፣ አገዛዙ የሰጠዉን በጥልቅ እንከናማ የሆነ ቅርጽና ይዘት እያረምን፣ የተከፋፈሉ አካላቱን እያስተባበርን፣ እንዲሁም የጠፋዉን መልሰን እያለማን መሆኑን ለማስታወስ ነዉ።

ፋና  እና ታዲያ ችግሩ ምንድን ነዉ? በዛሬዉ የለዉጥ ንቅናቄ በሁለተኛ ደረጃ የፈረጅካቸዉ የአገራዊ አነሳስ እንከኖች ከዚህ ማሳሰቢያህ ጋር ግንኙነት አላቸዉ? ካላቸዉስ ከግንኙነታቸዉ የምናገኘዉ ግንዛቤ ምንድን ነዉ?

ነጸረ  አዎ፣ አላቸዉ። ግን ግንኙነታቸዉ የሚሰጠን ትምህርት አሉታዊ ነዉ።

ፋና  እንዴት ነዉ አሉታዊነቱ?

ነጸረ  የዛሬዉን የለዉጥ ንቅናቄ ሙሉ የኢትዮጵያ ቅርጽ ወይም ባለቤትነት በግልጽ ማስቀመጡ ያሉ የአገራዊ አነሳስ ክፍተቶችን፣ድክመቶችንና ችግሮችን በተፃራሪ አጣርቶ ያሳየናል። ተፈላጊና አገር ጠቃሚ የአነሳስ ዘዴዎችን ከማይፈለጉና አገር ጐጂ ከሆኑ “የለዉጥ” እንቅስቃሴ መንገዶች ወይም ኢትዮጵያዊነትን ለሌላ አላማ በስልትና ታክትክ ደረጃ መሣሪያ ከሚያደርጉ የአገዛዙም የተቃዉሞዉ ጐራም ጥረቶች ጋር በማፃረር ልዩነታቸዉን ይበልጥ ጉልህ ያደርጋል። አያይዞም ለለዉጥ እንደ አገር የምንነሳባቸዉን አሉታዊ ሁኔታዎች በስልታዊ ግንዛቤ ጨብጠን ክፍተቶችን ለመድፈን፣ ሁኔታዎቹን ለመለወጥ ይረዳናል።

ልባዊት  እዚህ ዋና ነጥብህ ላይ ትንሽ ትኩረት ለማከል፣ የጠቆምከዉን የትግል መንገዶች ወይም አይነቶች ተፃራሪነት ተገንዝበን የኢትዮጵያን አንድነት በመጠበቅ ለምናካሂደዉ የፖለቲካ ለዉጥ ሥርዓታዊነት ወሳኝ ነዉ ብዬ አስባለሁ። በትግሉ ብሔራዊ አንድነታችንን አድሰንና አጠናክረን ማረጋገጥ ካቃተን ከዉስጥም ከዉጭም የሚሰነዘሩብንን ጥቃቶች መመከት ብቻ ሳይሆን ለመላ የአሪቱ ዜጐችና ባህላዊ ማኅበረሰቦች የሚበጅ መሠረታዊ አገር አቀፍ ለዉጥ ማምጣትም ይሳነናል ወይም ይከብደናል። ይህ አይነት ሩቅ ሂያጅ መዋቅራዊ ለዉጥ በንጹሁ ነገዳዊ/አካባባዊ በሆነ “ራስን በራስ የመወሰን” ወይም የመታደግ እቅድና ንቅናቄ አይመጣም። ስለዚህ ነጸረ እንዳመለከትከዉ የለዉጡን ሙሉ አገራዊነት ከጅምሩና በትግል ሂደት ማረጋገጥ የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችንን ዘር ዘለል የኢኮኖሚ፣ የህብረተሰብ፣ የባህልና የመስተዳደር ችግሮች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ ግልጽ ማድረግ ያስችለናል። ተገቢ መፍትሔዎቻቸዉንም ለማበጀት ይረዳናል። ስለ ተጨማሪ የለዉጥ ትግሉ አገራዊ አነሳስ ችግሮች የቀረነዉ አስተያየታችንን ከመስጠታችን በፊት ግን ነጸረ አንተ የጀመርከዉን ቀጥለህ ትሄድበት?

