የዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ባርኔጣ
Christopher Furlong

ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች መካከል ግጭቶች ተነስተው የተማሪዎች ህይወት ጠፍቷል፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

በብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የተቋረጠ ሲሆን ተማሪዎችም ወደየአካባቢያቸው እየተመለሱ ነው። በተለያዩ አካባቢዎችም የሀገር ሸማግሌዎች ነገሩን ለማረጋጋት እየሞከሩ ቢሆንም ተማሪዎቹ ለመመለስ ምን ዋስትና ይዘን ነው የሚል ጥያቄ እያነሱ ነው።

ምን ተከሰተ?

የግጭቱ መንስኤ ከሁለት ሳምንታት በፊት በወልዲያ ከተማ በወልዲያ ስፖርት ክለብ እና በመቀሌ ከተማ ደጋፊዎች መካከል በተከሰተው ግጭት የሰው ህይወት መጥፈተና የንብረት ዘረፋና ውድመትን የተከተለ ነው።

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ግጭትን ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተቀሰቀሰው ረብሻ ህይወት ጠፍቷል።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን፤ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አለማየሁ ከበደ ለአማራ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ እንደገለፁት ደግሞ አንድ ተማሪ ሞቷል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ተማሪዎች እንደቆሰሉና በባህርዳር ሪፈራል ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነም የአማራ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ዘገባ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ በጎንደርና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች ቆስለዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች በባህርዳር ያነጋገሯቸው የባህርዳርና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል።

ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው የሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ለደህንነታቸው በመስጋት ወደቤታቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ደብረ-ታቦር ዩኒቨርሲቲ አሁንም በፀጥታ ኃይሎች እንደተከበበና ትምህርትም እንዳልተጀመረ ተመራቂ ተማሪ የሆነችና የአዲስ አበባ ልጅ ለቢቢሲ ገልፃለች።

ምንም እንኳን የዩኒቨርስቲው አስተዳደር በመጪው ሰኞ ትምህርት ይጀመራል ብለው ማስታወቂያ ቢለጥፉም በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ ተማሪዎች በስተቀር ግቢው ጭር እንዳለም ትናገራለች።

ያለፈው ሰኞ ሌሊት ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ጩኸት እንደተረበሸና የፀጥታ ኃይሎች ገብተው ለማረጋጋት እንደተሞከረ ገልፃለች።

ግርግሩ ማክሰኞም ቀጥሎ ረፋዱ ላይ ተማሪዎች ዱላ ይዘው ተቃውሟቸውን እንደገለፁም ትናገራለች።

አብዛኛው ተማሪዎች በዚያ ቀን ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን ትናገራለች።

ምንም እንኳን በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በብሔር መቧደናቸው የተለመደ ቢሆንም እንደዚህ አይነት ግጭቶች በባለፉት ሶስት ዓመታት አይታ እንደማታቅ ትናገራለች።

“ይህቺ ተማሪ በጥቂት ቀናት ውስጥ ትምህርት ካልተጀመረ ወደ አዲስ አበባ እመለሳለሁ” ስትል ሌላኛዋ የዩኒቨርሲቲው የውኃ ምህንድስና ተማሪ “ብዙ ሰው ተገድሏል” የሚል ወሬ እየተነዛ በመሆኑ ፈርታ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳለች።

ከተማው ሰላም ቢሆንም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚወራው አንፃር ግጭቱ ይቆማል የሚል ሀሳብም የላትም። “ግቢ ሰላም ሆኗል ወደ ትምህርት ገበታችሁ ተመለሱ” የሚል መልዕክት የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ቢያስተላልፉም ደህንነቷን ለማስጠበቅ በቂ እንዳልሆነ ትናገራለች።

በተመሳሳይ የወለጋ ተማሪዎችም እስካሁን ነገሮች እንዳልተረጋጉ ይናገራሉ። “ወደ ቤታችን መመለስ እንፈልጋለን” በማለት ትምህርት ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ለቢቢሲ ይገልፃሉ። በአዲግራት ዩኒቨርስቲም ቢቢሲ ያነጋጋራቸው ተማሪዎች ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።

በባህር ዳር ከተማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሻንጣቸውን ይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ
አጭር የምስል መግለጫ በባህር ዳር ከተማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሻንጣቸውን ይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ

የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ምን ይላሉ?

በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የብሄር፣ብሄረሰብና ህዝቦች በዓል ሲከበር በሙዚቃ የተነሳ ቀላል ግጭት ወደ ቡድን ፀብ አምርቶ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። በዚህም ምክንያት ግጭቱ ለተከታታይ ቀናት ቀጥሏል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዛይድ ነጋሽ “ተማሪያችንን በማጣታችን ትልቅ ኃዘን ተሰምቶናል” ይላሉ።

የክልልና የከተማው አመራር ድርጊቱን በፅኑ ያወገዘ ሲሆን የዓዲግራት ህዝብ ድርጊቱን በመቃወም ድምፁን አሰምቷል።

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሀገር ሽማግሌዎች ግጭቶቹን ለማረጋጋት እየሞከሩ ሲሆን የመማር ለማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል መንገዶች እየተመቻቹ መሆኑን ዶ/ር ዛይድና የደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲው ዶ/ር አለማየሁ ከበደ ገልፀዋል።

“የሟቾችን ቁጥር ከፍ በማድረግ በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የሚወጣው መረጃ የማይታመንና ነገሩን የሚያጋግል ነው።”ይላሉ ዶ/ር ዛይድ

መንግስት ምን እያደረገ ነው ?

