December 17, 2017 00:22

የሲቪል ህግ ስርዓት (civil law system) የሚከተሉ ሀገራት በአብዛኛዉ የሚካፈሉት የወንጀል ህግ ጽንሰ ሀሳብ የበላይ አለቃህ ወንጀል እንድትሰራ ቢያዝህ ወንጀሉን እስከሰራህዉ ድረስ ወንጀለኛ ነህ:: ወንጀል እንድትሰራ አለቃህ ሲያዝህ እንቢ በል ::የአለቃህን ትዕዛዝ ተቀብለህ ወንጀሉን የሰራህዉ እንደሆነ ወንጀለኛ ነህ::በአለቃህ ማሳበብ አትችልም በማለት ያብራራል::

ኢህአዴግ የሚባለዉ ድርጅት ዉስጥ የተሰበሰቡ እና ተሰብስበዉ የነበሩ ወንጀለኞች ትንታኔያቸዉ ሁሉ ያስገርማል:: ወያኔ የሚባለዉ ርኩስ መንፈስ ያለበት ሀይል ስለሆነ የሚያዘዉ በሀገሪቱ የሚሰራዉ ወንጀል እና ሀጢያት ሁሉ የወያኔ ነዉ ይሉሃል::እነሱ በወያኔ መረብ ዉስጥ ሆነዉ እና የወያኔን አይነት ወንጀል እየሰሩ ወያኔን ብቻ ከሰዉ እራሳቸዉን ከደሙ ነጻ ያወጣሉ::በርግጥም የሚያሞኙት አላጡም::

ሰሞኑን 60 ሶማሌዎች በኦሮሚያ ክልል ተጨፍጭፈዋል:: ለዚህ ወንጀል ተጠያቂዉ ማን ነዉ? እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በርካታ የአማራ ማህበረሰብ ላይ በኦሮሚያ ዉስጥ የጭፍጨፋ እርምጃ እየተወሰደባቸዉ ነዉ:: ተጠያቂዉ ማን ነዉ? ወያኔ ብቻ?

ከወራት በፊት በግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠር የኦሮሞ ህዝብ ከሶማሊ ክልል በአንድ ጊዜ እንዲፈናቀል ተደርጓል::የተገደለዉ ምን ያህል እንደሆነ ከፈጣሪ በቀር የሚያዉቅ የለም::ጋምቤላ ክልል ላይ በአንዋኮች ላይ ምን ተደረገ? ደቡብ ክልል ላይ በአማራ ላይ ምን ተፈጸመ? አሁንም በመላ ሀገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምን እየተከናወነ ነዉ? ተማሪዎቹ የሚጨፈጨፉት በማን ነዉ?

ለዚህ ሁሉ ወንጀል ማን ነዉ ተጠያቂዉ?ህዉሃት ብቻ?

እያንዳንዱ ኢህአዴግ የሚባል ወንጀለኛ ሀይል ዉስጥ የተሰባሰበዉ ነዉ:: ኦሮሞዎች ሲገደሉ በሶማሌ ክልል መሪዎች ብቻ መለጠፍ አይቻልም::ወይም በህዉሃት ብቻ ማሳበብ አይቻልም::ሁሉም የኢህአዴግ አካል እና አመራር ሁሉ ተጠያቂ ነዉ::ኦሮሞን እመራለሁ የሚለዉ ኦህዴድ ጭምር ተጠያቂ ነዉ::ጎሰኝነትን : ጥላቻን እና መከፋፈልን ከወያኔ ተምረዉ እና ከወያኔ ጋር ሆነዉ ኢትዮጵያን ያመሷት ሁሉ ወንጀለኞች ናቸዉ::