ነጸረ  እሺ፤ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ይበልጥ ከባድ ሆነዉ  በሁለተኛ ደረጃ የገጠሙን የአገራዊ አነሳስ ችግሮች አሉ። ዝርዝር ሐተታ ዉስጥ ሳልገባ ጠቅለል አርጌ ለመናገር፣ በጉደኛዉ የወያኔ “አብዮታዊ” አገዛዝና የፖለቲካ አለም ዉስጥ ምንም ነገር (የአገር አንድነት፣ ህገ መንግሥት፣ ፌደራላዊነት፣ ዲሞክራሲ፣ ምክር ቤት፣ የሰላምና እርቅ ድርድር፣ ወዘተ) ሃቀኝነት ወይም እዉንነት የለዉም። ምንም ነገር የሚመስለዉን አይደለም። ሞገደኛዉ የወያኔ ፖለቲካ በኃልዮም ሆነ በገቢር የአገርና የኅብረተሰብ እዉነታዎችን የሚገልጽ ወይም የሚወክል ሳይሆን እዉነታዎቹን በአስመሳይ የዉሸት ቅጅዎችና ፈጠራዎች የሚተካ ነዉ። ለዘለቄታዉም ባይሆን አገራችን ራሷ በዚህ አይነት ለከት የለሽ አስመስሎ (simulation) እዉን ሉአላዊነቷንና ከፖለቲካ ቀዳሚነቷን አጥታለች። በዚህ መልክ የአስመስሎዉ ሁለ ገብነት ለዛሬዉ የለዉጥ ንቅናቄ አገራዊ አነሳሳችን ከመቸዉም ጊዜ ይበልጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ፈጥሯል።

ዘርይሁን  ሆኖም የዛሬዉን የአገር አንድነትን ዉጥረት ለጊዜዉ ወደ ጐን አርገን የብሔሮችንና ሕዝቦችን ማንነቶች ስናይ ለጠቀስከዉ የአስመስሎ ወረራ በተመሳሳይ መልክና መጠን ሰለባ እንዳልሆኑ እንረዳለን። እዚህ ላይ ችግሩ በተማሪዉ ንቅናቄ ነጥሮ የወጣዉን አብዮታዊ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስ ዉሰና ጽንሰሃሳብ በመሠረቱ ያማከለ አገራዊ የትግል አነሳስ በደርግም በወያኔም አብዮተኞችና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች መጨናገፉ ነዉ። ትግሉ ከጽንሱና አጀማመሩ ትክክል ሆኖ ሳለ በአምባገነናዊ ሃይሎች ተወላግዶ ሥራ ላይ ዋለ። ችግሩ የአብዮታዊ ሃሳብ አፈጻጸም ነበር።

ፋና  ይህን ጉዳይ ከአማራጭ አካባባዊ/ነገዳዊ ማንነት ጋር አያይዘን በሁለተኛዉ የዉይይታችን ክፍል የምንዳስስዉ ስለሆነ አሁን ምንም ያህል ሳንሄድበት ነጸረ ያቀረበዉን ሃሳብ እንቋጨዉ። ግን ዘሪሁን የሰነዘርከዉ ሃሳብ ላይ ለጊዜዉ ጠቅለል አርጌ በጥያቄ መልክ አንድ ነገር ልበል። ልባዊትም እዚህ ላይ እንዲሁ አሳጥረሽ የምትይዉ ካለ እንሰማሽና ወደ ነጸረ እንመለሳለን። ዘሪሁን የለገስከን አስተያየት ያልተለመደ ባይሆንም አጠያያቂ ነዉ። መሠረታዊዉ ጥያቄ በዘመናዊ የአገር አብዮቶች ታሪክ ቃል በቃል የሰፈሩ መነሻ  ሃሳቦቹንና ግቦቹን በአተረጓጐምና በተግባር አልቀለበሰም ወይም አላጣመመም፣ የገዛ ልጆቹንም አልበላም፣ የሚባለዉ አብዮት የትኛዉ ነዉ? የፈረንሳይ፣ የሩሲያ? የቻይና? የኤርትራ? በሌላ አባባል፣ በአፈጻጸሙ “መወላገድ” ያልደረሰበት፣ “ቅጂ” ያልሆነ “የመጀመሪያ” (“original”) አገራዊ አብዮት ኖሮ ያዉቃል? በኢትዮጵያም የአብዮተኝነት ልምድ ችግራችን እንዲሁ ከአፈጻጸም የቀደመና ያለፈ ነበር። ልባዊት ለዘሪሁን አጭር ምላሽ አለሽ?

