አማርኛን እናዘምን! እናሰልጥን!
አማርኛ ከዘመናዊው አኗኗርና አስተሳሰብ በተለይም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በብቃት አብሮ ሊራመድ አለመቻሉ በተለይ አሁን በዘመነ ‘ኢንተርኔት’ እጅግ አግጥጦ የወጣ ሃቅ ነው። አገሪቱም ለአማርኛ ቋንቋ የልማት እቅድ የላትም። የተያዘው የደመነፍስ ጉዞ የተቻለውን በአማርኛ የልተቻለውን በእንግሊዝኛ እያደባለቁ መሄድ ነው። የዚህ አካሄድ መድረሻው ለብዙዎቻችን የተሰወረ አይደለም። በሌላ በኩል በህሊና እንመራ የሚሉ ጥቂት ዜጎች ዘመናዊ አስተዳደር ወደአገሪቱ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ዘመናዊውን አኗኗር በአማርኛ የመምራትን አስፈላጊነት ተገንዝበው ሰዋስዉን በማተትና መዛግብተ ቃላትን በማጠናቀር አማርኛን ለማዘመን ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል፤ የቋንቋውን የልማት ጎዳና ጠርገዋል። በመሃሉም በመንግስት ትእዛዝና ድጋፍ እንዲሁም በታላላቅ ምሁራን ተሳትፎ በተከወነ ትልም በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽንሰሀሳቦች መተርጎሚያ ይሆናሉ የተባሉ የአማርኛ ቃላት ተፈጥረው በመዛግብተ ቃላት ታትመዋል፤ መልካም ጅምር ቢሆንም ሁሉም እንደሚያውቀው ውጤቱ ያልጠቀመ በከንቱ የቀረ ትልም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አማርኛን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ የማድረግን አስፈላጊነት የሚለፍፉ ጩኸቶች ተበራክተዋል፤ አርአያነት ያላቸው ጥቂት የግል ጥረቶችም ታይተዋል። እዚህ ላይ ጥርጊያውን መንገድ ይዞ፣ ከውድቀት ተምሮና የወገንን ተነሳሽነትና አስተዋጽኦ አለኝታ አድርጎ ዘላቂ ትልም ማበጀት ያስፈልጋል። እኔም በዚህ አጋጣሚ በስነልሳን ተማሪነቴ የበኩሌን ለማድረግ ድምጼን በማሰማት ጩኸቱን ከማድመቅ ባለፈ ለአንድ አሰርት አመታት ያህል ባደረግሁት ምርምር ያገኘሁትን እጅግ ጠቃሚ የምለውን የቃላት ፍች ምርመራና የአዳዲስ ቃላት አፈጣጠር ዘዴ ለማካፈል፣ እንዲሁም የሌሎችን ታታሪ ግለሰቦች ተግባራዊ አስተዋጽኦዎች በማስተባበር የአማርኛን ልማት ለመምራት አቅጃለሁ።

እቅዴን ለማስተዋወቅ መነሻ እንዲሆነኝ ስለአማርኛ መሰልጠን አስፈላጊነት በጽኑ አምነው (እኔ በማውቀው ከዛሬ ሰባትና ስምንት አመታት ጀምረው) የፈጠሯቸውን ቃላት እያስተዋወቁ የ’አማርኛ ይሰልጥን’ ጥሪአቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙትና ስለጉዳዩም ጥሩ ውይይት ያስጀመሩት ዶ/ር መስፍን አረጋ አማርኛ አሁን ስላለበት ሁኔታ የሰጡትን አጭር ግምገማና መፍትሔ ያሉትን የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በመቃኘት