December 31, 2017

በገነት ዓለሙ

የካቲት 2010 ዓ.ም. ሲመጣ የ1966 አብዮት 44 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ከ1966 አብዮት እስከ ዛሬ ድረስ ያለው ጊዜ ከዴሞክራሲ እንቅስቃሴ አኳያ የብዙ ነገር ድፍርስርስ በተለያየ ሙቀትና ንቅናቄ ሲናጥና ሲንቦጫረቅ የታየበት፣ የሚተነው ተኖ የሚዘቅጠው ዘቅጦ ሊጠራ ነው ሲባል ተመልሶ እንብክብኩ መውጣትና ሲከፋም ተከልብሶ የንፋስና የትቢያ እራት መሆን፣ እንደገና ጥንስስና ቅራሪ ቢጤ እዚያም እዚያም መቋጠር የቀጠለበት ረዥም የመንገጫገጭ ጊዜ ነው፡፡

ቅድመና ድኅረ 1966 አብዮተኝነት ያፈጀ ቀኖነኛ አመለካከትን አናግቷል፡፡ ምክንያታዊና ነባራዊ አመለካከትን ጠርቷል፡፡ ስለኅብረተሰብ የልውጠት ታሪክ፣ ስለመንግሥት ምንነትና አመጣጥ፣ ስለመደቦች፣ ስለብዝበዛና ጭቆና ግንዛቤን አስፍቷል፡፡ የነፃነትና የእኩልነት ንቃትንና የትግል ፍላጎትን አሳድጓል፡፡ ይህ ሁሉ ነበር ነው፡፡ ከጎጥ፣ ከብሔርና ከአገር አድማስ አሳልፎ ከዓለም አቀፍ የትግል አጋርነት ጋርም አስተዋውቆ ነበር፡፡ ሆኖም እንጭጭነት፣ ልብልብነት፣ ጀብደኝነትና የወታደራዊ አምባገነንነት ድቆሳ ያስከተለው ውድቀት ብልጭ ብሎ የነበረውን አዲስ ግንዛቤና የትግል ስሜት እንዲጠራና እንዲበስል ዕድል አልሰጠውም፡፡ የነበሩት ቡድኖች ድምጥማጣቸው እስኪጠፋ ተሰባበሩ፡፡

ብዙ የተዘመረለትና የተንበለበለለት ‹‹ሶሻሊዝም›› በየትኛውም የኑሮ ዘርፍ የግል ምርጫንና ተነሳሽነትን የገነዘ፣ ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሥራ በፍላጎት ለመተው እንኳ ዕድል የማይሰጥ፣ መካን የኢኮኖሚና የፖሊስ ሥርዓት መሸፈኛ ሆነ፡፡ የሕዝብ ብሶትና ተቃውሞ መሰባሰቢያ አካል ባልነበረበት ሁኔታ ከላይ እስከ ታች የተዘረጋው ቢሮክራሲያዊ አዛዥነትና አንኳችነት ውጤቱ ኅብረተሰቡን መዝምዞ መጨረስ ሆነ፡፡

ባላባታዊ መኳንንትነት ቢወገድም የአዳሪ አሳዳሪነት የአደግዳጊ አስደግዳጊነት፣ የደጅ አስጠኝነትና የእጅ መንሻ ግንኙነቱ በደርግ ዘመንም ታድሶና ሰፍቶ ቀጠለ፡፡ በቅኔና በአዝማሪ አወዳሽነት ላይ መፈክራዊ አወዳሽነት ተጨመረ፡፡ ሌላ ምርጫ በሌለበት፣ በጠበበትና በሚሽቆለቆል የእንጀራ ገመድ መታሰር፣ እንዳፈቀደ ወደ እስር ቤት መወርወርና መገረፍ፣ ስድብ፣ ግልምጫና ጥፊ ሁሉ ቀለብ በሆነበት፣ ክብረ ቢስ አኗኗር ህሊናና መንፈስ ደቀቀ፡፡ አውቆ ማጥፋት፣ ለሐሰት መሰገድ፣ እስስትነት አላካኪነት እምነትንና ሰዎችን ለጥቅም መሸጥና መዝረፍ የጊዜው የኑሮ ዘይቤ ተደረገ፡፡

አስተሳሰብና ግንዛቤ የኋሊት ሄደ፡፡ ‹‹ሰፊው ሕዝብ››፣ ‹‹ትግል››፣ ‹‹ፖለቲካ››፣ ‹‹አብዮት››፣ የሚባሉ ነገሮች ለጆሮ አስጠሉ፡፡ ይሞገስ የነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ‹‹እያጎረሰና እያለበሰ ባስተማረው በደጉ ኃይለ ሥላሴ ላይ ግፍ የዋለ›› ተደርጎ ይታይ ጀመር፡፡ መደቦችን ያመጣው ጠንቀኛው ሶሻሊዝም ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ደም መፋሰስንና ትርምስን የአብዮት ባህሪ አድርጎ ማየት መጣ፡፡

ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢይዝ ከዴሞክራሲያዊው ትግል አንፃር ከቁልቁለት መመለሻ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ‹‹የሕዝብ የራስ በራስ አስተዳደር››፣ ‹‹ነፃነት›› እና ‹‹እኩልነት›› ያገጠጠ የቡድናዊ ምዝበራ ሽፋን ሆኖ አረፈው፡፡ ልሽቀት ከቀድሞ በበለጠ ሰፋ፡፡ ለገዥ ቡድን ማደርና መደለል (አለዚያ መንጓለል) የመሾሚያ፣ የመሸለሚያና የመዝረፊያ መንገድ መሆኑ ቀጠለ፡፡ መሽቆጥቆጥ፣ ደጅ መጥናትና ጉቦ አቅራቢነት፣ ጎሰኛ – ጎጠኛ አስተሳሰብና መወጋገን ፖለቲካዊ ክብር አግኝቶ ተራባ፡፡ ሌላ አዛዥና አርበድባጅ ቢሮክራሲያዊ መኳንንት ተደራጀ፡፡

የኢሕአዴግ አገዛዝ ከቀዳሚዎቹ ጋር ሲነፃፀር ሐሳብን የመግለጽና የመደራጀት የተሻለ ዕድል የተገኘበት፣ የፖለቲካ ቡድኖችም የተፈጠሩበትና ምርጫ የሚካሄድበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፖለቲካና ፖለቲካዊ ቡድድንን ዛሬም አጋጣሚን የሚጠብቁ ጥቅመኞች የሚራኮቱበት አንድ መስክ ሆኖ እንዳለ አለ፡፡ ደርግ በወደቀ ማግሥት ወደ ኢሕአዴግ የሰኔ ኮንፈረንስ ከሮጡት ብዙዎቹ ይኸው ጥቅመኝነት የወለዳቸው ነበሩ፡፡ ከዚያም በኋላ ኢሕአዴግ በየብሔሩ ሰው በመብራት እየፈለገ ንቅናቄ ሁን፣ አካባቢህ ላይ ልሹምህ እያለና አምባሳደርና ሚኒስትር እያደረገ አጋጣሚያዊ የፖለቲካ ንግዱ ደራ፡፡ ዛሬም ፖለቲካና መቦዳደን በሰፊው ይሠራበታል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ ገብቶ ወፍራምና የማይነጥፍ ኪራይ መሰብሰቢያ ‹‹ምድር›› ለመቆናጠጥ፣ በብሔርና በኅብረ ብሔር ታጋይነት የውስጥና የውጭ የገንዘብ ድጋፍ ለመሰብሰብ፣ በሰፊ ወይም በቁራጭ ሥልጣን ላይ ጉብ ለማለት ይሰላል፣ ይሠራል፡፡

