16/12/2017

አጀንዳ መስጠት ያልቻለ ተቃዋሚ አጀንዳ ሲቀበል እንደሚኖር ግልፅ ነው። ስለዚህ ከዚህ ለመውጣት ከተቀባይ ወደ ሰጪነት ከቆሞ ቀር ፖለቲካ ወደ ተራማጅነት የህወሓትን አበሳ እያወሩ ከመኖር አበሳቸውን ወደ ማሳየት መሸጋገር ያስፈልጋል፤ እንዴት ለሚለው ጥቅል የመፍትሄ አቅጣጫ አክዬ ጥቆምታዬን ጨምሬ አራግፌያታለሁ።

ዋናው ነገር ኦህዴድ የጀመረው መገዳደር እስከ ቀጠለ ያንን ለመጠቀም ከጎኑ የሚሰለፍ ተሸንፎ ከተንበረከከ እሱንም ጨምሮ የሚታገል ኃይል ጉልበት ፈጥሮ የመውጣቱ ጉዳይ ነው። እስከ አሁን ያለው የህዝብ ትግል ህወሓት በፈለገ ጊዜ የሚያዳፍነው ቢሆን ቀድሞም አይነሳም ነበር። ጥልቅ ግምገማ አድርገናል፤ ታድሰናል፤ የማያዳግም እርምጃ እየወሰድን ነው፤ ዋና ዋና አመፅ አነሳሾች በቁጥጥር ስር የዋሉ በመሆኑ እና ህዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን ስላረጋገጠ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስተናል፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት…ምን ያላሉት አለ ?

በዚህ ሁሉ መሐል ህዝብ እምቢ ብሎ ያምፃል፣ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይጣሳል፤ እነሱ ይገላሉ ያስራሉ ፣ መግለጫ ያወጣሉ፣ የፌስቡክ ወሬ ነው አመፅ የለም በማለት ሊያስተባብሉ ይሞክራሉ፤ አጀንዳ ለማስቀየር በብሔረሰብ መካከል ግጭት ይፈጥራሉ፤ ትግሉ ሄድ መጣ ሞቅ ቀዝቀዝ ይበል እንጂ እየገደሉ ደም እየተቃቡ ጥላቻ እያሳደጉ መጡ እንጂ የመፍትሄ ፍንጭ አላመጡም። እናም ከህወሓት የሁለት ወራት ግምገማ ጉልበተኛው የአድዋ ቡድን ስልጣን ጠቅልሎ ብቅ ከማለት በቀር ለዘላቂ መፍትሄ መልስ ሊሰጥ እንዳልቻለ ሁሉ ህወሓት ከሚጋልባቸው ድርጅቶች ጋር የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በሚል ስም ስለተሰበሰበ የሚመጣ መልስ የለም።

መቼም ኦህዲድ ህወሃትን ደፍጥጦ በበላይነት እንደማይቆም ይታወቃል። በመካከላቸው ያለው የውስጥ ቅራኔ ለትግሉ አስተዋፅዎ መኖሩን ተገንዝቦ የኦህዴድ የእስካሁኑን አካሄድ ለራስ አማራጭ በትኩረት ማየት በርታ ሲልም ማገዝ ፈፅሞ የበሬ ቆለጥ ይወድቃል ብሎ ከመጠበቅ ተስፋ ጋር ሊገናኝ አይገባም ይልቁንም የጠላትን ስስ ብልትና ክፍተትን ከመረዳት አንግል ሊታይ የሚገባው ይመስለኛል። በፍፃሜው ላይ ኦህዴድ ለህወሃት ሊንበረከክ እንደሚችል መገመት ጤናማና ተገቢ ቢሆንም መንበርከኩ አይቀርም በሚል ልማዳዊ ግምት ብቻ ማገዝ የራስን ተግል በሚረዳበት ወቅትም በተጠራጣሪነት ልማድ ተቸክለን መቅረቱ የሚጠቅም አይመስለኝም።