እጀምራለሁ። በተለይ “ሰገላዊ አማረኛ (አማሮምኛ)” በሚል ርእስ በተለያዩ ድረገጾች ያወጡት ጽሑፍ መሪ ሃሳባቸውን የያዘ ነው። ዶ/ር መስፍን በዚህ ጽሑፋቸው ያቀረቧቸው ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ይጠቃለላሉ፦  አማርኛ እንግሊዝኛ ባደረሰበት ጥቃት ተዳክሞ ወደ መጥፋት እየተቃረበ ይገኛል ይላሉ። የጥቃቱንም ሁኔታ በወታደራዊ አቋምና በጦርነት ይመስሉታል።  ለጥቃቱ መሪና አባሪ የሆኑትም ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ባለስልጣኖች ናቸው ሲሉ ይከስሳሉ።  እሳቸው ‘መሰሪ’ ያሉት የነዚህ ወገኖች የጥፋት ስልትም ተራውን ህዝብ የራሱን ቋንቋ ንቆ እንግሊዝኛን እንዲያከብር ማሳመን ነው።  በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች አማርኛን እንዳይናገሩ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው የልጆችን ስም እንዲሁም የማእርግ፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የህንጻዎች፣ የሸቀጦች፣ ወ.ዘ.ተ ስሞችን ከአማርኛ ይልቅ በእንግሊዝኛና በሌሎች የውጭ ቋንቋዎች መሰየሙ ራስን የመናቅና ማንነትን የማጣት መታያዎቹ ናቸው ይላሉ።  ታላላቅ የቀድሞ የአማርኛ ቋንቋ ሊቃውንትን ጠቅሰው አማርኛን ለጥቃት ያጋለጠው እንደነዚያ ያሉ ጠባቂዎቹን በማጣቱ ነው ሲሉ ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።  የአማርኛ ጥፋት የኋላ ኋላ የማህበረሰቡ ማንነት ጥፋት ስለመሆኑ ያስጠነቅቃሉ።  በመጨረሻም አማርኛ በአለም ከሚገኙ አበይት ከሚባሉ ቋንቋዎች አቻ ከመሆንም አልፎ በብዙ እጥፍ ሊበልጥ የሚያስችለው ስርዓት እንዳለው ይጠቁሙና፣  አማርኛን ለማዳን አሁን የሚያስፈልገው የተዛባውን ስርአቱን ማስተካከልና አዳዲስ ቃላትን መፍጠር ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ። አዳዲስ ቃላትን የመፍጠሪያው ዘዴም ከአማርኛ ስርአት ጋር እያስማሙ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች መቅዳት ነው ይላሉ። በዚህ አይነት ራሳቸው የአማርኛን ቃላት (በተለይ)፟ ከኦሮምኛ ቃላት ጋር በማዳቀል ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እሳቤዎች መወከያ የፈጠሩትን የቃላት ስብስብ ‘አማሮምኛ’ ወይም ‘አማሮሚፋ’ ይሉታል። ያዘጋጁትን የቃላት ስብስብና የቃላት አፈጣጠሩን ዘዴ ቢቀበሏቸው ኢትዮጵያውያን በራስ መተማመንንና ታላቅነትን መልሰው እንደሚቀዳጁ ይመክራሉ።