በሁሉም ጎራ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትንና የብሔር መብትን ለዚህ ዓይነት ዓላማ መንገድ አድርገው የሚጠቀሙ ከዴሞክራሲነት ጋር ግን ግንኙነት የሌላቸው ጥቅመኞች በርካታ ናቸው፡፡ ለፍቼ ያደራጀሁትና ያጠናቀርኩት ፓርቲዬ እያሉ ድርጅትን እንደገዛ ንብረት ማሰብ፣ የፓርቲንም ሆነ ሌላ ታሳቢ ሥልጣንን የልፋት ድርሻ፣ የውርስ ሀብት አድርጎ መቁጠር በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎችም ውስጥ ያለ የአገር ጠንቅ ነው፡፡ ቀውጢና ፈታኝ ሰዓት ሲመጣ መካካድ፣ አንድ ላይ ያቦኩትን በሌላው ላይ ማላከክ፣ ወደ ሌላ መገልበጥ ወደ ላይ መሳብ . . . ሙልጭልጮሹ ተነገሮና ተጽፎ አያልቅም፡፡ ኢሕአዴግም ጨው እያሳየም፣ እያስፈራራም፣ ሰው እየገዛም የመንግሥትን ገለልተኛ የአስተዳደርና የዳኝነት ወዘተ. ድጋፍ እየነፈገ ይከፋፍላቸዋል፣ ይበትናቸዋል፡፡ የውስጥ ደንባቸውን ማክበርና መከተል የመሰለ ቀላልና ግልጽ ነገር ለገላጋይ የሚያስቸግር ውስብስብ ያደርግባቸዋል፡፡
ለፖለቲካ መብቶች፣ ለፍትሕና ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ፓርቲ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አይሆንም፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችንም እንዲያው ብልጭ ድርግምና ከምበል ቀና የሚሉ ጥረቶች ታይተዋል ከማለት በላይ ብዙ መናገር ያስቸግራል፡፡ ዴሞክራሲንና ነፃነትን መውደድና መናፈቅም ብቻውን ዴሞክራት አያደርግም፡፡ ዴሞክራት ከተግባር ጋር በሚገናዘብ የዴሞክራሲና የእኩልነት አመለካከታዊ ለውጥ ውስጥ ራሱን አስገብቶ ፀረ ዴሞክራሲን ይዋጋል እንጂ፣ መወጣጫውንና የግል ዝናውን በማመቻቸት ሥራ አይዋጥም፡፡ ዴሞክራት የቅልበሳና የመላሸቅ ዕድልን ለማምከን፣ ለመከታተል፣ ለማጋለጥና ለማስወገድ የሚያስችል የራሱ መጠበቂያ ያለው፣ ከመንግሥት አወቃቀርና አሠራር እስከ ሕዝብ ዓይንና ወሳኝነት ድረስ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት እስካልተደራጀ ድረስ፣ ነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት መብቶች አስተማማኝ ተከባሪነት እንደማይኖራቸው አውቆ ለዘላቂነታቸው የሚታገልና እስኪሳካም የማይዘነጋ መሆን አለበት፡፡ ተከራክሮ ማሳመንና ማመንን፣ በድምፅ የተበለጠበትን የፓርቲን ውሳኔ ማክበርን ዘላቂ ጥቅሜ ብሎ አርቆ የሚያይ የፓርቲ በእርጅና መበላትና አለመበላት ዴሞክራሲያዊነትን ከማጣትና ካለማጣት ጋር ተያያዥ እንደሆነ የሚያውቅ፣ ለድርጅት የውስጥ ዴሞክራሲ ሁልጊዜ የሚቆም፣ ለአምልኩኝ ባይነት፣ ለሴረኝነትና ለሻጥረኝነት ፀር የሆነ ነው ዴሞክራት፡፡

ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የእኩልነትና የዴሞክራሲ አስተሳሰብ አሠራር ያለበትና የሚኖርበት፣ ሥልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም አካል እንዳይዋጥ ቅንብር የሚበጅበት፣ ለዓላማ፣ ለአሠራርና ለውሳኔ መታመን የሚለመድበት ነው፡፡ ለዚህም ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የዴሞክራሲ አስተዳደር ትንሽዬ ቤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከተጠቆሙት ፍሬ ነገሮች አንፃር የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት ያጋጠመን እንቅፋት፣ መሰናልክና ወጥመድ ታጋዩን ብቻ ሳይሆን ትግሉን የበላ ነው፡፡ መከራውና ውጣ ውረዱም ከባድ ነው፡፡

መጀመርያ ነገር መገኛችን ራሱ ‹‹ክፉ›› መነሻ ነው፡፡ በአማላጅና በእጅ መንሻ መቅረብ ከምድራዊ ኑሮ ባሻገር ከአምላክ ጋር ባለ መንፈሳዊ ግንኙነትም ውስጥ ለረዥም ዘመን ሲሠራበት የቆየ፣ አሁንም እየበዛ እየከፋ ያለበት አገር ነው፡፡ በኅብረተሰባችን ውስጥ የሃይማኖት መምህር የአምላክ ወኪል የጽድቅ ካርኒ ቆራጭ ነው፡፡ በአለቃና በምንዝር፣ በአስተማሪና በተማሪ፣ በዳኛና በባለጉዳይ፣ በአስተዳዳሪና በሕዝብ መካል ያለው ግንኙነት በሰጋጅነትና በአሰጋጅነት ውስጥ የሚዳክር ነው፡፡ ሹም ወይም አለቃ የሚፈልገውን አውቆ ሐሳብንና አስተያየትን ከማስማማት፣ ሻል ከተባለም ዝም ከማለት ገና አልተወጣም፡፡ የህዳሴው መሪ ነኝ በሚለው በኢሕአዴግ ውስጥ በራሱ የመሪን ንግግር እንደ እግዜር ቃል መጠበቅና የተነፈሰውን ሁሉ (አንዲት ቃልም ለመቀየር ሳይደፍሩ) ማራገብ ሙያ ሆኖ የነገሠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አለቃ ሲመጣ ከሥራ ላይ ተነስቶ መቆምና መሽቆጥቆጥ በእኛ አገር አክብሮት ነው፡፡ ይህንን አለመፈጸም ከንቀት ይቆጠራል፡፡ ቂም ያስይዛል፡፡ ዝናው የተናኘ ሊቅ ቢተች ወይም በትንሹ አንተ ተብሎ ቢጠራ በእኛ አገር ከበደል የሚቆጥረው ጥቂት አይደለም፡፡ የአንድን ሰው አስተሳሰብና ሥራውን በተለይም በይፋ መተቸት በእኛ ኅብረተሰብ ውስጥ ንቀትና ፀብ ፍለጋ ነው፡፡ ስህተት ቢኖር እንኳ ሰው ሳይሰማ ቢነግረው/ቢነግረኝ ያስብላል፡፡ ለሰው አፍ ሳያሳጡ በሚተቹበትም ጊዜ ከመልካም የሚቆጠረው ፍርጥ ያለው ሳይሆን የተሸፋፈነው ትችት ነው፡፡ መንገድ ላይና አውቶብስ ውስጥ ታክሲ ሠልፍ ላይ ሰውን ገፍቶና ረግጦ ወይም ሌላ ጥፋት ሠርቶ ይቅርታ የማይልና በጓደኞቹ ፊት ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ሞት የሚመስለው እንደሞላ ሁሉ፣ በፖለቲከኞችም ዘንድ ይህ ችግር ከፍቶ ሰፍቶ ሞልቷ፡፡ ስህተትን ከማረም ይልቅ በስህተት መቀጠልን (‹‹እንደ ተከበሩ መቀጠልን››) የሚመርጥ ጭራሽኑም ትችት ለመስማት ጆሮውንም የሌላውን ጆሮ ጭምር የሚጠቀጥቅ ሞልቷል፡፡ ትችትን በትችት ሳይሆን ‹‹እሱ እኮ እንዲህ ያለ ሰው ነው›› በማለት የሚያሸንፍ እንደ ልብ ነው፡፡

