24 December 2017

ታደሰ ገብረማርያም

በአዲስ አበባ ከተማ 74 ከመቶ የሚሆኑት አረጋውያን ለከፍተኛ፣ እንዲሁም 97 ከመቶ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መዳረሻ የምግብ እጥረት እንደሚገጥማቸው ተነገረ፡፡ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ለአረጋውያን›› በሚል ርዕስ ታኅሣሥ 12 ቀን 2010 .. የኢትዮጵያ ጡረተኛና አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር ባካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ  እንደተመለከተው፣ ለምግብ እጥረቱ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ድጋፍ አናሳ መሆን እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያቀረቡት የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ከፍተኛ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አማን ዋቢ እንዳሉት፣ ምንም ገቢ አለመኖር ወይም አነስተኛ ገቢ መኖር፣ የምግብና የሌሎች ፍላጎቶች ዋጋ መናር፣ የጤና ችግርና ወጪ መክፈል አለመቻል ለምግብ እጥረቱ መከሰት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የሥራ ቅጥርና የገቢ ማስገኛ ተደራሽ አለመሆን፣ አረጋውያንን የሚረዱ ድርጅቶች እምብዛም አለመኖርም ችግሮች ናቸው፡፡ አረጋውያን ከቤተሰብና ከዘመድ፣ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከሌሎች ውስን ድጋፍ ቢያገኙም፣ የማኅበረሰቡ ድጋፍ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መሄዱም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ጡረተኞችና አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንደሻው ታዬ እንደገለጹት፣ አረጋውያን በሦስት እንደሚከፈሉ፣ አንደኛው ሁሉ ነገር የተሟላላቸው መሥራትና መስጠት የሚችሉ፣ እንዲሁም በልምድና በዕውቀትም ብቁ የሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ትንሽ ድጋፍ ቢደረግላቸው መንቀሳቀስ፣ መሥራትና አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን ናቸው፡፡ ድጋፍ ለሚሹ አረጋውያን ተገቢውን እንክብካቤና ድጋፍ ለሚሰጡ እንደ መቄዶኒያ ለመሳሰሉት ድርጅቶች አስፈላጊውን በማመቻቸት ረገድ ብሔራዊ ማኅበሩ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተፅዕኖ ለመፍጠር ለየብቻ ከሚደረገው የማስማሚያ (ሎቢ) ሥራዎች በተጨማሪ ‹‹አረጋውያን ተግባራዊ ምላሽ ይሻሉ›› በሚል የተለያዩ ፊርማዎችን በማሰባሰብ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅሬታ ሰሚ አካል እንዲደርስ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ደኅንነት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር፣ አገሪቱ የፈቀደላትን አቅም ሁሉ ለአረጋውያን ማድረግ እንደሚገባት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ላይ ቢደነገግም፤ አስፈጻሚ አካላትም አረጋውያንን ተጠቃሚና ተሳታፊ ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም አዋጅ ቢወጣም መሥሪያ ቤታቸው እነዚህ በተገቢው መንገድ ተፈጻሚነት አግኝተዋል የሚል ግምት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡   አስፈጻሚ አካላት ለዚህ ችግራቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ለአረጋውያን ድጋፍ ተብሎ የተቀመጠ በጀት የለንም የሚል መሆኑን አቶ ፈለቀ ጠቁመው፣ ሆኖም መንግሥት ለአስፈጻሚ አካላቱ የሚመደበው በጀት በአጠቃላይ መሆኑንና በበጀቱም ውስጥ የአረጋውያንን ጉዳይ እያካተቱ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ስድስት በመቶ ወይም ከአምስት ሚሊዮን በላይ አረጋውያን እንዳሉ ይህ ቁጥር በ2042 .. ወደ አሥር በመቶ እንደሚያድግ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር በአረጋውያንና ጡረተኞች ደኅንነት ዙሪያ የሚሠሩ 38 ማኅበራት አንድ ላይ በመሆን በ1990 .. የመሠረቱት ተቋም ሲሆን፣ ዕውቅና ያገኘውም በ1993 .. ነው፡፡

ሪፖርተር.