ኤርትራዊያን ስደተኞችGetty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኤርትራዊያን ስደተኞች

የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በከሰላ አካባቢ በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዘው የነበሩ ዘጠና ስምንት ኤርትራዊያንን አስለቀቁ።

ጊርባ በሚባል አካባቢ በሚገኝ የምሥራቅ ተሪንጋ ጫካ ውስጥ በሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተይዘዉ የነበሩት 98 ኤትራዊያንን ነፃ እንዳወጡ የምስራቅ ሱዳን የከሰላ ኣከባቢ የወንጀል ጉዳዮች ሃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አብዱላሂ ኢል ሳይቅ ለሱዳን የዜና አገልግሎት በሰጡት መረጃ አረጋግጠዋል።

የማስለቀቅ ጥረቱ በተደረገበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎቹ ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ የተደረገ ቢሆንም የደረሰጉዳት እንደሌለ ተገልጿል።

ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ በኩልም በርካታዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ መሐመድ ኢል ፋይዝ ናይም ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ እገታ ነፃ የወጡት ኤርትራዊያን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበር ሲያቋርጡ ይሁን ወይም ተገደው የተያዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል።

ሃላፊው ጨምረው እንደገለፁት እነዚህ ነፃ የወጡት 57 ወንዶችና 41 ሴቶች ሲሆኑ አምስት ህፃናት ከታገቱት ውስጥ ይገኙበታል። የጤና ሁኔታቸው እስከ አሁን በውል ባይታወቅም፤ ካሉበት አካባቢ ወዲ ሸሪፈይ ተብሎ ወደሚጠራ የስደተኞች መጠለያ ሲወሰዱ ያሉበት ሁኔታ እንደሚጣራ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ስለደህንነታቸው የሚያሰጋ ምንም ነገር የለም ተብሏል። ጉዳያቸውንም በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ይከታተለዋል ብለዋል።

የከሰላ ዞን ባለስልጣናትም በዚህ ዓመት በአካባቢው የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና አፈናን ለማስቆም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የሱዳን መንግሥት በድንበሩ አካባቢ የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በአግባቡ አልተቆጣጠረም በሚል በአሜሪካ መንግሥት ሲወቀስ ቆይቷል።

የሱዳን መንግሥት ባለፈዉ የፈረንጆች ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች የታፈኑ ኤርትራዊያንን ከሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ነፃ በማውጣቱ ሲወደስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያንን አስገድዶ ወደ ሃገራቸው በመመለሱ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲወቀስ ቆይቷል።

SOURCE    –