አማራዎች ሲገደሉ ጣትን ወደ በደቡብ ክልል መሪዎች ወይም በኦሮሚያ ክልል መሪዎች ወይም በህዉሃት መሪዎች ላይ ብቻ መቀሰር አይቻልም::ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እና አመራሮች ተጠያቂ ናቸዉ::ብአዴን የሚባለዉ አማራን እመራለሁ የሚለዉ ድርጅት ጭምር::ሌላዉ ቀርቶ ዛሬ በስደት ሀገር እንደ ተቃዋሚ እንገፍ እንተፍ የሚሉት ቁዝር የወያኔ ድርጅት መስራች የነበሩ ወይም ወያኔን ለአስራ አምስት አመታ እና ለሃያ አመታት ሲያገለግሉ የነበሩ እና ትናንትና በአማራ ህዝብ ላይ የጥላቻ ፕርሮፖጋንዳ ሲያሰራጩ የነበሩ ሁሉ ወንጀለኛ ናቸዉ:: በምድር የሚፈርድ አካል ባይኖርም ህጉ ቀድሞ ፈርዶባቸዋል ከህጉ ፍርድ በሃልዎት አያመልጡም::የሰዉ ሰራሹ ህግ ባይፈርድባቸዉም እንኳን የአምላክ ህግ ይፈርድባቸዋል እና:: ንጉስ ዳዊት ብዙ ሚስቶች እያሉት የሚስኪኑን ሰዉ አንድ ሚስት በማማገጡ ብሎም ያንኑ ምስኪን በወንጀል በማስገደሉ እግዚአብሄር ቀጥቶታል:: አልታይም ብሎ ወንጀሉን ቢሰራዉም ሁሉን የሚያይ አምላክ ከፍርድ አልዘገዬም::

የኢትዮጵያን ህዝብ ያጋደላችሁ: ያስገደላችሁ: ከወያኔ ጋር የተባበራችሁ: ወያኔን እያገለገላችሁ ያላችሁ: ዘረኝነት በመዝራት ኢትዮጵያ ከምድረ ገጽ ትጠፋ ዘንድ የሰራችሁ ሁሉ ከፍርድ እንደማታመልጡ አትርሱት::በሰዉ ባይሆን በእግዚአብሄር ትቀጣላችሁ::ሌላዉ ቀርቶ አንዱን ወንጀለኛ ከሳችሁ አንዱን ወንጀለኛ የምታጀግኑ እዉራኖች ሁሉ ከፍርድ አታመልጡም::ወያኔን ኮንኖ ኦህዴድን ማንገስ: ወያኔን ረግሞ ብአዴን ከፍ ከፍ ማድረግ: ወያኔን ኮንንኖ ደህዴንን ማወደስ ሁሉም ወንጀል ነዉ::ከወንጀለኛ አካላት ትዕዛዝ እየተቀበሉ ህዝባችንን የሚያሳርዱ ናቸዉና::ህዝባችን በልዩ ልዩ ቦታ ሲታረድ ወንጀልን አልተቃወሙም እና::

ዛሬ አንዳንድ ተንታኝ ነን የምትሉ ወይም ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነን የምትሉ በብልጠት እና በማምታታት አንዱን ወንጀለኛ ከሌላዉ ወንጀለኛ ለማጋጨት ብለን ነዉ አንዱን ኮንነን ሌላዉን የምናወድሰዉ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል:: ወይም አንዳንድ ሰዎች ኦሮሞ ስለሆኑ የኦሮሞ ወንጀለኛ ኦህዴዶችን ለማጀገን ወይም አማራ ስለሆኑ የአማራ ድርጅት ተብሎ የተሰዬመዉን የብአዴን ወንጀለኞችን ለማጀገን ደፋ ቀና እያሉም ሊሆን ይችላል::

ሆኖም ወንጀል እና ወንጀለኝነትን በህዝባችን ህሊና ዉስጥ እየዘራችሁ: ወንጀል እና ወንጀለኝነትን ህዝቡ እንዳይጸየፍ እያበረታታችሁ ብሎም ኢትዮጵያዉያንን እያሳረዱ ያሉትን ወንጀለኛ ሀይሎች እንደ ብሄራዊ ጀግና እየሰበካችሁ ነዉና በሰዉ ባይሆን በሰማይ አምላክ መቀጣታችሁ አይቀርም:: እግዚአብሄር ሀሰት እና ወንጀለኝነትን መጸየፉን ብታምኑም ባታምኑም እዉነታዉ ግን በሰማይ ህግ ወይም በምድር ህግ አለዚያም በሁለቱም መጠየቃችሁ እንደማይቀር አለመረዳታችሁ አሳዛኝ ነዉ::