ስለዴሞክራሲና ዴሞክራትነት እንዲህ እንዳሁኑ በጋዜጣ የምንጽፈውም፣ ስለ ‹‹ምክንያታዊነት›› የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና ምሁራንን እንዲሁም ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን›› እየጋበዙ በቴሌቪዥን የሚያስተምሩንም፣ የተነሱት ችግሮች አይነካኩንም ብንል ሙልጭ ያለ ውሸት መናገር ይሆናል፡፡ ዘመናዊ ዕድገት ባልነቀነቃት አገር ውስጥ ችግሮች መኖራቸው አያስገርምም፡፡ የሚያስገርመው ዴሞክራት ነን እያሉ የግል ፖለቲካዊ ጭፍራ አሰባሳቢነትን፣ እኔ ብቻ ልዘዝ ባይነትን፣ ለምን ተተችቼ ለምን ተጠየቄ የሚሉ ኩርፊያንና የመሳሰሉ ችግሮችን ለማራገፍ አለመጣር ነው፡፡ በእኛ አገር ፖለቲከኞች ዘንድ የሚታየው መበጣበጥ፣ በጎጥ፣ በብሔረሰብና በየፖለቲካዊ ጌታ ዙሪያ ቡድን ለይቶ መቆም ሁሉ ከዚህ ዓይነት እክትነት (ኮተታምነት) እና ከፓርቲ ውስጣዊ ዴሞክራሲ ጉድለት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አገራችን ውስጥ የፓርቲ መሪዎች ሲወዛገቡ ማየት የተለመደና የሆነ የሌላ ነገር ምልክትም ነው፡፡ የአመራር ብቃትን የሚፈትኑና ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ከባድ ሁኔታዎችና ጉዳዮች የፖለቲካ ድርጅቶችን ቢያጋጥማቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ዛሬም ወደፊትም ያጋጥማል፡፡ የፓርቲ አመራር አጥፊ ውሳኔና አካሄድ ሊይዝ የሚችልበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታም ያጋጥማል፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት ላይ ፀረ ዴሞክራት ሾልኮ ቢወጣ ወይም የተመረጠ የመስተዳድር ቡድን ዴሞክራሲን የሚቃረን አካሄድ ቢያሳይ፣ ሌላ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ መፍጠር መሄድ ሳያስፈልግ በዚያው ሥርዓት ውስጥ ማስተካከል እንደሚኖር ሁሉ ፓርቲም ዴሞክራሲያዊ ሕይወት እስካለው ድረስ አምባገነን ልሁን ባይነትና የሐሳብ ልዩነት በመጣ ቁጥር የግልበጣ ሴራ ማዘጋጀት፣ ወይም አንጃ ሠርቶ መነጠል ግድ መሆን ያለበት ነገር አይደለም፡፡ ባለው ዴሞክራሲያዊ አሠራር አመራር ይስተካከላል፡፡ አለመግባባት ይወገዳል፡፡ የሐሳብ ልዩነት እየተፋተገና እየተረታታ ይቀራረባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ሕይወትና የሐሳብ ነፃነት የሌለበት ፓርቲ የቱንም ያህል ትክክል አቋም ቢይዝ ሄዶ ሄዶ ማርጀቱና መምከኑ አይቀርም፡፡ በአንድ ሰው ብስለት ወይም ሌላ ነገር ላይ ተንጠልጥሎ ቢቆይ እንኳን ግለሰቡ አቅሙን ሲጨርስ አብሮ ያበቃለታል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለየብቻ ጠንክሮ መውጣትም ሆነ ወደ አንድ ትልቅ ፓርቲ ወይም ግንባር መሰባሰብ ኢሕአዴግ ከመቀናቀን ቦዝኖ አለማወቁ እውነት ነው፡፡  ቅንጅት፣ ኅብረት፣ መድረክና አንድነት ቁስለኞቹ ናቸው፡፡ የተወሰኑ መሪዎችን ነውጠኛ እያሉ ማሰር፣ ‹‹ነውጠኛ›› ያልሆኑት ሕግ አክብረው መንቀሳቀስ ይችላሉ እያሉ ልዝብ አንጃ እንዲያደራጁ በመገፋፋት ሌላ አዲስ ፓርቲ መፍጠር፣ እንደ ተፈለገው ሳይሆን ሲቀር ደግሞ በውስጥ አርበኛ የሚመራ ቡድን ቅንጅት ወይም ኦብኮ ወይም አንድነት ወይም . . . እኔ ነኝ እንዲል ማድረግ የማይረሳና የተለመደ ሥራና አሠራር ነው፡፡ ዛሬ የመከፋፈል፣ የመሰንጠቅ ወይም የህልውና አደጋ ከውስጡ የገጠመው ኢዴፓም ቀድሞውንም ቢሆን በዚያ የቅንጅት ወቅት በተለየ ሁኔታ የኢሕአዴግ ቁስለኛ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ በ‹‹በጎ›› የመታየቱ ውጤት ‹‹የእኔ ነው››፣ የውሸት ተቃዋሚ ነው፣ የክፉ ቀን እጅ ነው የማለትን መርዘኛ መልዕክት ረጭቷል፡፡