ልባዊት  አዎ፣ አለኝ። በተማሪዉ ንቅናቄ፣ በተለይ በነዋለልኝ መኮንን ስታሊናዊ ጥንስሱና አለም አቀፍ አቀራረጹም ቢሆን “የብሔሮች ጥያቄ” በተለይ ኢትዮጵያዊ እዉንነትም ሆነ አነሳስ ነበረዉ የሚባል አይደለም። ሥር ነቀል ተብዬዉ የተማሪዎች ንቅናቄ ፖለቲካ ንቅናቄዉን ራሱን አገራዊ ሥር መሠረት የነሳ፣ ለአገር ችግሮች መፍትሔዎች ለማበጀት ከመሞከረ ይልቅ ኢትዮጵያን/ኢትዮጵያዊነትን አካቶ እንደ ችግር (“የብሔሮች እስር ቤት” አድርጐ) ያየ እንደነበር እዉቅ ነዉ። የተማሪዉ ጽንፈኛ ግራ ክንፍ አመራር ሆን ብሎም ይሁን ባለማስተዋል አገርን የአብዮታዊ ለዉጥ ኢላማ እንጂ ባለቤት ያላደረገ የአስተሳሰብ ፓራዳይምና የትግል መመሪያ ፈጠረ። የቀጠለዉ ወይም የተረፈዉ (በደርግና በወያኔ “አበዮታዊ” አገዛዞች እንዳየነዉ) ፍጹም አስከፊ ታሪክ ነዉ…ነጸረ መቀጠል ትችላለህ።

ነጸረ  መልካም፤ ቀደም ብዬ የኢትዮጵያን መንግሥት፣ ፖለቲካና ህብረተሰብ ዛሬ ስላጥለቀለቀዉ የእዉነታ አስመስሎ ስናገር ሁኔታዉን ያየሁት ከወያኔ አገዛዝ ጋር ባለዉ ጉልህ ግንኙነት ነበር። ነገር ግን ችግሩ ከአገዛዙ ባህሪ ወይም ገጽታ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። በተጨማሪ፣ ገዢዉ የትግሬ ቡድን በቀጥታ ወይም በቅርቡ ይቆጣጠራቸዋል በማይባሉ “ተቃዋሚ” ወገኖች ዘንድም ይከሰታል። ከነዚህ ወገኖች መካከል ግንቦት ሰባት የተባለዉ ድረጅት በዋናነት የሚጠቀስ ነዉ። የአስመስሎዉ ሁኔታ እንግዲህ አገዛዙና ተቃዋሚ የሆነ (ወይም የተባለ) የተወሰነ ወገን በፉክክርም ይሁን ግልጽ ሆኖ በማይታይ ትብብር የፈጠሩት እንደሆነ እንረዳለን። ይህ አኳኋን ደግሞ የዛሬዉን የለዉጥ ትግልና የሕዝብ አመጽ አገራዊም አካባባዊም አቅጣጫ የማስያዙን ሥራ በድርቡ አዳጋች ያደረገ ነዉ።

ዘርይሁን  ግንቦት ሰባትን በሚመለከት ነጸረ በጠቆምከዉ መልክ ምንም ያህል የአስመስሎ ችግር አይታየኝም። ድርጅቱ በሁለገብ መንገድ የለዉጥ ንቅናቄ አራማጅነቱ በኢትዮጵያ የሚኪያሄዱ የሕዝብ አመጾችን ማቀናበር አመቺ የሚያደርግ ትብብርና ድጋፍ ከኤርትራ ገዢ ፓርቲ እንደሚያገኝ አይክድም። በዚህ አይነት ተጓዳኝነትም የራሱን አገራዊ ግቦች፣ በተለይ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲ የመለወጥ አላማ፣ እንደሚከታተል ገልጿል። መሠረታዊ ልዩነት ባላቸዉ፣ ተቀናቃኝ በሆኑም፣ ሃይሎችና ወገኖች መካከል የጋራ ጠላት ላይ ያነጣጠረ ወይም በተወሰኑ የወል ጥቅሞች ዙሪያ ቋሚም ባይሆን ጊዜያዊ የስልትና የታክቲክ ኅብረት መፍጠር ምንጊዜም ያለ ነዉ።