ዋና ዋና ነጥቦቻቸውን ዘርዘር አድርገን ስንገመግም፣ እንግሊዝኛ በአማርኛ ላይ ስላደረሰው በደል ያስረዱበትን ተውኔታዊ ገለጻ የተጠቂነትን አስተሳሰብ ለማጕላትና አንባቢን በቁጭት ለማነሳሳት የተከተሉት የአቀራረብ ዘይቤ ነው ብለን እንተወው። እውነት ግን አማርኛን ያቈረቈዘው እንግሊዝኛ ነው? አይደለም! የአማርኛ ባለቤቶች ለራሳቸው ካለማወቃቸው፣ በተለይም ከሌላው አለም የሚመጣውን የዘመናዊነትን እውቀትና ብልሃት ከባህሪው አስማምቶ እንዲቀበል፣ ለዘለቄታውም የእውቀትና የብልሃት ፈጠራ መሪና ዘዋሪ እንዲሆን ቋንቋቸውን ለማመቻቸት ካለመትጋታቸው የተነሳ፣ ከሸቀጥ ጋር ስሙን፣ ከአስተሳሰብ ጋር ብሂሉን (በተለይ) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ እየሰገሰጉ የቋንቋቸውን የመፍጠር አቅም አዳከሙት እንጂ እንግሊዝኛ ቋንቋ በአማርኛ ላይ ያደረሰው ጥቃት የለም። እንዲያውም የአማርኛ ባለቤቶች ቢያውቁበት እስካሁን ሳይንስ የከሰተውን ሩቅና ረቂቅ አለም ለመመልከት እንግሊዝኛ መነጽራቸውና መንገድ መሪያቸው ነበር። እዚህ ላይ ሰዎች እንጂ ቋንቋዎች እንደማይጠቃቁ ጸሐፊው ይስቱታል ብዬ አይደለም። ነገሩ ራስን ከመጣል እንጂ ከተጠቂነት አንጻር መቅረብ የለበትም ለማለት ነው።

እንግሊዝኛን በጠላትነት በማየት አማርኛን አንታደገውም። ታላቅነቱንና ሃያልነቱን እንዴትም ያግኘው፣ እንግሊዝኛ ዛሬ ታላቅና ሃያል ቋንቋ ነው። እርግጥ ነው እንግሊዝኛ አሁን አለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት እንደማንኛውም ቋንቋ እንደነበረ ማስታወሱ አማርኛም የመላቅና የማየል ተስፋ እንዳለው በማመልከት ቀናእያን ዜጎችን ለቋንቋቸው ማደግ እንዲጥሩ ያነቃቃል። ሆኖም እንግሊዝኛ ድንገት ተነስቶ ከሌሎች ቋንቋዎች ቃላትን አግበስብሶ እንደዳበረና እንዳየለ አድርጎ ማቅረቡ ግን እውነተኛውንና ብናውቀው የሚጠቅመንን የእድገቱን ምስጢር ከራስ መሰወር ይሆናል። እንግሊዝኛ ከሚዘውረው ስልጣኔ ጋር በታታሪ ባለቤቶቹ ብርቱ ጥረት ተከብክቦ የዳበረ ቋንቋ ነው። ይልቅስ እንግሊዝኛ ለዛሬው አቅሙ የበቃበትን የእድገት ሂደቱን መርምሮ ለአማርኛ ማሰልጠኛና ማዘመኛ የሚረዳውን ብልሃት መቅሰም ይበጃል።

‘አማርኛን ያዳከመው የኢትዮጵያውያን ምሁራንና ባለስልጣኖች መሰሪ ተግባር ነው’ ማለት የባለስልጣኖችንና የምሁራንን የአገር ራእይ ቅድስና የሚገመግም አስተያየት ነው። መነሻ ሀሳባችን ‘ባልስልጣኖችንና ምሁራንን ጨምሮ ባለአገሮቹ አገራቸውን የሚያለማ እንጂ የሚያጠፋ ራእይ ይዘው አይነሱም’ ነው። ወደተሻለ መደምደሚያ ባያደርሰንም ነገሩን እንዲህ ብንመለከተው ይሻላል። ከጅምሩ የትናንት ህጻናት የዛሬዎቹ ባለስልጣኖችና ምሁራን፣ በአገር ውስጥም ሆነ ወደውጭ አገር እየተሻገሩ የምእራባውያንን ስልጣኔና ዘመናዊውን እውቀት በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲቀስሙ ሲደረግ፣ በቀዳሚነታቸው የተማሩትን ለተከታዮቻቸው በአማርኛ ቋንቋ እያስተማሩ የኋላ ኋላ አማርኛ ራሱን ችሎ የዘመናዊ እውቀት መዘውር እንዲሆን ቋንቋውን የማሰልጠንና