እንዲህ ያለ ‹‹በዕውቅ የተዘጋጀ›› ወይም የዘወትር የተቀናቃኝ አፈና ለመከላከልና በአሸናፊነትም ለመወጣት የገዛ ራስ ፓርቲን በዴሞክራሲያዊ መርህ ማደራጀት የግድ ነው፡፡ ይህም ማለት የፓርቲው ተግባራት የሚከናወኑት በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው አማካይነት እኩል መብት ባላቸው በጠቅላላው የፓርቲው አባላት ነው፡፡ የፓርቲው መሪዎች የአመራር አካላትና የፓርቲው ተቋማት በሞላ በምርጫ የሚቋቋሙ፣ ለመራጫቸውም ተጠያቂና በሌሎችም ሊተኳቸው የሚችሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በዚህ ዴሞክራሲያዊ መርህ ውስጥ ለመፍታት፣ በተለይም ለዴሞክራቶች ብዙ ጩኸትና መዋደቅ ባላስፈለገ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲዎች ሁሉ ያለፉበትንና ያሉበትን ሁኔታ በቅጡ በመገምገም በአመለካከት፣ በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በትግል ሥልት መስተካከል ያለበትን መለየትና (የፓርቲ መተዳደሪያ መናኛ ክፍተቶችን ጨምሮ) ለአቅመ ቢስ ትንንሽነትም መውጫውን መንገድ ማሰብም ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡

የአንድ ፓርቲ ባህሪ በራሱ የውስጥ ማንነት ብቻ ሳይሆን በተቀናቃኞችም ባህሪ የሚወሰን በመሆኑ፣ የፓርቲዎች የእርስ በርስ በጎ ግንኙነት የሁሉንም ወገን የፀባይ መሻሻልን ያስከትላል፡፡ በምንነጋገርበት ጉዳይ ደግሞ ቀዳሚው ነገር ራስን በዴሞክራሲያዊ መርህ ማደራጀት፣ የድርጅትን የውስጥ ዴሞክራሲ ፋይዳ ማወቅና እሱኑ መኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመበስበስ ምሳሌ የሚሆኑ ቡድኖች/ፓርቲዎች እጥረት የለባትም፡፡

የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ትግል በደርግ የተደመሰሰው ፓርቲዎች የጋራ መገናኛ የለንም፣ አይኖረንም ብለው እርስ በርስ በሚያጠፋፋ የጠላትነት ፖለቲካ ውስጥ በመቀሰፋቸው ነው፡፡ ምርጫ 97 ይዞት የመጣው ዓይነተኛ ለውጥና ዕድገት መና የቀረውና ቅልበሳና ድቆሳ የቀናው፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የፖለቲካ መስመሮቻቸውን በአግባቡ ሳያቀራርቡና ኢዴሞክራሲያዊነትን ሳያራግፉ ከተጠራጣሪነት፣ ከመሰሪ ሥሌትና ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት ሳይላቀቁና የአገሪቱ ብሔረሰቦች የተያያዙበትን ጠንካራ የትግል ትብብር ሳያበጁ በመቅረታቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እንኳንስ መሪ ሆነው በነበረው ድል ላይ ድል ሊያስመዘግቡ ራሳቸው ‹‹የአህያ ባል . . . ›› መተረቻ ሆነው፣ የአንዱ ቁርጥ እስኪለይ ሌላው ጥግ በመያዝና ራስን በማዳን ጅል ብልጠት ተራ ገብተው ተደቆሱ፣ አስደቆሱ፡፡

እዚህ ምሳሌ ውስጥ አዲስ መካተት የማይሻ እንዲሁም በለውጥ ውስጥ ለመኖር የሚፈልግ ፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲውን ማጎልበትና መኖር አለበት፡፡ የመረጃና የነባራዊ ግንዛቤዎች ድርቅ እንዳይኖርበት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ራሱን ማስገባት ግዴታው ነው፡፡ የመተዳደሪያ ደንቡ፣ የሥልጣን አካላት የእርስ በርስ ግንኙነት ምንነት የሚፈተሸውና ‹‹ተመርቆ የሚከፈተው›› እንዲህ እንዳሁኑ ችግር ሲያጋጥምና መተማመን ሲናጋ መሆን የለበትም፡፡ የፓርቲው መሪዎች የፓርቲው የሥልጣን አካላትና ተቋማት በሙሉ በምርጫ የሚቋቋሙ ተጠያቂነታቸውም ለመራጫቸው የሆነ፣ የሚወርዱም የሚወጡትም በምርጫ ስለመሆኑ ከሚደነግግ ሕገ ደንብ ውጪ መሆን መጀመርያ የዴሞክራት ወግ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የሚጣላ ፓርቲ ራሱን ፓርቲ ባይል ይመረጣል፡፡

ሐሳቦችና ጉዳዮች እየወጡ መነጋገሪያ እንዲሆኑ ማድረግንም ፓርቲዎች በዚህ የኢትዮጵያ ውስን ሁኔታም ውስጥ መጣርና መጋር አለባቸው፡፡ ለዚህ የውስጥ ጋዜጣና ውይይት አንዱ መንገድ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ያለዚህ አይኖርም ብሎ መዝጋቢውን የመንግሥት ተቋም ወጥሮ መያዝና ይህንንም እያወጡና እያሳጡ ግፊት ማድረግ መነሻ ግዴታቸው ነው፡፡ ለእውነትና ለሕዝብ ቅርብ መሆን፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ከፓርቲ አባላት ውጪ መወያያ እንዲሆኑና ጥናቶች እንዲካሄዱባቸው ማነሳሳትም ሌላ ኃላፊነት ነው፡፡ የተቃራኒ ፓርቲዎችን አቋም መመርመርና አባላቱ በክፍት አዕምሮ እንዲገመግሙ ማድረግ የራስን አቋም ጥንካሬ ለመፈተሽና ለማጥራትም አላስፈላጊ ነው፡፡ የተቀናቃኙን ድርጅት አቋም ከአባላቱ ሊደብቅ የሚሻ የራሱ አቋም እንደይተችና ጥፋቱ እንዳይጋለጥ የሚጥር ፓርቲ በመበስበስ መንገድ ውስጥ የሚጓዝ ለጥቃት የተጋለጠና እንኳንስ ‹‹ኃይለኛ የውጭ እጅ›› ገብቶበት በገዛ ራሱ ሞቱን የሚጠራ ፓርቲ ነው፡፡