ፋና  ግን እኮ ዘርይሁን የፖለቲካ ድርጅቶችን ወይም የአገዛዞችን አላማዎች ዕዉቂያችን እነዚህ አካላት ስለራሳቸዉ በሚሰጡት የቃል በቃል ገለጻ ግንዛቤያችን ብቻ አይወሰንም። ከድርጅቶችና አገዛዞች ይፋ ገለጻ በስተጀርባ ያሉ መነሻ ጥቅሞችንና ሁኔታዎችን፣ ስዉር የሆኑ ወይም ሆን ተብለዉ የተድበሰበሱ አጀንዳዎችንና ሌሎች ዉስጣዊም ዉጫዊም አነሳሽ ምክንያቶችን እግምት ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ሻቢያ ከወያኔ አገዛዝ ጋር ካለዉ ደመኛነት ባሻገር ዛሬ በኢትዮጵያ የሚኪያሄደዉን የለዉጥ ትግል በግንቦት ሰባት ድርጅት አማካኝነት የራሱ ጉዳይ ያደረገበት አነሳሽ ምክንያት ምንድን ነዉ? በጉዳዩ ክትትል ሻቢያ ከድርጅቱ የሚያገኘዉ ወይም የሚጠብቀዉ ጥቅምስ ምን አይነት ነዉ? የድርጅቱ ነዉ የተባለዉ፣ ግን በሻቢያ የበላይ ተቆጣጣሪነት የትግራይና የኤርትራ ታጣቂዎች በዋናነት የተካተቱበት የጦር ሃይል በእዉነት የግንቦት ሰባት “ሁለ ገብ” ትግል አካል ወይም የኢትዮጵያ አገራዊ ሃይል የሚባል ነዉ? የጦር ሃይሉ ለአመታት በቦዘኔነት በኤርትራ ከመከተት በቀር በኢትዮጵያ ምድር ተንቀሳቅሶ ይህ ነዉ የሚባል የትግል ዉጤት ያላሳየዉ ለምንድን ነዉ? እነዚህ ጥያቄዎች ነጸረ ያመለከተዉን የአገራዊ ትግል አነሳስ/አኪያሄድ ችግር የሚያሳዩ ይመስለኛል…ልባዊት ምን ትያለሽ እዚህ ላይ? ከዚያ ነጸረ ትቀጥላለህ።

ልባዊት  ልክ ነህ ፋና፣ ግን የግንቦት ሰባት ድርጅት መሪዎች ሃሳባቸዉንና ግቦቻቸዉን በየጊዜዉ በይፋ ሲያስታዉቁ ያሏቸዉን ነገሮች ስናይም ድርጅቱ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል የአገራዊ አኪያሄድ ችግር ያለዉ መሆኑን ነዉ የሚያሳዩት። የኢትዮጵያን ዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ የባሕር በርን (አሰብን) በሚመለከት፣ ሲጠየቁ ምንም አገራዊ የፖሊሲ አቋም አንወስድም፣ ሁሉ ነገር የወያኔ አገዛዝ በሕዝብ ትግል ከተወገደ በኋላ ይወሰናል ነዉ ያሉት። ይህ እንግዳ የሆነ አባባል የግንቦት ሰባት ድርጅት አሰብ የኤርትራ ነዉ ብሎ ከደመደመዉ የሻቢያ አገዛዝ ጋር ያለዉ “አላቻ ጋብቻ” (ተጓዳኝነት) ድርጅቱ ላይ ያሳደረበትን ተጽእኖ የሚያንጸባርቅ ይመስለኛል። ተጓዳኝነቱ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለዉጥ (integral transformation) ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም። የወያኔን አገዛዝ በሁለገብ ትግል እንጥላለን ግን ሥልጣን የመያዝ እቅድ የለንም የሚለዉ የትም ተሰምቶ የማይታወቀዉ የግንቦት ሰባት ድርጅት መሪዎች አነጋገርም በተመሳሳይ መንገድ አመኔታን የሚፈታተን ነዉ። ባጭሩ፣ ድርጅቱ ፖለቲካዊ ማንነቱን፣ እንዲሁም የትግል አላማዉንና ዘዴዉን ግልጽ ያደረገ ንቅናቄ ሳይሆን የሚፃረሩና የሚጋጩ ክርክሮች በጠምዛዛና አሻሚ የፖለቲካ ቋንቋ ያቀረበ ነዉ። ዛሬም በሕዝብ አመጾች ሁሉ (ለምሳሌ ቀደም ብሎ በጐንደር፣ ሰሞኑን ደግሞ በወልድያ) አለሁ ባይነቱ ወይም ተባይነቱ እንዲሁ ሊታመን የማይችል ነዉ። አባባሉ እዉን ድርጊቶችንና ሁኔታዎችን ዘጋቢ ወይም ገላጭ ሳይሆን  ነጸረ እንደምትለዉ የእዉነታ አስመስሎ  ነዉ። ብዙዎች ተራ ዉሸት ይሉታል። ሁኔታዉ በጠቅላላ የግንቦት ሰባት ንቅናቄን የተቃዉሞ ሚና እና ሥራ አጠያያቂ ያደረገ ነዉ። ከአንዳንድ አገር ወዳድ ወገኖች (ለምሳሌ ከአርበኖች ግንባር) ጋር መቀናጀት የሞከረ ቢሆንም ንቅናቄዉ ራሱ የአገር ወዳድ ተቃዉሞ ሃይል ሊባል የሚችል ነዉ ወይ? እንዲህ አይነት ሃይል ሳይሆን  ባመዛኙ ዳያስፖራዊ በሆኑ እንቅስቃሴዎችና መገናኛ ብዙሃን የእዉን አገራዊ ተቃዉሞዉን ቦታ ያዥ ብቻ ሆኖ የሚሠራ አይደለምን? በዚህ አሠራሩስ ዋናዉ ተጠቃሚ ማነዉ? አገር ወዳድ ታጋዮችና የጐበዛ አለቆች ወይስ ሕወሓትና ሻቢያ? እንግዲህ በስሌትም ይሁን በዉጤት የተቃዉሞዉ ምህዳር በግንቦት ሰባትና ተባባሪዎቹ እንዲህ መያዙ ወይም የተያዘ መምሰሉ ያተረፈዉ ነገር ምንድን ነዉ? ማለትም፣ ንጹሕ አገር ወዳድ ተንቀሳቃሾችንና አመጸኞችን የግንቦት ሰባትን “ሽብርተኝነት” ደጋፊዎች ወይም አራማጆች ናቸዉ በሚል የሐሰት ዉንጀላ የወያኔ አገዛዝ ሰለባ ከማስደረጉ ባሻገር? የለዉጥ ትግሉ ድርጁ አስኳል ወይም የስበት መኻል የሆነ እዉነተኛ አገራዊ ሃይል እስከ ዛሬ ድረስ ላለመነሳቱ የግንቦት ሰባት ፖለቲካና ሚዲያ መረብ በቦታ ያዥነት አስተዋጽዎ አላደረገም ወይ?