የማዘመን ስራ በእቅድ አልተሰራም። በዚህ እቅድ መጕደል የተነሳ የኑሮ ልማዶቹን በዘፈቀደ ‘ማዘመን’ የጀመረው አገሬው፣ ቋንቋውንም እንደአሮጌዎቹ ልማዶቹ እየተወ እንግሊዝኛን እየተቀበለ አዘገመ። ጊዜውም ረዘመና ይኸው ዛሬ ተራና የዘወትር የሚባሉ ሃሳቦችን እንኳ በአማርኛ ቃላት መግለጽ እስከሚቸግር ድረስ አማርኛ ደበዘዘ። ይህን ችግር ባለስልጣኖችና ምሁራን በመሰሪነት ባያመጡትም በግዴለሽነትና በንዝህላልነት እንዲንሰራፋ በመተዋቸው ወቀሳው አይቀልላቸውም።

በሌሎች አበይት የኑሮ ዘርፎች አማርኛ እስካሁን ተገልሎ የቆየባቸውን አገልግሎቶቹን ትተን ዶ/ር መስፍን ያነሷቸውን ጥቂቶቹን ብንመለከት፦ አዎ ዛሬ ህጻናቱ፣ የንግድ ተቋማቱ፣ የወታደርና የፖሊስ ማእርጎች፣ ወዘተ. በአማርኛ መሰየማቸው ቀርቶ በእንግሊዝኛ እየሆነ ነው። ግን ሊያስደንቀን አይገባም። እንግሊዝኛ ቋንቋን ‘በጥራት ለማስተማር’ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ልጆች ከእንግሊዝኛ በቀር አማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ የሚያሳፍሩና የሚያሸማቅቁ ማስታወቂያዎች እየተለጠፉና እየተለፈፉ ነው። ይህም ሊያስደነግጠን አይገባም። በግልጽም ሆነ በስውር ብዙው ሰው ‘በዘመናዊ ኑሮ አሸናፊ ለመሆን ዋነኛው መሳሪያ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እውቀት ነው’ ብሎ ያምናልና። አማርኛ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳለ ይህን እምነት በቀጥታ መጋፈጥ አይቻልም። አማርኛ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳለ የተዘረዘሩትን የማንነት ቀውስ ምልክቶች እያነሳን ሰዎችን “ማንነታችሁ ነውና አማርኛችሁን ጠብቁት” በማለት የለውጡን ሂደት አንገታውም። የማንነታቸው ጥፋት ሰዎችን ስለማያሳስባቸው ሳይሆን የጥፋቱ ሂደት በጣም አዝጋሚና ወዲያው የማይታይ በመሆኑ በግሉ የኑሮ እሽቅድድም የራስን ደረጃ ለማሻሻል ከመፍጨርጨር አልፈው የጋራ ለሆነው ማንነት ተገቢውን ትኩረት ስለማይሰጡት ነው። ስለዚህ እንደኢኮኖሚው ልማት ሁሉ አማርኛን በማሰልጠን ለዘመናዊ አኗኗር ብቁ መሳሪያ የማድረጉ አስፈላጊነት በጽኑ ሊታመንበት የሚገባው በመንግስት ባለስልጣኖችና በምሁራን ነው።

ምሁራንና ባለስልጣኖች ቋንቋቸው ሰልጥኖ ለዘመናዊ አስተሳሰብና አኗኗር ብቁ መሳሪያ ቢሆን የሚገኘውን ጠቀሜታ አይስቱትም። ጉዳዩ ለተግባሩ አፈጻጸም እስካሁን አስተማማኝ ዘዴ አለመኖሩ ነው። ዶ/ር መስፍን የሳይንስና የቴክኖሎጂ እሳቤዎችን የሚወክሉ የአማርኛ ቃላትን ለመፍጠር ያስችላል ያሉት የአማርኛ የቃል ዘሮችን ከኦሮምኛ ወይም ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የቃል ዘሮች ጋር የማዳቀል ወይም አዳዲስ የቃል ዘሮችን