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ የሰሞኑ ችግር መነሻ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ሃይሎችን ተልዕኮ ያነገቡ ተማሪዎች የፈጠሩት መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

መንግስትም ችግሩ ውስብስብ በመሆኑ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ሁኔታውን የሚከታተልና በፌደራል ደረጃ ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙንም ገልጸዋል።

ብዙ ተማሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት የትምህርት ገበታቸውን ጥለው እንደሄዱ ሚኒስትሩ ተናግረው ፤ ለማረጋጋትም የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተቋማቱ እንዲገኙ መደረጉን ይገልፃሉ።

ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ስራ እየሰራ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።

ከዛሬ ጀምሮም በሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮችና በዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራር አባላት በ22 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመዘዋወር ችግሩን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና በስሜት እንዳይነዱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ተማሪ የላከችልን ምስል እንደሚየሳየው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ አካላት ተከቧል
አጭር የምስል መግለጫ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች ተማሪ የላከችልን ምስል እንደሚያሳየው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ አካላት ተከቧል

ነፃ መድረኮች

“ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያለው ችግር መነሻው የአስተዳደርና የተለያዩ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። በአጠቃላይ የሀገሪቱ ችግር ነፀብራቅም ነው” በማለት የኢፌድሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ደ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

“ተማሪዎች ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ። መብታቸው ነው። ይህንን መብታቸውን ለማስከበር ተማሪዎቹ የአካዳሚክ ነፃነትና መደራጀት አለባቸው። በዚህ መንገድ ጥያቄያቸውን በተለያየ መንገድ ሊያቀርቡ ይችላሉ” ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ መድረክ ሊዘጋጅላቸው እንደሚገባ ያምናሉ።

“እንደዚህ ዓይነት መድረክ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለማቅረብ ይጠቅማል። በዚህ መንገድ ካልሆነ አሁን ባለው መንገድ የትም ሊደረስ አይችልም” ይላሉ።

በእርግጥም ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ እንዲያደርጉና ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ሊፈቀድላቸው ይገባልም ይላሉ።

ችግሩ በዚሁ መንገድ ከቀጠለ ትምህርት ከመሰናከልም ባለፈ ሌላ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ዶ/ር ነጋሶ ይጠቁማሉ።

“አሁን ባለው የብሄር መቧደን የሚፈጠር ግጭት ወደ ብሄር ጥላቻና ብሎም ወደ ዘር መጠፋፋት ሊያደርስ ይችላል።” በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ከዶክተር ነጋሶ በተቃራኒው አጀንዳው ተማሪዎቹ ተደራጅተው ሃሳባቸውን የማቅረብ ብቻ ሳይሆን “የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ እያለ እንዴት እናትርፍ’ የሚለው ዋነኛ አጀንዳ እንደሆነ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ሰይፈ ኃይሉ ይገልፃል።

ግጭትና የተማሪዎችን ሞት ለመቀነስ ተማሪዎች በየክልላቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ መደረግ አለባቸው በማለትም መፍትሄ የሚለውን አስቀምጧል።

ሁኔታዎች አሁን ባለው መልኩ ከቀጠሉና የአንድ ብሄር ተወላጅ ከሌላ ብሄር ተወላጅ ጋር መጠላላቱ፣ መሰዳደቡ ከቀጠለ ዜጎች በህይወታቸው ሊከፍሉ ስለሚችሉ ጉዳዩ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባም ይጠቁማል።

“ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መለየያየት የምንችልበት መንገድ ሊታሰብበት ይገባል” በማለት ይገልፃል።

ዶ/ር ነጋሶ ግን እንገንጠል የሚሉ ቢኖሩም መገንጠል የሚፈልግ ህዝብ እንደሌለ ያምናሉ።

“ሀይ ባይ የለም”

ዋናው ጉዳይ የችግሮቹ መንስኤ ምንድን ናቸው ተብሎ መጠናት እንዳለበትና እየደረሱ ላሉት ችግር መፍትሄ ከሚመለከተው አካል ሊሰጥ እንደሚገባ ዶ/ር ነጋሶ ይናገራሉ።

አቶ ሰይፈ ለችግሩ መነሻ ሆኗል የሚላቸው የጋራ እሴቶችን ያለመገንባትና ህገ በመንግስቱ የተካተቱት የሰዎች ክብርና ሰብአዊ መብቶች ዘብ ሆኖ የሚቆም ኃይል አለመፈጠር መሆኑን በዋናነት ይጠቅሳል።

ለተፈጠሩ ግጭቶች ዋና ተጠያቂ ገዥውን ፓርቲ ያደረገው ሰይፈ” መንግሥት በማዕበሉ ላይ ገብቶ እየዋኘ ነው።ከአጠቃላይ ማህበረሰቡና በተለይ ከተማረው ክፍል በኩል ሀይ ባይ ጠፍቷል።” ይላል።

SOURCE   –  BBC/AMHARIC