ነጸረ  ጉዳዩን ምላሽ በማይጠብቁ ገላጭ ጥያቄዎች ጥሩ አስቀምጠሽዋል። በአስመስሎ ጽንሰሃሳብ ፈርጀን የምናየዉ የአገዛዙንም ሆነ የግንቦት ሰባት ድርጅትን ተናጠል እርምጃዎች፣ የንግግር ዘይቤዎችና ዉሸቶች ወይም ተግባራዊ ድርጊቶች ላይ ያልቆሙ ተለዋዋጭ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር መዋቅር ነጸብራቅንም ነዉ። የእዉነታ አስመስሎ ፖለቲካ በሰፊዉ የኢትዮጵያን “ተራማጅነት” ባህል/ቅርስ የሚገለጽ ፓራዳይማዊ ወይም ሥርዓታዊ ጐን አለዉ። ለምሳሌ በደርግም በወያኔም አገዛዝ ልብ ብለነዋል። በተለይ ዛሬ በወያኔ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሥር አገራዊ፣ ማኅበራዊና ተቋማዊ እዉነታዎችን አስመሳዮቻቸዉ በሆኑ መርሃዊ ትርጉም የለሽ ቅጅዎች (ግልባጮች) የመተካቱ ባህል በሁሉም ረድፍ – በፖለቲካ፣ በመስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና በመንፈሳዊ ኑሮ – መገለጫዎች አሉት። የአስመስሎ ፖለቲካ ባህል ያልወረረዉ፣ ከዉስጥ ያልቦረቦረዉና በቁሙ ያልገደለዉ የኢትዮጵያ ስቪል ኅብረተሰብ ዘርፍ የለም። ስለዚህ…

ፋና  ላቋርጥህና ነጸረ፣ የዚህ ሁሉ ሕዝብና አገር አፋኝ እዉነታ አስመሳይ “አብዮታዊ”/“ተራማጅ” ፖለቲካ መስፋፋት ምንጩ ምንድነዉ? በተለይ በወያኔ አገዛዝ አነሳሽና አስፋፊ ምክንያቶቹ ምንድናቸዉ ትላለህ?
ነጸረ   በሰፊዉ አለም አቀፍ ከነበረ ኮምኒስታዊ አስተሳሰብና ገቢር የፈለቀ ነዉ። በአገራችን አገባቡ አትኩረን ስናየዉ ዋናዉ ምንጩ ሥር ነቀል የተባለ ለዉጥ አራማጆች የለዉጡን ሂደት ባልተገደበ የፖለቲካ ሃይል ለመቆጣጠር መገፋፋትና መነሳሳት ይመስለኛል። በዚህ አይነት “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አገዛዝ በአገሪቱ ዜጐችና ማኅበረሰቦች ሕይወት ዉስጥ ዛሬ የወያኔ ስታልናዊ/ፋሽስታዊ ፖለቲካ ሰርጐም ተሽሎክልኮም ገብቶ “ማንነታቸዉን” ሳይቀር የራሱ ተቀጥላና ታክቲካዊ መሣሪያ አድርጓል። ብሔራዊ ሕይወትና ነፃ አገራዊ ተንቀሳቃሽነት ያለዉን እዉን የህብረተሰብ ክፍልና የፖለቲካ ወገን ሁሉ አገዛዙ ራሱ በፈላጭ ቆራጭነትና መሰሪነት እንደፈለገ በሚነዳዉ የዉሸት ቅጂ ወይም መንትያ (counterfeit double) ተክቷል። በዚህ መልክ ነዉ ለምሳሌ ብአዴን በሕወሓት የበላይ ቁጥጥር ሥር የአማራን ሕዝብ “ወካይ” የሆነዉ። ባጭሩ ይህ ይመስለኛል በአገራችን የእዉነታ አስመሳይ ፖለቲካ ተስፋፊነት ዋና ምክንያት። በአስመስሎ አማካኝነት ሕወሓት አገራዊና ማኅበራዊ እዉነታዎች ላይ በቀጥታም በዘወርዋራም መንገዶች ያልተገደበ የፖለቲካ ቁጥጥር ለማድረግ በቅቷል። ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት ራሱን ባጋነነ አድራጊ ፈጣሪነት የአገር ጉዳዮችን በመኖፖል መቆጣጠር ችሏል። አያይዞም ነባሩን (የደርግን) እዉነታ አስመሳይ “አብዮታዊ” አገዛዝ በማባባስ ጠቦ አገርና ሕዝብ አጥባቢ በሆነ የማንነት ፖለቲካ ቀጣይ አድርጓል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ተስፋፊ የአስመስሎ ፖለቲካ በቀጥታ ከገደብ የለሽ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እዉነታ ጋር የተያያዘ ነዉ።

