የፌዴራል መንግሥት በውክልና የወሰደውን የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን መልሶ አስረከበ

አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነዋ

የፌዴራል መንግሥት በውክልና የወሰደውን የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን መልሶ አስረከበ

31 December 2017

ውድነህ ዘነበ

የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ተደረጉ
የፌዴራል መንግሥት በውክልና ተረክቦ ያስተዳድር የነበረውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን መልሶ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረከበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ረቡዕ ታኅሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአምስት ዓመታት በላይ ተለይቶ የቆየውን የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ባለሥልጣንን፣ ከኢትዮጵያ ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ ተረክበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በድጋሚ የተረከበውን ገቢዎች ባለሥልጣን እንዲመሩ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴን ዋና ዳይሬክተር አድርጎ ሹሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ነበር፡፡ በቢሮው ሥር በሚተዳደርበት ወቅት በወ/ሮ በላይነሽ ተክላይ ይመራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የከተማውን ገቢዎች ባለሥልጣን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማሳደግና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ወጪ ፍላጎቱን ለማሟላት በሚል ምክንያት፣ የከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን ከእነ ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ ወደ ፌዴራል መንግሥት መዛወሩ አይዘነጋም፡፡

በፌዴራል መንግሥት ውክልና በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ‹‹የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት›› በሚል ስያሜ፣ የከተማውን ገቢ እየሰበሰበ ለአስተዳደሩ ሲያስረክብ ቆይቷል፡፡

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሚያቅደውን ያህል መሰብሰብ ባይችልም፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ ግን በየዓመቱ መሻሻል እያሳየ መምጣቱ ይነገራል፡፡

ለአብነት በ2009 ዓ.ም. 11 ወራት 31.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ መሰብሰብ የቻለው ግን 26.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ዕቅዱን እንዳላሳካ የሚያሳይ ቢሆንም፣ ከአሥር ዓመት በፊት ግን ይህ ገንዘብ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥም እንደማይሰበሰብ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ሺሰማ፣ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2008 ዓ.ም. የከተማውን መሥሪያ ቤቶች በድጋሚ ሲያዋቅር አቶ ሺሰማ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ቻይና በማቅናታቸው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአስተዳደሩ ተለይተው ነበር፡፡ አቶ ሺሰማ ቻይና ከሚገኘው ጂያንግዚ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ንግድ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

አቶ ሺሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ወደ አዲስ አበባ ሲዛወር የሰው ኃይሉም አብሮ ይዞራል፡፡

‹‹አሠራሩን ይዞ ይቀጥላል፡፡ የቴክኖሎጂ፣ የመረጃና የሕግ ምንጮቹ አንድ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ሺሰማ ገልጸዋል፡፡