ቁልፍ የሆነው ጥያቄ የአንድነት ሃይሉና አክራሪ የጎሣ ፓለቲከኞች በአንድ የፓለቲካ መርህ ስር እስካልመጡ የህወሃት የግፍ ዘመን እንደሚቀጥል መገንዘቡ ላይ ይሆናል። ለድሉ ጊዜ መራዘም ምክንያትም የህወሃት ጥንካሬ ሣይሆን የነዚሁ የጎሣ ፓለቲከኞች ፓለቲካዊ አሻጥር ዋነኛውን ስፍራ ይይዛል፤ እኛ ያላቦካነው አይጋገር፤ እኛ ያልመራነው ትግል ይዳፈን ከሚል ጨለምተኝነት ለመውጣት መቁረጥ ያስፈልጋል። እነዚህ ሁለት የፖለቲካ ጠርዞች የትግል አንድነት ፈጥረው ህወሃትን ከመፋለም ይልቅ ከህወሃት ፍርፋሪ መጠበቁን እስካልተው ለውጥ ምኞትን ሊሻገር አይችልም፤ ከተራ ቂመኝነት ወጥተን በስልት እና በአሰላለፍ ብንለያይ እንኳን በአላማ አንድነት እስካልተጋመድን ትግሉ ገት ሊኖረው እንደማይችል መገንዘቡ ጠቃሚ ይሆናል። በተለይ ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካም ሆነ የሐይማኖት እና ሌሎች መብቶች አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ ጎሳዊ ሳይሆን አጉራዊ ድርጅት እንዲፈጠር እና ጎልብቶ እንዲወጣ ጎሳ ተኮሮች ጥያቄያቸውን አደራጅተው ለማስከበር በአስተማማኙ ሀገራዊ አንድነት ስር እስካልተሰለፉ ወንበዴው የህወሓት ቡድን በጀመረው የሞት መንገድ ቢወድቅ እንኳን መሰረታዊ እና ተፈላጊው ለውጥ ሱና እንደሚሆንብን መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል።

ከወንበዴው የህወሓት ቡድን ጋር እያሰረም እየገደለም እያሰደደም ቢሆን እንኳን ጉዳት ለሚቀንስ ለውጥ ሲባል መነጋገር ይገባል በሚል መርህ ወደዚያ ወገን የፖለቲካ ቅልውጥ እያረጉ ወዲህ በተቃዋሚነት ከተሰለፈ ኃይል ጋር አይን ለአፈር መባባሉን ለማቆም ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። የትግል ስልት የድርጅቶች ምርጫ መሆኑን አምኖ መቀበል እገሌ ለውጥ አላመጣም እያሉ ከማላዘን እኔ የተሰለፍኩበት ትግል ምን አመጣ ብሎ መመርመር ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። ቅንነት እና መግባባት የጎደለው በመፈራረጅ የናወዘ ለውጥ ፈላጊ ከፈላጊነት አልፎ የለውጥ ባለቤት ሊሆን አይችልም። በተቃዋሚነት ጎራ ተሰልፎ እርስ በራስ በጠላትነት እየተያዩ ከወዲያ ወገን ጨቋኝን ለብሔራዊ መግባባት እና እርቅ በር ዘጋ እያሉ ሲከስሱ መኖር በእጅጉ እራስን ያስገምታል። እናም ከከሳሽነት ገምቢ ካልሆነ ጥላቻን የበለጠ ከሚገምድ ትችት እንውጣ፤ መሳደብ መብት ሳይሆን ብልግና መሆኑ ላይ ግንዛቤ እንያዝ። ለመነጋገር ተነጋግሮም ለመግባባት እንዘጋጅ። አንዴ የህወሓትን ሌላ ጊዜ የህዴድ እና የብአዴንን አሁን ደግሞ ኢህአዴግ የሚለውን የህወሓት የስም ስልቻ ስብሰባ ከመጠበቅ ስለራስ ስብሰባ እናስብ። መውጫ በሩ ይሄ ይመስለኛል።
ሃሳብን ማጋራት እንጂ ሽቅብ ምክር ተደርጎ አይወሰድብኝ።