ፋና  መልካም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ማወቁ ደግሞ ለዛሬዉ የዉጥ ትግል እንድምታ አለዉ። ነገደ ብዙዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገዉ ያስመሳይ ፖለቲካም ሆነ የጐሣ አገዛዝ ጥገና ወይም ቅየራ ሳይሆን ጠቅላላ የፖለቲካ ሥርዓት ለዉጥ መሆኑን ያመለክታል። እንግዲህ ለመጀመሪያው የጭዉዉታችን ክፍል የመደብነዉ ጊዜ እያለቀ ነዉ። ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያ ለሚደረጉ የለዉጥ እንቅስቃሴዎች አገር መነሻም መዳረሻም አኳኋኑን በሚመለከት ጥቂት መደምደሚያ አስተያየቶች አስተናግደን ዉይይቱን እናገባድ። ዘሪሁን ካንተ ልጀምርና ለመዝጊያ ምን ትላለህ?

ዘርይሁን  እሽ፣ አመሰግናለሁ። ዉይይታችንን ወድጄዋለሁ፤ አንዳንድ ዋና ዋና ጉዳዮችን ማጥራት አስችሎናል። እኔ ለመደምደሚያ የምሰነዝረዉ አስተያየትም እንዲሁ በአጣሪ ትችት መንፈስ የቀረበ ነዉ። አስተያየቴ አገራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) ራሱ ላይ ያለንን ወይም ሊኖረን የሚገባ ቅድመ ግንዛቤን የሚመለከት ነዉ። ኢትዮጵያዊነት አንድነታችን ነዉ፤ የወል ብሔራዊ ሕይወታችን መገለጫ መሆኑ አይካድም። ነገር ግን በሆነ ያለሆነ ርዕዩተአለማዊ፣ ወገንተኛ ወይም ጐሠኛ ቅርጽና አተረጓጐም የሚጣጣ አይደለም። ይልቅስ ከዜጐች ነፃነት፣ ከባህላዊና ማኅበራዊ ብዙሃንነት፣ ከአካባባዊነት፣ እንዲሁም ከፖለቲካ አስተሳሰብ አኳያ የተለያዩ አቀራረቦችንና ሁኔታዎችን አቻችሎና አዛምዶ በእቅፉ የያዘ አገራዊ ባህል ነዉ። ባህሉን የአገሪቱ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ አካላት በጠንካራ እምነትና ተገቢነት የራሳቸዉ ሊያደርጉት የሚችሉት የጥቅሞቻቸዉ፣ መብቶቻቸዉና እሴቶቻቸዉ ማረጋገጫ ሲሆን ነዉ። እንዲሁም የጋራ ኢትዮጵያዊነታቸዉ የየቅል አኗኗራቸዉን ቅርጾችም በሚያንጸባርቁ ዘዬዎች መግለጽ ወይም መቃኘት ሲያስችላቸዉ ነዉ። በዚህ መልክ ነዉ አገራዊ ህልዉናችን የዛሬዉ ለዉጥ ትግል መነሻ ሆኖ የሚታየኝ።

ፋና  ጥሩ፤ አገር የለዉጡ መዳረሻም ነዉ ብለህ የምታስበዉስ እንዴት ነዉ፣ ባጭሩ?