ወደአማርኛ የማስገባት ዘዴ (ምንም እንኳ ቃላቱ በአማርኛ ቋንቋ ስርአተ ቃላት እንዲዋለዱና እንዲረቡ ሆነው ቢፈጠሩም) ከነባሮቹ ቃላት ጋር ጥብቅ የድምጽና የፍች ትስስር የማያሳዩ ባእድ ቃላትን የሚያበዛ ነው1። ከሌላ ቋንቋ በማዳቀል የሚፈጠሩትም ሆነ በቀጥታ የሚገቡ ቃላት ለአስተናጋጁ ቋንቋ በሁለመናቸው እንግዳ ናቸው። ስለዚህ ለመለመድ በጣም አዳጋች ይሆናሉ። አዳዲስ ቃላት በቀላሉ የሚለመዱት ከነባሮቹ ቃላት ጋር ሊመረመር የሚችል ስርአታዊ የፍችና የድምጽ ትስስር ሲኖራቸው ነው። የቃላት አፈጣጠሩ ዘዴም ይህን እውነት ያገናዘበ መሆን አለበት። ዶ/ር መስፍን በተለይ ከኦሮምኛው ጋር የማዳቀሉን ሃሳብ በባህል ማስተሳሰሪያነቱና በፖለቲካ ውጥረት ማርገቢያነቱ አይተውት በልዩ ልዩ የሳይንስ ዘርፎች ያላቸውን እውቀት ተመርኩዘው በብርቱ ትጋት በርካታ ቃላትን ፈጥረው ቢያሳዩንም፣ በመሰረቱ የተከተሉት ዘዴ የአማርኛ ቋንቋን ስነሕይወት በጥልቀት ያላገናዘበ ነው። እንዲህ ባእድ ቃላትን እየፈጠሩና እየተዋሱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እሳቤዎችን የመሰየሙ አካሄድ በሌሎችም የቋንቋ ልማት ጥረቶች ተሞክሮ ምንም ያህል አላራመደም።

ቋንቋን የማዘመንን ዘዴ በቀጥታ ከእንግሊዝኛ ልንቀዳው አንችልም፤ ምክንያቱም እንግሊዝኛ በእቅድ አልዘመነም። የዘመናዊነት ለውጥ ጅምሩ ከታየ በኋላ ግስጋሴው በአስተውሎት መታገዙ ባይቀርም፣ የምእራቡ አለም አኗኗር ወደዘመናዊነት የተሸጋገረው በተፈጥሮአዊ ሂደት እንጂ እንደኛ አርአያ ተከትሎ ‘ልማት’ ተብሎ ታቅዶለት አይደለም። የእንግሊዝኛ ዘመናዊነትም በአብዛኛው እዚያው በኑሮው ለውጥ መሃል የሆነ ነው። በታቀደ ልማት በአፋጣኝ ወደዘመናዊነት ለመሸጋገር የሚያልሙ ማህበረሰቦች ግን እውቀትን የልማታቸው ሃይል ማድረግ የሚሹ ከሆነ ለቋንቋቸውም መዘመን የልማት እቅድ ሊያበጁለት ይገባል። በተፈጥሯዊ ሂደት የዘመኑትን የምእራባውያን ቋንቋዎችን አስተዳደግ ከመመርመር ቋንቋ እንዴት እንደሚለማ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ዋናው ምርምር ግን የራስን ቋንቋ ተፈጥሯዊ የፈጠራ አቅም እማወቅ ላይ ማተኮር አለበት። ሆኖም ጥቂት የማይባሉ የምሁራን ትውልዶች ያለፉበት በአብዛኛው የአውሮፓውያን ቋንቋዎች ጥናት ባስገኘው ስነዘዴ ላይ የተመሰረተው ዘመናዊው የቋንቋ ጥናትና ምርምራችን ክፋቱ፣ አማርኛ ቋንቋ ስርወቃላትን ከ(ምስረታና እርባታ) አምዶች ጋር አስማምቶ በአምደቃላቱ ላይ ምእላዶችን ከመለጠቅ፣ ወይም ቃላትን ከቃላት ከማጣመር ያለፈ የቃል ፈጠራ አቅም እንዳለው አላስገነዘበንም። የአማርኛን የቃል ፈጠራ አቅም ለመገንዘብ የሚያስፈልገው የስርወቃላቱን ረቂቅ ፍች አንጥሮ ማውጣትና ስርወቃላቱ የተመሰረቱባቸውን ድምጾች የፍች አስተዋጽኦ መመርመር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ታዲያ በትምህርት ቤት ቆይታዬ ከተለመደው የቃላት ምስረታ ትንታኔ ላፈነገጡ የቃላት ግንኙነቶች ተስማሚ ማብራሪያ