የድርጅት ውስጣዊ ዴሞክራሲ የጥቅም ጉዳይ አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የጋራ አመራርን ያሰፍናል፡፡ የጋራ አመራር ባልፈዘዘበት ድርጅት ውስጥ የግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት መንገድ ይጠበዋል፡፡ የድርጅት አመራር ከላይ በተቀመጡ ጥቂት ሰዎች እንዳይጠለፍ ወይም በእነሱ አስተዋይነት ላይ ብቻ እንዳይወሰን የውስጥ ዴሞክራሲያዊ መድረኮች ወሳኝ ናቸው፡፡ መላ አባላቱ ከጊዜ ጊዜ ሐሳብ እንዲያመነጩና እንዲያዋጡ የውስጥ ጋዜጣ ዕድል ይሰጣል፡፡ የማያቋርጥ ሐሳብ የመስጠትና የመቀበል ሒደት ይኖራል፡፡ ሁሉንም ያሳተፈ ተከራክሮ ማሳመን የቻለ ሐሳብ፣ ግንዛቤና ሥልት ይመራል፡፡ ይህ አሠራር ድርጅትን ለመምራት ብቃት አለኝ የሚል ሁሉ ወንበር በመያዝ ላይ እንዳይተናነቅ ይረዳል፡፡

የድርጅት ውስጠ ዴሞክራሲ አለመግባባት የሚፈታበት የዳኝነት መድረክም ነው፡፡ ወደ ምርጫ ቦርድ ወይም ሌላ አካል የሚሄደው የፓርቲው የውስጥ አወቃቀር ይህንን ማድረግ ሲሳነው ነው፡፡ እንዲያ ያለ ፓርቲ ውስጥ መኖር በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በፓርቲው የውስጥ አሠራር መድረክ የተረታ ወገን ወይም ግለሰብም፣ የአብላጫውን ውሳኔ የማክበር ኃላፊነት የሐሳብ ተቀባይነት ለማግኘት ከሚደረግ የትኛውም ዓይነት ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ ትግል የላቀ ዋጋ አለው፡፡ በቀጥታ የድርጅቱን ህልውና የሚመለከት ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ውሳኔው የተሳሳተ ቢሆን እንኳን ‹‹ለበጎ ውጤት›› ተብሎ ውሳኔውን መሻርም፣ ሕግንና ዴሞክራሲያዊ አሠራርን መጣስና በድርጅቱ ላይ ጥቃት መፈጸም ነው፡፡ ይህ በመንግሥት ደረጃም እንደዚያው ነው፡፡

የፓርቲው አመራር ሊያፍነው በማይችል የውስጥ ጋዜጣና የስብሰባ ዕድል ሐሳቦች እንደ ልብ መንሸራሸርና መፋተግ መቻላቸውም መተንፈሻ ፍለጋ ከፓርቲ ውጪ መሄድን ያስቀራል፡፡ ድርጅቱ አቋም ባልወሰደባቸው ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየትንና አቋም በመገናኛ ብዙኃን መስጠት መብት ነው፡፡ ድርጅቱ አቋም ከያዘ በኋላ ግን ያንን እየተቃረኑ የእኔ የግል አቋምና እምነት እንዲህ ነው እያሉ መለፈፍን ከመብት ለመቁጠር መሞከር ግን ‹‹አንዱም ሳይያዝ›› እንዲሉ፣ የውስጥ ልዩነቶችንና ባለልዩነቶችን እየተጠጉ ድርጀቱ ለመሰንጠቅ ለሚጥሩ መሰሪዎች ሰፊ መንገድ መስጠት ይሆናል፡፡

ሌላም ችግር አለ፡፡ ሸሪክና የደጋፊ ድምፅ ለማግኘት ሲባል ጥቅም ነክ ድርድሮችና ድለላዎች ሁሉ የሚሄዱበትን ‹‹የፓርላማ ኮሪደር ሹክሹክታ›› Lobby ማድረግን በተለመደ ዴሞክራሲያዊ አሠራርነት በአገራችን ፓርቲዎች ውስጥ ማስገባትም ለአንጃነት ፈቃድ ከመስጠት አይለይም፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅንጅት ውህደት ጊዜ አቶ ልደቱ አያሌው ቁልፍ ናቸው ከተባሉ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲርቅ የተደረገው ‹‹በውስጥ ለውስጥ ምክክር›› እንደነበር ከብርሃኑ ነጋ መጽሐፍ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ መንገድ ይልቅ ለዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚጠቅመው እከሌ ለዚህ ቦታ ያንሳል፣ እከሌ የተሻለ ብቃት አለው ብሎ ፊት ለፊት በመመካከር ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡

ቀጥተኛም ሆነ የሽፍንፍን አፈና በሌለበት አሠራሩን በውስጡ እያጠናከረ የሚሄድ ፓርቲ ልዩነትና ቅሬታ እያራገቡ ድርጅትን ለመሰነጣጠቅ ለሚፈልጉ ጥቅመኞችና ሰርጎ ገቦች በቀላሉ አይበገርም፡፡ ተንኮለኞች እንዳይደበቁና ተዳፍነውም እንዳይከርሙ ገና በእንጭጩ እንዲጋለጡና እንዲነቀሱ በማድረጉ ደኅንነቱን ለመጠበቅ የተሻለ አቅም ይኖረዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የአንድ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ሕይወት ደብዝዞ እንዳይጠፋ የሚጠብቀው የመላ አባላቱ ንቁነት ነው፡፡ ንቁነት እንዴት? ንቁነት ምንድነው?