ዛሬ 60 የሶማሌ ማህበረሰብ አባላት ሲታረዱ ለምን ብአዴን አይቃወም? ለምን ኦህዴድ አይቃወምም? ትናንት ኦሮሞዎች : እንዲሁም አማራዎች ሲጨፈጨፉ ሁሉም እያዩ ዝም የሚሉት ምን ስለሆኑ ነዉ? ወያኔ ብቻ ተጠያቂ ነዉ ማለት አይቻልም:: አንድ የኢህአዴድ አባል ድርጅት ወይም አንድ የኢህአዴግ አባል ግለሰብ ጉልበት ባይኖረዉ ተሰሚነት ባይኖረዉ ወይም ጮሆ የሚሰማዉ ቢያጣ የሚሰራዉን ወንጀል አዉግዞ እስከዛሬም ከወንጀለናዉ ኢህአዴግ ጋር በመሰራቱ ወንጀለኛ መሆኑን አምኖ እና ለሰራዉም ወንጀል ህዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ከድርጅቱ ለቆ መጥፋት ይችላል::አንድ ሰዉ ወንጀል ለማዉገዝ ከርሱ ጎሳ ላይ ወንጀል እንዲሰራ መጠበቅ የለበትም::ጎሰኝነት በራሱ ወንጀል ነዉ::ጎሰኝነት ማለት ህዝብን መለያዬት: የኔ ወገን ባቻ ይድላዉ: ሌላዉ ይጥፋ: ወይም ደግሞ የኔ ጎሳ እስካልጠፋ ድረስ የሌላዉ ጎሳ ቢጠፋ አይመለከተኝም ብሎ ማሰብ ነዉ::

ስለሆነም እነዚህን ወንጀለኞች ተስፋ አድርጋችሁ ወንጀለኛዉን ወያኔን ለመቃወም ወንጀለኞቹን ኦህዴድን እና ብአዴን ለማንገስ የምትንጠራወዙም ያዉ ወንጀለኛ ናችሁ::ኢትዮጵያን የናንተ የተምታታ እና የተሳከረ ትንታኔ አያድናትም::የምትድን ከሆነ እዉነትን የሚፈርድ እግዚአብሄር ያድናታል እንጅ::ወያኔን ከነ ሰንኮፉ: ከነ ተባባሪ ወንጀለኞቹ እና ከሀሳብ ተጋሪዎቹ ጋር ሁሉ ነቅሎ መጣል እና የኢትዮጵያን ህዝብ እዉነተኛ ሰላም እና ዲሞክራሲ እንዲያገኝ ለማድረግ ቁርጥ እና ጥርት ያለ ትግል ማድረግ ሲገባ አንዱን ወንጀለኛ በሌላዉ ወንጀለኛ ለመተካት የምታሽቃብጡ ሁሉ የህዝብ ጠላት እና ወንጀለኛ መሆናችሁን ህዝብ በአርምሞ እያስተዋለ በልቡ እንደሚያዝን እንዳትዘነጉት::

አሁንም የራሳቸዉን ጎሳ ጥቅም እና ፍላጎት ብቻ በማስቀደም የሚራወጡ የወያኔ ተባባሪ ሀይላት: በኢህ ዴግ ድርጅት ዉስጥ በግንባር አባልነት የተሰገሰጉ ድርጅቶች ሁሉ ወንጀለኛ : የኢትዮጵያ የጥፋት ምንጭ ናቸዉ::በነዚህ ሀይሎች ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ተገፍቶ ተገፍቶ አሁን ለደረሰበት የሰቆቃ እና የመከራ ዘመን የበቃዉ::እነዚህ ወንጀለኞች አንዱን ካንዱ የተሻለ ለማድረግ የምትራወጡ ሁሉ ያዉ ወንጀለኛ ናችሁ:: እናም ታጋይ ከሆናችሁ ትግላችሁ ጥርት ያለ እና ወያኔን ከነ ሰንኮፎቹ እና ተባባሪ ወንጀለኞቹ የሚነቅል ይሁን::

የሀሳብ አቀንቃኝም ከሆናችሁ የሀሳባችሁ ፍሰት ጥርት ባለ እዉነት: ሰበአዊነት እና ዲሞክራሲያዊነት ላይ ይጽና::ኢትዮጵያ እንድትድን ከፈለጋችሁ እዉነትን : ፍትህን : ዲሞክራሲያዊነትን እና ሰበአዊነትን ብቻ ተስፋ አድርጉ::ለዚህም ሀቅ ብቻ ተዋደቁ::