ሳፈላልግ የተከተልኩት አግጣጫ የአማርኛ ቃላትን የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ ዘልቄ እንድመለከት አስቻለኝ። እንግዲህ ይህን የፍችተድምጽ ተዛምዶ ነው የአማርኛ ድልብ የቃላት ፈጠራ አቅም ነው የምለው። ወደዚህ ግኝት እንዴት እንደደረስኩ ከዚህ በታች በአጭሩ አስረዳለሁ። ግኝቱም ለቃላት ፈጠራ እንዴት ሊውል እንደሚችል በተከታይ ክፍል እመለስበታለሁ።

መጀመሪያ ቀጥተኛ የስርወቃል ዝምድና በሌላቸው የአማርኛ ቃላት መካከል የድምጽና የፍች መቀራረብ እንዳለ አስተዋልኩ2። ከዚያም በጠቅላላው በቃላት ውስጥ የሚታየው የፍች-ተድምጽ ጥምረት መነሻው ከስርወቃላት ዝቅ ባለ ደረጃ ይጀምራል ከሚል መላምት ደረስኩ። በምርምሬ ሂደትም በልቡናዬ ከስርወቃል በሚፈጠሩ ቃላት ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ድምጽ ለሚገነባው ቃል ረቂቅ የፍች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተሰማኝ። ከዚህም ተነስቼ ድምጾች በተናጥልና በጥምረት የሚኖራቸውን ረቂቅ የፍች አስተዋጽኦ 1ኛ) የባለሁለት ተናባቢ ሁለት ዛላ (ምሳሌ፦“ዛለ”) ስርወቃላትን ረቂቅ ፍች ከባለሁለት ተናባቢ ሶስት ዛላ (ምሳሌ፦”ዘለለ”) እና አራት ዛላ (ምሳሌ፦ “ዘለዘለ”) ስርወቃላት ጋር በማገናዘብ 2ኛ) የያንዳንዱን ድምጽ ረቂቅ ፍች በመጀመሪያ ያንኑ ድምጽ በመድገም ከሚፈጠሩ ባለአንድ ተናባቢ ሁለት ዛላ (ምሳሌ፦“ዛዛ”፣”ላላ”) ስርወቃላት፣ ከዚያም ያንን ድምጽ ከሚይዙ ተዛማጅ ባለብዙ (2-4) ተናባቢና ባለብዙ ዛላ ስርወቃላት ጋር በማገናዘብ አንጥሮ ማውጣት እንደሚቻል ተመለከትኩ። ከዚያም ረቂቅ ፍቻቸው የተለዩት የሁለት ተናባቢ ቅንጅቶች በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ በበቂ ድግግሞሽ በባለሶስትና በባለአራት ዛላ ስርወቃላት (ምሳሌ፦ “ዘለ” በ“ዘለመ” እና በ“ዘለበደ”) ውስጥ ሲገኙና አቃፊዎቹ ስርወቃላት የታቃፊዎቹን ረቂቅ ፍች ሲጋሩ ከመመልከት፣ የአማርኛ ቃላት የፍች ትስስር ሃረጋቸው ከስርወቃል ወርዶ እስከ ጥምርና ነጠላ ድምጾች ደረጃ እንደሚዘልቅ ተገነዘብኩ። ይህ የፍች-ተድምጽ ጥምረት ክሳቴ ከራሴ የግል ስሜትና ካደረግኩት ትንታኔ አልፎ በቋንቋው ተናጋሪዎች ልቡና ይኖር እንደሆን ለማወቅ ባደረግኩት መጠይቃዊ ቅኝት በአስተማማኝ መጠን ማረጋገጫ አግኝቼበታለሁ።

