ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ ትግል ማድረጊያ መሣሪያዎች መሆናቸውን የመንግሥት ሪፖርት አመለከተ

31 December 2017

ዘመኑ ተናኘ

ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማርና ችግር ፈቺ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ከማከናወን ይልቅ፣ የፖለቲካ ትግል ማድረጊያ መሣሪያዎች እየሆኑ መምጣታቸውን በመንግሥት የተዘጋጀ ሪፖርት አመለከተ፡፡

ሪፖርቱ የቀረበው ግጭት ተቀስቅሶባቸው በነበሩ 19 ዩኒቨርሲቲዎች በመዟዟር ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ግብረ ኃይል፣ ታኅሳስ 19 እና 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር አዳራሽ ባካሄደው ስብሰባ ነው፡፡

የግብረ ኃይሉ አካል የነበሩ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ብሔር ተኮር ግጭት በተቀሰቀሰባቸው 19 ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማርና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከማከናወን በዘለለ፣ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቦች በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ እየታመሱ እንደሆነ የሚያመላክት ሪፖርት ቀርቧል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ከባድ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ፣ ለዚህ ፈታኝ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሠራ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል መባሉን ባለሥልጣኑ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በብሔር በመደራጀት ተማሪዎች እርስ በርሳቸው በፍራቻ ዓይን እየተያዩ እንደሆነ፣ ይህንን ስሜትና አመለካከት መቀየር ካልተቻለ ባለፈው ተከስቶ ከነበረው ግጭት የባሰ ችግር ሊከሰት እንደሚችል የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመላክት አስረድተዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ በውስን ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ያልተጀመረባቸው ዲፓርትመንቶች እንዳሉ ከመጠቆሙም በላይ፣ በግጭት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው ያልተመለሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ በዝርዝር ውይይት እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ብሔር ተኮር ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የማስተማር ሥራቸውን አቋርጠው የቆዩ ዩኒቨርስቲዎች እንዳሉ  መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመማር የማስተማር ሒደት ሙሉ በሙሉ እንዳልተጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) ሐሙስ ታኅሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ተቀስቅሶ ለነበረው ግጭት አንዱ ምክንያት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከተከሰተው ግጭትና ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ ካለው ችግር በተጨማሪ፣ ተማሪዎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ማቅረባቸውን በግብረ ኃይሉ ሪፖርት መቅረቡ ታውቋል፡፡

አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር ሥራቸውን እንደጀመሩ እየተነገረ ቢሆንም፣ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው የቀሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ክፍሎች መኖራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከግቢ ወጥተው የነበሩ ተማሪዎች እንዲመለሱ ጥሪ እየተላለፈ ቢሆንም፣ በግጭቱ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የሄዱ ተማሪዎች መመለስ እንዳልቻሉ  በሪፖርት መቅረቡ ታውቋል፡፡

ግጭቱ ከተከሰተና የአራት ተማሪዎች ሕይወት ካለፈ ወዲህ በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ዝቅተኛ እንደሆነ፣ ግንኙነታቸውም በፍርኃት የተሞላ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡

በተማሪዎች መካከል ያለውን የፍርኃትና የጥላቻ አዝማሚያ በመስበር ትክክለኛ የመማር ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ከባለሥልጣኑ ገለጻ መረዳት ተችሏል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት መንስዔና የመፍትሔ አቅጣጫ ትኩረት አድርጎ ሲካሄድ የነበረው የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ግጭት ተከስቶባቸው ወደ ነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ተሰማርቶ የነበረው ግብረ ኃይል ውይይት፣ ዓርብ ታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. መጠናቀቁ ታውቋል፡፡

Source     –   Ethiopian Reporter