ዘሪሁን  አገራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) ዛሬና ነገ በለዉጥ ጐዟችን የምንደርስበትም የሚሆነዉ፣ አንደኛ ላለፉት ጥቂት አስርተ አመታት፣ በተለይ በጉደኛዉ ወያኔ ያገዛዝ ዘመን፣ ብዙ ዉዝግብና ጥፋት ስለደረሰበት መልሰን የምናረጋጋዉ፣ የምናድሰዉና የምናጠናክረዉ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነዉ። ሁለተኛ፣ ብሔራዊ ባህላችን እንከን የለሽ ሆኖ ወይም ላንዴም ለሁሌም ተከናዉኖና ተረጋግጦ በታሪክ የተሰጠን ሳይሆን በትዉልዶች ቅብብሎሽ ቀጣይ ሆኖ የሚጠበቅ፣ የሚያድግና የሚዳብር መሆኑን ተረድቼ ነዉ። ጥልቅ ታሪካዊ ሥሮች ያሉት ብሔራዊ ህልዉናችን ወደፊት የመልማት ትልቅ እምቅ አቅም  (possibility/potential) አካቶም ወይም አላማና እቅድ ሆኖም ነዉ ከቅድመ አያቶቻችን በሃላፊነት የተረከብነዉ። በዚህ ግንዛቤ መሠረት ነዉ ኢትዮጵያዊነት የዛሬዉ አገር አቀፍ የለዉጥ ትግል መነሻ ብቻ ሳይሆን መዳረሻም ነዉ የምለዉ።

ፋና  ልባዊት ትቀጥዪ?

ልባዊት  እሺ፤ ኢትዮጵያዊነት፣ የጋራ ብሔራዊነታችን፣ ራሱን የቻለ እሴት ወይም ምንነት እንዳለዉ ለአገር ወዳድ ወገኖች ግልጽ ነዉ። ይህን ዉስጣዊ ምንነቱን በታሪክ ሂደት ያዳበረዉ ከአገሪቱ ብዙሃን ባህላዊ ማህበረሰቦች ጋር  በፈጠረዉ የብሔራዊ እሴት ሰጥቶ መቀበል ትስስር እንደሆነም አይካድም። በዛሬዉ አገር አድን ትግል ሙሉ ኢትዮጵያዊነትን እንደ እሴት መኻል ማረጋገጥ አስፈላጊ የሆነባቸዉን ሁለት የተዛመዱ ምክንያቶች ጠቁሜ ልዝጋ። አንደኛ፣ ለትግሉ ዘለቂ አነሳስ ራሱ ወሳኝ አስተዋጽዎ አለዉ። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚደረጉ የሕዝብ አመጾችና እንቅስቃሴዎች ሆን ተብለዉም ይሁን በግብታዊነት ለሚፈልቁ ግርግሮች፣ ሁከቶች፣ ዉዝግቦችና ያልተረጋገጡ አስጊ ሁኔታዎች ብሔራዊ አንድነታችን መቋቋሚያና ማረጋጊያ ይሆናል። ሁኔታዎቹ አካተዉ ከቁጥጥር ዉጭ እንዳይሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን ለማንም የማይበጅ የርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ እንዳይገቡ መከላከያ ሃይል ነዉ። ሁለተኛ፣ ቀደም ብዬ እንዳመለከትኩት፣ በለዉጥ ትግሉ ሂደት አንድነታችንን አረጋግጦ መነሳት የገጠሙንን ጐሣ ተሻጋሪ የሆኑ ሰፋፊ የነፃነት፣ የፍትሕ፣ የዲሞክራሲና የልማት ጉዳዮችና ችግሮች በመርህና ንድፈ ሃሳብም ሆነ በስልት ለመፍታት አስፈላጊ ነዉ። ምክንያቱም ችግሮቹ አካባቢና ዘር ዘለል የሆነ አገር አቀፍ መዋቅራዊ ትስስር ያላቸዉ ስለሆኑ በተለያዩ “የራስን ዕድል በራስ ወሳኝ” በተባሉ ተናጠል ደሴታዊ የማንነት ፖለቲካ እቅዶችና ታክቲኮች ሊፈቱ አይችሉም። ጉዳዮቹ በዚህ መንገድ በቂ መፍትሔዎች ማግኘታቸዉ ይቅርና በሚገባ የሚገለጹና የሚጨበጡም እንኳን አይደሉም። ስለዚህ በዛሬዉ የሥርዓታዊ ለዉጥ ንቅናቄ የአገራዊ አነሳስንና አኪያሄድን መሠረታዊነት እንረዳለን።