ከዚህ ግኝት በመነሳት የቃላት ግንባታውን ስርአት እንደሚከተለው ማደራጀት ይቻላል። ለቃላት የድምጽ-ተፍች ጽንስ የሆኑትን ጥምርና ነጠላ ድምጾች3 ዘረቃል ብንላቸው፣ ዘረቃላቱ በተጨማሪ ድምጾች እየተዶጐሙና እየተጐላመሱ ስርወቃላትን ይፈጥራሉ፤ ስርወቃላቱ ደግሞ በስነምእላዳዊ ሂደት ለቃላት ግንባታ መሰረት ይሆናሉ። እንግዲህ አንድም የቃላትን የፍች መሰረት እስከዘረቃላት ድረስ ወርደን መረዳት እንችላለን፤ ሁለተኛም የቃላት ምስረታ በነባር ስርወቃላት ብቻ እንደማይወሰን እናምናለን፤ እናም በፍቻዊ መሰረታቸው እንግዳ ያልሆኑ አዳዲስ ስርወቃላትንም መፍጠር እንችላለን ማለት ነው። በርግጥም በዚህ አይነት የቃላትን ረቂቅ ፍችዎች በጥልቀት መመርመርና አዳዲስ ስርወቃላትን ከቋንቋው ስርአት ሳይወጡ መፍጠር ከተቻለ፣ በትውስት ቃላት ተደንግሮ የቆመው የቋንቋው ተናጋሪዎች ምናብም ይነቃና እሳቤዎቹን በቋንቋው መሰየሙን ይቀጥላል።

በመጨረሻም አንባቢዎቼን በተከታዩ የፍች ትንታኔና የቃላት ፈጠራ ማብራሪያ ጽሑፌ እንድንገናኝ ስቀጥር፣ በተለይ ደግሞ ዶ/ር መስፍን አረጋ ጥልቅ የሳይንስ እውቀትዎን፣ ልዩ የቋንቋ ችሎታና አስተውሎትዎን፣ የማይበገር የስራ ትጋትዎን፣ እንዲሁም ነዲድ የአገር ፍቅር ስሜትዎን ይዘው አሁን ያስተዋወቅሁትንና በተከታይ የማብራራውን አዲስ የቃላት አፈጣጠር ዘዴ በጥሞና እንዲገመግሙና አስተያየትዎን እንዲሰጡ በአክብሮት በመጋበዝ ነው። እንዲሁም ዶ/ር መስፍን፣ የአማርኛን ስነሕይወት በጥልቀት ባገናዘበ ሁኔታ በብሩህ ምናብዎ አዳዲስ ቃላትን እየፈጠሩ በቅርቡ በሚመሰረተው የ‘አማርኛን እናሰልጥን’ ህብረት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሰላም! በዛ ተስፋው አያሌው ለጥያቄና ለአስተያየት፦ btadata@gmail.com

1 እዚህ ላይ የዶ/ር መስፍን ጽሁፍ በየድረገጹ ታትሞ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ በነበረበት ጊዜ ፍሥሓ የተባሉ አስተያየት ሰጪ የቃላት ፈጠራው ዘዴ “ዛሬን ከትናንትም ከነገም፣ ትውልዱን ከአበውም ከውሉድም፣ የማይለይ …” ይሁን ያሉትን፣ እንዲሁም ቦጋለ ዳኜ የተባሉ አስተያየት ሰጪ “አንዳንድ ጊዜ ቃላቱን በቀላሉ ለመያዝ በውስጣቸው ያለው መነሻ ዘር ስለማይታወቅ ማስታወስ ይቸግራል።” ማለታቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። 2 ይህ ሁነት በሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎችም በተወሰነ ደረጃ ስለመታየቱ ቀደም ያሉ ሊቃውንት ገልጸዋል። የፍች-ተድምጽ ተዛምዶ በአረብኛ ቋንቋ ጥልቅ የቃላት ግንኙነት ስርአት ስለመሆኑ በተለይ ጆርጅ ቦዋስ በርከት ያሉ ምርምሮችን አድርገዋል። 3 በነገራችን ላይ የዚህን ግኝት ንደፈሃሳባዊ ዋንነት ለመመልከት የስነፍች መሰረታዊ አሃዶች (semantic atoms) ባልተለዩበትና ንድፈሃሳባዊ ብያኔ ባላገኙበት የቋንቋ ጥናት ሳይንስ ነጠላ ድምጾችን አላባዎች (elements)፣ ጥምሮቹን ደግሞ ውሁድ (compound) ልናደርጋቸው እንችላለን። ቃላት ቁሳዊም ሆነ ፍቻዊ ባህርያቸውን የሚወርሱት በውስጣቸው ካሉት አላባዎችና ከአደረጃጀታቸው ነውና ።