ሕዝብ ማለት መንግሥት፣ መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው እንደሚባለው ማሳሳቻ በዚህም ዘርፍ ‹‹አመራር ማለት ድርጅት ድርጅት ማለት አመራር ነው፣ እንደኛ ሆናችሁ ሁሉን ሥሩት›› ከሚል ኃላፊነትን ከመሸሽ አባዜ የተላቀቁ ንቁ አባላት ወሳኝ ናቸው፡፡

መስዋዕትነትን የተራ ደጋፊና የአባል፣ በ‹‹ስደት›› ማምለጫ የአመራር አባላት ወግ አድርገው የሚያስቡ ብልጣ ብልጦች መጫወቻ የማይሆኑና ድርጅታቸው በቆራጦች የሚመራ ስለመሆኑ ትኩረት የሚሰጡ ንቁ አባላት ያስፈልጋሉ፡፡

የድርጅታቸውን መተዳደሪያ ደንብ የሰርክ ግንዛቤና መሣሪያ አድርገው ከራሳቸው ጋር ያዋሀዱ ንቁ አባላት የግድ አስፈላጊ ናቸው፡፡ እንዲሁም በድርጅትና በግለሰብ አምላኪነት ዓይናቸው የማይከለል፣ ጠያቂ አዕምሮ ያላቸውና የድርጅታቸውን አካሄድ ሥራችን ብለው የሚከታተሉ፣ ጥፋትና ስህተት ሲሠራ አሳልፈው ነገር ከተበላሸ በኋላ ተመፃዳቂና በሆዴ ይዤው እንዳልቀር የሚል ተቺነት የማይጫናቸው፣ በዝምታም ይሁን በንቃት ድጋፋቸውን ሰጥተው አብረው ከወሰኑ በኋላ ለውሳኔውና ለሚከተለው ውጤት የጋራ ኃላፊነትን ከመውሰድ ፈንታ፣ የሐሳቡ አመንጪና ዋና ተከራካሪ የነበረውን ግለሰብ ኃላፊና ተጠያቂ (የስብሰባን ውጤት የግለሰብ ሥራ) የማድረግ ዘመናዊ ሾላካነትን የሚዋጉ፣ በአጠቃላይ ለእውነታ፣ ለመረጃ፣ ለዕውቀትና ለለውጥ ሁልጊዜ ቅርብ ለመሆን የሚጣጣሩና የሚተጉ ንቁ አባላት ያስፈልጋሉ፡፡

የዚህ ዓይነት ዴሞክራቶች ድርጅታቸውን ከመበስበስ ያርቃሉ፡፡ የወኪልና የወካይ ግንኙነትን በተራው ኑሮ ውስጥ ሁሉ ከገባበት የተገላቢጦሽ አሠራር ነፃ ያወጣሉ፡፡ ከሕግ ከሕገ ደንብ ውጪ በሥልጣን መቆየትና ከተወሰነ የጊዜ ገደብ በላይ ሥልጣን ይዞ መቆየትን የሚመርቁ የአፄ በጉልበቴዎችን አብጤነት ይከላከላሉ፡፡ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ድልና ግንባታ ትልቅ ኃይል መሆን ይችላሉ፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አደገኛና አሥጊ ሁኔታ ለመረዳት የዚህ ወይም የዚያ ፓርቲ አባል መሆን አያሻም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ችግሩን ከመረዳት በላይ መፍትሔ የሚያመጣላትና መፍትሔ የሚሆናት አሁኑኑ በአስቸኳይ ትፈልጋለች፡፡

ተነጋግሮና ተደማምጦ የጨዋታ ሕጉን ተከትሎ መፍትሔ የመሻት ሥልጡንነት ያልፈጠረባቸው፣ በገዥና በተቃዋሚ ጎራ ተከፋፍለው ከመጠዛጠዝና በተበታተነ ሩጫ ከመታመስ የሚያድን የፖለቲካ ሀብት የሌላቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በጋራ የሚያብከነክናቸውና አንድ ልብ የሚያደርጋቸው ሕመሞችና ብሶቶች የማይሰማቸው ፓርቲዎች ግን፣ የዚህ አሁን የተደቀነብን ችግር መፍትሔ የመሆን አደራ ሊሸከሙ አይችሉም፡፡

ኢትዮጵያ የነፃነትና የዴሞክራሲ ውድ መፈክር ያነገቡ ወገኖችን ሁሉ እጃችሁ ከምን ትላለች!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ሪፖርተር