ፋና  በመጨረሻ፣ ነጸረ ካንተ እንስማና ዉይይታችንን እንዝጋ። በነገራችን ላይ፣ ኢትዮጵያዊነት የዛሬዉ የለዉጥ ንቅናቄ መዳረሻ ስለመሆኑ ዘሪሁን ያካፈለንን ሃሳብ አንተ ቀደም ብለህ ጠቀስ አድርገኸዉ ብቻ ስላለፍክ ጉዳዩ ላይ ያለህ አስተያየትህ ከዘሪሁን አመለካከት የተለየ ከሆነ ልዩነቱን እግረ መንገድህን ባጭሩ ልትነግረን ትችላለህ።
ነጸረ  በጉዳዩ ከዘሪሁን የተለየ ሃሳብ የለኝም፤ እንዲያዉም አስተዉሎዉን ከፍ ያለ ዋጋ ሰጥቼ እጋራለሁ። ሙሉ ኢትዮጵያዊነት የዛሬዉ ለዉጥ ትግል  መነሻነቱን የሚያረጋግጥ አስተሳሰብ ነዉ። ኢትዮጵያዊነት እዉንና እምቅ አገራዊ አቅሞች/ሃይሎች እንደሚዋሐዱበት ያመለክታል። ለመዝጊያ ያለኝ አስተያየት ይህን አመልካች ሃሳብ የሚያጠናክር ነዉ። አገራዊ ህልዉናችን የሚዳሰስና የሚታይ ተጨባጭነት ያለዉ እዉነታን ያንጸባርቃል፣ ግን በዚህ አይነት ቀጥታና ቅርብ እዉነታ ብቻ ተገላጭ አይደለም። የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችን ፖለቲካዊ ሃሳቦች፣ መርሆችና አቋሞች (“ዲሞክራሲ”፣ “ፌደራላዊነት” ወዘተ) ሊስተናገዱበትና የመስተዳደር አካሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ አቋም ወይም ሥርዓት አይደለም። ተቀናንሶ ወደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ወይም ርዩተአለም ዝቅ ሊደረግ አይችልም። ሙሉ ብሔራዊ ሕይወታችን አገር ወዳድ ስሜታችንን እርግጥ ያካትታል፣ ሆኖም በራስ አድን ንቅናቄ አነሳሱ፣ ስምሪቱና እንቅስቃሴዉ የሚነዳዉ ምክንያታዊና ስልታዊ ሃሳብን ባገለለ ስሜታዊነት አይደለም።
እንደ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን እንግዲህ የሃሳቦችን አንድነት፣ የአካባቢዎችን ድምርና የድርጅቶችን ኅብረት ያለፈ፣ አልፎም እነዚህን ግብአቶች እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰር፣ ያዋሓደ፣ የራሱ ልዩ አገራዊ ሕንፀት ወይም መዋቅር አለዉ። አገራዊ አገባባቸዉ እስከተጠበቀ ድረስ ግብአቶቹ አንጻራዊ ልዩነት እንጂ ፍጹም ለየብቻነት የላቸዉም። ይልቅስ የሙሉ ብሔራዊ ህልዉናችን አካላት ናቸዉ። ኢትዮጵያዊነት በስሜት እዉስጣችን ያለዉ፣ አዙረንም በምክንያታዊ ሃሳብ የምናየዉ፣ እንዲሁም በእዉን የምንኖረዉ በዚህ መሉ መዋቅሩና ገጽታዉ ነዉ። ለዛሬዉ የለዉጥ ትግል መነሻም መድረሻም የሚሆነዉ በዚህ ሰፊ መልክና መጠኑ ነዉ። በመጨረሻ፣ ከማንኛዉም አገር የተለየ የራሱ ተጨባጭ ቅርጽ የያዘዉ የጋራ ብሔራዊነታችን ዘሪሁን እንዳለዉ አንድኛዉን ተጠናቆና ተረጋግጦ በታሪክ የተሰጠን ሳይሆን በተከታታይ ትዉልዶች እንዳስፈላጊነቱ በቀጣይነት የሚጠናቀቅና የሚረጋገጥ ሆኖም ነዉ። ጨረስኩ።

ፋና  እሺ፣ የመጀመሪያዉ ክፍል ዉይይታችን እዚህ ላይ አበቃ። በክፍል ሁለት የዛሬዉ የኢትዮጵያ አገራዊ የለዉጥ ንቅናቄ ዉስጥ የአካባቢዊ እንቅስቃሴዎችን አቀራረጽና አገባብ ለመዳሰስ፣ አማራጭ አቅጣጫዎችም ለማጠቆም እንነጋገራለን። እስከዚያዉ ደህና ሁኑ።

ተስፋዬ ደምመላሽ
tesfayedemmellash@gmail.com